1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ የካቲት 14 ቀን፣ 2008 ዓ.ም

ሰኞ፣ የካቲት 14 2008

በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ውድድር የማንቸስተር ሲቲው አሠልጣኝ ማኑኤል ፔሌግሪኒ ከባድ ስህተት ፈጽመዋል። ቡድናቸው በቸልሲ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ ተሰናብቷል። ዌስትሐም ዩናይትድ በተመሳሳይ ብላክ በርንን ለከባድ ሽንፈት ዳርጎታል። አፍሪቃውያን ተጨዋቾች በአውሮጳ የእግር ኳስ ውድድሮች ሣምንቱን በስኬት አጠናቀዋል።

https://p.dw.com/p/1I02m
Bundesliga Hannover 96 - FC Augsburg Torwart Marwin Hitz
ምስል picture-alliance/dpa/J. Stratenschulte

ስፖርት፤ የካቲት 14 ቀን፣ 2008 ዓ.ም

አፍሪቃውያን ተጨዋቾች በአውሮጳ የተለያዩ የእግር ኳስ ውድድሮች የሣምንቱ ማሣረጊያ ላይ ብቃታቸውን አስመስክረዋል። የቡርኪናፋሶው አማካይ ቸልሲ 5 ለ1 እንዲያሸንፍ አድርጓል። አንጎላዊው አጥቂ በስፔን ላሊጋ የመጀመሪያ ግቡን አስቆጥሯል። ካሜሩናዊው የማላጋ ግብ ጠባቂ የክርስቲያኖ ሮናልዶን ፍፁም ቅጣት ምት አድኗል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ አወዛጋቢ በኾነ መልኩ አሸንፏል። ከሌቨርኩሰን ጋር ያደረገው የትናንቱ ጨዋታ ለ10 ደቂቃ ግድም ተቋርጦ ነበር። ጀርመናዊው የከባድ ሚዛን ቡጢኛ ለአምስተኛ ጊዜ አሸናፊ ኾኗል።

የዌስት ሐሙ የክንፍ ተመላላሽ ናይጀሪያዊው ቪክቶር ሞሰስ ቡድኑ በኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ ብላክ በርንን 5 ለ1 ባሸነፈበት ጨዋታ አቻ የምታደርገውን ግብ ማስቆጠር ችሏል። ከቱርኩ ፌኔርባኅ ቡድን በውሰት የመጣው ሌላኛው ናይጀሪያዊ የዌስት ሐም አጥቂ ኤማኑኤል ኤሜኒኬ ደግሞ ኹለት ግቦችን ከመረብ አሣርፏል።

የቡርኪናፋሶው አማካይ በርትራንድ ትራዎሬ በጭንቅላቱ ወደኋላ ገጭቶ ለቸልሲ አምስተኛዋን ግብ አስቆጥሯል። ዲዬጎ ኮስታ ለቸልሲ የመጀመሪያዋን ግብ በ35ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ካሳረፈ ከኹለት ደቂቃ በኋላ ነበር ዴቪድ ፋውፓላ ለማንቸስተር ሲቲ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው። ግቧን አስቆጥሮ ከጓደኞቹ ጋር ደስታውን በሚገልጥበት ወቅት ግን ከቸልሲ ደጋፊዎች አካባቢ ሣንቲሞች ተወርውሮባቸዋል። የቸልሲ ቡድን የመገናኛ አውታሮች ተጠሪ ሣንቲም ወርዋሪዎቹን ማንነታቸውን ካጣራን በኋላ ከእንግዲህ ስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ድርሽ እንዳይሉ እናግዳቸዋለን ብለዋል።

አወዛጋቢ በኾነ መልኩ በርካታ ታዳጊ ተጨዋቾችን አሰልፈው የአምስት ለአንድ ከባድ ሽንፈት የገጠማቸው የማንቸስተር ሲቲው አሠልጣኝ ማኑኤል ፔሌግሪኒ ይቅርታ አልጠይቅም ብለዋል። አሠልጣኙ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረው ዝነኛው የኤፍ ኤ ካፕ ውድድርን አላከበሩም፤ ለዚያም ነው ስድስት ታዳጊ ተጨዋቾችን ያሰለፉት የሚል ቅሬታ ተሰንዝሮባቸዋል። ማንቸስተር ሲቲ መቀመጫውን አቡዳቢ ባደረጉ ባለቤቶቹ መተዳደር ከጀመረ ከስምንት ዓመት ወዲህ የትናንቱ ሽንፈት ከባዱ ተብሎ ተመዝግቦበታል።

Deutschland Fußball Bundesliga Bayer Leverkusen - FC Bayern München
ምስል Getty Images/Bongarts/L. Baron

ስፔን ውስጥ ደግሞ በላሊጋው ግጥሚያ ካሜሩናዊው የማላጋ ግብ ጠባቂ ካርሎስ ካሜኒ የሪያል ማድሪዱ አጥቂ የክርስቲያን ሮናልዶን ፍፁም ቅጣት ምት አድኗል። ከጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብሎ ግን ለለሪያል ማድሪድ ብቸኛዋን ግብ በጭንቅላት ያስቆጠረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ነበር። የማላጋው ራውል አልቤንቶሳ 66ኛው ደቂቃ ላይ በግራ እግሩ ከመሬት ጋር አጋጭቶ የላካት ኳስ ከመረብ በማረፍ ጨዋታው አንድ እኩል ተጠናቋል።

እዛው የስፔን ላሊጋ ግጥሚያ ውስጥ የራዮ ቫሌካኖው አጥቂ አንጎላዊው ማኑቾ በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያው የኾነችውን ግቡን ማስመዝገብ ችሏል። በሴቪላ 2 ለባዶ ሲመራ የነበረው ራዮ ቫሌካኖ አቻ የወጣው ከረፍት መልስ ተቀይሮ የገባው ማኑቾ እና ሚኩ ባስቆጠሯቸው ግቦች ነው።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የሔርታ ቤርሊኑ አይቮሪኮስታዊ አጥቂ ሶሎሞን ካሉ ከቮልፍስቡርግ ጋር አቻ የተለያዩበትን ብቸኛ ግብ አግብቷል። ግቧ በውድድር ዘመኑ 11ኛ ተብላ ተመዝግባለታለች።

የዶርትሙንዱ ግብ አዳኝ ፒየር ኤመሪክ ኦቦምያንግ ምናልባትም ወደ የፈረንሣዩ የስፖርት ጋዜጣ ሌ ኪፕ የ26 ዓመቱ አጥቂ «የልጅነት ሕልሜ ለሪያል ማድሪድ መጫወት ነው» ማለቱን ጠቅሶ ዘግቧል። ለሪያል የመጫወት ፍላጎቱ ደግሞ አያቱ አጊላ የተሰኘችው የስፔን ከተማ ሰው መኾናቸው ነው። ከተማዋ ከማድሪድ 110 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው የምትርቀው።

እናም ጋቦናዊው አጥቂ ከአራት ዓመት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት አያቱ አንድ ቀን ለሪያል ማድሪድ እንደሚጫወት ቃል ገብቶላቸው እንደነበር ተናግሯል። «ያ ከባድ ቢኾንም ሁል ጊዜም ግን በአዕምሮዌ አለ» ብሏል።

ስፔናዊቷ እናቱ ልጃቸው ወደ ሪያል ማድሪድ ቢመጣላቸው «ታላቅ ስጦታ» እንደነበረ ገልጠዋል። ፒየር ኤመሪክ ኦቦምያንግ የምንግዜም ተምሳሌት የኾነው የሪያል ማድሪድ የጥንቱ ተጨዋች ሁጎ ሣንቼዝ ነው።

ኮከብ ግብ አግቢ ኾኖ የውድድር ዘመኑን ለማጠናቀቅ ከሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ጋር ትንቅንቅ የገባው ፒየር ኤመሪክ ኦቦምያንግ ወደ ሪያል ማድሪድ ለማቅናት ግን የቦሩስያ ዶርትሙንድ ፍቃድ ያስፈልገዋል። ለዶርትሙንድ እስከ 2020 ድረስ ነው የፈረመው። ገና የአራት ዓመት ውል ይቀረዋል። በነገራችን ላይ ፒየር እስካሁን 22 ኳሶችን ከመረብ ካሳረፈው ከሮበርት ሌቫንዶቭስኪ የሚበለጠው በአንድ ግብ ብቻ ነው።

በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ ትናንት ቸልሲ ማንቸስተር ሲቲን አምስት ለአንድ ጉድ አድርጎታል። ዌስትሐም ዩናይትድ በተመሳሳይ ብላክበርን ሮቨርስን የግብ ጎተራ አድርጎ አሰናብቶታል። ክሪስታል ፓላስ ቶትንሐም ሆትስፐርን ትናንት እንዲሁም ዋትፎርድ ሊድስ ዩናይትድን ከትናንት በስትያ አንድ ለዜሮ አሸንፈዋል። ዌስት ብሮሚች በሪዲንግ 3 ለ1 ሲሸነፍ፤ ኤቨርተን በርመስን 2 ለባዶ አሸንፎዋል። አርሰናል ከሁል ሲቲ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል። ዛሬ ማንቸስተር ዩናይትድ ከሽሮውስቤሪ ይጋጠማሉ።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ደግሞ ዶርትሙንድ 1 ለ0 ያሸነፈበት ጨዋታ ከማወዛገብም አልፎ ለዐሥር ደቂቃ ያኽል ተቋርጦ ነበር። ጨዋታው የተቋረጠው የባየር ሌቨርኩሰኑ አሠልጣኝ ሮጀር ሽሚድት ከሜዳው ወጥተው ወደ ተዘጋጀላቸው የአሠልጣኞች ማረፊያቸው አልሄድም በማለታቸው ነበር። በ64ኛው ደቂቃ ላይ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብ ጋቦናዊው አጥቂ ያገባው ሽቴፋን ኪስሊንግ ላይ ጥፋት ተፈጽሞ ቅጣት ሳይሰጥ ጨዋታው ያላግባብ በመቀጠሉ ነው በሚል ቅሬታ ነበር አሠልጣኙ ያንገራገሩት። የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር አሠልጣኙ ላይ የዲሲፕሊን ክስ መስርቷል።

የከባድ ሚዛን ባለድሉ ፌሊክስ ሽቱርም
የከባድ ሚዛን ባለድሉ ፌሊክስ ሽቱርምምስል Getty Images/AFP/D. Grombowski
ፒየር ኤመሪክ ኦቦምያንግ
ፒየር ኤመሪክ ኦቦምያንግምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen
የሌቨርኩሰን አሠልጣኝ ፌሊክስ ዝዋየር
የሌቨርኩሰን አሠልጣኝ ፌሊክስ ዝዋየርምስል Getty Images/AFP/P. Stollarz

ጨዋታው እንዲቋረጥ ያደረጉት የመሀል ዳኛው ፌሊክስ ዝዋየርም ቅጣት ሊጠብቃቸው እንደሚችል ተገልጧል። ጨዋታው ከዘጠኝ ደቂቃ በላይ ተቋርጦ የተጀመረው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ አጥቂ አኹን የሌቨርኩሰን የስፖርት ዳይሬክተር ሩዲ ፎለር የሌቨርኩሰኑ አሰልጣኝ ከሜዳ ካልወጡ ጨዋታው ሙሉ ለሙሉ ይቋረጣል በማለታቸው ነበር። የ48 ዓመቱ አሰልጣኙ ለትናንቱ ድርጊታቸው ይቅርታ ጠይቀዋል።

ቡንደስ ሊጋውን በ59 ነጥብ እየመራ የሚገኘው ባየር ሙይንሽን ከታች ያደገው ዳርምሽታድት ቡድንን ቅዳሜ ዕለት 3 ለዜሮ አሸንፏል። ለባየር ሙይንሽን ቶማስ ሙይለር ኹለት ግቦችን አስቆጥሯል። በዚህ የጨዋታ ዘመን 17 ግቦች አሉት፤ በግብ ብዛት በቡንደስሊጋው ሦስተኛ ነው። ሦስተኛዋ ግብ የፖላንዱ አጥቂ የሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ናት። ለድርምሽታድት ብቸኛዋን ግብ ከመረብ ያሳረፈው የቀድሞው የባየርን ተጨዋች ዣንድሮ ቫግነር ነው።

ቡጢ
ጀርመናዊው የከባድ ሚዛን ቡጢ ተፋላሚ ፌሊክስ ሽቱርም ለአምስተኛ ጊዜ ባለድል ኾኗል። የ37 ዓመቱ ፌሊክስ በተቀራረበ የዳኞች ነጥብ ኦበርንሐውሰን ጀርመን ውስጥ ትናንት ያሸነፈው የሩስያው ተፋላሚ ፍዮዶር ቹዲኖቭን ነው። ፌሊክስ በውድድር ዘመኑ ካከናወናቸው 48 ግጥሚያዎች የትናንቱ 40ኛ ድሉ ነበር። ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ በሩስያዊው የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል ችሏል።

የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማሕበራት ፌዴሬሽን በእንግሊዘኛ ምኅጻሩ FIFA ፕሬዚዳንቱ የ79 ዓመቱ ሴፕ ብላተር በሙስና ቅሌት ከታገዱ ወዲህ ከመቼውም በበለጠ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። የቀድሞው ፕሬዚዳንቱን ማን ይተካቸው የሚለው ፌዴሬሽኑን እያወዛገበ ነው። ኾኖም የፊታችን ግን ውዝግቡ ያከትማል ተብሏል። 209 የእግር ኳስ ማኅበራትን ያቀፈው ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቱን መምረጥ ብቻ ሳይሆን አዲስ የአሠራር ለውጥ ዕቅዱን ድምጽ ይሰጥበታል ተብሏል። የፊፋ የለውጥ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ካራድ ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽኑ በአስቸኳይ ከችግር መፋጠን እንዳለበት ቀደም ሲል አሳስበው ነበር። ኾኖም ፊፋ አዲስ ፕሬዚዳንት መርጦ ከገባበት ቀውስ በአፋጣን ይወጣ እንደኾን ግን ወደፊት የሚታይ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

FIFA-Logo
ምስል picture-alliance/dpa/Steffen Schmidt

አዜብ ታደሰ