1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ታኅሣሥ  9 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. 

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 9 2010

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በህንድ ኮልካታ የ25 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር በወንድም በሴትም አሸናፊ ኾነዋል። የቀድሞው የከባድ ሚዛን ባለድል ቡጢኛ ታይሰን ፉሪ የዓለማችን ምርጥ የከባድ ሚዛን ቡጢኛን «መጣኹልኽ ጠብቀኝ» ሲል ዝቷል። አንቶኒዮ ግሪዝማን ትዊተር ላይ የለጠፈው ምስሉ መጠነ ሰፊ ውግዘት አስከትሎበታል።

https://p.dw.com/p/2pauZ
Deutschland bundeliga Gladbach gegen Köln
ምስል Reuters/T. Schmuelgen

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ ታህሳስ 9፣ 2010 ዓም

ኮልካታ ህንድ ውስጥ በተከናወነው የ25 ኪሎ ሜትር የግማሽ ማራቶን ሩጫ በወንዶችም በሴቶችም ፉክክር ኢትዮጵያውያኑ ተወዳዳሪዎቻቸውን ልቀው አንደኛ ወጥተዋል። በወንዶች ፉክክር የ5000 እና 10000 ሜርት የዓለም ሩጫ ውድድር ክብር-ወሰን ባለቤቱ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከተፎካካሪዎቹ ጥሶ በመውጣት በአንደኛነት አሸንፏል። ቀነኒሳ 25 ኪሎ ሜትሩን ያጠናቀቀው 1 ሰዓት ከ13 ደቂቃ ከ48 ሰከንድ በመሮጥ ነው። በተለይ ከ21ኛው ኪሎ ሜትር አንስቶ አፈትልኮ የወጣው ቀነኒሳ ውድድሩን ሲያጠናቅቅ የቅርብ ተፎካካሪው የነበረው የኤርትራው ጸጋይ ጥዑመ ከእይታ ውጪ ነበር። በውድድሩ ጸጋይ ኹለተኛ የወጣው  ቀነኒሳ ፉክክሩን ካጠናቀቀ ከ41 ሰከንድ በኋላ በመጨረስ ነው። የታንዛኒያው አውጉስቲኖ ሱሌ በ1 ሰዓት ከ14 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ በመግባት በሦስተኛነት አጠናቋል። 

በተመሳሳይ የሴቶች ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ደጊቱ አዝመራው በ1 ሰዓት ከ26 ደቂቃ ከ01 ሰከንድ ሮጣ በመግባት በአንደኛነት አጠናቃለች።  ኬንያዊቷ ዕውቅ አትሌት ሄላ ኪፕሮፕ ከደጊቱ በ3 ሰከንዶች ተበልጣ ኹለተኛ ወጥታለች።  1 ሰዓት ከ26 ደቂቃ ከ28 ሰከንድ የሮጠችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ድባቤ ኩማ ታንዛኒያዊቷ ፋይሉና ማታንጋን ተከትላ የአራተኛ ደረጃ አግኝታለች።   
 
እግር ኳስ
ኬንያ ውስጥ ሲከናወን የነበረው የምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ማኅበር ምክር ቤት (Cecafa) እግር ኳስ ጨዋታ በአዘጋጇ ኬንያ የዋንጫ አሸናፊነት ተጠናቋል።  ኬንያ የዘንድሮውን የሴካፋ ዋንጫ ጨዋታ ትናንት በድል ያጠናቀቀችው ለፍጻሜ ከደረሰችው ዛንዚባር ጋር ተጋጥማ ነው። ዛንዚባር በፍጹም ቅጣት መለያ ምቱ 3 ለ2 ተረትታ ኹለተኛ ደረጃን አግኝታለች። የፍጻሜ ግጥሚያው በጭማሪ ሰአት የተጠናቀቀው 2 ለ2 በኾነ ውጤት ነበር። የዋንጫው ባለቤት የኾኑት የሐራምቤ ክዋክብቱ ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን በማዳን የኬንያ ምርጥ ተጨዋች መኾኑን አስመስክሯል። በግማሽ ፍጻሜው በዛንዚባር የተሸነፈችው ኡጋንዳ ለደረጃ በተደረገው ግጥሚያ ቡሩንዲን 2 ለ1 ረትታ ሦስተኛ ወጥታለች። 

Kenianische Fußballfans vor dem TV
ምስል imago/Africa Media Online

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሊቨርፑሉ ጀርመናዊ አሰልጣኝ ዬይርገን ክሎፕ ምንም እንኳን ቡድናቸው ትናንት በርንማውስን 4 ለ0 ቢያንኮታኩትም መሪው ማንቸስተር ሲቲ ላይ ግን የማይደረስ ነው ብለዋል። ሊቨርፑል ትናንት በፊሊፕ ኮቲንሆ፤ ሞሐመድ ሣላኅ፤ ዴያን ሎቭሬን እና ሮቤርቶ ፊርሚኖ አራት ግቦች ተንበሽብሾ ወጥቷል፤ ኾኖም ግን ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ በ18 ነጥቦ ተበልጦ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በቡድናቸው አቋም ደስተኛ እንደኾኑ የገለጡት አሰልጣኝ ዬይርገን ክሎፕ ከአራቱ ምርጥ ቡድኖች አንዱ ኾነው በመጨረስ በሚቀጥለው የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ መኾን ግባቸው እንደኾነ አስታውቀዋል። 

በአንጻሩ የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪኝሆ የፕሬሚየር ሊጉ ዋንጫን ለመሪው ማንቸስተር ሲቲ በመተው ተስፋ እንዳልቆረጡ ተናግረዋል።  በትናንቱ ድል ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ያላቸውን ልዩነት ወደ 11 ነጥብ ማጥበብ ችለዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት ዌስት ብሮሚችን 2 ለ1 ድል ያደረገው  በሮሜሉ ሉካኩ እና በጄሴ ሊንጋርድ ሁለት ግቦች ነው። ከቸልሲ በ3 ነጥብ በልጦ ኹለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ አጠቃላይ 41 ነጥብ አለው።  ቅዳሜ እለት ቸልሲ ሳውዝሀምፕተንን እንዲሁም አርሰናል ኒውካስልን 1 ለ0 አሸንፈዋል። አርሰናል ከሊቨርፑል በአንድ ነጥብ ተበልጦ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

Bundeliga Fussball VfL Wolfsburg vs. 1899 Hoffenheim
ምስል Getty Images/Bongarts/R. Hartmann

ዛሬ ኤቨርተን ከስዋንሲ ሲቲ ይጋጠማሉ። በፕሬሚየር ሊጉ በመሪነት በኩራት የሚንጎማለለው የፔፕ ጓርዲዮላ ቡድን ማንቸስተር ሲቲ በሊግ ካፕ የሩብ ፍጻሜ ውድድር ማክሰኞ እለት ላይስተር ሲቲን እንደሚያሸንፍ ይጠበቃል። ማንቸስተር ሲቲ በዘንድሮ የውድድር ዘመን አስደናቂ ድሉ የተጀመረው የጨዋታ ዘመኑ ከመጀመሩ በፊት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለወዳጅነት በተደረገው ግጥሚያ ቶትንሀምን 3 ለ0 ድል ያደረገ ጊዜ መኾኑን አሰልጣኙ ተናግረዋል። በትናንቱ ግጥሚያም ማንቸስተር ሲቲ ቶትንሀምን 4 ለ1 ዳግም አሸንፏል። የፔፕ ጓርዲዮላ ቡድን በ16 ጨዋታዎች በተከታታይ በማሸነፍ ኃያልነቱን አስመስክሯል። 

ቡንደስሊጋ፥
በጀርመን ቡንደስሊጋ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይፕሲሽ 10ኛ ደረጃ ላይ በሰፈረው ሔርታ ቤርሊን  3 ለ2 ተሸንፏል። መሪው ባየር ሙይንሽን በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 18 ደረጃ ላይ የሚገኘው ኮሎኝ ቡድንን በጠበበ ልዩነት 1 ለ0 አሸንፏል። በባየርን እና ኮሎኝ መካከል የ35 ነጥብ ልዩነት አለ። ባየርን 41 ነጥብ ሲኖረው፤ ኮሎኝ በ6 ነጥብ ብቻ ተወስኗል። የባየር ሙይንሽኑ የክንፍ ተጨዋች አሪየን ሮበን ቡድኑ ለጀርመን ካፕ  ዋንጫ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር በሚኖረው ግጥሚያ ሊሰለፍም ላይሰለፍም እንደሚችል አሰልጣኙ ዛሬ አስታውቃል። የ33 ዓመቱ አጥቂ አሪየን ሮበን ዛሬ ከቡድኑ አባላት ጋር ልምምድ ያደረገ  ቢኾንም ከ16ቱ ምርጥ ተጨዋቾች መካከል የሚሰለፈው ግን ብቃቱ ታይቶ እንደኾነ ቡድኑ ይፋ አድርጓል። አሰልጣኝ ዩፕ ሄንከስ «ሮበን አኹን ባለው አቋሙ አደጋ መጋፈጥ አያስፈልግም» ማለታቸው ይታወሳል። ሆፈንሃይምን ትናንት 2 ለ1 ያሸነፈው ዶርትሙንድ 28 ነጥብ ይዞ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  በ2 ነጥብ በልጦት 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሻልከ ቅዳሜ እለት ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋር እኩል ተለያይቷል።   
 
ላሊጋ፥
 በላሊጋው ዛሬ ሪያል ቤቲስ ከማላጋ ጋር ይጋጠማሉ። መሪው ባርሴሎና ዴፖርቲቮ ላኮሩኛን ትናንት 4 ለ0 አንኮታኩቷል። በትናንቱ ግጥሚያ የባርሴሎናው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ምንም እንኳ ያገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት ግብ ጠባቂው ቢይዝበትም ሉዊስ ሱዋሬዝ እና ፓውሊንሆ እያንዳንዳቸው ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል። ሜሲ የሳተው ፍጹም ቅጣት ምት የተገኘው ሉዊስ ሱዋሬዝ ፍጹም ቅጣት ክልል ውስጥ ጥፋት ስለተፈጸመበት ነበር። ከምንም በላይ ግን ቅዳሜ የሚከናወነው የሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና ግጥሚያ ይጠበቃል። በላሊጋው ባርሴሎና በ42 ነጥብ መሪነቱን አስጠብቋል። አትሌቲኮ ማድሪድ በ36 ነጥብ ኹለተኛ ነው። ቫለንሺያ በ34 ነጥብ ይከተላል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሪያል ማድሪድ 31 ነጥብ ይዞ ደረጃው አራተኛ ነው። ሪያል ማድሪድ ከሌጋኔስ ጋር የነበረው የዛሬ ጨዋታ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።

Spanien Fußball FC Barcelona gegen Deportivo Alaves 1:2
ምስል picture alliance/Cordon Press/E. Ivanova

በበጋ የተጨዋቾች ዝውውር ወቅት ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ሊያቀና ጫፍ ደርሶ በስተመጨረሻ ሐሳቡን የቀየረው የአትሌቲኮ ማድሪዱ ኮከብ አንቶኒ ግሪዝማን  ትዊተር ገጹ ላይ ያሰፈረው ምስሉ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል። የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ተጨዋቹ ወደ ቡድናችን ዝር እንዲል አንፈልግም ብለለዋል። ግሪዝማን ትዊተር ላይ ለጥፎት የነበረው ፎቶግራፉ ላይ ሰማያዊ የቅርጫት ኳስ ተጨዋች መለያ ለብሶ፤ ኳስ ይዞ ይታያል፤ አፍሮ ጸጉሩ ተከምሮም ገጹና ገላው ጥቊር ቀለም ተቀብቷል።  በርካቶችን ያስቆጣው የአንቶኒዮ ግሪዝማን ፎቶግራፍ « የ80ዎቹ ፌሽታ» ከሚለው ጽሑፍ ጋር  የሣቅ ምልክትም ተያይዞበታል። የብሪታንያ ሠራተኛ ፓርቲ የምክር ቤት አባል የኹኑት ዳቪድ ላሚ  አንቷን ግሪዝማንን ከተቹት መካከል ይገኙበታል ጥቊሩ የምክር  ቤት አባል፦ «የ80ዎቹ ፌሽታን ለመግለጥ እጅግ በጣም ብዙ የተለያዩ መንገዶች አሉ» ሲሉ ትዊተር ላይ ጽፈዋል። ግሪዝማን በአድናቂዎቹ ውትወታ ወዲያውኑ ከትዊተሩ ላይ የደመሰሰው ፎቶግራፍ ላይ የሚታየው መልኩ በአጠቃልይ በጽልመት የተዋጠ ነው። 

ግሪዝማን «ኧረ ተረጋጉ ሰዎች፤ እኔም እኮ የሀርለም ግሎቤትሮተርስ ደጋፊ ነኝ፤ ደግሞም ይኼ ክብር መስጠቴ ነው» ብሎ ነበር። ተቃውሞው ሲያይልበትም፦ «ካስቆጣዃችሁ ይቅርታ» የሚል መልእክት በትዊተሩ ገጹ አስነብቧል። 

Tyson Fury gegen Wladimir Klitschko Boxen
ምስል Reuters/K. Pfaffenbach

ቡጢ፥

የቀድሞ የከባድ ሚዛን ቡጢ ቀበቶ ባለቤት የነበረው ብሪታንያዊው ቡጢኛ ታይሰን ፉሪ በማንኛውም ውድድር እንዳይስሳተፍ የተጣለበት የሁለት ዓመት ገደብ ተጠናቀቀ። ቡጢኛው ገደቡ ተጥሎበት የነበረው አበረታች ንጥረ-ነገር ተጠቅመሃል በሚል ነበር። ታይሰን ፉሪ ወደ ውድድር ሲመለስ በመጀመሪያ መግጠም የሚፈልገው ከዓለም ሻምፒዮኑ አንቶኒ ጆሹዋ ጋር ነው። «ወደ ውድድር ስመለስ ከምንዜውም በተሻለ በደንብ ተጠናክሬ ነው። በትክክል የኔ የነበሩትን የዓለም ቀበቶዎቼንም ለማስመለስ ተዘጋጅቻለሁ» ብሏል። ታይሰን ፉሪ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2015 ኅዳር ወር ላይ በአስደናቂ ኹኔታ ቭላድሚር ክሊችኮን ካሸነፈ በኋላ የሰበሰባቸው ቀበቶዎቹ በጸረ አበረታች ንጥረ-ነገር ኩባንያ ትእዛዝ ተነጥቆበታል። ኩባንያው ታይሰን ፉሪን  በ2016 አበረታች ንጥረ-ነገር ተጠቅመኻል በማለት በጥፋተኛነት ቅጣት ጥሎበታል። አኹን ቅጣቱን ያጠናቀቀው ብሪታንያዊ የከባድ ሚዛን ቡጢኛ «አንቶኒ ጆሹዋ መጣኹልህ» ሲል  ከአንቶኒ ጆሹዋ ጋር መግጠም እንደሚፈልግ ትዊተር ላይ አስታውቋል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ