1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ኅዳር 1 ቀን፣ 2012 ዓ.ም

ሰኞ፣ ኅዳር 1 2012

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን ከአዲሱ ጊዜያዊ አሰልጣኙ ጋር ስኬታማ ኾኗል። ሊቨርፑል በጀርመናዊ አሠልጣኙ በመሪነት ግስጋሴው ቀጥሏል። በማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸንፈዋል። ቻይና ውስጥ በተከናወነው የናንቻንግ ማራቶን የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ትናንት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃን ተቆጠጥረው ለድል በቅተዋል።

https://p.dw.com/p/3Sq89
Fußball Bundesliga FC Bayern München - Borussia Dortmund
ምስል Getty Images/Bongarts/S. Widmann

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ዋና አሰልጣኙን ያሰናበተው ባየር ሙይንሽን በጊዜያዊ አሰልጣኙ ድል ተቀዳጅቷል። ዋነኛ ተቀናቃኙ ባቦሩስያ ዶርትሙንድን ቅዳሜ ዕለት ድባቅ መትቶታል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ከግስጋሴው የሚገታው አልተገኘም።  የስጋት ምንጩ የነበረው ማንቸስተር ሲቲን ትናንት በሰፋ ልዩነት አሸንፎ የነጥብ ልዩነቱንም አስፍቷል። ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ቻይና ውስጥ በተከናወነው የናንቻንግ ማራቶን የሩጫ ውድድር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ድረስ ተከታትለው በመግባት ድል ተቀዳጅተዋል። ኬንያውያን ባየሉበት የወንዶች ፉክክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት የሦተኛ ደረጃን አግኝቷል። ኢትዮጵያዊው አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ እና ኬኒያዊቷ ሯጭ ሩት ቼፕንጌቲች በዓለም አቀፍ የማራቶኖች እና የረዥም ርቀቶች ውድድር ማኅበር የዘንድሮ ምርጥ ሯጮች ተብለው ተሸልመዋል።

እግር ኳስ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ከሰሞኑ ድክመቱ ራሱን አድሶ ብቅ ብሏል። በቡንደስሊጋ ዋነኛ ተፎካካሪው ቦሩስያ ዶርትሙንድን 4 ለ0 በኾነ አሸማቃቂ ውጤት ድል አድርጎታል። ባለፈው ሳምንት ዋና አሰልጣኙ ኒኮ ኮቫች በአይንትራኅት ፍራንክፉርት የ5 ለ1 ከባድ ሽንፈት ከገጠማቸው እና ከቡድኑ ከተሰናበቱ በኋላ በጊዜያዊነት በሚያሰለጥኑት በሐንሲ ዲተር ፍሊክ አመራር ነው ለድል የበቃው። በዕለቱ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ፤ ሠርጂዬ ግናብሬ እና ጓደኞቹ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ላይ አይጥ እና ድመት ነው የተጫወቱባቸው ሲል ኪከር የተሰኘው የድረ ገጽ ጋዜጣ ዘግቧል።

Fußball Bundesliga FC Bayern München - Borussia Dortmund
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Schrader

በእርግጥም የቀድሞ የቦሩስያ ዶርትሙንድ ተጨዋች ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ የዕለቱ ምርጥ ተጨዋች ኾኖ ገኖ ታይቷል። ቡድኑ 4 ለ0 ሲያሸንፍም በ17ኛው እና በ76ኛው ደቂቃዎች ላይ ኹለት ኳሶችን ከመረብ አሳርፏል።  ኹለተኛዋ ግብ የቀድሞ ቡድኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ላይ 14ኛዋ ግብ ኾና ተመዝግባለታለች፤ በዚያም ክብረ ወሰን ሰብሯል።  ከዚህ ቀደም ጌርድ ሙይለር ዶርትሙንድ ላይ 13 ግቦችን በማስቆጠር ክብረወሰን ይዞ ቆይቶ ነበር።

በ47ኛው ደቂቃ ላይ ግናብሬ ሲያስቆጥር፤ ማትስ ሁመልም በስኅተት 80ኛው ደቂቃ ላይ በራሱ ላይ አስቆጥሯል። በዚህም ባየር ሙይንሽን 4 ለ0 በኾነ ሰፊ ልዩነት ቦሩስያ ዶርትሙንድን አሸንፏል።

በተገኘው ድል የተደሰተው የባየር ሙይንሽን ዋና ሥራ አስፈስጻሚ፦ ካርል ሐይንስ ሩመኒገ ጊዜያዊ አሰልጣኙ ባሉበት እንደሚቀጥሉ ይፋ አድርጓል «ላልተወሰነ ጊዜ ከሐንሲ ጋር እንቀጥላለን። በአሁኑ ወቅት ጥሩ ሠርቶ እንድንተማመንበት አድርጓል» ሲል። ጊዜያዊ አሰልጣኙ የቡድኑን አሰላለፍ ቀይረውታል በተወሰነ መልኩ። ታክቲክ በነጠቀም ቡድኑ ኳስ ይዞ እንዲጫወት አድርገዋል። አሰልጣኙ መጀመሪያ ያደረጉት፤ ከፊት ያሉ ተከላካዮችን በደንብ ወደ ኋላ መሳብ ነው። ዮሹዋ ኪሚሽ እና ሌዮን ጎሬትስካን ጨምረው አማካዩን በስድስት አጠናከሩት። በተጨዋቾች መካከል ብዙም መራራቅ ስላልነበር ማጥቃቱ ላይ አይለዋል። እንደውም ቦሩስያ ዶርትሙንድ ላይ ከ4 በላይም ማስቆጠር ይችሉ ነበር።

አሰልጣኙ ታክቲክ ላይ ብቻ አላተኮሩም፤ የተጨዋቾች መረጣ እና አሰላለፍ ላይም ትኩረት አድርገዋል። ወጣቱ አልፎንሶ ዳቪስን ከክንፍ ተመላላሽነት ወደ ግራ ተከላካይነት ስበውታል። ቶማስ ሙይለርን ከቀኝ ፊት አጥቂነት ወደ መሀል አምጥተው ቡድኑን ባለው ልምድ እንዲመራ አድርገዋል፤ ውጤትም አስገኝቷል። ቶማስ ሙይለር ለባየርን ሙይንሽን ለ500ኛ ጊዜ በተሰለፈበት የቅዳሜው ግጥሚያ 2 ግቦችን ማመቻቸት ቢችልም ግብ ሳያስቆጥር ግንቀርቷል።   

Fußball Bundesliga FC Bayern München - Borussia Dortmund
ምስል picture-alliance/dpa/S. Hoppe

ባየር ሙይንሽን አሊያንስ አሬና ስታዲየሙ ውስጥ ዶርትሙንድን ስድስት ጊዜ አሸንፎታል። ውጤቱም (4፡0፣ 5፡0፣ 6፡0፣ 4:1፣ 5:1እና 2:1) ነበር። የባየር ሙይንሽኑ ጊዜያዊ አሰልጣኝ፦ ሐንሲ ዲተር ፍሊክ በሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ የግሪኩን ኦሊምፒያኮስ ፒሬኡስን ረቡእ ዕለት 2 ለ0 አሸንፈው ነበር። በዚህም ባየርን ሙይንሽንን ለሻምፒዮንስ ሊጉ ቅድመ ሩብ ፍጻሜ አብቅተውታል።

በሻምፒዮንሽ ሊግ አራተኛ ዙር ግጥሚያ ባየር ሙይንሽን 12 ነጥብ ይዞ ከምድቡ በ1ኛነት አልፏል። ቶትንሀም በ7 ነጥብ ኹለተኛ ነው። ጄሮም ቦአቴንግ፤ ፊሊፕ ኮቲንሆ እና ቲያጎን ተቀያሪ ወንበር ላይ አስቀምጠው፦ ዣቪ ማርቲኔዝ፤ ጎሬትስካ እና ኮማንን አሰልፈዋል።  ኦሊምፒያኮስ ፔሪኡስ በመከላከል ስልት ስለገባ ለአዲሱ አሰልጣኝ ፈተና ኾኖባቸው ነበር።

በመጀመሪያው አጋማሽ 45 ደቂቃ 70 በመቶ ኳስ በቁጥጥር ስር ቢያደርጉም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ቆይተዋል። ከረፍት መልስ በስተመጨረሻ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ 69ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥሯል። ኪሚሽ በሰያፍ መጥኖ ያሻማውን ኮማን የግብ ማእዘን ሲመልስበት ነው ሌቫንዶቭስኪ ከመረብ ያሳረፍው። ከዚያ በ89ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በሰርጂዬ ግናብሬ የተቀየረው ፔሪሲች ሜዳ በገባ በ30 ሰከንድ ግብ አስቆጥሯል። በዚያም ባየር ሙይሽን 16 ቡድኖች ወደ ሚገኙበት ቅድመ ሩብ ፍጻሜ አልፏል።

በቡንደስሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ ባየር ሙይንሽን 3ኛ ነው፤ 21 ነጥብ አለው።  ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ 25 ነጥብ ሰብስቦ ይመራል። ላይፕሲሽ በ21 ነጥብ ኹለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ፍራይቡርግ በግብ ክፍያ ተበልጦ አራተኛ ደረጃ ይዟል። ሆፈንሀይም በ20 ነጥቡ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ከሻልከ ጋር ተመሳሳይ 19 ነጥብ ያለው ዶርትሙንድ በግብ ልዩነት 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  

በአይንትራኅት ፍራንክፉርት 5 ለ1 ከተሸነፉ በኋላ በተሰናበቱት አሰልጣኝ ኒኮ ኮቫች ምትክ ባየር ሙይንሽን አዲስ አሰልጣኝ በአፋጣኝ ለመቅጠር ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጓል። ጥሪ የተደረገላቸው አሰልጣኝ ቶማስ ቱሁል እና ኤሪክ ቴን ሀግ በቡድናቸው ፓሪ ሴንት ጄርሜ እና አያክስ ቢያንስ እስከ ጨዋታ ዘመኑ ማብቂያ ድረስ መቆየት እንደሚሹ ገልጠዋል። ራልፍ ራኚክ ድንገተኛ ውሳኔ ማሳለፍ እንደማይሹ በመግለጥ ጉዳዩን ለአማካሪያቸው አስተላልፈዋል። አርሰን ቬንገርም ታስበው ነበር። ከባየር ሙይንሽን አመራር ጋር ግን የተግባቡ አይመስልም። ካርል ሐይንትስ ሩመኒገ በሩቁ በስልክ ልንግባባ አልቻልንም፤ «ከእሳቸው ጋርም ለአላስፈላጊ መጨናነቅ ፍላጎቱ የለኝም» ሲል አክሏል።

Fußball Bundesliga FC Bayern München - Borussia Dortmund
ምስል Reuters/A. Gebert

ከባየርን ሙይንሽን አሰልጣኝ ኒኮ ኮቫች እና ከኮሎኝ አሰልጣኝ አሒም ቢየርሎርዘር ቀጥሎ በቡንደስሊጋው የማይንትሱ አሰልጣኝ መሰናበታቸው ትናንት ይፋ ኾኗል። የ41 ዓመቱ ሣንድሮ ሽቫርትስ የተሰናበቱት ቡድናቸው ባለፈው በላይፕሲሽ 8 ለ0 ከተንኮታኮተ በኋላ ወደ ቡንደስሊጋው ዘንድሮ ባደገው ኡኒዮን ቤርሊን ቅዳሜ ዕለት 3 ለ2 በመሸነፉ ነው። አሠልጣኙ ካለፉት 11 ጨዋታዎች በ8ቱ ተሸንፈዋል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውድድር ሊቨርፑል ዘንድሮ ኃይል ኾኖ ቀጥሏል። 26 ጨዋታዎች ከፊቱ የሚቀሩት ሊቨርፑል እስካሁን በሰበሰበው 34 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን እየመራ ነው። በኹለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይስተር ሲቲ ቅዳሜ ዕለት አርሰናልን 2 ለ0 በማሸነፍ ነጥቡን 26 ማድረስ ችሏል። ሊቨርፑል ትናንት ዋነኛ ተፎካካሪው ማንቸስተር ሲቲን 3 ለ1 በማደባየቱ ግን ላይስተር ሲቲ በ8 ነጥብ ልዩነት ኹለተኛ ደረጃን ይዟል። ክሪስታል ፓላስን ቅዳሜ ዕለት በተመሳሳይ 2 ለ0 ያሸነፈው ቸልሲ ተመሳሳይ ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማንቸስተር ሲቲ በ25 ነጥቡ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የዓለማችን ምርጥ የእግር ኳስ ተጨዋች ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በጥቂት ቀናት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በመቀየሩ ጨዋታ ከመጠናቀቁ በፊት ስታዲየሙን ለቆ መውጣቱ አነጋጋሪ ኾኗል። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ቡድኑ ጁቬንቱስ ኤስ ሚላንን 1 ለ0 ባሸነፈበት የሴሪ አው ውድድር በማውሎ ዲባላ ተቀይሮ የወጣው በ55ኛው ደቂቃ ላይ ነበር።

የጁቬንቱሱ አሰልጣንኝ ማውሪትሲዮ ሣሪ ስለ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ድርጊት ተጠይቀው ጨዋታው ከመጠናቀቁ 3 ደቂቃ ቀደም ብሎ ስታዲየሙን ለቆ ስለመውጣቱ የሚያውቁት ነገር አለመኖሩን ገልጠዋል። ኾኖም፦ « እውነት ከኾነ ከቡድኑ ጓደኞቹ ጋር ሊፈታው የሚገባ አንድ ችግር ነው» ብለዋል። ከክርስቲያኖ ጋር ግን ችግር እንደሌለባቸው ዐሳውቀዋል። የዓለም ምርጥ እግር ኳስ ተጨዋች ተብሎ ለአምስት ጊዜያት ክብርን ለተቀዳጀው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ግን የአሰልጣኙ ድርጊት እንደስድብ ነው የኾነበት።

Fußball UEFA Champions League Ajax Amsterdam - Juventus FC
ምስል Imago Images/Beautiful Sports

አሠልጣኝ ማውሪትሲዮ ሣሪ ብዙም ሳያብራሩ፦ «ተጨዋቾች ሲቀየሩ መናደዳቸው ምንም አዲስ ነገር የለውም» ሲሉ ተናግረዋል። ጉልበቱ ላይ መጠነኛ ጉዳት የገጠመው የ34 ዓመቱን ተጨዋች አሠልጣኛ ሣሪ ባለፈው የሩስያው ሎኮሞቲቭ ሞስኮውን 2 ለ1 ባሸነፉበት የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያም ቀይረውት ነበር።  

የቀድሞው የባየር ሙይሽንሽን፤ የጀርመን እና የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ቡድኖች ዋና አሰልጣኝ የነበረው ዩይርገን ክሊንስማን የሔርታ ቤርሊን አማካሪ ቦርድ አባል ሊኾን ነው። በጀርመን ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በዘመኑ ወሳኝ አጥቂ የነበረው ዩይርገን ክሊንስማን ላለፉት ሦስት ዓመታት በእግር ኳስ ዙሪያ አልሠራም። የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የአምስት ዓመት አሰልጣኝነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ አኹን የሔርታ ቤርሊን አማካሪ ቦርድ አባል በመኾን ወደ እግር ኳሱ ይመለሳል ማለት ነው።

በሴቶች እግር ኳስ ግጥሚያ ወደ ዌንብሌይ ስታዲየም ያቀናው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን የእንግሊዙ አቻውን ባለቀ ሰአት በተገኘ ግብ 2 ለ1 አሸንፏል። ከ77 ሺህ በላይ ተመልካቾች በተገኙበት ስታዲየም የተደረገው የወዳጅነት ግጥሚያ አዝናኝ ነበር።

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያዊው አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ እና ኬኒያዊቷ ሯጭ ሩት ቼፕንጌቲች የጎርጎሪዮሱ (2019) «ምርጥ የማራቶን ሯጭ» በሚል ለሽልማት በቁ። ሽልማቱ ዐርብ ምሽት የተሰጣቸው ማራቶን በተወለደባት የግሪኳ አቴና ከተማ ውስጥ ነው። ሁለቱ አትሌቶች በዓለም አቀፍ የማራቶኖች እና የረዥም ርቀቶች ውድድር ማኅበር (AIMS) መስፈርት ተሸላሚ የኾኑት በዓመቱ ውስጥ ባከናወኗቸው ውድሮቻቸው ተገምግመው ነው።

እንደ የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማኅበር (IAAF)ዘገባ፦ ከ«ምርጥ የማራቶን ሯጭ» ሽልማት በተጨማሪ ሌሎች ሽልማቶችም ተሰጥተዋል። ፈረንሳይ ውስጥ የሚታተመው የሎኪፕ ጋዜጣ ምክትል ዋና አርታኢ ጋዜጠኛ አላን ሉንሰንፍሊሽተር የሕይወት ዘመን ስኬት ተሸላሚ ኾኗል። አላን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1975 እስከ 2013 ድረስ 17 የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን ዘግቧል።

Symbolbild - Marathon
ምስል Colourbox/Labrador

የቻይናው ዢያሜን ማራቶን የአረንጓዴ ሽልማት አግኝቷል። በዚህ ዘርፍ ከቻይና ውድድር አዘጋጆች ሽልማት ሲያገኝ ዢያሜን ማራቶን የመጀመሪያው ነው።  የውድድሩ አዘጋጆች በከባቢ አየር ጥበቃ፤ ተረፈ ምርቶች ማስወገጂያ ስልት እና ስለ ከባቢ አየር ግንዛቤ በማስጨበጥ ላበረከቱት አስተዋጽዖ ነው ተሸላሚ መኾን የቻሉት። አዘጋጆቹ ከ2015 ጀምሮ 130,000 ችግኞችን በመትከል «የዢያማን የፍቅር ደን» የተሰኘው ጫካ እንዲፈጠር አስችለዋል።

የዩኒሴፉ ሐርሞኒ ጄኔቫ ማራቶን የዘንድሮ የዓለም አቀፍ የማራቶኖች እና የረዥም ርቀቶች ውድድር ማኅበር ተሸላሚ ኾኗል። ውድድር አዘጋጆቹ ከዩኒሴፍ ጋር በመቀናጀት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2010 ጀምሮ በንጹሕ ውኃ አቅርቦት እና የንጽህና አጠባበቅ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽዖ ነው ተሸላሚ የኾኑት።

የቡርኪናፋሶው ቢሊፎ የተሰኘ ለወጣቶች የተቋቋመ ድርጅትም በርካታ የውድድር አልባሳትን በማሰባሰብ ተሸልሟል። ድርጅቱ 1000 ኪሎ ግራም የልብስ ክምሮችን ማሰባሰብ ችሏል። ድርጅቱ አካል ጉዳተኞች እና ስደተኞች በውድድሮች ተሳታፊ እንዲኾኑ በመርዳቱም ጭምር ነው የተሸለመው።

Logo IAAF Weltleichtathletikverband

ቻይና ውስጥ በተከናወነው የናንቻንግ ማራቶን የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ትናንት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃን ተቆጠጥረው ለድል በቅተዋል። አትሌት መልካም ግዛው ውድድሩን በአንደኛነት ያጠናቀቀችው 2 ሰአት፤ ከ29 ደቂቃ ከ01 ሠከንድ በመሮጥ ነው። ልጅ ከወለደች በኋላ ወደ ውድድሩ ተመልሳ ለድል የበቃችው ከአራት ዓመት በኋላ መኾኑን «ኢንዲፔንደንት ኦንላይን» የተሰኘው የደቡብ አፍሪቃው የድረገጽ ጋዜዛ ዘግቧል። በቀሉ ቤጂ ከ26 ሰከንዶች በኋላ ውድድሯን በማጠናቀቅ የኹለተኛ ደረጃን አግኝታለች። ከስምንት ወራት በፊት በውሺ የማራቶን ሩጫ ወቅት ካስመዘገበችው ሰአት የትናንቱ ከአንድ ደቂቃ በላይ የዘገየ ነው። ጋዲሴ ነጌሳ የግሏን ሰአት በማሻሻል ሦስተኛ ወጥታለች። ጋዲሴ ከበቀሉ በአንድ ደቂቃ ከ3 ሰከንዶች በመቀደም 2 ሰአት፤ ከ30 ደቂቃ፤ ከ30 ሰከንድ ሮጣ ነው ሦስተኛ ደረጃን ያገኘችው።

በወንዶች ተመሳሳይ ፉክክር አንደኛ እና ኹለተኛ የወጡት ኬንያውያን ናቸው። ኢትዮጵያዊው አትሌት ታደሰ ተመቻቹ 2 ሰአት፤ ከ11 ደቂቃ፤ ከ31 ሰከንድ ሮጦ  የሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል። ኬኒያውያኑ ኪፕሊሞ እና ኮስማስ ኪዬያ አንደና እና ኹለተኛ ወጥተዋል። ቻይና ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረገው ውድድር በአንደኛነት ያሸነፈው ኪፕሎሞ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ፦ 2 ሰአት፤ ከ09 ደቂቃ፤ ከ54 ሰከንድ ነው። በዚህ ውጤቱም በቦታው ተይዞ የቆየውን ክብረ ወሰን መስበር ችሏል። የቦታው ክብረወሰን ተይዞ የቆየው በሀገሩ ልጅ ዳግላስ ኪሜሊ ነበር። ኪፕሎሞ ባለፈው ዓመት በቦታው የተያዘውን ክብረ ወሰን ያሻሻለው በ3 ደቂቃ ከ32 ሰከንድ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ