1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ኅዳር 8 ቀን፣ 2012 ዓ.ም

ሰኞ፣ ኅዳር 8 2012

በአውሮጳ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የቤላሩስ አቻውን በሰፋ ልዩነት ቢያሸንፍም ቡድኑ ብዙ ማሻሻል የሚገባው ነገር አለ ተብሏል። እሑድ ኅዳር 7 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ዕለት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሩጫ ውድድር በአዲስ አበባ ተከናውኗል። በውድድሩ 45 ሺህ ሰዎች ተሳታፊ መኾናቸው ተገልጧል።

https://p.dw.com/p/3TFqv
EM Quali Deutschland Weißrussland
ምስል Imago-Images/M. Müller

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

እሑድ ኅዳር 7 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ዕለት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሩጫ ውድድር በአዲስ አበባ ተከናውኗል። በውድድሩ 45 ሺህ ሰዎች ተሳታፊ ኾነዋል። በውድድሩ ተሳታፊ የነበሩ ሁለት ወጣቶች እና የውድድሩ ዋና ሥራ አስኪያጅን በስልክ አነጋግረናል። በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮች ደግሞ የአውሮጳ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ተከናውነዋል። የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የቤላሩስ አቻውን በሰፋ ልዩነት ቢያሸንፍም ቡድኑ ብዙ ማሻሻል የሚገባው ነገር አለ ተብሏል። በሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ግጥሚያ  አዲስ ወጣት ተጨዋች ብቅ ብሏል። 

በአውሮጳ ዋንጫ የእግር ኳስ የማጣሪያ ጨዋታ በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ ሃገራት ተከናውኗል። ነገ ከሰሜን አየርላንድ ጋር የሚገጥመው የጀርመን ቡድን ቅዳሜ ዕለት ቤላሩስን 4 ለ0 ድል አድርጓል። ኾኖም ቡድኑ ቤላሩስን ያሸነፈበት ጨዋታ ትችት ገጥሞታል። የአሰልጣኝ ዮኣሒም ሎይቭ ወጣት ቡድን ጨዋታው ከተጀመረ ከግማሽ ሰአት በላይ ግብ ማስቆጠር ተስኖት መቆየቱ ለትችት ከዳረጉት ነገሮች ውስጥ ይገኛል። 

በሌላ መልኩ ደግሞ ቡድኑ ካስቆጠራቸው አራት ግቦች መካከል ሁለቱ ከጨዋታ ውጪ ኾነው ሊመዘገቡ ይገባል የሚል አስተያየት ይሰነዘራል። በእርግጥም ግቦቹን ያስቆጠሩት ተጨዋቾች ግብ ሲያስቆጥሩ ለመለየት በሚያስቸግር መልኩ ከጨዋታ ውጪ ነበሩ። 

EM Quali Deutschland Weißrussland
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Meissner

ዕውቁ ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየር ለቤላሩስ የተሰጠውን ፍጹም ቅጣት ምት ግብ ከመኾን ባያድን እና አንድ ከርቀት የተመታች ኳስን አየር ላይ ተንሳፎ በድንቅ ኹኔታ ባያጨናግፍ ኖሮ ምናልባት የጀርመን ቡድን ኹለት እኩል ሊለያይ ይችል አለያም ጨዋታውም ሊቀየር ይችል ነበር።

በምድብ ሐ መሪ የኾነው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን 18 ነጥብ ይዟል። የኔዘርላንድ ቡድን በ16 ይከተለዋል። ነገ የሚገጥመው ሰሜን አየርላንድ13 ነጥብ ያለው በመኾኑ የነገው ጨዋታ ለሰሜን አየርላንድ የሞት ሽረት አይነት ነው። ቤላሩስ ከምድቡ 4 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አንድ ነጥብ ብቻ ያላት ኢስቶኒያ በምድቡ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ትገኛለች። 

ዛሬ ምሽት ስፔን ከሩማንያ፤ እንዲሁም ስዊድን ከፋራዎ ደሴቶች ጋር ይጋጠማሉ። ግሪክ ከፊንላንድ፤ ኖርዌይ ከማልታ፤ ዴንማርክ ከአየርላንድ እንዲሁም ጣሊያን ከአርመንያ ጋር ዛሬ ምሽት ይጫወታሉ።  

አትሌቲክስ
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 19ኛ ዙር ውድድር ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ ሲከናወን 45 ሺህ ሰዎች መሳተፋቸው ተገልጧል። ውድድሩ በሰላም ተጀምሮ በሰላም የተጠናቀቀ ሲኾን አዝናኝ እንደነበረም የሩጫው ተሳታፊዎች ገልጠዋል። ወጣት ትርሲት ጉተማ የውድድሩን ድባብ እንዲህ ትገልጣለች።

በሩጫው ወቅት የተለያዩ ጭፈራዎች፤ ቀልዶች ዝማሬ እና የፖለቲካ መልእክቶችም ሲንጸባረቁበት እንደነበር ተሳታፊዎች ይናገራሉ። በግል ሥራ ተዳዳሪ የኾነው ታደሰ ወልደ አማኑኤል በትናንቱ የሩጫ ውድድር ተሳታፊ ነበር፤ በውድድሩ ጎልተው የወጡ ጉዳዮችን ሲያብራራ «ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ የፖለቲካዊ ነገሮችን ይዞ ነበር» ብለዋል።
አቶ ኤርሚያስ አየለ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። በሚቀጥለው 20 ዓመቱን የሚደፍነው ታላቁ ሩጫ ዘንድሮ ስኬታማ እንደነበር ተናግረዋል። 
የሜዳ ቴኒስ
ወጣቱ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ሽቴፋኖስ ጺጺፓስ በ17 ዓመታት የሚበልጠው ዕውቁ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ሮጀር ፌዴሬርን ማሸነፉ በርካቶችንን አስደምሟል። ያም ብቻ አይደለም፦ የ21 ዓመቱ ወጣት ግሪካዊ በቴኒስ ባለሞያዎች ማኅበር ፍጻሜ የኦስትሪያው ዶሚኒክ ቲምን ድል አድርጎታል። ውድድሩን በመላው ዓለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በቴሌቪዥን ተመልክተውታል።

Spanien: Mutua Madrid Open -  Rafael Nadal
ምስል picture-alliance/O. Barroso

ማንተጋፍቶት ስለሺ