ስፖርት፤ ኅዳር 26 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.
ማክሰኞ፣ ኅዳር 27 2009በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ አራተኛ ዙር የእግር ኳስ ጨዋታ አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ መጪው ፋሲል ከነማ መሸነፉ ብዙዎችን አስደምሟል። ኢትዮጵያ ቡና አቻ ወጥቷል። በሳምንቱ ማሳረጊያ ላይ በተከናወነው የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ አራተኛ ዙር ውድድር ቅዱስ ጊዮርጊስ ጎንደር ከነማ ውስጥ ባደረገው ጨዋታ በፋሲል ከነማ 2 ለ1 ተሸንፏል። አንድ እኩል ቆይቶ ባለቀ ሰአት በተሰጠ ፍጹም ቅጣት ምት ቅዱስ ጊዮርጊስን የረታው ፋሲል ከነማ ቡድን ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ቡና ቡድንንም መርታቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ቡና ከአዳማ ከተማ ጋር ተጋጥሞ አንድ እኩል ወጥቷል። አርባምንጭ ከተማ ጅማ ከተማን 3-0 ፤ ድሬዳዋ ከተማ አዲስ አበባ ከተማን እንዲሁም ሲዳማ ቡና ወላይታ ድቻን 1-0 በሜዳቸው አሸንፈዋል። መከላከያ ወልድያን 2-0 ማሸነፍ ተሳክቶለታል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርተዋል።
ፖላንድ ውስጥ በተከናወነው የዓለም ጁ ጂትሱ ፍልሚያ የመጨረሻው ዙር ላይ የደረሰ ኢትዮጵያዊ ተፋላሚ ነው ያሬድ ንጉሤ። አሰልጣኙ ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ በኢሜል የላኩልን መልእክት እንደሚያመለክተው ያሬድ በዓለም አቀፍ ውድድር መስፈርት ያገኘው ነጥብ ከአፍሪቃ አንደኛ ያሰኘዋል ብለዋል። ያሬድ በፖላንዱ ውድድር ግማሽ ፍጻሜ የደረሰው ነዋዛ በተሰኘው የብራዚሉ ጁ ጂትሱ ያሬድ ፍልሚያ ነው።
ዓለም አቀፍ ውድድር ለያሬድ አዲስ አይደለም። «ለውድድር አዲስ አይደለሁም በዓለም አቀፍ ውድድር ለሁለተኛ ጊዜ ነው የተወዳደርኩት» ያለው ያሬድ በውድድሩ ነሐስ ሜዳሊያ ለማምጣት የነበረው ዕድል ያመለጠው የጨዋታውን አዲስ ሕግ አለማጤኑ እንደሆነ ገልጧል። «በኔዋዛ ውድድር ላይ ብዙ ተወዳዳዎች ቅሬታ አቅርበዋል» ሲል የገለጠው ያሬድ «በነጥብ ደረጃ እኔ ነበርኩ የምመራው። ግን ለኔዋዛ ጁጂትሱ ውድድር አዲስ በመሆኔ» አራተኛ ወጥቻለሁ ብሏል።
በኢትዮጵያ ውድድሩ ለማከናወን ብዙ ዕድሎች እንደሌሉም ገልጧል። ውድድሩ እንዲስፋፋ እና ወደፊት በርካታ ኢትዮጵያውያንም ዕድሉን እንዲያገኙ ለማድረግ አስፈላጊው ጥረት ቢደረግ መልካም ነው። ያሬድ «አሁን የነበረው ስህተት እንዳይደገም ለማድረግ የተለያዩ ስልጠናዎች ይደረጉልኛል» ብሏል። የያሬድ አሰልጣኝ ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ ፖላንድ ውስጥ በሚደረገው ቀጣዩ ውድድርም ያሬድ «አፍሪቃን ወክሎ» እንደሚወዳደር በኢሜል መልእክታቸው ገልጠዋል።
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሚድልስቦሮው እና ሁል ሲቲ ዛሬ ማታ ተስተካካይ 14ኛ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። ትናንት እስከ 75ኛው ደቂቃ ድረስ 3 ለ1 ሲመራ የቆየው ሊቨርፑል በ4 ለ3 ሽንፈት ነጥብ ጥሏል። የሊቨርፑል ግብ ጠባቂ ሎሪስ ካሪየስ ከተቆጠሩበት አራት ግቦች ሦስቱን ማዳን ይችል ነበር ሲሉ ብዙዎች ተችተዋል። ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ግን ለሽንፈታችን ግብ ጠባቂው ሎሪስ ካሪየስ ብቸኛ ተጠያቂ መሆን የለበትም ብለዋል። በእርግጥ ግን የትናንቱ ጨዋታ ሎሪስ ካሪየስ ደካማ ሆኖ የታየበት ነበር ማለት ይቻላል።
ቸልሲ ቅዳሜ ዕለት ማንቸስተር ሲቲን 3 ለ1 አሸንፎ ነጥቡን 34 በማድረሱ የደረጃ ሰንዘረዡን እየመራ ነው። ዌስትሀም ሲቲን 5 ለ1 ያንኮታኮተው አርሰናል 31 ነጥብ ይዞ ቸልሲን በቅርብ ርቀት ይከተለዋል። ሽንፈት የቀመሱት ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ 30 ነጥብ አላቸው፤ ሊቨርፑል በግብ ክፍያ በልጦ 3ኛ ደረጃ ይዟል። ቶትንሀም ቅዳሜ ዕለት ስዋንሲ ሲቲን5 ለ0 አደንዝዞ ነጥቡን 27 ቢያደርስም በደረጃ ሠንጠረዡ ግን ከማንቸስተር ሲቲ ዝቅ ብሎ አምስተኛ ነው። በነገራችን ላይ በቀይ ካርድ የተሰናበተው የማንቸስተር ሲቲው አጥቂ ሰርጂዮ አጉዌሮ አራት ጨዋታዎችን እንደሚቀጣ የእንግሊዝ እግር ኳስ ማኅበር ዛሬ አስታውቋል። ትናንት ከኤቨርተን ጋር አንድ ለአንድ አቻ የተለያየው ማንቸስተር ዩናይትድ በ21 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ዘንድሮ ከታችኛው ዲቪዚዮን ያደገው ላይፕትሲሽ ቡድን ኃያላኑን ልቆ መሪነቱን እንደጨበጠ ነው። ላይፕትሲሽ ቅዳሜ ዕለት ሻልከን 2 ለ 1 ድል አድርጎ የሰበሰበው ሦስት ነጥብ ተደምሮለት ቡንደስሊጋውን በ33 ነጥብ እየመራ ይገኛል።
ዐርብ እለት ማይንትስን 3 ለ1 ድል አድርጎ 3 ተጨማሪ ነጥብ ማግኘት የቻለው ባየር ሙይንሽን ከመሪው ላይፕትሲሽ በ3 ነጥብ ከመበለጥ ግን አልዳነም። ኮሎኝ በሆፈንሃይም ሲሸነፍ፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ተጋጣሚው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 4 ለ1 አደባይቷል። ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋር ያለውን ነጥብም ወደ አንድ ዝቅ አድርጎ 6ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል።
ትናንት ከአውስቡርግ ጋር ገጥሞ አንድ እኩል የተለያየው አይንትራኅት ፍራንክፉርት 25 ነጥብ አለው፤ በአምስተኛ ደረጃ ይገኛል። ሔርታ ቤርሊን ወራጅ ቃጣናው ጠርዝ ላይ የሚገኘው ቮልፍስቡርግን 3 ለ2 በማሸነፍ ነጥቡን 27 አድርሷል። ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ባየር ሙይንሽን በ3 ነጥብ ብቻ ነው ዝቅ ብሎ የሚገኘው። አራተኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ከሚከተለው ሆፈንሀይም በ2 ነጥብ ይበልጣል።
ቬርደር ብሬመን ኢንግሎሽታድትን 2 ለ1 ሲያሸንፍ፤ ሌቨርኩሰን ከፍራይቡርግ አንድ ለአንድ አቻ ወጥቷል። ትናንት ሐምቡርግ ዳርምሽታድትን 2 ለ0 ቢያሸንፍም በ7 ነጥቡ ብቻ ተወስኖ 17ኛ ደረጃ ላይ ማንጎላጀጁ ግን አልቀረለትም። ሐምቡርግ በአንድ ነጥብ የሚበልጠው መጨረሻ ደረጃ ላይ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ የወሰደው ኢንግሎሽታድትን ብቻ ነው። በዚሁ ከቀጠሉ ተደጋግፈው ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን ማሽቆልቆላቸው አይቀርም።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አርያም ተክሌ