ቡግና ወረዳ ከ79 ሺህ በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ይሻሉ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 14 2017በአሁኑ ጊዜ በወረዳዉ በሚገኙ 16 ቀበሌዎች ከችግሩ ጋር በተያያዘ የሞቱ ሕጻናት ቁጥር አምስት መድረሱን በአካባቢው ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች በሚመራው አስተባባሪ ኮሚቴ ዉስጥ አባል የሆኑት አቶ ፀጋው ታደሰ ይናገራሉ።
የቡግና ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ዓለሙ በበኩላቸዉ በዓለም የምግብ መርሃግብር WFP እና በዩኒሴፍ በኩል የመድኃኒት እና አልሚ ምግብ ለእናቶችና ሕጻናት እየደረሰ ነዉ ብለዋል። በተለይም አካባቢው በተደጋጋሚ በድርቅ የተጎዳ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እየተደረገ ያለዉ ድጋፍ በቂ አይደለም የሚሉት አንድ የአካባቢው ኗሪ በመንግሥት በኩል የሚደረገው ድጋፍ የዘገየ ነው ይላሉ።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽንዲያቆን ተስፋው ባንታብል ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ የኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ለ110 ሽህ ተጠቃሚዎች የምግብ እህል ማጓጓዝ ተጀምሯል ብለው ነበር። ይሁን እንጁ የቡግና ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢምረዉ ሙሌ በመንግሥት በኩል ይደርሳችኋል ከተባለው የምግብ ድጋፍ ውስጥ እስካሁን የደረሰ የለም ነው ያሉት።
አሁን በወረዳው ከተፈጠረው ድርቅና የምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ 79,418 ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸዉ ቢሆንም በመንግሥት በኩል እየመጣ ነው የተባለው 4000 ኩንታል እህል ግን በቂ አይደለም ሲሉ ነው የቡግና ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢምረዉ ሙሌ የሚናገሩት።
ኢሳያስ ገላው
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ