1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ሚያዝያ  2 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

ሰኞ፣ ሚያዝያ 2 2009

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የእግር ኳስ ጨዋታ ፍልሚያ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በኃያሉ ባየር ሙይንሽን አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቷል። ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት ሰንደርላንድን ባያሸንፍ ኖሮ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ለሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ለመግባት የሚያስችለው ዕድል ያከትም እንደነበር አሰልጣኙ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/2b0gp
Bundesliga Bayern München Borussia Dortmund Lewandowski
ምስል Getty Images/A. Scheuber

ስፖርት፤ ሚያዝያ  2 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የእግር ኳስ ጨዋታ ፍልሚያ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በኃያሉ ባየር ሙይንሽን አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቷል። ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት ሰንደርላንድን ባያሸንፍ ኖሮ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ለሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ለመግባት የሚያስችለው ዕድል ያከትም እንደነበር አሰልጣኙ ተናግረዋል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ብሪታንያዊው ሌዊስ ሐሚልተን ድል ቀንቶታል። ወደፊት ፉክክሩ በእሱ እና ሁለተኛ በወጣው ጀርመናዊው አሽከርካሪ ሠባስቲያን ፌትል መካከል እንደሚሆን ገልጧል። በዓለም አቀፉ ውድድር ብዙም ኢትዮጵያውያን አሽከርካሪዎች ሲሳተፉበት በማይታይበት የብስክሌት ሽቅድምድም ጽጋቡ ግርማይ ጥሩ ውጤት አስመዝግቧል። ዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ የዓለም ዋንጫን በጋር ሊያሰናዱ ስለመዘጋጀታቸው እየተነገረ ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ 54 ነጥብ ይዞ 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል ዛሬ ከክሪስታል ፓላስ ጋር ይጋጠማል። ሦስት ተስተካካይ ጨዋታዎች ለሚቀሩት አርሰናል የዛሬው ጨዋታ ወሳኝ ነው። 

የጀርመን ቡንደስሊጋ ጨዋታዎች ላይ ቅኝት አድርገን ወደ ፕሬሚየር ሊግ እንመለሳለን። ባየርሙይንሽን ዘንድሮም እንደተለመደው ዋንጫውን በእጁ ለማስገባት እየገሰገሰ ነው። ቦሩስያ ዶርትሙንድን ከትናንት በስትያ 4 ለ1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል። በ10 ነጥብ ርቀት የሚከተለው ላይፕትሲሽ እስካሁን የሰበሰበው 58 ነጥብ ነው። ሆፍንሐይም ከመሪው ባየር ሙይንሽን በ17 ነጥቦች ተበልጦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ባየር ሙይንሽን አራቱን ግቦች ያስቆጠረው በተረጋጋ መልኩ ነበር። የመጀመሪያውን ግብ ፈረንሳዊው ፍራንክ ሪቤሪ ከመረብ ያሳረፈው ጨዋታው በተጀመረ በ4ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ፖላንዳዊው አጥቂ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ በ10ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛውን ግብ ለባየር ሙይንሽን ማስቆጠር ችሏል። 

Bundesliga Bayern München vs Borussia Dortmund Elfmeter
ሮበርት ሌቫንዶብስኪ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ላይ በፍጹም ቅጣት ምት ግብ ሲያስቆጥርምስል Getty Images/AFP/G. Schiffmann

በመጀመሪያው አጋማሽ 20ኛው ደቂቃ ላይ የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ጉዌሬሮ ኳሷን በግሩም ኹኔታ ግብ አስቆጥሯል። የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በባየር ሙይንሽን 2 ለ1 መሪነት ተጠናቀቀ። እናም ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ አራተኛው ደቂቃ ላይ ሆላንዳዊው አጥቂ አርየን ሮበን ሁለት ተጨዋቾችን አታሎ ወደ ግብ የላካት ኳስ ለባየር ሙይንሽን ሦስተኛ ግብ ኾና ተመዝግባለች። ሮበን በተደጋጋሚ ግብ ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ የተሳካለት በ49ኛ ደቂቃ ላይ  ነበር።

በ68ኛው ደቂቃ ላይ ሮበርት ሌቫንዶስቭስኪ ተጠልፎ በመውደቁ ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ከመረብ በማሳረፍ ጨዋታው በባየር ሙይንሽን 4 ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ተጠልፎ ሲወድቅ በደረሰበት ጉዳት የተቀያሪ አግዳሚ ላይ ተቀምጦ ትከሻውን ሲያሻሽ ታይቷል። 

በዛሬው የባየር ሙይንሽን ልምምድ ወቅት ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ፤ እንዲሁም ተከላካዮቹ ዣቪ ማርቲኔዝ እና ዳቪድ አላባ እንዳልተገኙ፤ በግል ግን ልምምድ ማድረጋቸው ተዘግቧል። ረቡዕ ዕለት ከስፔኑ ሪያል ማድሪድ ጋር ለሚኖረው የሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያ ብቁ ኾነው ሊገኑ እንደሚችሉ ተገምቷል።  

ለሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያው ዝግጅት ዛሬ በተደረገው ልምምድ ግብ ጠባቂው ማኑዌል ኖየር እና አጥቂው ቶማስ ሙይለር ወደ ቡድኑ መመለሳቸው ተዘግቧል። ማኑዌል ኖየር እግሩ ላይ በደረሰበት ጉዳት ያለፉት ሦስት ጨዋታዎች አምልጠውታል። ቶማስ ሙይለር በበኩሉ ሁለት ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ አልቻለም ነበር። «እንደተለመደው ልምምድ አድርጌያለሁ፤ ያ ለእኔ ጥሩ ምልክት ነው» ያለው ጀርመናዊው አጥቂ ቶማስ ሙይለር «ጥሩ ዝግጅት አድርገናል» ሲል ለቡድኑ የባየር ሙይንሽን ቴሌቪዥን ገልጧል። 

ረቡዕ ዕለት ከባየር ሙይንሽን እና ሪያል ማድሪድ ፍልሚያ ባሻገር፤ የስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ከእንግሊዙ ላይስተር ሲቲ ጋር ይጋጠማል። ማክሰኞ ደግሞ የጣሊያኑ ጁቬንቱስ ከሌላኛው የስፔን ኃያል ባርሴሎና ጋር እንዲሁም የፈረንሳዩ ሞናኩ ከጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር ለሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ይገናኛሉ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በቡንደስሊጋው የደረሰበት ከባድ ሽንፈት ሳይለቀው ነው ሞናኮን የሚያገኘው።

በቡንደስሊጋው የትናንቱ ግጥሚያዎች ደግሞ ሔርታ ቤርሊን እና ወራጅ ቃጣናው ላይ የሚንገታገተው ኢንግሎሽታድት ድል ቀንቷቸዋል። ሔርታ ቤርሊን በትናንቱ ድል ወደፊት ለአውሮጳ ሊግ የሚያበቃውን ደረጃ በቡንደስሊጋው የአግኝቷል።ሔርታ 43 ነጥብ ይዞ በአምስተኛ ደረጃ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ስር ይገኛል። የሔርታ ቤርሊን አሰልጣኝ ፓል ዳርዳይ ከድል በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በውጤቱ መደሰታቸውን ገልጠዋል። 

Bundesliga FC Ingolstadt 04 v SV Darmstadt 98 -
የኢንግሎሽታድቱ ፓስካል ግሮስ ዳርምሽታድት ላይ የመጀመሪያውን ግብ ሲያስቆጥርምስል Getty Images/Bongarts/A. Pretty

«ቀደም ሲል በሦስት ጨዋታዎች ብንሸነፍም ሞራላችን እንዳለ ነበር። ልጆቹ በራሳቸው እና በአጨዋወት ስልታችን ሙሉ እምነት ነበራቸው። በመጀመሪያው አጋማሽ ላደረጉት አድናቆቴ ከፍ ያለ ነው። በሁለተኛው አጋማሽ ሦስተኛ ግብ ብናስቆጥር ኖሮ ተጨዋቾቻችን ተረጋግተው፤ ሳይጨነቁ ደጋፊዎቻችንን የሚያዝናና ጨዋታ ማድረግ እንችል ነበር። ያ በእርግጥ አልተሳካም። ሆኖም ከዛ መማር ይገባናል።»

ሔርታ ቤርሊን አውስቡርግን 2 ለ0 ያሸነፈው በመጀመሪያው አጋማሽ በጆን አንቶኒ ብሩክስ እና ቫለንታይን ስቶከር ግቦች ነው። በ28 ነጥቡ ዳርምሽታድትን ብቻ በልጦ በወራጅ ቃጣናው በ17ኛ  ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢንግሎሽታድትም ትናንት ከኋላ ተነስቶ ለድል በቅቷል። ኢንግሎሽታድት በዳርምሽታድት ሲመራ ቆይቶ ነበር በስተመጨረሻ 3 ለ2 ለድል የበቃው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት ማንቸስተር ዩናይትድ ከሠንደርላንድ ጋር ወሳኝ ጨዋታ በማድረግ 3 ለ0 ድል አድርጓል። የማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ሆዜ ሞሪኝሆ «ከሊቨርፑል እና ከማንቸስተር ድል በኋላ የዛሬውን ጨዋታ ባናሸንፍ ኖሮ አራተኛ ደረጃ የማግኘታችን ስሌት ያከትምለት ነበር» ሲሉ ተናግረዋል። ሊቨርፑል ከትናንት በስትያ ስቶክ ሲቲን 2 ለ1 በማሸነፍ በደረጃ ሠንጠረዡ ሦስተኛነቱን ለጊዜው አስጠብቋል። 

57 ነጥብ ያለው ማንቸስተር ዩናይትድ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎቹን ሰባት ንጹህ ግቦችን በማስቆጠር ካሸነፈ የሊቨርፑልን ቦታ ይረከባል።  ሳዲዮ ማኔ፣ አዳም ላላና እና ጂቮክ ኦሪጂ የተጎዱባቸው የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ሁለቱን ብራዚሊያውያኑን ፊሊፕ ኮቲንሆ እና ሮቤርቶ ፊርሚኖን ማሰለፋቸው ሰምሮላቸዋል። በተለይ ፊርሚኖ ከመሀል ሜዳ የተላከለትን ኳስ መሬት ነጥሮ እንደተመለሰ በቀጥታ ወደ ግብ አክርሮ በመምታት ያስቆጠረው ግብ ድንቅ ተብሎለታል። ሁለቱ ብራዚላውያን ያለጉዳት በዚህ አቋማቸው ከቀጠሉ ሊቨርፑልን ያለምንም ጥርጥር ለሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ሊያበቁ እንደሚችሉ አሰልጣኙ ተናግረዋል። አጥቂው ዳንኤል ስቱሪጅ በሙሉ ጤንነት ለመመለስ እየተዘጋጀ መሆኑም ታውቋል። 

መሪው ቸልሲ ከትናንት በስትያ በርመስን 3 ለ1 እንዲሁም ማንቸስተር ሲቲ በተመሳሳይ ውጤት ሁልሲቲን 3 ለ1 ረትቷል። ቸልሲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ75 ነጥብ የደረጃ ሠንጠረዡን ይመራል። ማንቸስተር ሲቲ በ61 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  

Formel 1 Grand Prix Lewis Hamilton
የቻይና ሻንጋይ ፎርሙላ አንድ ውድድር አሸናፊ ብሪታንያዊው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተንምስል Reuters/A. Song


የመኪና ሽቅድምድም
ቻይና ሻንጋይ ውስጥ በተደረገው የፎርሙላ አንድ የሚኪና ሽቅድምድም ብሪታንያዊው ሌዊስ ሀሚልተን በተራው እሁድ ዕለት ድል ቀንቶታል። ባለፈው ውድድር አሸናፊ የነበረው ጀርመናዊው የፌራሪ አሽከርካሪ ሠባስቲያን ፌትል ነበር። የዘንድሮ የፎርሙላ አንድ ሽቅድምድም ውድድር ገና ሁለተኛ ዙር ላይ ቢገኝም የመርሴዲስ የበላይነት ግን ያከተመ ይመስላል። ቀደም ሲል ፍልሚያው በመርሴዲስ አሽከርካሪዎቹ ኒኮ ሮዝበርግ እና ሌዊስ ሐሚልተን ነበር። ኒኮ ከውድድር ዓለምራሱን በማግለሉ አሁን ፍልሚያው በሜርሴዲስ እና በፌራሪ አሽከርካሪዎች መካከል ኾኗል።  

ሰባስቲያን ፌትል እና ሌዊስ ሐሚልተን እስካሁን እኩል 43 ነጥብ በመሰብሰብ በአንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። የሬድ ቡሉ አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐን በ25 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ኾኖ ይከተላቸዋል። በብስክሌት ውድድር ደግሞ ኢትዮጵያዊው ጽጋቡ ግርማይ ከ30 ምርጥ ተወዳዳሪዎች መካከል 13ኛ ደረጃ አግንቷል። ጽጋቡ በስፔን አይበር ቅዳሜ ዕለት በተደረገው ሽቅድምድም በርካታ አውሮጳውያንን መቅደም ችሏል። 

የዩናይትድ ስቴትስ፣ የካናዳ እና የሜክሲኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር የ2026ቱን የዓለም ዋንጫ በጋራ ለማዘጋጀት እየተሰናዱ ስለመሆናቸው ጭምጭምታዎች ተሰምተዋል። ምናልባትም ሦስቱ ሃገራት ከ9 ዓመታት በኋላ የዓለም ዋንጫን በጋራ ሊያዘጋጁ ስለማቀዳቸው «ታሪካዊ መግለጫ» ዛሬ ማታ ኒውዮርክ ከተማ ውስጥ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ