1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ የካቲት 16 ቀን፣ 2012 ዓ.ም

ሰኞ፣ የካቲት 16 2012

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ  ከታች የሚገኙ ቡድኖች ከገቡበት አረንቋ ለመውጣት፤ ላይ ያሉት ደግሞ በዋንጫ ፉክክሩ ገፍተው ከፍ ለማለት ግብግቡ ብርቱ ነበር። በደረጃ ሰንጠረዡ ቀዳሚው ባየር ሙይንሽን የደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ከታች በተዘረጋ ቡድን በብርቱ ተፈትኗል። በከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ ታይሰን ፉሪ ድል ቀንቶታል።

https://p.dw.com/p/3YKwV
Boxen Deontay Wilder vs Tyson Fury
ምስል picture-alliance/AP Photo/I. Brekken

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ  ከታች የሚገኙ ቡድኖች ከገቡበት አረንቋ ለመውጣት፤ ወደ ላይ ያሉት ደግሞ በዋንጫ ፉክክሩ ገፍተው ከፍ ለማለት የነበረው ግብግብ ብርቱ ነበር። በደረጃ ሰንጠረዡ የመጀመሪያ አናት ላይ የሚገኘው ኃያሉ ባየር ሙይንሽን የደረጃ ሰንጠረዡ ላይ በተዘረጋ ቡድን በብርቱ ተፈትኗል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ  አርሰናል እና ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት  ድል ቀንቷቸዋል። ዛሬ ማታ ተስተካካይ ጨዋታውን የሚያደርገው ሊቨርፑልን በ19 ነጥብ የሚከተለው ማንቸስተር ሲቲም ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ሦስት ነጥብ ይዞ ወጥቷል። የ19 ዓመቱ ኖርዌያዊ የእግር ኳስ አጥቂ ኧርሊንግ ብራውት ሐላንድ በቡንደስሊጋው ያለፋታ ግብ ማስቆጠሩን ተያይዞታል። በከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ ታይሰን ፉሪ ድል ቀንቶታል። ማነው ተረኛ ተጋጣሚዬ እያለም በመፎከር ላይ ነው። 

ፕሬሚየር ሊግ

የአርሰናሉ አጥቂ ፒየር ኤመሪክ አውባሜያንግ ሁለት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ በሳምንቱ መጨረሻ በአውሮጳ ከዋክብት ከነበሩ አፍሪቃውያን ዘንድ ተሰልፏል። ትናንት ኤቨርተንን 3 ለ2 ድል ያደረገው አርሰናል ከበርንሌይ እኩል 37 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ ግን በልጦ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የአርሰናሉ አጥቂ ፒየር ኤመሪክ አውባሜያንግ
የአርሰናሉ አጥቂ ፒየር ኤመሪክ አውባሜያንግ ምስል Getty Images/AFP/D. Leal-Olivas

በደረጃ ሰንጠረዡ ማንቸስተር ሲቲን በሦስተኛነት የሚከተለው ላይስተር ሲቲን ተስፋ ያጨለመው ብቸኛ ግብ እንዲቆጠር ያመቻቸው የአልጀሪያው ተወላጅ የክንፍ ተጨዋቹ አፍሪቃዊው ሪያድ ማኅሬዝ ነው። በቅዳሜው ግጥሚያ ሪያድ በ80ኛ ደቂቃ ያመቻቻትን ኳስ ጋብርኤል ጂሰስ ከመረብ አሳርፎ በተገኘው ድል ማንቸስተር ሲቲ ነጥቡን 57 ማድረስ ችሏል። ላይስተር ሲቲ በ7 ነጥብ ይበለጣል። በደረጃ ሰንጠረዡ 76 ነጥብ ይዞ በቀዳሚነት የሚገሰግሰው ሊቨርፑል 24 ነጥብ ይዞ ወራጅ ቃጣና 18ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዌስትሀም ዩናይትድን ዛሬ ማታ ይገጥማል። ትናንት ዋትፎርድን 3 ለ0 ያሸነፈው ማንቸስተር ዩናይትድ 41 ነጥብ ይዞ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በዚህ ውጤቱ ለጊዜው የአውሮጳ ሊግ የዙር ውድድር ማለፊያውን አስጠብቋል።

ቸልሲ ቶትንሀምን 2 ለ1 ባሸነፈበት ዕለት፦ ጀርመናዊው የቸልሲ ተከላካይ አንቶኒዮ ሩዲገር ላይ ደጋፊዎች የተቃውሞ ጩኸት ሲያሰሙ ተደምጠዋል። ሩዲገር ከዚህ ቀደም ከቶትንሀም ጋር በነበረው ግጥሚያ የዘረኝነት ስድብ ሰለባ ኾኖ ነበር። ጉዳዩ ተጣርቶም ሩዲገር ላይ የዘረኝነት ስድብ ስቴዲየሙ ውስጥ አልተሰማም ከተባለበት ጊዜ አንስቶ ተጨዋቹ ኳስ በያዘ ቁጥር ከባላጋራ ቡድን ደጋፊዎች ዘንድ ተቃውሞ እየደረሰበት ነው። ስታዲየሙ ባለኝ ዘመናዊ ካሜራዎች ታግዤ ከፖሊስ ጋር ባደረግሁት ማጣራት ምንም የዘረኝነት ፍንጭ አላገኘኹም ቢልም ሩዲገር ግን የዘረኝነት ስድብ ሰለባ ኾኛለሁ ትግሌን አላቆምም ብሏል።

«ስታዲየም ውስጥ ጸረ ዘረኝነት መፈክሮችን ከፍ አድርጎ ማሳየት አለያም አምበሎች የኾነ ነገር እንዲያነቡ ማድረግ ብቻውን በቂ አይደለም» ያለው አንቶኒዮ ሩዲገር ከእንግሊዙ ፕሬሚየር ሊግ ባሸገር ጀርመን በቡንደስሊጋው የሚታየው ዘረኝነት ሊስተካከል ይገባል ሲል ተደምጧል።

በእርግጥም ስታዲየም ውስጥ ተጨዋቾች ዘረኝነት ስድብ ሲፈጸምባቸው ከተመልካቾች ዘንድ ድጋፍ እንደሚኢሻቸው ባለሞያዎች ይናገራሉ። ፍራንክፉርት አም ማይን ውስጥ በእግር ኳስ እና ዘረኝነት ባለሞያ የኾኑት ጌርድ ቫግነር ከአንቶኒዮ ሩዲገር ጋር የሚቀራረብ ነገር ተናግረዋል።

ጀርመናዊው የቸልሲ ተከላካይ አንቶኒዮ ሩዲገር
ጀርመናዊው የቸልሲ ተከላካይ አንቶኒዮ ሩዲገርምስል picture-alliance/dpa/PA wire/N. Carson

«ሙይንስተር ውስጥ የተደረገው እንዴት አይነት አጸፌታ ማድረግ እንዳለባቸ  ለሌሎች ቡድኖችም አብነት ሊኾን ይችላል።  ዘረኝነት ሲከሰት ልክ ፖርቶ ውስጥ ሞሳ ማሬጋ ብቻውን ከሜዳው እንደወጣው አይነት ጉዳዩን በደል ለደረሰበት ተጨዋቹ ብቻ መተው የለበትም። ይልቁንስ ተጨዋቾቹም ኾኑ የስታዲየሙ ታዳሚዎች ድጋፋቸውን ማሳየት ይችላሉ። ያ ቀና የኾነ እና ይበል የሚያሰኝ ነው።»

ሙይንስተር ውስጥ በጀርመን ሦስተኛ ሊጋ ተጨዋች የኾነው ሌሮይ ክዋድዎ ላይ እንደጦጣ በመጮኽ የዘረኝነት ስድብ ያሰማ የ29 ዓመት የስታዲየም ታዳሚ በደጋፊዎች ጥቆማ በመላ ጀርመን ለሦስት ዓመታት የትኛውም ስታዲየም እንዳይገባ ታግዷል።  5457 ታዳሚዎች የነበሩበት ግጥሚያ ቢኾንም ዘረኝነት በየትኛውም ቦታ ሊወገዝ ይገባል ሲሉ መገናኛ አውታሮች አስተጋብተዋል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ

መሪው ባየር ሙይንሽን በ33 ነጥብ ርቀት የሚበልጠው ፓዴርቦርንን ዐርብ ዕለት በመከራ 3 ለ2 አሸንፏል። በደረጃ ሰንጠረዡ 49 ነጥብ ሰብስቦ አንደኛ የኾነው ባየር ሙይንሽንን ላይፕሲሽ በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጦ ይከተላል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ አዲስ  ወጣት አጥቂ ማሰለፍ ከጀመረ ወዲህ በግብ እየተንበሸበሸ ነው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቅዳሜ ዕለት ቬርደር ብሬመንን 2 ለ0 አሸንፏል። ለዶርትሙንድ ማሸነፊያዋን ግብ በ66ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው የ19 ዓመቱ ኖርዌጂያዊ የእግር ኳስ አጥቂ ኧርሊንግ ብራውት ሐላንድ ነው። ሓላንድ ወደ ጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዘንድሮ ከተዘዋወረ በኋላ እጅግ ድንቅ ብቃቱን በማሳየት ላይ ይገኛል።

የባየር ሌቨርኩሰኑ ሞሳ ዲያቢ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን እየገለጠ
የባየር ሌቨርኩሰኑ ሞሳ ዲያቢ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን እየገለጠምስል Imago Images/Revierfoto

ለሻምፒዮንስ ሊግ የዙር ግጥሚያ ቡድኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንጀርሜን ጋር ተጫውቶ 2 ለ1 ባሸነፈበት ግጥሚያ ኹለቱንም ኳሶች ከመረብ ያሳረፈው ይኸው ሐላንድ ነው። ፓሪስ ሴንጄርሜን ላይ ያስቆጠረው ኹለተኛ ግብ በዶርትሙንድ አጭር ቆይታው 11ኛ ግቡ ኾኖ ተቆጥሮለታል። ይኽ ወጣት ተጨዋች እጅግ አስደማሚ የኾነው ከማንም በተሻለ ኹኔታ በአኹኑ ወቅት የግብ አዳኝ መኾኑን በማስመስከሩ ነው። ለቀድሞው ቡድኑ ሬድ ቡል ዛልስቡርግ እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ 40 ግቦችን፤ ሦስት ሔትሪኮችን አስቆጥሯል። ባለፉት ሰባት የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ብቻ ደግሞ ለኹለቱ ቡድኖች 10 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ድንቅ ተጨዋች ነው። ስምንቱ ለሬድ ቡል ዛልስቡርግ ያስቆጠራቸው ናቸው።

እጅግም ፈጣን ነው። ከእግር ኳሱ ባሻገር ፈጣን አትሌትነቱን ያገኘው ከወላጆቹ ሳይኾን አይቀርም። አባቱ እንግሊዝ ውስጥ የሊድስ ዩናይትድ እና ከ17 ዓመት በፊት ደግሞ የማንቸስተር ሲቲ ተከላካይ ተጨዋች ነበሩ። ሓላንድም የተወለደው እና እስከ ሦስት ዓመቱ ድረስ የቆየው እዛው እንግሊዝ ነበር። እናቱ ግሪ ማሪታ ደግሞ በኖርዌይ ብሔራዊ ሄፕታትሎን ማለትም በኹለት ቀናት ሰባት የጨዋታ አይነቶች የሚከናወኑበት ውድድር አሸናፊ ነበረች።

ለዶርትሙንድ ገና ለመጀመሪያ በተሰለፈበት እለት ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትሪክ መሥራት የቻለ ብርቱ ተጨዋች ሃላንድ ነው። በመጀመሪያ ቀን ተሰላፊነቱ በ23 ደቂቃዎች 3 ግቦችን ማስቆጠር የቻለም ፈጣን አጥቂ ነው። ያንን በቡንደስሊጋው ቦሩስያ ዶርትሙንድ አውስቡርግን 5 ለ1 ባሸነፈበት ግጥሚያ አስመስክሯል።

ኖርዌጂያዊ የእግር ኳስ አጥቂ ኧርሊንግ ብራውት ሐላንድ
ኖርዌጂያዊ የእግር ኳስ አጥቂ ኧርሊንግ ብራውት ሐላንድምስል Getty Images/Bongarts/J. Schüler

ብዙም ተጨዋቾችን አጉል ማወዳደስ የማያበዙት ቆፍጠን ያሉት የቦሩስያ ዶርትሙንዱ አሰልጣኙ ሉሲያን ፋቭሬ ራሳቸው እንኳን በሓላንድ እጅግ ነው የተመሰጡት። በጀርመንኛ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፦ «19 ዓመት ልጅ ገና ከመሰለፉ እንዲህ በግብ ሲንበሸበሽ ዐይቼ ዐላውቅም» በማለት አድናቆታቸውን መሸሸግ አልቻሉም። «ገና በተሰለፈ በመጀመሪያ ቀኑ ወዲያው 3 ግብ ነው ያስቆጠረው። ለእኛ ለቦሩስያ ዶርትሙንዶች በአጠቃላይ ጥሩ ነው። ከፍተኛ አቅም ያለው ልጅ ነው» ብለዋል።

ቦሩስያ ዶርትሙንድ አጥቂ ተጨዋቾቹ ላይ የመመሳሰል ነገር አለ፤ የምር ወሳኝ የኾነ የመሀል አጥቂ ተጨዋች እጥረት አለበት እየተባለ ነበር ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲተች የነበረው። ሓላንድ ግን ለየት ያለ ነው። አሰልጣኙ «መስመር ላይ ሲንቀሳቀስ ጥሩ ነው። ደግሞ ለእኛ ወደፊት እየገፋን እንድንጫወት ሌላ አይነት እድል ይዞልን ነው የመጣው» ብለዋል።  ለዶርትሙንድ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰለፈበት ቀን፤ ተቀይሮ እስኪገባ ድረስ አውስቡርግ ዶርትሙንድን 3 ለ1 እየመራ ነበር። በግማሽ ሰአት ውስጥ ግን ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ ዶርትሙንድ ጨዋታውን በ5 ለ3 ድል እንዲያደርግ በማስቻል ብቃቱን አስመስክሯል። 56ኛው ደቂቃ ላይ እንደገባ 3 ደቂቃ ከ4 ሰከንድ ብቻ ነው የቆየው ግብ ለማስቆጠር።

ላይፕሲሽ ቶትንሀምን በሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ 1 ለ0 ድል ባደረገበት ወቅት ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ጀርመናዊው ቲሞ ቬርነር በቡንደስሊጋው ሻልከን 5 ለ0 ባደባዩበት የቅዳሜ ዕለት ግጥሚያም ኹለተኛዋን ግብ ያስቆጠረው ይኸው ቲሞ ቬርነር ነው። አራት ግጥሚያዎች ላይ ግብ ማስቆጠር ለተሳነው ቲሞ ቬርነር የሰሞኑ ጅማሬው በቀጣይ በቡንደስሊጋው ዋነኛ ግብ አስቆጣሪዎች ተርታ ያሰልፈዋል። በ44 ደቂቃዎች 1 ግብ ከሚያስቆጥረው ኧርሊንግ ሃላንድ እና በየ82 ደቂቃው በአማካይ አንድ ግብ ከመረብ ከሚያሳርፈው ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ አንጻር የቲሞ ቬርነር በ93 ደቂቃ አንድ ግብ ማስቆጠርም ለአሰልጣኝ ጁሊያን ናገልስማን ምስጋና የሚያሰጥ ነው።   

በሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ የጀርመኑ ባየር ሙይንሽን ከእንግሊዙ ቸልሲ ጋር ነገ ማታ የሚያደርጉት ጨዋታ በብዙዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ነው። በተመሳሳይ ሰአት የስፔኑ ባርሴሎና ከጣሊያኑ ናፖሊ ጋር የሚያደርገው ጨዋታም ሌላኛው አጓጊ ፍልሚያ ነው። ከነገ በስትያ ደግሞ የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ የስፔኑ ሪያል ማድሪድን እንዲሁም ምሽት በተመሳሳይ ሰአት የጣሊያኑ ጁቬንቱስ የፈረንሳዩ ሊዮንን ይገጥማሉ።

የከባድ ሚዛን ቡጢ

ዲኦንታይ ዊልደርን ድል አድርጎ ቀበቶውን የተረከበው የከባድ ሚዛን ቡጢኛ ታይሰን ፉሪ
ዲኦንታይ ዊልደርን ድል አድርጎ ቀበቶውን የተረከበው የከባድ ሚዛን ቡጢኛ ታይሰን ፉሪምስል Reuters/S. Marcus

የብሪታንያ የከባድ ሚዛን ቡጢ ተፋላሚ ታይሰን ፉሪ ለድል በበቃበት ዕለት ከዴኦንታይ ዊልደርን ጋር ዳግም መፋለም እንደሚሻ ዐሳውቋል። ያ የማይሳካ ከኾነም ከሌላኛው የዓለማችን የከባድ ሚዛን ቡጢ ባለድል አንቶኒ ጆሹዋ ጋር መጋጠም ይፈልጋል። ቅዳሜ ዕለት ላስ ቬጋስ ውስጥ በተደረገው ፍልሚያ ድል በመቀዳጀት የዓለም የከባድ ሚዛን ቡጢ ቀበቶን ከዴኦንቴይ ከተረከበ በኋላ ድጋሚ ሊገጥመው መፈለጉን ይፋ አድርጓል። «ዴኦንቴይ ካልፈለገ ግን ወደ አጆ እንሂድ» ብሏል። የ30 ዓመቱ አንቶኒ ጆሹዋን በስሙ የመጀመሪያ ፊደላት በመጥቀስ።

አንቶኒ ጆሹዋ በዚሁ የዓለም ከባድ ሚዛን ቡጢ ዘርፍ የሚመደቡትን ሌሎች ቀበቶዎች በመላ አጠቃሎ የያዘ ብርቱ ተፋላሚ ነው። ምናልባትም በዕድሜ ተመጣጣኝ ለኾነው ለ31 ዓመቱ ታይሰን ፉሪ ግን የሀገሩ ልጅ አንቶኒ ጆሹዋ መከራ ሊያመጣበት ይችል ይኾናል። ታይሰን ፉሪ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2016 ሐምሌ ወር ውስጥ ከቭላድሚር ክሊችኮ ጋር ሊያደርግ የነበረውን የቡጢ ፍልሚያ በደረሰበት የአጥንት ጉዳት የተነሳ ሰርዞ ነበር። አራት ወራት ቆየት ብሎ ደግሞ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ተጠቅመሃል በሚል የብሪታንያ ጸረ-ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ኩባንያ ለኹለት ዓመታት አግዶት ቆይቷል። ያኔም በወቅቱ ያዓለማችን የከባድ ሚዛን ቡጢ ንጉሥ ከነበረው ክሊችኮ ጋር የነበረው ፍልሚያ ተሰርዟል።

በዘመኑ ብዙም አይደፈሬ የነበረውን ቭላድሚር ክሊችኮን ጉድ ያደረገው አንቶኒ ጆሹዋን ነው ታይሰን ፉሪ አኹን ና እንጋጠም ሲል የፎከረበት። በእርግጥ ታይሰን ፉሪም ለ19ኛ ጊዜ ቀበቶውን ለማስጠበቅ የገጠመው ቭላድሚር ክሊችኮን የዛሬ ዓምስት ዓመት ማሸነፍ የቻለ ነው። ከ5 ዓመት በኋላ ደግሞ አኹን ያሸነፈው ዴኦንቴይ ዊልደርም ለ11ኛ ጊዜ ቀበቶውን ለማስጠበቅ ነበ ርየተፋለመው። የመጀመሪያ ሽንፈቱ ኾኖ ተመዘገበበት እንጂ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ