1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሚያዝያ 24 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 24 2014

እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ኢትዮጵያውያት አዳጊ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ወደ ዓለም ዋንጫ ለመግባት ግስጋሴያቸውን ቀጥለዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናል ትናንት እጅግ ወሳኝ የሆነውን ድሉን አስመዝግቦ ደጋፊዎቹን በዓለም ዙሪያ አስቦርቋል። ማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑልም የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ተፋጠዋል።

https://p.dw.com/p/4AjID
Fussball Bundesliga Hertha BSC - 1. FC Union Berlin
ምስል Tilo Wiedensohler/camera4+/IMAGO

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ኢትዮጵያውያት አዳጊ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ታሪክ እየሠሩ ነው። በደረሶ መልስ የደቡብ አፍሪቃን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ድል ነስተው ወደ ዓለም ዋንጫ ለመግባት ግስጋሴያቸውን ቀጥለዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናል ትናንት እጅግ ወሳኝ የሆነውን ድሉን አስመዝግቦ ደጋፊዎቹን በዓለም ዙሪያ አስቦርቋል። ማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑልም የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ተፋጠዋል። በሁለቱም በኩል በቀሪ አራት ጨዋታዎቻቸው የሚፈጠር አነስተኛ ስኅተት ከዋንጫ ፉክክሩ ውጪ ሊያደርጋቸው ይችላል። ጀርመን ውስጥ በተከናወኑ የተለያዩ የሩጫ ዘርፎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ተቀዳጅተዋል። የሩስያ እና ቤላሩስ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾች ከውድድሮች መታገድ በተለያዩ ታዋቂ ስፖርተኞች ዘንድ ፍትሐዊ አይደለም የሚል ትችት እየተሰነዘረበት ነው።

አትሌቲክስ

Kenia Eldoret | Enda Iten Laufschuh
ምስል TONY KARUMBA/AFP

በጀርመን የባየርን ግዛት የአዲዳስ ዋና መሥሪያ ቤት በሚገኝበት ኼርሶጌናውራህ ከተማ ውስጥ በተከናወነው የጎዳና ላይ የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ተቀዳጅተዋል። ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ገነው በወጡበት የ5 ሺህ ሜትር የሩጫ ፉክክር አትሌት ሠንበሬ ተፈሪ አንደኛ በመውጣት አሸናፊ ኾናለች። ለድል የበቃችውም 14 ደቂቃ ከ37 ሰከንድ በመሮጥ ነው። የሀገሯ ልጅ አትሌት መዲና ኤይሳ ከሠንበሬ በ16 ሰከንዶች ተቀድማ የሁለተኛ ደረጃን አግኝታ ለድል በቅታለች። ኬንያዊቷ ሜርሲ ቼሮኖ መዲናን በ3 ሰከንድ ተከትላ የሦስተኛ ደረጃን አግኝታለች። ኢትዮጵያውያቱ መልክነች ውዱ እና ንግሥቲ ሐፍቱ የ5ኛ እና የ6ኛ ደረጃን ይዘዋል።

በወንዶች የ5 ሺህ ሜርትር ፉክክርም የኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ባለቤቱ ኢትዮጵያዊው አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ በአንደኛነት ለድል በቅቷል።  ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበትም 12 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ ነው። ኬንያውያን አትሌቶች ኒኮላስ ኪሜሊ እና ሌቪ ኪቤት 2ኛ እና 3ኛ ወጥተዋል። ለባህሬን የሚሮጠው አትሌት ብርሃኑ ባለው 4ኛ፤ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ጥላሁን ኃይሌ እና አዲሱ ይሁኔ የ5ኛ እና የ6ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

የ10 ሺህ ሜትር የሴቶች የሩጫ ፉክክር አንደኛ ደረጃም በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፈንታዬ በላይነህ ነው የተያዘው። ከ2ኛ እስከ 5ኛ ተከታትለው በመግባት ግን ኬንያውያን በረዥም ርቀት ብርቱ ተፎካካሪ መሆናቸውን ዐሳይተዋል። ኢትዮጵያዊቷ በቀለች ጉደታ 6ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ኪቢዎት ካንዲ ባሸነፈበት የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ፉክክር ግን ኬንያውያን የ2ኛ እና የ4ኛ ደረጃን ይዘዋል። የቡሩንዲው ሯጭ ሮድሪጌ ክዊዜራ የ3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ታደሰ ወርቁ እና ያሲን ሐጂ የ5ኛ እና 6ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

Marathonläufer
ምስል Fotolia/ruigsantos

በግማሽ ማራቶን የወንዶች ፉክክርም ኬንያውያንን መገዳደር አልተቻለም። ማቴው ኪሜሊ በ59 ደቂቃ ከ30 ሰከንድ የአንደኛ ደረጃን ይዞ አሸንፏል። የሀገሩ ልጆች ቤናርድ ኪሜሊ እና አልፍሬድ ባርካህ እንዲሁም አሞስ ኩርጋት ተከታትለው በመግባት ከ2ኛ እስከ 4ኛ ያለውን ቦታ ይዘዋል። ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ታደሰ ታከለ እና ታምራት ቶላ ለጥቂት በኬንያውያኑ ተቀድመው የ5ኛ እና 6ኛ ደረጃን ይዘዋል።

በተቃራኒው በግማሽ ማራቶን የሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያውያቱ ገነው በመውጣት ኬንያውያንን ድል ነስተዋል። አትሌት ትእግስት አሰፋ 1 ሰአት ከ7 ደቂቃ ከ28 ሰከንድ በመሮጥ በአንደኛነት ስታጠናቅቅ፤ የሀገሯ ልጆች አትሌት ቤዛ ዘርዓይ እና ዐይናዲስ መብራቱ 2ኛ እና 3ኛ በመውጣት ለድል በቅተዋል።

እግር ኳስ

የኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች አዳጊ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ደቡብ አፍሪቃን በደርሶ መልስ ውጤት 3-1 በማሸነፍ ወደ መጨረሻው ዙር ማለፍ ችሏል። አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ውስጥ የደቡብ አፍሪቃ ቡድን ትናንት 1 ለ0 ቢያሸንፍም ኢትዮጵያ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ 3 ለ0 ድል አድርጋ በመመለሷ በደርሶ መልስ ውጤት ለማለፍ ችላለች። በመጨረሻው ዙር የደርሶ መልስ ግጥሚያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካሸነፈ ለዓለም ዋንጫ ያልፋል ማለት ነው። በአራተኛው እና የመጨረሻው ዙር የኢትዮጵያ ተጋጣሚ የናይጄሪያ ቡድን ነው። ጋና ከሞሮኮ እንዲሁም ካሜሩን ከተንዛኒያ ጋር የመጨረሻ ዙር ግጥሚያዎች ይከናወናሉ። ከስድስቱ ቡድኖች አሸናፊ ሦስት ቡድኖች አፍሪቃን ወክለው ሕንድ በምታዘጋጀው የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ተሳታፊ ይሆናሉ። እድሜያቸው ከ20 በታች የኢትዮጵያ የሴቶች ቡድንም በድንቅ ብቃት ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ምናልባት እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ቡድናችን ማለፍ ከቻለ ታሪክ ያስመዘግባል ማለት ነው። የደርሶ መልስ ጨዋታዎቹ ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃሉ። ህንድ አዘጋጅ ሀገር በመሆኗ፤ ቻይና ሰሜን ኮሪያ ከውድድሩ በመውጣቷ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 የዓለም ዋንጫውን ማንሳት የቻለችው ጃፓንም ዘንድሮ ለዓለም ዋንጫ ካለፉት ውስጥ ትመደባለች። ኒውዚላንድ፤ ብራዚል፤ ኮሎምቢያ እና ቺሊም ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። ከሰሜን አሜሪካ፤ አውሮጳ እና አፍሪቃ ከእየ አኅጉሩ ሦስት ሦስት ሃገራት ይጠበቃሉ። ኢትዮጵያ አንዱ የመሆን እድሉ አላት።

Frauen Fussball in Tansania
ምስል Muzi Ntombela/empics/picture alliance

ፕሬሚየር ሊግ

ብራዚላዊው ተከላካይ ጋብሪዬል ዶ ሳንቶሽ በጭንቅላት ገጭቶ ባስቆጠረው ግብ አርሰናል በዌስትሀም ሜዳ እጅግ ወሳኝ የሆነ የ2 ለ1 ድል ትናንት አሰመዝግቧል።  የቀድሞ ተጨዋቻቸው የአርሰናል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታን ለገጠሙት የዌስትሀሙ አሰልጣኝ ዴቪድ ሞይስ በተከላካዮቻቸው ስህተት ለሽንፈት መዳረጋቸው እጅግ መሪር ነበር። በትናንቱ ግጥሚያ የአርሰናሉ አጥቂ ኤዲ ንኬቲያህ ወደ ግብ በመጠጋት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን እያደረገ ድንቅ ብቃቱን ዐሳይቷል። በወሳኙ ግጥሚያም አርሰናል ነጥቡን 63 አድርሶ የሻምፒዮንስ ሊግ አራተኛ እና የመጨረሻውን ቦታ ተቆጣጥሯል። ላይስተር ሲቲን ትናንት 3 ለ1 ያሸነፈው ቶትንሀም በአርሰናል የሚበለጠው በ2 ነጥብ ብቻ ነው። ስለዚህ አርሰናል የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስረገጥ ቀሪ 4 ጨዋታዎቹ ላይ ነጥብ ላለመጣል ጥርሱን መንከስ ይኖርበታል።

ትናንት በኤቨርተን የ1 ለ0 ሽንፈት አስተናግዶ የተመለሰው ቸልሲ ቀሪ አራት ጨዋታዎቹ ላይ ነጥብ የሚጥል ከኾነ በቀጣዩ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነት ቦታ ላይኖረው ይችላል ሲሉ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኁል አስጠንቅቀዋል። ቸልሲ 66 ነጥብ ይዞ ከስሩ ያለው አርሰናልን የሚበልጠው በ3 ነጥብ ብቻ ነው። ቶትንሀምን ደግሞ በአምስት።

Coronavirus in Premierleague FC Arsenal Trainer Mikel Arteta
ምስል AFP/G. Kirk

55 ነጥብ ይዞ 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ግን ቀሪ ሦስት ጨዋታዎቹን በመላ ቢያሸንፍ እንኳን ነጥቡን ከ64 ከፍ ማድረግ ስለማይችል ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ የመግባት እድሉ ያከተመ ይመስላል። ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ለመግባት አርሰናል ቀሪ አራት ጨዋታዎቹን በሙሉ ሊሸነፍለት ይገባል። ያ ደግሞ የማይመስል ነው። በዚያ ላይ 61 ነጥብ ይዞ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶትንሀም ከቀሪ አራት ጨዋታዎቹ አንዱን ካሸነፈ የማንቸስተር ዩናይትድ ነገር ያከትማል። አሁን እንኳን 18 የግብ ልዩነት አላቸው። ለአውሮጳ ሊግ ቦታውም ጠንክሮ መሥራት ይኖርበታል። ከምንም በላይ ግን ማንቸስተር ዩናይትድ ዛሬ ማታ ከብሬንትፎርድ ጋር የሚያደርገውን ግጥሚያ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

ድል የራቃቸው የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ራልፍ ራኚክ ግን የአውስትራሊያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንን ለመምራት በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የ2 ዓመት ውል መፈረማቸው ታውቋል።  የዛሬ ሁለት ዓመት የአውስትራሊያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንን ጀርመን ለምታዘጋጀው የአውሮጳ ዋንጫ ማብቃት ይጠበቅባቸዋል። አሰልጣኙ በፕሬሚየር ሊጉ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከ26 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት ዐሥሩን ብቻ ነው። ሊቨርፑል ኒውካስልን 1 ለ0፤ ማንቸስተር ሲቲ ሊድስን 4 ለ0 በማሸነፋቸው ሁለቱም ዋንጫውን ለመውሰድ ግስጋሴያቸውን ቀጥለዋል። ድሉን ለማስረገጥ በቀሪ አራት ጨዋታዎች አንዱ የአንደኛውን ነጥብ መጣል ብቻ ነው የሚጠብቀው።

ቡንደስሊጋ

የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ለመያዝ አንድ ነጥብ ብቻ የሚበለጠው ላይፕትሲሽ ዛሬ ማታ ተስተካካይ ጨዋታውን ያደርጋል። ከቦሩሲያ ሞይንሽንግላድባኅ ጋር በሚያደርገው ግጥሚያው ላይፕትሲሽ ካሸነፈ ነጥቡን 57 በማድረስ በቡንደስሊጋው 55 ነጥብ ይዞ 4ኛ የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታ የያዘውን ፍራይቡርግን ቦታ ያስለቅቀዋል። ላይፕትሲሽ ዛሬ ማታ አቻ ቢወጣ እንኳን የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታውን መረከቡ አይቀርም። ምክንያቱም በነጥብ ተስተካክሎ በግብ ልዩነት ግን ብዙ ስለሚርቅ። ላይፕትሲሽ 33 የግብ ክፍያ ሲኖረው፤ ከበላዩ የሚገኘው ፍራይቡርግ የግብ ክፍያው በግማሽ ያነሰ 16 ነው። ዛሬ ማታ ባዬር ሌቨርኩሰን ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋርም ይጫወታል። ትናንት አውግስቡርግን 4 ለ1 የረታው የቦን ከተማ ተጎራባቹ ኮሎኝ ቡድንም ወደ ሻምፒዮንስሊግ የመግባት እድል አለው። 52 ነጥብ ይዞ 6ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ ከላይፕትሲሽ የሚበለጠው በ2 ነጥብ ብቻ ነው።

RB Leipzig - 1. FC Union Berlin
ምስል Jan Woitas/dpa/picture alliance

በ75 ነጥቡ ተከታዩ ቦሩስያ ዶርትሙንድን በ12 ነጥብ የራቀው ባየርን ሙይንሽን የቡንደስሊጋውን ዋንጫ የፊታችን እሁድ ይረከባል። በእለቱ ወራጅ ቀጣና ግርጌ 16ኛ ላይ ከሚገኘው ሽቱትጋርት ጋር ይጫወታል። ከቀሪ ሁለት ጨዋታዎቹ የመጨረሻውን ግጥሚያ የቅዳሜ ሳምንት ከቮልፍስቡርግ ጋርም ያከናውናል። ምንም እንኳን በኮሮና የተነሳ ላለፉት 2 ዓመታት መሰባሰብ ባይፈቀድም ባየርን ሙይንሽን የእሁድ ሳምንት ግን ደጋፊዎቹ በተገኙበት የዘንድሮ የቡንደስሊጋው አሸናፊነቱን በከተማው እምብርት ማሪዬንፕላትስ አደባባይ እንዲያከብር በሙይንሽን ከተማ መዘጋጃ ቤት ተፈቅዶለታል። ግሮይተር ፊዩርት በመጣበት እግሩ ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን ተመላሽ ነው። ዘንድሮ ወደ ቡንደስሊጋው ያደደገው አርሜኒያ ቢሌፌልድም ለመሰናበት ጫፍ ደርሷል። ሽቱትጋርት ከታችኛው ዲቪዚዮን ሦስተኛ ቡድን ጋር በደርሶ መልስ በሚደረገው የማደግ እና ያለመውረድ ትንቅንቅ ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን ቀጣይ ሁለት ጨዋታዎችን መጠበቅ ይኖርበታል።

Manchester City vs Real Madrid - UEFA Champions League
ምስል David Ramos/Getty Images

ሻምፒዮንስ ሊግ

የሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ የመልስ ግጥሚያዎች ነገ እና ከነገ በስትያ በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከምሽቱ አራት ሰአት ላይ ይከናወናሉ። በሜዳው አንፊልድ 2 ለ0 ድል ያደረገው ሊቨርፑል በነገው እለት ስፔን ካስቴሊዮን አውራጃ ውስጥ በሚገኘው የቪላሪያል ኤስታዲዮ ዴ ላ ሴራሚካ ስታዲየም ይከሰታል።  ቪላሪያል በስፔን ላሊጋ የ7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በአንጻሩ ሊቨርፑል የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን ለመውሰድ ከሚገሰግሰው ማንቸስተር ሲቲ በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጦ የ2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሊቨርፑል ባለፈው ሳምንት ባደረገው ግጥሚያ የበላይነቱን ዐሳይቶ ነበር። በፕሬሚየር ሊጉ ከሚያሳየው ብቃቱ አንጻር ቪላሪያል ሊቨርፑል ላይ ከ2 ግብ በላይ አስቆጥሮ ወደ ፍጻሜው ለማለፍ እጅግ የሚከብደው ይሆናል። ሊቨርፑል ዘንድሮ አራቱን ዋንጫዎች ለመሰብሰብ ጫፍ ላይ ደርሷል። እስካሁን የካራባዎ ዋንጫን በእጁ አስገብቷል። በፕሬሚየር ሊጉም ከማንቸስተር ሲቲ ጋር አንገት ለአንገት ተያይዘዋል። በኤፍ ኤ ካፕ ለፍጻሜ ደርሷል። ነገ ቪላሪያልን ካሸነፈ ደግሞ ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜም ይደርሳል ማለት ነው።

Fußball | Champions League | Manchester City - Real Madrid
ምስል Dave Thompson/AP Photo/picture alliance

ረቡዕ ዕለት ማንቸስተር ሲቲ የስፔኑ ኃያል ሪያል ማድሪድን ለሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታ ለመግጠም ወደ ሳንቲያጎ ቤርናቤው ያቀናል። ሲቲም ማድሪድም የየሀገራቸውን ሊጎች ይመራሉ። በሜዳው ኤታድ ስታዲየም በጠበበ የግብ ልዩነት 4 ለ3 ያሸነፈው ማንቸስተር ሲቲ ብርቱ ፈተና ይጠብቀዋል። ከፊት መስመር አድብቶ የሚጠብቀው የግብ ቀበኛው ካሪም ቤንዜማ እና በክንፍ ተከላካዮችን በፍጥነት እና ታክቲኩ የሚያስጨንቀው ቪንሺየስ ጁኒዮር መከራ የሚሆኑበት ይመስላል። ካሪም ቤንዜማ ማንቸስተር ሲቲ ላይ ያስቆጠረው 3ኛ ግብ በሻምዮንስ ሊግ 14ኛ ግቡ ኾኖ ተመዝግቦለታል። ለማንቸስተር ሲቲም ሪያድ ማሬዝ እና ፊል ፎደን በቀኝ እና ግራ ክንፍ በፍጥነት የሚፈጥሩት ጫናም ለሪያል ማድሪድ አስጨናቂ መሆኑ አይቀርም። በአጭሩ የረቡእ ግጥሚያ ለሁለቱ ቡድኖች የሞት ሽረት ነው ማለቱ ይቀላል።

የሜዳ ቴኒስ

Australian Open Rafael Nadal  beim Spiel
ምስል Andy Brownbill/ASSOCIATED PRESS/picture alliance

የሩስያ እና ቤላሩስ ዕውቅ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾች ከዌምብሌ ውድድር መታገድ በዝነኛ ስፖርተኞች ዘንድ ቅሬታ አጭሯል። የዌምብሌ አዘጋጆች ሩስያ እና ቤላሩስ የአትሌቶቹን ድል ለፕሮፖጋንዳቸው ሊጠቀሙበት ይችላሉ ሲሉ ነው ከዌምብሌይ እና ከሌሎች የብሪታንያ ውድድሮች ያገዷቸው። የተጨዋቾቹ መታገድን ከተቃወሙ ታዋቂ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾች መካከል የስፔኑ ራፋኤል ናዳል ይገኝበታል። ራፋኤል ናዳል ሩስያ ዩክሬንን በመውረሯ ምክንያት የሩስያ እና ቤላሩስ ተጨዋቾችን ከዌንብሌ ውድድር ማገድ «እጅግ ፍትሐዊ አይደለም» ሲል በማድሪድ ውድድር ወቅት በትዊተር ጽፎ ነበር። እንደ ራፋኤል ናዳል ሁሉ ኖቫክ ጄኮቪች እና አንዲ ሙራይም ውሳኔውን ከተቹት ውስጥ ይገኙበታል። የዩክሬን የቀድሞው የቴኒስ ተጨዋች ሠርጌ ስታኮቭስኪ በአንጻሩ የሩስያ ተጨዋቾች መታገድን የተቃወመውን ስፔናዊ ተቃውሞ ትዊተር ላይ ጽፏል። የዩክሬን ሕጻናት የሜዳ ቴኒስ መጫወት አይችሉም፤ የዩክሬን ተጨዋቾችም ወደ ሀገራቸው መመለስ አይችሉም «ያስ ፍትሐዊ ነው ወይ» ሲል ነው ስፔናዊውን ዕውቅ ተጨዋች የተቸው። የዌምብሌ ውሳኔን የዓለም ቴኒስ ማኅበር እና የዓለም ቴኒስ ፕሮፌሽናሎች የወንዶችም የሴቶችም አዘጋጆች ተችተውታል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ