1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፣ ሰኔ 13 ቀን፣ 2008 ዓ.ም

ሰኞ፣ ሰኔ 13 2008

ፈረንሣይ ውስጥ በሚኪያሄደው የአውሮጳ እግር ኳስ ውድድር ጀርመንና እንግሊዝ ዛሬና ነገ ወሳኝ ጨዋታዎችን ያከናውናሉ። ሁለቱም ቡድኖች የማለፍ ዕድላቸው ሰፊ ቢሆንም ወደ ቀጣዩ ዙር የማያልፉበት አጋጣሚም ሊፈጠር ይችላል። የሩስያ የአትሌቲክስ ቡድን ከሪዮ ዴጄኔሮ ውድድር ሲታገድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቅድመ ዝግጅቶቼን እያጠናቀቅሁ ነው ብሏል።

https://p.dw.com/p/1JADh
Albanien Fussball Atmosphäre
ምስል DW/A. Muka

ስፖርት፣ ሰኔ 13 ቀን፣ 2008 ዓ.ም

በአውሮጳ እግር ኳስ ፍልሚያ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ዛሬ ማታ እንግሊዝ ከስሎቫኪያ፤ ሩስያ ከዌልስ ጋር ይጋጠማሉ። ጀርመን ከሰሜን አየርላንድ ጋር ወሳኝ ጨዋታዋን የምታከናውነው በነገው እለት ነው።

አትሌቲክስ

ከ46 ቀናት በኋላ ብራዚል ውስጥ በሚጀመረው የኦሎምፒክ ውድድር የሩስያ ቡድን እንዳይሳተፍ እገዳ ተጥሎበታል። የሩስያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በውድድሩ እንዳይሳተፍ የተጣለበት እገዳ መጽናቱን ዐርብ እለት ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል። ውሳኔው የተላለፈውም ሩስያ አትሌቶቿ ላይ ፈጣን ምርመራ አከናውና ዓለም አቀፉ ጸረ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ኩባንያ ማለትም (WADA) በጠየቃት መሠረት ለውጥ ባለማምጣቷ ነው ተብሏል። የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሀገራቸው የአትሌቲክስ ቡድን ከኦሎምፒክ ውድድር መታገዱን የፖለቲካ ውሳኔ ነው ሲሉ ተችተዋል። ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ያልተጠቀሙ የሩስያ አትሌቶች በሪዮ ኦሎምፒክ ሩስያን ወክለው ሳይሆን በግላቸው መሳተፍ እንደሚችሉ ተገልጧል።

የኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር በመጠቀም ቀደም ሲል ፈጣን ለውጦችን እንዲያመጡ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው ሃገራት መካከል ኢትዮጵያም ትገኛለች። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሓፊ አቶ ቢልልኝ መቆዪያ ኢትዮጵያ የሪዮ ዲ ጄኔሮ ኦሎምፒክ አያሰጋትም ብለዋል። ኢትዮጵያ በጥቂት ወራት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ አትሌቶች ላይ ምርመራ አድርጋ እንድታሳውቅ በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር የተሰጣትን ቀነ ገደብ መጠቀሟንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ማስጠንቀቂቃውን ተቀብላ በሀገር አቀፍ ደረጃ ፈጣን እንቅስቃሴዎችን አድርጋለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የምርመራ ውጤቱን በቀነ ገደቡ መሠረት ማቅረብ ባይችል ኖሮ ለዓለም አቀፉ ጸረ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ኩባንያ ማለትም ዋዳ ደንብ ባለመገዛት በሚል ከባድ ቅጣት ይጠብቀው ነበር። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለሪዮ ዴጄኔሮ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ቢያንስ 38 አትሌቶችን እንደሚያሳትፍ ገልጧል። ተወዳዳሪዎችን በተለይ የማራቶን ሯጮችን መርጦ የጨረሰ ሲሆን፤ በሌሎች የውድድር መስኮች የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን በመምረጥ ላይ መሆኑ ተገልጧል። የመረጣ ዝግጅቱም ከሚያዝያ አንድ የጀመረ መሆኑ ተጠቅሷል።

በማራቶን የሩጫ ውድድር በወንዶች እና በሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ አትሌቶች ስም ዝርዝር በፌዴሬሽኑ ድረገጽ ላይ ሰፍሯል። በዚህም መሠረት በወንዶች ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳዳሩ የማራቶን ሯጮች ከአንደኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ስም ዝርዝራቸው የሚከተለው ነው። በአንደኛ ደረጃ ለሚ ብርሃኑ የተመረጠ ሲሆን፤ ተስፋዬ አበራ፣ ፈይሳ ሌሊሳ እና ሌሊሳ ዲሳሳ እስከ አራተኛ ደረጃ አግኝተው መመረጣቸው ድረ-ገጹ ላይ ሰፍሯል። አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ድረ-ገጹ ላይ ያገኘው ነጥብ በሰባተኛ ደረጃ እንደሚገኝ ያመለክታል።

በሴቶች የማራቶን ሩጫ ደግሞ ኢትዮጵያን የሚወክሉት አራቱ አትሌቶች በቅደም ተከተል ትዕግስት ቱፋ 1ኛ፣ ማሬ ዲባባ 2ኛ፣ ትርፌ ፀጋዬ 3ኛ እንዲሁም አበሩ ከበደ 4ኛ መሆናቸው ተጠቅሷል።

እግር ኳስ

Rio 2016 Sambodromo
ምስል picture-alliance/dpa/M. Sayao
Symbolbild Doping Labor
ምስል picture-alliance/AP Photo/F. Coffrini

በአውሮጳ የእግር ኳስ ፍልሚያ ዛሬ ማታ ከጥቂት ሰአታት በኋላ ስሎቫኪያን የሚገጥመው የእንግሊዝ ቡድን ለማለፍ አቻ ብቻ መውጣት ይጠበቅበታል። በምድብ ለ የሚገኘው የእንግሊዝ ቡድን በ4 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ተጋጣሚው ስሎቫኪያ እና በተመሳሳሳይ ሰአት ሩስያን የሚፋለመው የዌልስ ቡድን እኩል 3 ነጥብ እና ተመሳሳይ የግብ ክፍያ ይዘዋል። ሩስያ በ1 ነጥብ እና በ1 የግብ ክፍያ ከምድቡ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

እንደ እንግሊዝ ወሳኝ ጨዋታውን በነገው እለት የሚያከናውነው የጀርመን ቡድንም ለማለፍ አቻ ብቻ መውጣት ይበቃዋል። ጀርመን ከምድብ ሐ በተመሳሳይ 4 ነጥብ ሆኖም በአንድ የግብ ክፍያ ከፖላንድ በልጦ በአንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ፖላንድ አንድ ንጹህ የግብ ክፍያ አለው። ጀርመን 3 ነጥብ ካላት ሰሜን አይርላንድ፤ ፖላንድ አንዳችም ነጥብ ከሌላት ዩክሬን ጋር አቻ መውጣት ብቻ ይጠበቅባቸዋል። ሁለቱም አቻ ከወጡ ወደ ቀጣዩ ዙር ያልፋሉ። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ዮኣሒም ሎቭ ቡድናቸው ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉ አንዳችም ጥርጥር እንደሌለው ተናግረዋል።

«ሰሜን አየርላንዶችን ማሸነፍ እንፈልጋለን። ደግሞም እናሸንፋለን። የምድቡም አሸናፊ እንሆናለን፤ እናም ዐሥራ ስድስቱ ምድብ ውስጥ ገብተን ሊል ውስጥ ዳግም እንጫወታለን። ከዚህ ውጪ ሌላ መንገድ አላውቅም።»

በምድብ ሀ የምትገኘው አዘጋጇ ሀገር ፈረንሳይ ትናንት ከስዊትዘርላንድ ጋር ያለምንም ግብ ብትለያየም ቀደም ሲል ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፏ በ7 ነጥብ ከምድቡ አንደኛ ሆና አልፋለች። ስዊትዘርላንድ 5 ነጥብ አልባንያ 3 እንዲሁም ሩማንያ 1 ነጥብ ብቻ አግኝተዋል። በትናንትናው ጨዋታ የስዊትዘርላንድ ሦስት ተጨዋቾች መለያ ሲጎተት እንደ ወረቀት ሲቀረደድ ታይቷል። ኳሱ ሲረገጥም መቦትረፉ «እንዴት ነው የጥራት ነገር» አስብሏል።

የመኪና ሽቅድምድም

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ዮኣሒም ሎይቭ
የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ዮኣሒም ሎይቭምስል picture-alliance/dpa/C. Charisius

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምምድም ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ ባኩ አዘርባጃን ውስጥ የተከናወነውን ውድድር ትናንት በአንደኛነት በማጠናቀቅ በ24 ነጥብ መምራት ችሏል። የመርሴዲስ አሽከርካሪው የቡድኑ አባል እንግሊዛዊው ሌዊስ ሐሚልተን በአምስተተኛነት አጠናቋል። ሌዊስ ሐሚልተን በጎርጎሪዮሱ የዘንድሮ ዓመት መግቢያ ላይ የተዋወቀው አዲሱ የውድድር ደንብን አማሯል። በፎርሙላ አንድ አዲስ ደምብ መሰረት የውድድሩ አሽከርካሪዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ ከቡድናቸው አባል በሬዲዮ ግንኙነት ርዳታ ማግኘት አይችሉም። ሌዊስ ሐሚልተንትናንት በሬዲዮ ግንኙነት የሞተር ችግር እንደገጠመው ደጋግሞ በማማረር ሲገልጥ ነበር። ቀጣዩ ዙር ሽቅድምድም እሁድ ሰኔ 26 ቀን አውስትሪያ ውስጥ ይከናወናል። ምናልባት ያኔ ሌዊስ ሐሚልተን አዲሱ የውድድር ደንብ ተዋህዶት ዳግም ወደ አሸናፊነቱ ይመለስ ይሆናል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ