1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት በ 2012 ዓ-ም

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2005

በመገባደድ ላይ የሚገኘው የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት 2012 ዓበይት ዓለምአቀፍ የስፖርት ውድድሮች የተካሄዱበት ነበር።

https://p.dw.com/p/173yG
ምስል Reuters

በመገባደድ ላይ የሚገኘው የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት 2012 ዓበይት ዓለምአቀፍ የስፖርት ውድድሮች የተካሄዱበት ነበር። በዓመቱ አጋማሽ ላይ በኡክራኒያና በፖላንድ በጋራ የተዘጋጀው የአውሮፓ እግር ኳስ ሻምፒዮና ውድድር ይካሄዳል። ውድድሩ በዋዜማው የኡክራኒያ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ረገጣ ጉዳይ ያስከተለው የምዕራቡ ዓለም ትችት ጥላውን ቢያሳርፍበትም በዝግጅት ረገድ ስኬታማ ሆኖ ነበር የተፈጸመው።

በውድድሩ አስተናጋጆቹ ሃገራት ፖላንድ በመጀመሪያው የምድብ ዙር፤ እንዲሁም ኡክራኒያ በቀጣዩ ዙር ስንብት ሲያደርጉ ፖርቱጋል፣ ስፓኝ፣ ኢጣሊያና ጀርመን ደግሞ ወደፊት በመራመድ ለግማሽ ፍጻሜ ይደርሳሉ። ፖርቱጋል በሩብ ፍጻሜው ቼክ ሬፑብሊክን 1-0 ስታሸንፍ ጀርመንም ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰችው እስከዚያው ባልተጠበቀ ሁኔታ ጠንካራ ሆና የተገኘችውን ግሪክን 4-2 በመርታት ነበር። ከግጥሚያው በፊት የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ጥቂትም ቢሆን በፍርሃት መዋጡ ታይቷል።

የዓለም ሻምፒዮኗ ስፓኝ በአንጻሩ ያለ ብዙ ድካም ፈረንሣይን 2-0 ስትረታ ኢጣሊያ ደግሞ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ ብርቱ ትግል ማድረግ ግድ ይሆንባታል። የኢጣሊያው ብሄራዊ ቡድን እንግሊዝን ያሸነፈው ከተጨማሪ ሰዓት በኋላ በፍጹም ቅጣት ምት በለየለት ግጥሚያ ነበር። ጨዋታው 4-2 ይፈጸማል። እንግዲህ የአራቱ ቀደምት ቡድኖች የግማሽ ፍጻሜ ጉዞ ይህን የመሰለ ነበር።

በግማሽ ፍጻሜው ዙር በተለይም የፖርቱጋልና የስፓን ግጥሚያ እጅግ ትግል የተመላበት ነበር። በመሆኑም የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመደበኛና በተጨማሪ ጊዜ እኩል ለእኩል ሲያበቃ ውጤቱ በፍጹም ቅጣት ምት ይለይለታል። ስፓኝ ምንም እንኳ የዓለም ሻምፒዮን ብትሆንም በምሽቱ ፖርቱጋልም ባሳየችው ያልተጠበቀ ጥንካሬ አሸናፊ ብትሆን ማንም ባልተደነቀ ነበር። ምነው የፍጻሜው ግጥሚያ ይህ በነበር ያሉም አልጠፉም። ለማንኛውም ስፓኝ በፍጹም ቅጣት ምት 4-2 አሸንፋ ወደ ፍጻሜው ስታልፍ ፖርቱጋልም በኩራት ስንብት ታደርጋለች።

UEFA EURO 2012 Spanien vs. Italien
ምስል Reuters

ሁለተኛው ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ በኢጣሊያና በጀርመን መካከል ሲካሄድ ኢጣሊያ እንደተለመደው የጀርመን መሰናከያ ትሆናለች። ኢጣሊያ ጀርመንን በ 2006 የዓለም ዋንጫ መስተንግዶዋም በርሊን ላይ በግማሽ ፍጻሜ ስታሰናብት አሁንም ይሄው ሁኔታ ይደገማል። ኢጣሊያ 2-1 ትረታለች፤ የጀርመንም የዋንጫ ህልም እንደገና ወደ ቅዠት ይቀየራል። በነገራችን ላይ ሁለቱን ጎሎች በእግርና በአናቱ ያስቆጠረው ማሪዮ ባሎቴሊ የጀርመንን ተከላካዮች ለብቻው ሲያደናብር የኢጣሊያ ልዕልና በዚያ መጠን የተጠበቀ አልነበረም።

ግማሽ ፍጻሜው በዚህ ሁኔታ ተጠናቆ ስፓኝና ኢጣሊያ ለፍጻሜ ሲደርሱ የዓለምን ትኩረት በሰፊው የሳበው የዋንጫ ግጥሚያም ኪየቭ ላይ ይካሄዳል። ስፓኝ በዚሁ ግጥሚያ 4-0 አሸንፋ የ 2012 የአውሮፓ ሻምፒዮን ስትሆን እርግጥ ውጤቱን በዚህ ስፋት የጠበቀው ማንም አልነበረም። ጥቂት ቀናት ቀደም ሲል ጀርመንን በድንቅ አጨዋወት አሸንፎ ለፍጻሜ የደረሰው የኢጣሊያ ብሄራዊ ቡድን የስፓኝን የኳስ ጠቢባን ማቆም ሲሳነው አልፎ አልፎ ሲበዛ የበታች ሆኖ ነበር የታየው። የኢጣሊያ ደጋፊዎች የግማሽ ፍጻሜ ድል ደስታ ዕድሜ አጭር ሆኖ ይቀራል።

የስፓኝ ብሄራዊ ቡድን በበኩሉ በኳስ ጠበብቱ በኢኒየስታና በሻቪ እየተመራ ለተከታታይ ሶሥተኛ ታላቅ ዓለምአቀፍ ድል በመብቃት አዲስ ታሪክ ያስመዘግባል። በ 2008 የአውሮፓ ሻምፒዮን፤ በ 2010 ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የዓለም ዋንጫ ባለቤትና እንደገና በ 2012 የአውሮፓ ሻምፒዮን ይሆናል። በአጭር ቅብብል የኳስ ጥበብ የተካነው የስፓኝ ብሄራዊ ቡድን በዕውነትም በወቅቱ በዓለም ላይ አቻ የማይገኝለት ነው።

Großbritannien Wirtschaft Olympia und Queen-Jubiläum stoppen vorerst britische Rezession
ምስል picture-alliance/dpa

እንግዲህ የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲጠናቀቅ ብዙም ሳይቆይ ቦታውን ለለንደኑ ኦሎምፒክ ጨዋታ ይለቃል። ታዲያ በእግር ኳሱ መድረክ የስፓኝ ብርሃን የደመቀውን ያህል በኦሎምፒኩ ጨዋታ ደግሞ ከሁሉም በላይ ፈክቶ የታየው የጃማይካው አትሌት የዩሤይን ቦልት ኮከብ ነበር። የጃማይካው የአጭር ርቀት መንኮራኩር በመቶ፣ ሁለት መቶና 4x100 ሜትር ሩጫ የቤይጂንግ ኦሎምፒክ ድሉን ከአራት ዓመት በኋላ መልሶ ይደግመዋል።

በተለይም በዱላ ቅብብል በ 36,84 ሤኮንድ ጊዜ የተገኘው አዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን የተለየ አድናቆት ነበር የተሰጠው። የጃሜይካ አትሌቶች በአጭር ርቀት ሩጫ ለአሜሪካ ብርቱ ተፎካካሪ እየሆኑ ሲሄዱ በመጪው ዓመትም ጠንክረው የሚቀጥሉ ለመሆናቸው የሚጠራጠር ማንም የለም። አሜሪካን ካነሣን እርግጥ በኦሎምፒክ ድሉ ከቦልት የላቀ ድርሻ የያዘው ድንቁ ዋናተኛ ማይክል ፌልፕስ ነው።

ፌልፕስ በለንደኑ ኦሎምፒክ ስንብት ሲያደርግ በጠቅላላው በ 18 ወርቅ፣ ሁለት ብርና አንድ ናስ ሜዳሊያ በዋናው ስፖርት ለረጅም ጊዜ የማይደፈር ክብረ-ወሰን ነው ያስመዘገበው። በለንደኑ ኦሎምፒክ አሜሪካ በ 46 ወርቅ 29 ብርና 29 ናስ ቀደምቷ አገር ስትሆን ቻይና በ 38 ወርቅ 27 ብርና 23 ናስ ሁለተኛ ወጥታለች። አስተናጋጇ ብሪታኒያ በአስደናቂ ሁኔታ 29 ወርቅ 17 ብርና 19 ናስ በማግኘት ሩሢያን ከኋላዋ አስቀርታ ሶሥተኛ ስትወጣ የስፖርቱ ውጤትም እንደ ዝግጅቱ ሰምሮላታል ለማለት ይቻላል።

የለንደኑ ኦሎምፒክ ከተነሣ የኢትዮጵያ ውጤትም በተለይ የአንጋፎቹ አትሌቶች በተለያየ ምክንያት መዳከም ሲታሰብ ችላ የሚባል አልነበረም። ኢትዮጵያ ቲኪ ገላና በማራቶን፣ ጥሩነሽ ዲባባ በአሥር ሺህና መሠረት ደፋር በአምሥት ሺህ ሜትር ባስገኟቸው ሶሥት ወርቅ ሜዳሊያዎች እንዲሁም በአንድ ብርና ሶሥት ናስ 24ኛ ስትሆን ከዋና ተፎካካሪዋ ከኬንያ በአራት ቦታዎች ከፍ ብላ መገኘቷ ራሱ አኩሪ ውጤት ሆኖ ሊታይ ይገባዋል። ከዚሁ ሌላ ወጣት ተተኪ አትሌቶች ብቅ ብቅ ማለታቸውን ማየቱም ተሥፋ ሰጭ ሁኔታ ነው።

London 2012 - Leichtathletik
ምስል picture-alliance/dpa

የኬንያው አትሌት ዴቪድ ሩዲሻ የራሱን የ 800 ሜትር የዓለም ክብረ-ወሰን በማሻሻል ያስገኘው እስካሁን አቻ ያልታየለት ውጤትም በዚህ አጋጣሚ ሊጠቀስ ይገባዋል። በሩጫው መጨረሻ የወጣው አንድሩው ኦሣጊ የገባበት ጊዜ እንኳ በቤይጂንጉ ኦሎምፒክ የጊዜ ስሌት ለወርቅ ሜዳሊያ ባበቃ ነበር። በዚህ ከባድ ውድድር የኢትዮጳያ ተሥፋ የነበረው መሐመድ አማን ኬንያዊውን ድንቅ አትሌት ለመፈታተን አለመቻሉም ታዲያ ብዙ የሚያስደንቅ አይሆንም።

ኦሎምፒኩን ተወት አድርገን ሌሎች የስፖርት ድርጊቶችን እናስታውስና ወደ ግንቦት ወር መለስ ስንል ሁለት የስፓኝ የእግር ኳስ ክለቦች ለፍጻሜ በደረሱበት የአውሮፓ ሊጋ ፍጻሜ ግጥሚያ አትሌቲኮ ማድሪድ አትሌቲክ ቢልባኦን 3-0 በማሸነፍ ከ 2010 ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ይሆናል። በዚህ በጀርመንም ያለፈው ግንቦት የቡንደስሊጋው ክለብ ቦሩሢያ ዶርትሙንድ ከሻምፒዮንነት ባሻገር ባየርን ሙንሺንን በፌደሬሺኑ ዋንጫ ፍጻሜም 5-2 በመርታት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለድርብ ድል የበቃበት ነበር።

በዚያው በግንቦት ወር ማብቂያ ላይ ሩሢያ ደግሞ ስሎቫኪያን በበረዶ ገና ፍጻሜ 6-2 በማሸነፍ የዓለም ሻምፒዮን ትሆናለች። ወደ መስከረም ሻገር ስንል በለንደንኑ ፓራሊምፒክስ ቻይና ፍጹም ልዕልና ስታሳይ የብሪታኒያና የጀርመን አትሌቶችም ታላቅ ውጤት ያስመዘግባሉ። በተከታዩ ጥቅምት ወር የሰባት ጊዜው የቱር-ዴ-ፍራንስ የቢስክሌት እሽቅድድም አሸናፊ አሜሪካዊው ላንስ አርምስትሮንግ የተከለከለ አጎልባች መድሃኒት በመውሰድ የተነሣ ድሉን በሙሉ ይገፈፋል።

Lance Armstrong
ምስል picture-alliance/dpa

ድርጊቱ አርምስትሮንግን ከዓለም የቢስክሌት ስፖርት ማሕበር ዕድሜ ልክ እስከመታገድም ነው ያደረሰው። በሌላ በኩል አሁን ዓመቱ ሊገባደድ በመቃረብ ላይ እንዳለ የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የጃማይካውን ዩሤይን ቦልትንና አሜሪካዊቱን አሊሰን ፌሊክስን የዓመቱ ድንቅ አትሌቶች ብሎ ሰይሟል። አሊሰን ፌሊክስ በለንደኑ ኦሎምፒክ በሁለት መቶ ሜትርና በሁለቱም የዱላ ቅብብል ሩጫዎች የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ነበረች።

ምርጫው ለፌሊክስ የመጀመሪያው ሲሆን ለቦልት ግን ባለፉት አምሥት ዓመታት ውስጥ አራተኛው መሆኑ ነው። የለንደኑ ድንቅ የኦሎምፒክ ጨዋታ ከተነሣ የቅይጥ ዲሲፕሊን ሄፕታትሎን ወርቅ አሸናፊዋ ጀሲካ ኤኒስና ከሶማሊያ የመነጨው የአምሥትና አሥር ሺህ ሜትር የወርቅ ባለቤት ሞ ፋራህም ሊጠቀሱ የሚገባቸው ናቸው።

በእግር ኳሱ መድረክ ደግሞ አርጄንቲናዊው የዓለም ድንቅ ተጫዋችና የባርሤሎናው ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ በአንድ የውድድር ወቅት ከ 86 ጎሎች በላይ በማስቆጠር በቅርቡ አርባ ዓመት ያለፈውን የጀርመኑን የጌርድ ሙለርን ክብረ-ወሰን ማሻሻሉ ተሳክቶለታል። ዳግማዊው ማራዶና ዘንድሮም አቻ ያልታየለት ሆኖ ነው ዓመቱን የሚያገባድደው።

Serena Williams Wimbledon 2012
ምስል AP

በቴኒሱ ዓለም ዓመቱ በተለይም አንጋፎቹ ሮጀር ፌደረርና ሤሬና ዊሊያምስ እንደገና አብበው የታዩበት ነበር። የስዊዙ ድንቅ ተጫዋች በእንግሊዙ ታላቅ የዊምብልደን ውድድር የብሪታኒያ ተጋጣሚውን ኤንዲይ መሪይን በፍጻሜው ሲያሸንፍ በርከት ያሉ ግሩም ጨዋታዎችንም አሳይቷል። በለንደን ኦሎምፒክ ግን ድሉ የመሪይ ነበር። አሜሪካዊቱ ሤሬና ዊሊያምስም በዩ ኤስ ኦፕን፣ በለንደን ኦሎምፒክ፣ በዊምብልደን፣ በማድሪድ ኦፕን ወዘተ በርካታ ድሎችን እያስመዘገበች ነው ዓመቱን ያሳለፈችው።

ታዲያ ዓለምአቀፉ የቴኒስ ፌደሬሺን የሰርቢያውን ኮከብ ኖቫክ ጆኮቪችንና አሜሪካዊቱን ሤሬና ዊሊያምስን ለዘንድሮው የዓለም ሻምፒዮንነት ሽልማት መርጦ ሰይሟል። ለዊሊያምስ ሽልማቱ ሶሥተኛው መሆኑ ነው። ጆኮቪች ለሁለት ተከታታይ ዓመታት በኤቲፒ ማዕረግ ተዋረድ ላይ ቁንጮ ሆኖ ሲቆይ ዘንድሮ የአውስትራሊያ ኦፕን ድሉን ማሰከበር፤ ለፍሬንችና ዩ ኤስ ኦፕን ፍጻሜ መድረስ፤ እንዲሁም ሌሎች አምሥት ድሎችን ማስመዝገብ ችሏል። በጥንድ የዓለም ሻምፒዮን ሆነው የተሰየሙት አሜሪካውያኑ ቦብና ማይክ ብራያን ናቸው።

Formel 1 Großer Preis von Brasilien Vettel Weltmeister
ምስል picture-alliance/dpa

በመገባደድ ላይ ያለው 2012 ዓ-ም በፎርሙላ-አንድ ሞተር ስፖርት አፍቃሪዎች ዘንድም አስደናቂ ሆኖ ነው ያለፈው። ወጣቱ ጀርመናዊ ዘዋሪ ዜባስቲያን ፌትል ባለፈው ወር የብራዚል ግራንድ-ፕሪ ዋና ተፎካካሪውን ፌርናንዶ አሎንሶን ቀድሞ ከግቡ በመድረስ ለተከታታይ ሶሥተኛ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን በቅቷል። ይህም በፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው።

ዓመቱ ከሰባት የዓለም ሻምፒዮን ማዕረግ በኋላ በቃኝ ብሎ ትቶት ወደነበረው ውድድር ለተመለሰው ለሌላው ጀርመናዊ ለሚሻኤል ሹማኸር ደግሞ የስንብት ነበር። እርግጥ ሹማኸር በውድድሩ አንዴ እንኳ ቀደምት መሆኑ አልተሳካለትም። ቢሆንም የሰባት ጊዜው ሻምፒዮን በታላቅ የፎርሙላ-አንድ ዘዋሪነት ሲታወስ እንደሚኖር አንድና ሁለት የለውም።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ