ስፖርት፤ መጋቢት 25 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.
ሰኞ፣ መጋቢት 25 2009ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ባደረጓቸው ውድድሮች ትናንት ድል ቀንቷቸዋል። ጀርመን ውስጥ በሁለት ከተሞች ማለትም በመዲናዪቱ በርሊን የግማሽ ማራቶን ሲከናወን በቦን ደግሞ የግማሽም የ42 ኪሎ ሜትርም ውድድር ነበር። በበርሊኑ የግማሽ ማራቶን ታዳጊ ኢትዮጵያውያን ተሳታፊ ነበሩ። የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለሚካኤል አትሌቶቹን በውድድር ቦታው በመገኘት አነጋግሯቸዋል። ወደዚያ ከማቅናታችን በፊት ግን ቦን ከተማ ውስጥ ወደተደረገው የማራቶን ሩጫ እንሻገር።
ትናንት ቦን ከተማ ውስጥ ከ200 ሺህ በላይ ታዳሚዎች በተገኙበት የማራቶን ሩጫ 13 ሺህ አትሌቶች ተሳታፊ ነበሩ። በውድድሩ ያለፈው ዓመት አሸናፊ ኬኒያዊው ኤድዊን ኮስጌይ አለያም ኢትዮጵያዊው ዘመኑ ወቅርነህ እንደሚያሸንፉ በብዙዎች ዘንድ ተጠብቆ ነበር። ኾኖም ውድድሩ በኬንያዊው አትሌት የ2:13:44 ሩጫ አሸናፊነት ተጠናቋል። ዘመኑ ሌላኛው ኬንያዊሆሴ ቱዌይን በመከተል በሦስተኛነት አጠናቋል። ትናንት የቦን ከተማ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ የአየር ጠባዩ አመቺ የሚባል ነበር። ዘመኑ ከኬንያዊው አሸናፊ 10 ደቂቃ ከ19 ሰከንድ ዘግይቶ ነበር የገባው። ያሸንፋል ተብሎ በተጠበቀበት ውድድር ሦስተኛ የወጣበትን ምክንያት ሲያብራራ ከ10 ሰአት በላይ በረራ በማድረጉ፣ ለሁለት ቀናት በጉዞ ላይ መሆኑ እና ረፍት አለማግኘቱ ተጽንኦ እንደፈጠሩበት ገልጧል።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደ ማራቶን ባሉ ጉልበት በሚጠይቁ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ሲነሱ በረዥም ርቀት ጉዞ የመጉላላታቸው ነገር ሊታሰብበት ይገባል። በቦን ማራቶን የሴቶች ፉክክር አሸናፊ የኾነችው ኬንያዊቷ ፕሪስካ ኪፕሮኖ ናት። የባለፈው ዓመትም አሸናፊ እሷው ነበረች።
ትናንት ለስለስ ባለው የቦን ከተማ ጸሓያማ ቀን የማራቶን ሩጫ ሲከናወን ነፋሻማ በሆነው በርሊንም የግማሽ ማራቶን ፉክክር ነበር። በበርሊኑ 37ኛው የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር ከ106 ሃገራት የተውጣጡ 34,000 አትሌቶች ተሳታፊ ነበሩ። 250.000 ሺህ የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎችም ውድድሩንም በተለያዩ አውራጎዳናዎች በመታደም ተከታትለዋል። 21 ኪሎ ሜትር የፈጀው ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበሩ አትሌቶችንም አበረታትተዋል። ገና በለጋ ዕድሜያቸው በበርሊን ግማሽ ማራቶን ላይ የመሳተፍ ዕድል ያገኙትን ኢትዮጵያውያን ታዳጊ አትሌቶች፦ ቤተልሔም ዘሪሁን እና ጋዲሳ ዘውዱን የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለሚካኤል አነጋግሮ ዘገባ ልኮልናል።
ከበርሊን ግማሽ ማራቶን እና ከቦን የማራቶን ሩጫ ውድድር ባሻገር በሮም ከተማም በዝናማማ የአየር ጠባይ ኢትዮጵያውያን አሸናፊ ኾነዋል። በወንዶች ፉክክር 2:07:30 በመሮጥ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሹራ ቂታታ አሸናፊ ለመሆን ችሏል። ሲከታተሉት የነበሩት ሁለት ኬንያውያን አትሌቶች ዶሚኒክ ሩቶ እና ቤንጃሚን ቢቶክ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል። በሴቶች ተመሳሳይ ውድድርም አሸናፊ የኾነችው ኢትዮጵያዊቷ ራህማ ጡሳ ስትሆን ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 2:27:21 ነበር። ኢትዮጵያውያቱ አትሌት መስተዋት ታደሰ እና አበባ ተክሉ ተከትለዋት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል።
ሮም ከዛሬ 57 ዓመት በፊት ባስተናገደችው የኦሎምፒክ ውድድር ጀግናው አበበ ቢቂላ በማራቶን ዘርፍ በባዶ እግሩ በመሮጥ በወቅቱ ባስመዘገበው ውጤት ማራቶን እና ኢትዮጵያ ከከተማዪቱ ጋር ተቆራኝተው ቀርተዋል። የኢትዮጵያውያኑ የትናንቱ አመርቂ ውጤት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በከተማዪቱ የነበረውን ድል አስታውሷል።
ከዚሁ ከአትሌቲክስ ውድድር ሳንወጣ፥ ትናንት በካሊፎርኒያ በተከናወነው የ5000 ሜትር የሩጫ ፉክክር የኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ባለቤቱ ኢትዮጵያዊው አትሌት ደጀን ገብረመስቀል ለአምስተኛ ጊዜ አሸናፊ ኾኗል። የገባበት ሰአት 13:27 ነበር።
እግር ኳስ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት አርሰናል ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ባደረገው ግጥሚያ ሁለት እኩል በመለያየት ነጥብ ጥሏል። አርሰናል 51 ነጥብ ይዞ ከሚገኝበት ስድስተኛ ደረጃ ወደላይ ፈቅ ለማለት ቀሪ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎቹን በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ያም ብቻ አይደለም፤ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የቀሩት ማንቸስተር ዩናይትድ እንዲሸነፍም መጸለይ አለበት። ማንቸስተር ዩናይትድ ነገ የሚጋጠመው ሰባተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ኤቨርተን ጋር ነው። የፊታችን እሁድ የሚገጥመው ደግሞ 20 ነጥብ ይዞ የደረጃ ሠንጠረዡ ጥግ 20ኛ ላይ ከሚያጣጥረው ሰንደርላንድ ጋር ነው።
በትናንቱ ጨዋታ የደረጃ ሰንጠረዡ ታች የሚገኙት ሚድልስቦሮው እና ስዋንሲ ሲቲም ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። ቅዳሜ ዕለት ኤቨርተንን 3 ለ1 ያሸነፈው ሊቨርፑል 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከስሩ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የቀረው ማንቸስተር ሲቲ ይገኛል። 58 ነጥብ ይዞ በሊቨርፑል በአንድ ነጥብ ይበለጣል። መሪው ቸልሲ በክሪስታል ፓላስ 2 ለ1 በመረታቱ በ69 ነጥቡ ተወስኗል፤ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኘው ቶትንሀም አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል። በርንሌይን ቅዳሜ ዕለት 2 ለ0 የሸኘው ቶትንሀም 62 ነጥብ አለው።
በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይኒክ 65 ነጥብ እና 54 የተጣሩ ግቦች ይዞ እየገሰገሰ ነው። ላይፕትሲክ በ52 ነጥብ እና 19 የግብ ክፍያ ይከተላለዋል። ሆፈንሀይም በ48 ነጥብ ሦስተኛ ሲሆን፤ ቅዳሜ እለት ከሻልከ ጋር አንድ እኩል የተለያየው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባየር ሙይኒክ ከሆፈንሀይም ጋር ነገ ማታ ይጋጠማል። ዶርትሙንድ 14ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው የሰሜን ጀርመኑ ሐምቡርግ ጋር የሚያደርገው ግጥሚያም ነገ ማታ በተመሳሳይ ሰአት ይከናወናል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ