1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ መጋቢት 19 ቀን፤ 2008 ዓ.ም.

ሰኞ፣ መጋቢት 19 2008

በአልጀሪያ ከፍተኛ ሽንፈት የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ይጋጠማል። ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከሶማሌና ከጅቡቲ ጋር ስትጫወት በተመሳሳይ ሰፊ የግብ ልዩነት ታሸንፍ ነበር። በአልጀሪያ ግን ዘንድሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሞታል። ጀርመን በሜዳዋ ባደረገችው የወዳጅነት ጨዋታ በእንግሊዝ ተሸንፋለች።

https://p.dw.com/p/1IKz7
Berlin Deutschland vs England Deutsche Choreographie
ምስል picture-alliance/GES/Helge Prang

ስፖርት፤ መጋቢት 19 ቀን፤ 2008 ዓ.ም.

ብዙዎችን በነካ መልኩ ብሔራዊ ቡድኑ የግብ ጎተራ ኾኗል። እንግሊዝ ስትመራ ቆይታ ጀርመንን በሜዳዋ በርሊን ውስጥ ድል አድርጋለች። ቤልጂየማዊው ብስክሌተኛ በውድድር ወቅት በደረሰበት አደጋ ሕይወቱ አልፋለች። የአንዲ ሙራይ ታላቅ ወንድም በሜዳ ቴኒስ ጣምራ ውድድር በነጥብ አንደኛ ኾኗል።

እንግሊዝ ጀርመንን 3 ለ2 ባሸነፈችበት የቅዳሜ ዕለቱ ጨዋታ ያልተሰለፈው አምበሉ ዋይኔ ሩኒ በቡድኑ የሚኖረው ተስፋ አጠያያቂ ነው ሲሉ በርካታ ተንታኞች ተናግረዋል። በእርግጥ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2004 ዓመት ፖርቹጋል ውስጥ በተከናወነው የአውሮጳ ዋንጫ በ18 ዓመቱ መሰለፍ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ያልተለየው ዋይኔ ሩኒ አሁን በ30 ዓመቱ የመጨረሻው ይኾን? ወደ በኋላ ላይ እንመለስበታለን። በቅድሚያ ኢትዮጵያ ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ከአልጄሪያ ጋር ያደረገችውን ጨዋታ እንቃኝ።

ኢትዮጵያ 7 ለ0 አሸነፈች። ማንን? ሶማሊያን። መቼ? ከዛሬ 47 ዓመት በፊት፤ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1969 ዓመት። ዘመኑ በብዙዎች ዘንድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወርቃማ የሚባልበት ነበር። አልጀሪያ 7 ለ1 አሸነፈች። ማንን? ኢትዮጵያን። መቼ? ዘንድሮ። በርካቶች ዘንድሮ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከምን ጊዜውም በላይ የቁልቁለት ጉዞ ላይ እየተንደረደረ ነው ሲሉ ይደመጣሉ። በብሥራት ኤፍ ኤም 101.1 ሬዲዮ የስፖርት ጥንቅር ዋና አዘጋጅ መንሱር አብዱልቀኒ ግን የተለየ ሐሳብ አለው።

ለአፍሪቃ ዋንጫ ኢትዮጵያ እና አልጀሪያ ከ48 ዓመት በፊት አንስቶ ያደረጓቸውን ሰባት ጨዋታዎች ብንመለከት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደ ዘንድሮው ከባድ ሽንፈት ገጥሞት አያውቅም። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1968 ዓመት መስከረም ወር ላይ ኢትዮጵያ እና አልጀሪያ ተገናኝተው፤ አሸናፊዋ ኢትዮጵያ ነበረች፤ ለዚያውም 3 ለ0። ሁለቱ ሃገራት በ1982 መጋቢት ወር ላይ ዳግም ተገናኙ፤ አልጀሪያ የኢትዮጵያ መረብን መድፈር አልቻለችም፤ ጨዋታው ያለምንም ግብ ነበር የተጠናቀቀው።

በ1994 መስከረም ወር ተገናኙ፤ ሁለቱም ግብ ሳይቆጠርባቸው እንደተከባበሩ ተለያዩ። በዓመቱ በ1995 ሚያዝያ ወር ላይ አልጀሪያ 2 ለ0 አሸነፈች። ከዚያ በኋላ ሁለቱ ሃገራት የዛሬ ሁለት ዓመት ባደረጓቸው የደርሶ መልስ ጨዋታዎች አሸናፊዋ አልጀሪያ ብትሆንም፤ ከ3 ግብ በላይ ማስቆጠር ግን አልቻለችም ነበር። 3 ለ1 እና 2 ለ1 ነበር አልጀሪያ ያሸነፈችው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለፈው ቅዳሜ ብሊዳ አልጀሪያ ውስጥ ከሶማሌ ቡድን ጋር የሚቀራረብ የ7 ለ1 የሽንፈት ዕጣ ስለምን ደረሰው?

ኢትዮጵያ በምትገኝበት የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ምድብ አልጀሪያ በ9 ነጥብ እና በ12 የተጣራ ግብ እየመራ ይገኛል። ሲሸልስ እና ኢትዮጵያ ተመሳሳይ 4 ነጥብ አላቸው። 2 የግብ ዕዳ ያለባት ሲሸልስ 5 የግብ ዕዳ ያለባትን ኢትዮጵያን በልጣ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሰፍራለች። አንዳችም ነጥብ የሌለው ሌሶቶ በአምስት የግብ ዕዳ አራተኛ ነው። የአልጀሪያ ቡድን በአዲስ አበባ ስታዲየም ነገ ከኢትዮጵያ ጋር የመልስ ጨዋታውን ያደርጋል።

የእንግሊዝ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ ሮይ ሆድግሰን ምንም እንኳን ቡድናቸው ጀርመንን በሜዳው 3 ለ2 ድል የነሳው አምበሉ ዋይኔ ሮኒ በሌለበት ቢሆንም፤ የዩሮ 2016 ዋነኛ ተሰላፊ እንደሆነ ግን ዳግም አረጋግጠዋል። የእንግሊዙ አጥቂ ዋይኔ ሩኒ በርሊን ውስጥ በተከናወነው የቅዳሜው ጨዋታ ቀደም ሲል ጉልበቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት የተነሳ መሰለፍ አልቻለም ነበር። እንግሊዝ 2 ለ0 ስትመራ ቆይታ ጀርመንን በሜዳዋ ድል ያደረገችው በወጣት ተጨዋቾችዋ ነው። ለእንግሊዝ ከተቆጠሩት ሦስቱ ግቦች ሁለቱን ያስቆጠሩት የቶትንሐሞቹ ሐሪ ኬን እና ኤሪክ ዲየር ናቸው። የላይስተር ሲቲው ጂሚ ቫርዲም በድንቅ ሁኔታ በቄንጥ አግብቷል። በተከላካይ በኩል ከታየው መሳሳት በስተቀር የእንግሊዝ ቡድን ለዩሮ 2016 አቋሙ ጠንካራ ይመስላል።

በአንፃሩ ወሳኝ ተከላካዩ ጀሮሜ ቦዋቴንግን በጉዳት ያላሰለፈው የጀርመን ቡድን የተከላካይ ክፍሉ አማካዩን ማገናኘት ተስኖት ተስተውሏል። ለጀርመን ሁለቱን ግቦች ቶኒ ክሮስ በቀጥታ አክርሮ በመምታት እንዲሁም ማሪዮ ጎሜዝ በጭንቅላት በመግጨት አስቆጥረዋል። ማሪዮ ጎሜዝ ያስቆጠራት ግብ በዓለም አቀፍ ውድድሩ የ4 ዓመታት ቆይታ የመጀመሪያዋ ግብ ኾና ተመዝግባለታለች። ቀደም ሲል ከመረብ ያሳረፋት ኳስ በመሥመር ዳኛ ስህተት ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽራበታለች።

የዓለም ዋንጫ ባለድሉ የቀድሞው ተጨዋች እና አምበል ሉታር ማቲያስ በጀርመን እና እንግሊዝ የወዳጅነት ግጥሚያ የ19 ዓመቱ ወጣት ዴሌ ዓሊን የዕለቱ ምርጥ ተጨዋች ብሎታል።

ጀርመን ለአውሮጳ ዋንጫ አቋሟን ለመፈተሽ ነገ ከጣሊያን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ታደርጋለች። በእንግሊዝ የደረሰባት ሽንፈት የፈጠረውን ድንጋጤ ለማስወገድ ከጣሊያን ጋር የምታደርገውን ጨዋታ በጥንቃቄ እንደምትመለከተው ተገልጧል። ጣሊያንም ጀርመንም ላለፉት ሁለት የአውሮጳ ዋንጫ የፍጻሜ ውድድሮች መድረስ የቻሉ ናቸው። በእርግጥ በሁለቱም የፍጻሜ ግጥሚያዎች በስፔን ድል ቢሆኑም ማለት ነው። የዛሬ ስምንት ዓመት ጀርመን ለፍጻሜ ከስፔን ጋር ደርሳ 1 ለ0 ተሸንፋለች። ከአራት ዓመት በፊት ደግሞ ጣሊያን ስፔንን ገጥማ 4 ለ0 በሆነ ሰፊ ልዩነት እጅ ሰጥታለች።

ለጣሊያኑ ጁቬንቱስ የሚጫወተው የጀርመኑ አማካይ ሳሚ ከዲራ በነገው ጨዋታ ሀገሩ ጣሊያንን እንደምታሸንፍ ባለሙሉ ተስፋ ነው። «የነገውን ጨዋታ ስኬታማ ለመሆን እንጥራለን። ጀርመን ከጣሊያን ጋር የምታደርገው ጨዋታ ምንጊዜም የሚጠበቅ ነው። በጉጉት ነው የምንጠብቀው» ብሏል።

የስዊድኑ አጥቂ ዝላታን ኢብራሒሞቮች የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቡድኖች ተሰልፎ ከሚጫወትበት ከፓሪስ ሴንጀርሜይን ቡድን ሊያስፈርሙት መፈለጋቸውን ገለጠ። የ34 ዓመቱ አጥቂ ከማንቸስተር ዩናይትድ፣ ከቸልሲ አለያም ከአርሰናል ለአንዱ ሊፈርም እንደሚችል እየተነገረ ነው።

የላይስተር ሲቲው ጂሚ ቫርዲ
የላይስተር ሲቲው ጂሚ ቫርዲምስል Getty Images/L. Griffiths
ኢትዮጵያውያን ኳስ አፍቃሪዎች
ኢትዮጵያውያን ኳስ አፍቃሪዎችምስል DW/H. Turuneh

ዝላታን ከፓሪስ ሴንጀርሜይን ቡድን ጋር የገባው ውል ሊጠናቀቅ አንድ ወር ከግማሽ ብቻ ነው የሚቀረው። ውሉ እንዳበቃም ከፓሪስ ሴንጀርሜይን እንደሚለቅ እና ፈረንሳይ ውስጥም እንደማይቆይ ፈረንሣዮች የሚታወቁበትን እና የሚኮሩበትን መዲናይቱ ፓሪስ ውስጥ የሚገኘው የአይፍል ማማን በማጣቀስ አስረግጦ ተናግሯል። «የአይፍል ማማን በእኔ ሐውልት ከቀየሩት ያኔ እዚሁ እቀራለሁ» ሲል ፈረንሣይ የመቆየቱ ነገር የማይታሰብ መሆኑን በማያወላዳ መልኩ ገልጧል።

ዝላታን ኢብራሒሞቪች አውሮጳ ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ አራት ሃገራት የሊግ ቡድኖች ተሰልፎ ለአራቱም ዋንጫ ማስገኘት ችሏል። የሆላንዱ አያክስ ሁለት ጊዜ ዋንጫ እንዲያገኝ ካደረገ በኋላ፤ በጣሊያን ሴሪ አም ጁቬንቱስ ሁለት ጊዜ ዋንጫውን እንዲጨብጥ አስችሏል። የጁቬንቱስ ሁለቱም ዋንጫዎች ግን በሀገሪቱ በተከሰተው እና ካልቾፖሊ በተሰኘው የእግር ኳስ ቅሌት የተነሳ ተነጥቋል።

የስዊድኑ አጥቂ ዝላታን ኢብራሒሞቮች
የስዊድኑ አጥቂ ዝላታን ኢብራሒሞቮችምስል picture-alliance/dpa/BPI/J. Garcia

በነገራችን ላይ፦ ካልቾፖሊ የዛሬ ዐሥር ዓመት በጣሊያን ፖሊስ ይፋ የሆነ የእግር ኳስ ቅሌት ነው። በወቅቱ ዋነኞቹ የጣሊያን ቡድኖች የሚፈልጉት ዳኛ እንዲያጫውታቸው በተደጋጋሚ የሚያደርጉት የስልክ ንግግር መረብ በፖሊስ መጠለፍ ቅሌቱ ይፋ እንዲሆን አስችሏል። እዛው ጣሊያን ውስጥ ዝላታን ኢብራሒሞቪች ከኢንተር ሚላን ጋር ተሰልፎ ሦስት ዋንጫዎችን ማሸነፍም ችሏል።

ከዚያም ወደ ስፔን በማቅናት የላሊጋውን ዋንጫ ከባርሴሎና ጋር ድል ማድረግ ተሳክቶለታል። የድል መዝሙሩንም እየዘመረ ተመልሶ ያቀነው ወደ ጣሊያን ነበር። ጣሊያን ውስጥ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2011-2012 በተደረገው የሴሪኣ ግጥሚያ ኤስ ሚላንን ለዋንጫ ባለቤትነት አብቅቶታል። ያኔ ለእሱ በተከታታይ ስምንተኛ ዋንጫው ነበር።

ከአንዱ ሀገር ወደሌላኛው ሀገር ቡድኖች እያቀያየረ በሄደበት ሁሉ የዋንጫ ባለቤት የሚሆነው ስዊድናዊ አጥቂ፤ በመቀጠል ከጣሊያን ወደ ፈረንሣይ ነበር ያቀናው። እዚያም የፓሪስ ሴንጄርሜይን መለያን ለብሶ በመሰለፍ ቡድኑ ላለፉት አራት የፍፃሜ ጨዋታዎች አሸናፊ በመሆን አራት ዋንጫዎችን በተከታታይ እንዲሰበስብ አብቅቷል።

ፓሪስ ሴንጀርሜይን የእግር ኳስ ቡድን
ፓሪስ ሴንጀርሜይን የእግር ኳስ ቡድንምስል picture-alliance/dpa/Y. Valat

በዘንድሮው የፈረንሣይ ሊግ ግጥሚያ ቡድኑ ፓሪስ ሴንጄርሜይን ትሮይን 9 ለ0 ባደባየበት ጨዋታ አራቱ ግቦች የዝላታን ኢብራሒሞቮች ናቸው። ይኽን ድንቅ ግብ አዳኝ ነው እንግዲህ እነ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ቸልሲ እና አርሰናል የተረባረቡበት። የ34 ዓመቱ አጥቂም አንደኛቸው ጋር እንደሚያቀና ገልጧል። «ለአሁኑ ፓሪስ ሴንጄርሜይን ውስጥ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን አልቆይም። እዚህ የአንድ ወር ተኩል ጊዜ ይቀረኛል» ሲል ተናግሯል። የዝላታን ኢብራሒሞቪች ቀልብ የትኛው የእንግሊዝ ቡድን ላይ እንደሚያርፍ ባይታወቅም በቅርቡ ግን በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ላይ በግዙፍ ሰውነቱ እየተሯሯጠ ግብ ሲያድን ማየታችን አይቀርም።

ቤልጂየማዊው ብስክሌተኛ አንቶኒ ዴሞቲ ትናንት ቤልጂየም ውስጥ በተከናወነው የብስክሌት ውድድር በደረሰበት አደጋ ሐኪም ቤት ውስጥ ሕይወቱ አለፈች። በ150 ኪሎ ሜትር የትናንቱ የብስክሌት ፉክክር በተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭት የ25 ዓመቱ ወጣት ብስክሌተኛ ሕይወቱ ያለፈችው በሞተር ብስክሌት ራስ ቅሉ ላይ በመገጨቱ ነበር። የቤልጂየም የሀገር ውስጥ የቀድሞ ባለድል የንስ ዴቡሼርም በደረሰበት የግጭት አደጋ በሕክምና ላይ እንደሚገኝ ተጠቅሷል።

በወንዶች የሜዳ ቴኒስ ጣምራ ውድድር የሁለት ጊዜያት የዓለም ባለድሉ አንዲ ሙራይ ታላቅ ወንድም ጂሚ ሙራይ በኮምፒውተር ቅንብር ስሌት መሠረት የዓለማችን ቁጥር አንድ ተጨዋች ለመሆን በቃ። ጂሚ ሙራይ ትናንት አንደኛ የሆነው ሳይወዳደር ነው። አንደኛ የወጣበትም ምክንያት ቀደም ሲል በኮምፒውተሩ ስሌት መሠረት የአንደኛነት ነጥብ የነበረው ብራዚላዊው ማርሴሎ ሜሎ ተሸንፎ ነጥብ በመጣሉ ነው።

ማርሴሎ ነጥብ በመጣሉ ከነበረበት የአንደኛነት ደረጃ ወደ ሁለተኛነት ዝቅ ብሎ ቦታውን ለጂሚ ሙራይ አስረክቧል። የ30 ዓመቱ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች የዓለማችን ቁጥር አንድ ጣምራ ውድድር አንደኛ ለመሆን ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን አከናውኗል። ቀደም ሲልም ጂሚ ሙራይ ታናሽ ወንድሙን አንዲ ሙራይን በነጠላ ግጥሚያ አሸንፎት ነበር።

ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ