ስፖርት፤ መጋቢት 30 ቀን፣ 2011 ዓ.ም
ሰኞ፣ መጋቢት 30 2011የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለጃፓኑ የኦሎምፒክ ውድድር ለመሳተፍ በድል ጎዳና እየገሰገሱ ነው። ዩጋንዳን በደርሶ መልስ 4 ለ2 የረቱት ሉሲዎቹ ከምዕራብ አፍሪቃዊቷ ካሜሩን ጠንካራ ተፎካካሪዎች ጋር ይፋለማሉ። በዩጋንዳው ጨዋታ ግብ ያስቆጠረችው አጥቂን ቃለ መጠይቅ አድርገናል። ጨዋታው ላይ ዳሰሳ ያደረገ የስፖርት ተንታኝ ሐሳብም አካተናል። የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ በኤፍ ኤ ካፕ ድሉ ማግስት ለሻምፒዮንስ ሊግ ወሳኝ ፍልሚያ ራሱን እያዘጋጀ ነው። በፕሬሚየር ሊጉ ዋነኛ ተፎካካሪው ሊቨርፑልም ነገ ምሽት በተመሳሳይ ሰአት ለሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ ወሳኝ ጨዋታውን ያከናውናል። በጁጂትሱ የትግል ስፖርት ኢትዮጵያውያን ተፋላሚዎች ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ሜዳሊያዎችን አስገኝተዋል። በአፍሪቃ የመረብ ኳስ ጨዋታ ከኢትዮጵያ ሁለት ቡድኖች ተካፋይ ኾነውዋል።
በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ የእግር ኳስ ግጥሚያ ቅዳሜ እለት ብራይተንን 1 ለo ያሸነፈው ማንቸስተር ሲቲ ለሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ ከሀገሩ ቡድን ቶትንሀም ጋር ነገ ማታ ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናል። ሌላኛው የእንግሊዝ ቡድን ሊቨርፑል ከፖርቹጋሉ ፖርቶ ቡድን ጋር ነገ ምሽት በተመሳሳይ ሰአት ለሩብ ፍጻሜ ይጫወታል። በፕሬሚየር ሊጉ ሊቨርፑል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ሲቲን በኹለት ነጥብ በልጦ ይገኛል፤ 82 ነጥብ ሰብስቧል።
የእንግሊዙ ማንቸስተር ዩናይትድ ከስፔኑ ኃያል ባርሴሎና፤ እንዲሁም ሌላኛው የስፔን ተፋላሚ አያክስ ከጣሊያኑ ጁቬንቱስ ጋር በሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ የሚጋጠመው ረቡዕ ምሽት በተመሳሳይ ሰአት ነው።
በሊቨርፑል የ3 ለ1 የደርሶ መልስ ሽንፈት ከሻምፒዮንስ ሊጉ የተሰናበተው የጀርመኑ ባየር ሙይንሽን በቡንደስሊጋው ዋነኛ ተፎካካሪው ቦሩስያ ዶርትሙንድን ቅዳሜ እለት ጉድ አድርጎታል። ባየር ሙይንሽን ዶርትሙንድን የጎል ጎተራ ባደረገበት ጨዋታ ያሸነፈው 5 ለ0 ነበር። የደረጃ ሰንጠረዡንም በአንድ ነጥብ በልጦ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ተረክቧል። ባለፉት ተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ኹለት ጊዜ ሽንፈት የገጠመው ቦሩስያ ዶርትሙንድ 63 ነጥብ አለው።
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከአንድ ዓመት በኋላ በጃፓን በሚካሄደው የበጋ ኦሎምፒክ ውድድር ተካፋይ ለመኾን የመጀመሪያ ደረጃ ማጣሪያውን አልፏል። ቡድኑ አሁን በኹለተኛው ዙር የማጣሪያ ውድድር የሚገጥመው የካሜሩንን ቡድን ነው። በካምፓላ ከተማ ፊሊፕ ኦሞንዲ ስታዲየም ውስጥ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረችው ለብሔራዊ ቡድኑ በአጥቂ መስመር ተሰላፊዋ የኾነችው ሎዛ አበራን በስልክ አነጋግረናታል። ብሔራዊ ቡድኑ ለድል የበቃው ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በመላ ተቋቁሞ እንደኾነ ተናግራለች።
የእግር ኳስ ስፖርት ተንታኙ ዖምና ታደለ ብሔራዊ ቡድኑ ከዚህ ቀደም ያከናወናቸውን ጨዋታዎች እንዲሁም የቀጣይ ተጋጣሚው የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን ወቅታዊ ኹኔታን በመገምገም ቀጣዩን ብሏል።
ሌላው ባሳለፍነው ሳምንት ለኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች ደማቅ ድል ኾኖ የተመዘገበው ኢትዮጵያውያን ተፋላሚዎች በአፍሪቃ የጁጂትሱ ትግል ስፖርት አራት ሜዳሊያዎችን ማስመዝገባቸው ነው። ሞሮኮ ማራኬሽ ከተማ ቤንጒረር ውስጥ የተከናወነው የጁጂትሱ የአፍሪቃ ፉክክር ላይ አትሌት ያሬድ ንጉሤ በሁለት የውድድር ዘርፎች የወርቅ እና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ኾኗል። ያሬድ ቪዬና ኦስትሪያ፣ ፖላንድ እንዲሁም ዱስልዶርፍ ጀርመንን በመሳሰሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ልምድ ያካበተ አትሌት ነው።
በሴት ተወዳዳሪዎች ዘርፍ ደግሞ መስከረም ዓለማየሁ ነጋሽ በኹለት የውድድር ዘርፎች የብር እና የነሐስ ሜዳሊያዎች አስገኝታለች። የወርቁም ኾነ የብር ሜዳሊያው በኢትዮጵያ የጁጂትሱ ስፖርት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘ መኾኑ ተገልጧል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የጁጂትሱ ስፖርት ማኅበራት የተውጣጡት የአዲስ አበባው ተፎካካሪ ወንድሙ ደሳለኝ እና የአዋሳው ተፋላሚ ምንሊክ መሥፍን ሜዳሊያ ባያስገኙም ብርቱ ተፎካካሪ እንደነበሩ ተጠቅሷል። አትሌቶቹ በሞሮኮው ውድድር ታላቅ ልምድ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። በሞሮኮው ውድድር ከዐሥር ሃገራት የተውጣጡ 191 አትሌቶች ተሳታፊ ነበሩ።
የሞሮኮ ፌዴሬሽን እና ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያውያኑን አትሌቶች የመጓጓዣ፣ የመኝታ እና ሌሎች ወጪዎችን እንደሸፈኑ ተገልጧል። ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባት የኢትዮጵያ ጁዶ ጁጂትሱ ፌዴሬሽንን ለመመስረትም ጥረት እየተደረገ መኾኑን ለዶይቸ ቬለ (DW) የፖርት ክፍል የደረሰን መረጃ ይጠቁማል።
ላለፉት ሁለት ሳምንታት በመቐለ ሲካሄድ የሰነበተው 3ኛው የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች የስፖርት ሻምፒዮና ባሳለፍነው ቅዳሜ ተጠናቋል። በኦሎምፒክ፣ ፓራ ኦሎምፒክና ባህል ስፖርቶች ሲካሄድ የሰነበተው ሀገር አቀፍ የስፖርት ውድድሩ ከሰባት ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ3500 በላይ ስፖርተኞች ተሳትፈውበታል። የውድድሩ አዘጋጆች እንደገለፁት፣ በተለይም በኦሎምፒክና እግርኳስ ስፖርቶች በርካታ ተስፋ የሚጣልባቸው ተማሪ ስፖርተኞች በውድድሩ መታየታቸው ተገልጧል።
በኦሎምፒክ ውድድሮች ኦሮምያ ክልል 58 የወርቅ ሜዳልያዎች በማግኘት ውድድሩን በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ፣ አማራ ክልል 50፣ ትግራይ 34 ወርቅ ሜዳልያዎች በማግኘት ተከታታይ ደረጃዎች ይዘዋል። በፓራ ኦሎምፒክ ስፖርቶች ኦሮምያ በአጠቃላይ 83 ሜዳልያዎች በማግኘት የበላይ ሲሆን፣ አማራ 39፣ ትግራይ 38 ሜዳልያዎች በማስመዝገብ ተከታትለው ውድድሩ ጨርሰዋል። ሌላው ስፖርተኛ ተማሪዎቹ የተሳተፉበት ውድድር የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ናቸው። በዚሁ ውድድር የአማራ ክልል ባህል ስፖርት ተወዳዳሪዎች 8 ወርቅ ሜዳልያ በማስመዝገብ ቀዳሚ ሆነው ያጠናቀቁ ሲሆን፣ ትግራይና አዲስ አበባ ተከታዮቹ ደረጃዎች ይዘዋል።
በመዝግያው ዕለት በተካሄደው የወንዶች እግርኳስ ፍፃሜ ኦሮምያ ደቡብ ክልልን አንድ ለባዶ በመርታት አሸናፊ ኾኗል። በአጠቃላይ ኦሮምያ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ ሲሆን አማራ ሁለተኛ ትግራይ ሶስተኛ በመሆን ውድድራቸው አጠናቀዋል። የፀባይ ዋንጫው ለአዲስ አበባ ተበርክቷል።
በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች የስፖርት ሻምፒዮና በርካታ ተተኪ ስፖርተኞች የሚፈሩበት መኾኑን አዘጋጆቹ ለዶይቸ ቬለ (DW) ገልፀዋል። ከሁለት ዓመት በኋላ የሚደረገው 4ኛ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ስፖርት ሾምፒዮና ኦሮምያ ክልል እንዲያዘጋጅ መመረጡ በመዝግያው ዕለት ይፋ መደረጉን የመቀሌው ወኪላችን ሚልዮን ኃይለ ሥላሴ የላከልን የጽሑፍ ዘገባ ይጠቁማል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ