ሰኔ 27 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.
ሰኞ፣ ሰኔ 27 2008ጀርመን በጉዳት እና በቢጫ ካርድ ወሳኝ ተጨዋቾቿ አይሰለፉም። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ኒኮ ሮዝበርግ የቡድኑ ባልደረባ የሆነው ሌዊስ ሐሚልተን ተሽከርካሪን ገጭቶ ለማደናቀፍ ቢሞክርም ማሸነፍ ግን አልቻለም። ድል ወደ ሐሚልተን ዞራለች።
በ103ኛው የቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ኢትዮጵያዊ ብስክሌተኛ ተሳታፊ ኾኗል።
ኢትዮጵያ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1950 አንስቶ ብስክሌተኞችን በኦሎምፒክ ስታሳትፍ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ አስቆጥራለች። ሆኖም እጅግ ከባድ ፉክክር በሚታይበት የቱር ደ ፍሯንስ ተከታታይ ውድድር ላይ ኢትዮጵያዊ ብስክሌተኛ ሲሳተፍ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ይኾናል።
የጣልያኑ ላምፓሬ ሜሪዳ ቡድን ውስጥ ታቅፎ የሚወዳደረው ኢትዮጵያዊ ብስክሌተኛ ጽጋቡ ገብረማርያም ግርማይ ይባላል። ለኦሎምፒክ እንደሚወዳደር የተገለጠው ኢትዮጵያዊ ብስክሌተኛ ጽጋቡ የ20 ዓመት ወጣት ከመሆኑ በፊት በሩዋንዳ የብስክሌት ሽቅድምድም አምስተኛ ደረጃ አግኝቶ ነበር። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2013 ጋቦን በተደረገው ውድድርም አምስተኛ ሲወጣ፤ በታይዋን አጠቃላይ ውድድር የሁለተኛነት ደረጃን መጎናጸፍ የቻለ ብስክሌተኛ ነው።
በቱር ደ ፍሯንስ ውድድር ለመሳተፍ መታጨቱ እንዳስደሰተው የተናገረው ብስክሌተኛ ጽጋቡ «ቱር ደ ፍሯንስ ለእኔ 21 ደረጃ ያለውን ተከታታይ ውድድር መጨረስ ብቻ አይደለም» ብሏል። «ልዩ የሆነ ነገር የመሥራት ጉዳይ ነው። አንዳች ነገር ለማድረግ ደግሞ ዝግጁ ነኝ፤ ለመፋለም ዝግጁ ነኝ» ሲል ለራዲዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል ተናግሯል። ጽጋቡ በዛሬው ውድድር ከ198 ተወዳዳሪዎች 178ኛ ወጥቷል።
የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አማካይ ሳሚ ከዲራ ከፈረንሳይ ጋር ለሚደረገው የአውሮጳ እግር ኳስ የግማሽ ፍጻሜ ውድድር መሰለፍ እንደማይችል አሰልጣኙ ገለጡ። ሳሚ ከዲራ ጀርመን በሩብ ፍጻሜው ጣሊያንን ባሸነፈችበት ጨዋታ በደረሰበት የጡንቻ መለጠጥ እንደማይሰለፍ ለጋዜጠኞች የተናገሩት አሰልጣኝ ዮኣሒም ሎቭ ናቸው።
«ሳሚ ከዲራ በሐሙሱ ጨዋታ በእርግጠኝነት አይሰለፍም። ምናልባት ለፍጻሜ መሰለፍ ይችል እንደሆነ የሚቻለንን እናደርጋለን» ሲሉም አክለዋል አሰልጣኙ። በተመሳሳይ ጨዋታ ጉልበቱ ላይ ጉዳት የደረሰበት አምበሉ ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር ግን ማርሴይ ውስጥ ለሚደረገው ጨዋታ ሊደርስ ይችል ይኾናል ሲሉ አሰልጣኙ ተናግረዋል። አጥቂው ማሪዮ ጎሜዝ ታፋው ላይ ባጋጠመው ጉዳት ከውድድሩ ወጥቷል። ተከላካዩ ማትስ ሑመልስ ቢጫ ካርድ በማየቱ ከፈረንሳይ ጋር በሚደረገው ፍልሚያ መሰለፍ አይችልም።
ጀርመን ከጣሊያን ጋር ያደረገችው የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያ በአቻ በመጠናቀቁ በተጨመረው ሰአትም ግብ ሊቆጠር አልቻለም። አጠቃላይ ጨዋታው መፈራራት የነበረበት ሆኖም ጀርመን የበላይነት ያሳየበት ነበር። አሸናፊውን ለመለየት የተደረገው የመለያ ምት ለብዙዎች እጅግ ልብ ሰቃይ ነበር፤ ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየርም።
«እንዲህ አይነት የመለያ ምት አጋጥሞኝ አያውቅም። በእውነት በጣም ነበር የተራዘመው። ገዱ ለእኛ ነበር። ሁለቱም ግብ ከመሆን ያዳንኳቸው ኳሶች አሁንም ድረስ ከአዕምሮዬ አይጠፉም። አንደኛው ወደላይ ነበር የተመታው። ሌላኛው ደግሞ ሲመስለኝ ግብ ለማስቆጠር በቀጥታ ፊት ለፊት ነበር የተመታው። እናም ቦኑቺ ለሁለተኛ ጊዜ ግብ እንዲያስቆጥርብኝ አልፈለኩም ነበር። የዕድል ነገር ኾኖ ኳሷን ይዤባታለሁ።»
ማኑዬል ኖየር ጣልያኖች ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ባያገቡ ኖሮ ቡድናቸው ወደ መለያ ምት ሳይገባ ያሸንፉ እንደነበር ተናግሯል። ተከላካዩ ጄሮም ቦዋቴንግ ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በእጁ የነካትን ኳስ ትንሽ ዕድለ ቢስ አድርጎናል ሲል ገልጦታል። በተረፈ ግን የበላይነት የነበረው ቡድናችን ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፉ ይገባዋል ብሏል። ቢጫ ካርድ ያየው ተከላካዩ ማትስ ሁመልስ የመለያ ምቱን ለመምታት ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ክልሉ ሲያመራ የተሰማውን እንዲህ ገልጧል።
«ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ክልሉ ስታመራ ጉዞው በእርግጥም እጅግ ይራዘምብሃል። በዚህኛው ጥግ ወይንስ በእዛኛው ጥግ ልምታው እያልክ ደጋግመህ ታሰላስላለህ። ፍጹም ቅጣት ምቱ የመሰናበቻ በመሆኑ በጣም ነበር እፎይታ የተሰማኝ። በፍጹም መሰናበት አይገባንም። ስለዚህ (ቡፎን)በጣቶቹ ጫፎች ብቻ ነክቷት ኳሷ ከመረብ ስታርፍ በጣም ነው የተደሰትኩት። መቼም ትንሽ ዕድል ታክሎበት ነው መግባቱ።»
ዮናስ ሔክቶር በበኩሉ ቡድናቸው በመከላከሉ በኩል ከትንሽ ክፍተት በስተቀር ጥሩ እንደተጫወተ ተናግሯል። «ይልቅስ መጠነኛ ችግር የነበረብን ከወደፊት በኩል ነበር» ብሏል። ከፊት በኩል ሌሎቹ ጨዋታዎች ላይ ያሳየነውን ያኽል በጣም ጠንካራ አልነበርንም ሲልም አክሏል። ከሁሉም በላይ ግን የጀርመን ቡድን ወደ ቀዛዩ ዙር በማለፉ መደሰቱን ገልጧል።
«የዕድል ነገር ሆኖ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈናል። ከ120 ደቂቃ በላይ የፈጀ እጅግ አስቸጋሪ ፍልሚያ ነበር። የቻልነውን ሁሉ አድርገናል። በእርግጥ በኋላ ላይም ማኑዌል ኖየር ኳሷን ግብ ከመሆን በማዳኑ ዕድለኞች ነን።»
ጣሊያንን በመለያ ምት 6 ለ 5 ያሸነፈችው ጀርመን የፊታችን ሐሙስ አዘጋጇ ፈረንሳይን ትገጥማለች። ትናንት ፈረንሳይ አይስላንድን 5 ለ2 ያሸነፈበት ጨዋታ የፈረንሳይ የበላይነት የታየበት ነበር። አይስላንድ እንግሊዝን ከመንገድ ባስቀረችበት ጨዋታ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ያሳየችው የመከላከል ጨዋታ ምናልባትም በፈረንሳይ ይደገም ይሆናል የሚል ግምት ነበር። ሆኖም አይስላንዶች ሜዳው ላይ ብዙም ሳይቆዩ የግብ ክልላቸው በፈረንሳዮች በተደጋጋሚ በመደፈሩ መከላከሉ የማይታሰብ ነበር። የፈረንሳይ እና የጀርመን አሸናፊ ረቡዕ ከሚፋለሙት ፖርቹጋል እና ዌልስ አሸናፊ ጋር እሁድ ለዋንጫ ይገናኛሉ።
የእግር ኳስ ተጨዋቾች የዝውውር ዜና
በማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝነት በኦልትራፎርድ በይፋ ዛሬ ሥራ የጀመሩት ሆሴ ሞሪንኞ የዶርትሙንዱ ሔንሪክ ሚኪታሪያንን ሊያስመጡ እንደሆነ ተዘግቧል። አሰልጣኙ ቀደም ብሎ ተከላካዩ ኤሪክ ባይሊ እና ዝላታን ኢብራሒሞቪችን ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ እንዲፈርሙ አስደርገዋል። ከአሠልጣኝ ሌዊ ቫንጋል የተረከቡትን የማንቸስተር ዩናይትድ ቡድን እንደ አዲስ በማዋቀር ላይ ናቸው ተብሏል።
ማንቸስተር ሲቲን የተረከቡት የቀድሞው የባየር ሙይንሽን አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ደግሞ ከኢልኪ ጉንዶዋን እና ኖሊቶ በኋላ ሦስተኛ ተጨዋች ማስፈረማቸው ተዘግቧል። ማንቸስተር ሲቲ ያስፈረመው በአውሮጳ እግር ኳስ ጨዋታ ወቅት በዓለም አቀፍ ውድድር የመጀመሪያ ግቡን ሩማንያ ላይ ያስቆጠረው ዩክሬናዊው ኦሌክሳንደር ዚንቼንኮን ነው። የ19 ዓመቱ የክንፍ ተጨዋች ለፔፕ ጓርዲዮላ ሦስተኛ ፈራሚ ተጨዋች ሆኗል።
የሊቨርፑል ደጋፊዎች ጀርመናዊ አሠልጣኛቸው ዩርገን ክሎፕ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው አማካይ ማህሙድ ዳሁድን ሊያስመጡ ነው በሚል ደስታቸውን ገልጠዋል። የ20 ዓመቱ ወጣት የሚጫወተው በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ለቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ተሰልፎ ነው።
ስቶክ ሲቲ የቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድ የክንፍ ተጨዋች የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው ናኒን ወደ ፕሬሚየር ሊግ ለማምጣት ጥረት እያደረገ ነው።
ስፔናዊው አጥቂ ፈርናንዶ ቶሬስ ለተጨማሪ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ለመቆየት ለአትሌቲኮ ማድሪድ አዲስ ውል ፈርሟል። ባለፈው የጨዋታ ክፍለጊዜ ፈርናንዶ ቶሬስ ለቡድኑ 44 ጊዜ ተሰልፎ 12 ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።
የመኪና ሽቅድምድም
የመርሴዲስ አሽከርካሪው ሌዊስ ሐሚልተን በትናንቱ የአውስትሪያ የመኪና ሽቅድምድም የመጨረሻ ዙር ላይ በቡድን አባሉ በኒኮ ሮዝበርግ ቢገጭም አሸናፊ ኾኗል። የሐሚልተንን መርሴዲስ የገጨው የሌላኛው መርሴዲስ አሽከርካሪ ኒኮ ሮዝበርግ የ10 ሰከንድ ቅጣት ደርሶበታል። በውድድሩም ኒኮ ሮዝበርግ ማክስ ፈርሽታፐን እና ከኪም ራያከነን ኋላ አራተኛ ወጥቷል። በትናንቱ ድል ሌዊስ ሐሚልተን ከኒኮ ሮዝበርግ ጋር ያለውን አጠቃላይ የነጥብ ልዩነት ወደ 11 ዝቅ ማድረግ ችሏል። ኒኮ እስካሁን 153 ነጥብ ሲሰበስብ፤ ሌዊስ ሐሚልተን 142 ነጥቦች አሉት። ሁለቱ አሽከርካሪዎች በተመሳሳይ የመርሴዲስ ቡድን ውስጥ ሆነው እርስ በእርስ የሚያደርጉት ፉክክር ቡድኑን እንዳይጎዳው አሳስቧል።
የሜዳ ቴኒስ
ሮጀር ፌዴሬር በዊምብልደን የሜዳ ቴኒስ ውድድር አሜሪካዊው ስቴቭ ጆንሰንን በተከታታይ 6-2 6-3 7-5 በማሸነፍ ለሩብ ፍጻሜ አልፏል። ሮጀር ፌዴሬር በቀጣዩ ጨዋታ የክሮሺያው ማሪን ሲሊችን ይገጥማል።
የኮሪያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በቻይና ቤጂንግ ኦሎምፒክ ውድድር ባለድል የነበረው ዋናተኛ ፓርክ ታይ ህዋን የሚታገድ ከሆነ ለሪዮ ኦሎምፒክ እግሩን እንደማያነሳ አስታወቀ። ፓርክ በኦሎምፒክ መስክ በ400 ሜትር ነፃ ቀዘፋ ዋና ለሀገሩ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘ የመጀመሪያው ዋናተኛ ነው። ዋናተኛው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 ዓመት ከመላው የእስያ ጨዋታዎች ውድድር ቀደም ብሎ በተደረገለት ምርመራ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ተጠቅሟል በሚል የ18 ወራት እገዳ ተጥሎበት ነበር።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ