ስፖርት፤ ሚያዝያ 10 ቀን፤ 2008 ዓ.ም.
ሰኞ፣ ሚያዝያ 10 2008
ሚያዝያ 10 ቀን፤ 2008 ዓ.ም. በተከናወነው የቦስተኑ የማራቶን የሩጫ ውድድር በወንድም በሴትም ኢትዮጵያውያን አሸናፊ ሆነዋል። በሴቶች ፉክክር አፀደ ባይሳ አንደኛ ወጥታለች። የገባችበት ሰአት 2:29:19 ነው። ቲርፊ ጸጋዬ ሁለተኛ ወጥታለች። በወንዶች ፉክክር ኢትዮጵያውያኑ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው ገብተዋል። ኃይሌ ለሚ ብርሃኑ አንደኛ የገባበት ሰአት 2:12:45 ነው። ሌሊሳ ዴሲሳ እና የማነ አዳነ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል።
በሐምቡርጉ ማራቶን ተስፋዬ አበራ እና መሰለች መልካሙ ትናንት አሸንፈዋል። አስቸጋሪ ንፋስ ባይኖር የውድድሩ ክብር ወሰን ሊሰበር ይችል ነበር ተብሏል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ግብ አዳኙ የሌስተር ሲቲ አጥቂ ጂሚ ቫርዲ ከሜዳ በቀይ ተሰናብቷል። ተጨማሪ ቅጣት ሊጠብቀው ይችል ይሆናል። ሊቨርፑል ተጋጣሚውን ድል አድርጎ ለአውሮጳ ሊግ የማለፍ ዕድሉን አስፍቷል። አርሰናል ነጥብ ጥሏል። ቸልሲ በማንቸስተር ሲቲ በሰፋ የግብ ልዩነት 3 ለ0 ተሸንፏል ተሸንፏል። በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና በተከታታይ ለሦስተኛ ጊዜ እጅ ሰጥቷል። አትሌቲኮ ማድሪድ አጋጣሚውን በመጠቀመ በነጥብ ከባርሴሎና ጋር መስተካከል ችሏል። በመኪና ሽቅድምድም ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ ለሦስተኛ ጊዜ በተከታታይ አሸንፏል፤ የዘንድሮውን የዓለም ውድድር የማሸነፍ ዕድሉ ሰፊ ነው ተብሎለታል።
የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፤ የጀርመን ቡንደስ ሊጋ እና የስፔን ላሊጋ ጨዋታዎች አበይት ክስተቶችን እንቃኛለን። በቅድሚያ ግን ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ሐምቡርግ ጀርመን ውስጥ ያስመዘገቡትን ድል እናስቀድም።
ትናንት ሰሜናዊ ጀርመን ሐምቡርግ ከተማ ውስጥ በተከናወነው የማራቶን ሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያኑ ሯጮች በወንድም በሴትም ድል ቀንቷቸዋል። በሴቶች ፉክክር አሸናፊ የሆነችው መሰለች መልካሙ ናት። መሰለች ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 2:21:54 ነው። መሰለች የገባችበት ሰአት በሐምቡርግ ማራቶን ከተመዘገበው ክብርወሰን ከ2 ደቂቃ ከፍ ያለ ነበር።
በወንዶች ተመሳሳይ የሩጫ ውድድር ተስፋዬ አበራ 2:06:58 በመሮጥ አንደኛ ሆኗል። በሦስት ወራት ልዩነት በማራቶን ሩጫ ሲያሸንፍ የሐምቡርጉ ሁለተኛው ነው። ቀደም ሲል በዱባዩ ማራቶን 2:04:23 በመሮጥ አንደኛ ወጥቶ ነበር። ሁለቱም ኢትዮጵያውያን የማራቶን ሯጮች ከ109 ቀናት በኋላ በሪዮ ዴጄኔሮ ብራዚል በሚካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ጠንካራ ውጤት ለማስመዝገብ ተስፋ አድርገው ነበር። ሆኖም በወቅቱ የነበረው ነፋሻ አየር የፈለጉትን ያህል ሰአት ሊያስመዘግቡ እንዳላስቻላቸው ተገልጧል።
በሐምቡርጉ የሴቶች ማራቶን ሩጫ ውድድር ሁለተኛ የወጣችውም የቀድሞ ባለድሏ መሠረት ኃይሉ ናት። የገባችበት ሰአት 2:26:26 ነው። የሦስተኛነቱን ቦታ በሚያስደንቅ ሁኔታ ጀርመናዊቷ ሯጭ አኒያ ሼርል መያዝ ችላለች።
በወንዶች ፉክክር ተስፋዬ አበራን በመከተል ሁለተኛ እና ሦስተኛ የወጡት ኬንያውያኑ ፊሊሞን ሮኖ እና ጆስፋት ኪፕሮኖ ናቸው።
እግር ኳስ
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የእግር ኳስ ፉክክር መሪው ባየርን ሙይንሽን ተጋጣሚውን 3 ለ0 ድል አድርገዋል። በ7 ነጥብ ልዩነት ከሥሩ የሚከተለው ቦሩስያ ዶርትሙንድም በተመሳሳይ ውጤት ተጋጣሚውን ድል ነስቷል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ትናንት ከሐምቡርግ፤ ባየርን ሙይንሽን ደግሞ ከትናንት በስትያ ከሻልከ ጋር ነበር የተጋጠሙት።
78 ነጥብ ይዞ ቡንደስሊጋውን ለሚመራው ባየርን ሙይንሽን ቀዳሚዎቹን ሁለት ግቦች ያስቆጠረው ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ነው። በእለቱ ግጥሚያ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ የነበረው አርቱሮ ቪዳል ማሳረጊያዋን ሦስተኛ ግብ በ73ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።
ቦሩስያ ዶርትሙንድ በዐሥር ተጨዋቾች የተወሰነው ሐምቡርግን ትናንት 3 ለ0 ባሸነፈበት ጨዋታ የ17 ኦመቱ ወጣት ክሪስቲያን ፑልሲች በቡንደስሊጋው የመጀመሪያ ሆኖ የተመዘገበለትን ግብ አስቆጥሯል። የሐምቡርጉ ግብ ጠባቂ ሬኔ አድለር በ52ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተው ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል አልፎ ሺንጂ ካጋዋን ጠልፎ በመጣሉ ነበር። አጋጣሚውን ተጠቅሞ በሰፋ ልዩነት ድል ያደረገው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ነጥቡን 71 ማድረስ ችሏል።
በአጠቃላይ ውጤቱ የተደሰቱት የቦሩስያ ዶርትሙንድ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኅል በጨዋታው ወቅት ድክመት ያሉትንም አልሸሸጉም።
«በጥቅሉ ተደስቻለሁ። በእርግጥ የተወሰኑ ግራ መጋባቶች እና ጥንቃቄ አልባ ስህተቶች ነበሩ። ለምሳሌ ማኒ ቤንደር ለጥቂት 1 ለ0 ዋጋ አስከፍሎን ነበር። በዚህም አለ በዚያ ግን በሚገባ በትጋት ነው የተጫወትነው። ጨዋታውን ፈጠን ለማድረግ ክፍተቱን እስክናገኝ ድረስ በእርግጥ ትንሽ ጊዜ ወስዶብናል። ቢሆንም ግን ሁሉም ጥሩ ነው።»
ቅዳሜ እለት በተከናወኑ ሌሎች ጨዋታዎች፦ ባየር ሌቨርኩሰን አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 3 ለ0 እንዲሁም ቬርደር ብሬመን ቮልፍስቡርግን 3 ለ2 ረትተዋል። ከታችኛው ምድብ ዘንድሮ በእድገት ወደ ቡንደስ ሊጋው የመጡት ዳርምሽታድት እና ኢንግሎሽታድት ተገናኝተው ጨዋታው በዳርምሽታድት 2 ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሽቱትጋርት በአውስቡርግ 1 ለ0፤ ሔርታ ቤርሊን በሆፈንሃይም 2 ለ1 ተሸንፈዋል።
ትናንት በተከናወነ ጨዋታ ደግሞ ስርጭታችን የሚገኝበት የቦን ከተማ ተጎራባች የሆነው ኮሎኝ ማይንትስን 3 ለ2 አሸንፏል። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው የኮሎኙ የግራ ክንፍ ተከላካይ ዮናስ ሔክቶር የትናንቱ ውጤት እጅግ እንዳስደሰተው ገልጧል።
«የትናንትናውን ውጤት ለተመለከተው በእርግጥም የሆነ ነገር ይዘን መውጣት እንደሚገባን የታወቀ ነበር። ተፋልመናል። ባለፉት ሳምንታት በሚያናድድ ሁናቴ ነጥቦችን ከእጃችን ያስነጠቅንባቸው ብዙ ጨዋታዎችን አከናውነናል። አሁን ግን ከዚያ በተለየ ነው የተጫወትነው። ነገርዬውን አዙረን ባገኘነው ነጥብ ሲበዛ ደስተኞች ነን። »
ቬርደር ብሬመን፣ አይንትራኅት ፍራንክፉርት እና ሐኖቨር ወራጅ ቃጣናው ውስጥ ይገኛሉ። የደረጃ ሰንጠረዡ ጠርዝ ላይ የሚገኘው ሐኖቨር እና መሪው ባየር ሙይንሽን የነጥብ ልዩነታቸው 57 ደርሷል።
በጉዳት ለረዥም ጊዜ ከባየር ሙይንሽን ተገልሎ የነበረው የጀርመኑ ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ ጀሮሜ ቦዋቴንግ ዛሬ ከቡድኑ ጋር ልምምድ አድርጓል። የ27 ዓመቱ የባየርን የመሀል ተከላካይ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ከሦስት ወራት በፊት ከሐምቡርግ ጋር በነበረው የመልስ ጨዋታ ነበር።
ነገ እና ከነገ ወዲያ ለጀርመን እግር ኳስ ማኅበር የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ይከናወናሉ። ነገ ምሽት መሪው ባየር ሙይንሽን ከቬርደር ብሬመን፤ ረቡዕ ደግሞ ዶርትሙንድ ከሔርታ ቤርሊን ጋር ይገናኛሉ። በነገው ጨዋታ የባየር ሙይንሽን ተጨዋቾች የተሻለ መጫወት እንደሚገባቸው አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ አስጠንቅቀዋል። «ከሻልከ ጋር በመጀመሪያው አጋማሽ እንዳከናወንነው አይነት ጨዋታ ካደረግን ያኔ ዋንጫ ደህና ሰንብች ነው» ሲሉ ለጋዜጠኖች ተናግረዋል።
የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር አሸናፊ በቡንደስ ሊጋው ውድድር ለሻምፒዮንስ ሊግ ያላለፈ ከሆነ በቀጥታ ወደ አውሮጳ ሊግ ዋንጫ ውድድር ይገባል። የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ውድድር ከቡንደስ ሊጋው እና ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ቡንደስ ሊጋ 64 ቡድኖች የሚሳተፉበት በጀርመን እግር ኳስ ከቡንደስ ሊጋው ቀጥሎ ወሳኝ የሚባል ፉክክር ነው ነው።
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዛሬ ማታ ስቶክ ሲቲ ከቶትንሐም ሆትስፐር ጋር ይጋጠማል። ማክሰኞ ደግሞ ማንቸስተር ሲቲ ከኒውካስል ዩናይትድ ጋር ይገናኛል። ሊቨርፑል ከኤቨርተን፣ ዌስትሀም ዩናይትድ ከዋትፎርድ እንዲሁም ክሪስታል ፓላስ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ረቡዕ ይፋለማሉ።
የሣምንቱ ማሳረጊያ ውድድሮች ግን አስደማሚ በሆነ መልኩ ነው የተጠናቀቁት። ትናንት በተከናወኑ ጨዋታዎች ቀዳሚዋን ግብ በሳንቼዝ አስቆጥሮ ሲመራ የነበረው አርሰናል ከክሪስታል ፓላስ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። ለአርሰናል የጀርመኑ ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ ሜሱት ኦዚል ተደጋጋሚ ድንቅ ሙከራዎችን አድርጎ ነበር።
ትናንት በዐሥር ተጨዋቾች የተወሰነው መሪው ሌስተር ሲቲ ባለቀ ሰአት ባገኘው ፍፁም ቅጣት ምት ከዌስትሀም ዩናይትድ ጋር ሁለት እኩል ተለያይቷል። ለሌስተር ሲቲ የመጀመሪያዋን ግብ በ18ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ግብ አዳኙ ጂሚ ቫርዲ ነው። 55ኛው ደቂቃ ላይም ጥሩ የግብ ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ሆኖም ግን ብዙም ሳይቆይ ጂሚ ቫርዲ 56ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የተጠለፈ በመምሰል ዘሎ በመውደቁ ሁለት ቢጫ ካርድ በማየት በቀይ ከሜዳ ተሰናብቷል።
ጂሚ ቫርዲ ቀይ ካርድ ሲሰጠው ዳኛው ላይ በብስጭት ያሳየው እንቅስቃሴ ለቅጣት ሊዳርገው እንደሚችል ተገልጧል። ምናልባትም ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ቀጣይ ጨዋታዎች ላይ እንዳይሳተፍ ሊታገድ ይችላል። ዌስትሀም ዩናይትድ አቻ የምታደርገውን ግብ በፍፁም ቅጣት ምት ያገኘው 84ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። 86ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛዋ ግብ ተቆጥራ ሌስተር ሲቲ ሽንፈት አጠላበት። ሆኖም መደበኛ የጨዋታ ክፍለጊዜው ተጠናቆ በተጨመረው የባከነ ሰአት ማለትም 95ኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት ሌስተር ሲቲ አቻ መውጣት ችሏል። ጨዋታውም በዛው ተጠናቋል።
ሊቨርፑል በርመስን 2 ለ1 በማሸነፍ ለአውሮጳ ሊግ የመሳተፍ ዕድሉን አለምልሟል። 32 ጨዋታዎችን ያከናወነው ሊቨርፑል በ51 ነጥብ ስምነተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና በሊዮኔል ሜሲ ብቸኛ ግብ በባዶ ከመሸነፍ ቢድንም፤ በቫሌንሺያ 2 ለ1 ተረትቷል። ለሊዮኔል ሜሲ ግን 500ኛ ግቡ ሆኖ ተመዝግቦለታል። አትሌቲኮ ማድሪድ ግራናዳን 3 ለ0 ማንኮታኮት ብቻ አይደለም የባርሴሎና ሽንፈት በነጥብ እንዲስተካከል አስችሎታል። ባርሴሎናም አትሌቲኮ ማድሪድም 76 ነጥብ አላቸው፤ ባርሴሎና በግብ ክፍያ የደረጃ ሰንጠረዡን ይመራል። ሪያል ማድሪድ አንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ይከተላል። ትናንት ቪላሪያል በራዮ ቫሌካኖ 2 ለ1 ድል ተነስቷል። አትሌቲኮ ቢልባዎ ማላጋን አንድ ለምንም ሲያሸንፍ፤ ሴቪላ ከዴፖርቲቮ ዴ ላኮሩኛ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። ስፖርቲንግ ጂዮን፣ ሌቫንቴ እና ጌታፌ ወራጅ ቃጣና ውስጥ ይገኛሉ። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በርካታ ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ይመራል። እስካሁን 31 ግብ አስቆጥሯል። የባርሴሎናዎቹ ሉዊስ ሱዋሬዝ እና ሊዮኔል ሜሲ በ26 እና 23 ግብ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ግብ አግቢዎች ናቸው።
በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ታሪክ ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ ሻንጋይ ውስጥ የተደረገውን ፉክክር በአንደኛነት በማጠናቀቅ ሦስት ውድድሮችን በተከታታይ በማሸነፍ 10ኛው አሽከርካሪ ሆነ። ከዚህ ቀደም ሦስት ውድድሮችን በተከታታይ ያሸነፉት 9ኙ ተወዳዳሪዎች የፍፃሜው ባለድል መሆን የቻሉ ናቸው። በዚህም ኒኮ ከወዲሁ የዘንድሮ አጠቃላይ ውድድር አሸናፊ ሊሆን ይችላል ተብሏል። ዋነኛ ተፎካካሪው ሌዊስ ሐሚልተን በሰባተኛነት አጠናቋል። በአጠቃላይ ድምር ውጤት ኒኮ ሮዝበርግ 75 ነጥቦችን በመሰብሰብ አንደኛ ነው። ሌዊስ ሐሚልተን እስካሁን ያለው 39 ነጥብ ነው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ