1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ የካቲት 19 ቀን፣ 2010 ዓ.ም.

ሰኞ፣ የካቲት 19 2010

በቶኪዮ ማራቶን ኢትዮጵያ እና ኬንያ የአንደኛነቱን ደረጃ ቢቆናጠጡም፤ በጃፓን አንድ ሚሊዮን የን ገንዘብ የተንበሸበሸው ግን በወንዶች ውድድር ሁለተኛ የወጣው ጃፓናዊ አትሌት ነው። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፤ ቡንደስ ሊጋ፤ ላሊጋ እና ትናንት የተጠናቀቀው የክረምት ኦሎምፒክ ጭዋታን እንቃኛለን፡፡

https://p.dw.com/p/2tLH0
Südkorea Pyeongchang- Abschlussfeier der Olympischen Spiele
ምስል Reuters/P. Kopczynski

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ማንቸስተር ዩናይትድ በሮሜሉ ሉካኩ ተሳክቶለታል። ቸልሲ በቀጣዩ የሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ እንደሚያሰጋው አሰልጣኙ ተናግረዋል።  ኃያሉ ባየር ሙይንሽን በብኝነት መገስገሱን ተያይዞታል። ዶርትሙንድ በ20 ነጥብ ርቀት እያዘገመ ይከተለዋል። ሪያል ማድሪ  ነገ ከኢስፓኞላ ጋር ይጫወታል።  በደቡብ ኮሪያው የፒዮንግ ቻንግ የክረምት ኦሎምፒክ ፍጻሜ ዩናይትድ ስቴትስ በ20 ዓመት ታሪክ በሜዳሊያ ብዛት ዝቅተኛ ነጥብ አስመዝግባለች። ኖርዌይ  በሕዝብ ብዛት ከዐሥር እጥፍ በላይ የምትበልጣት ጀርመንን አስከትላ በአንደኛነት አጠናቃለች።

አትሌቲክስ

በቶኪዮ ማራቶን ኢትዮጵያ እና ኬንያ የአንደኛነቱን ደረጃ ቢቆናጠጡም፤ በጃፓን አንድ ሚሊዮን የን ገንዘብ የተንበሸበሸው ግን በወንዶች ውድድር ሁለተኛ የወጣው ጃፓናዊ አትሌት ነው። በቶኪዮው ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ብርሐኔ በሴቶች ውድድር አንደኛ ወጥታለች።  በወንዶች ኬንያ ቀንቷታል፤ የአንደኛነቱን ደረጃ ያገኘው ዲክሰን ቹምባ ነው። ብርሐኔ በአንደኛነት ያጠናቀቀችው 2 ሰአት ከ19 ደቂቃ ከ51 ሰከንድ በመሮጥ ነው።

Symbolbild Selbstläufer
ምስል Colourbox

ኬኒያዊው ዲክሰን 2 ሰአት ከ5 ደቂቃ ከ30 ሰከንድ ሮጦ በመግባት አንደኛ ወጥቷል። እሱን ተከትሎ ጃፓናዊው አትሌት ዩታ ሺታራ 2 ሰአት ከ6 ደቂቃ  ከ11 ሰከንድ በመሮጥ ጃፓን ውስጥ ለ16 ዓመት ተይዞ የቆየውን ክብር ወሰን ሠብሯል። አትሌት ዩታ አንድ ሚሊዮን የን ማለትም  936,000 ዶላር የተሸለመው በጃፓናውያን የተያዘውን  የሀገር ውስጥ ክብር ወሰኑን በአምስት ሰከንድ ልዩነት በመስበሩ ነው። እስከ ዛሬ በጃፓናውያን ተይዞ የቆየው ክብር ወሰን  እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2002 በቶሺናሪ ታካኦካ የተያዘው የ2 ሰአት ከ6 ደቂቃ ከ16 ሰከንድ ጊዜ ነው። የ26 ዓመቱ ጃፓናዊ የተሸለመው ገንዘብ በሩጫ ውድድር ታሪክ ከፍተኛ ከሚባሉት ውስጥ የሚመደብ ነው።

ፕሬሚየር ሊግ 

80 ሚሊዮን ዩሮ ከስክሶበታል፤ ባለፈው የበጋ ወር ከኤቨርተን ሲያስመጣው፡፡ ማንቸስተር ዩናይትድ ሮሜሉ ሉካኩን ወደ ኦልትራፎርድ ለማስመጣት ያን ሁሉ ዩሮ ሲያፈስ የቤልጂጉ አጥቂ በፕሬሚየር ሊጉ እቁንጮው ላይ ያደርስኛል በሚል ተስፋ ነበር። ሮሜሉ ሉካኩ ማንቸስተር ዩናይትድ ከማንቸስተር ሲቲ፣ ከሊቨርፑል አሊያም ከሌሎች ቡድኖች ጋር ባደረገው ግጥሚያ በአጠቃላይ 900 ደቂቃዎች ተስልፎ ተጫውቷል፡፡ ኾኖም 17 ኳሶችን ወደ መረብ ዓልሞ ቢሰድም እስከ  ትናንት ድረስ አንዱንም ሳያስቆጥር ቆይቷል፡፡ በዚህም የተነሳ በተለይ ባለፈው ሳምንት በቀድሞው የፕሬሚየር ሊግ ዕውቅ ተጨዋች ጋሪ ኔቨል ሳይቀር ብርቱ ትችት ደርሶበት ነበር፡፡ ትናንት ግን ቤልጂጋዊው ተሳክቶለታል፡፡ 

Champions League Manchester United v FC Base Lukaku
ምስል picture-alliance/empics/N. French

ማንቸስተር ዩናይትድ ቸልሲን 2ለ1 በማሸነፍ በደረጃ ስንጠረዡ ሁለተኛነትን እንዲቆናጠጥ ሮሜሉ ሉካኩ ቀዳሚ አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡ ምንም እንኳን ትናንት ቸልሲ በ32ኛው ደቂቃ ላይ በዊሊያን ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ መምራት ቢችልም ከ7 ደቂቃ በላይ እንዳይዘልቅ ያሰናከለው ይኸው ቤልጂጋዊው አጥቂ ነው፡፡ 39ኛው ደቂቃ ላይ ሮሜሉ ሉካኩ ማንቸስተርን አቻ የምታደርገውን ግብ ከመረብ በማሳረፍ የመጀመሪያው አጋማሽ አንድ እኩል ተጠናቀቀ፡፡ ከረፍት መልስ 75ኛው ደቂቃ ላይ ጄሲ ሊንጋርድ በጭንቅላት ገጭቶ ያስቆጠራትንም ግብ በድንቅ ኹናቴ አሻምቶ ያመቻቸው ይኸው የ24 ዓመት ወጣት አጥቂ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሮሜሉ ሉካኩ ባለፈው የውድድር ዘመን በ39 ጨዋታዎች 21 ኳሶችን ከመረብ ማሳረፍ የቻለ አጠቂ ሲኾን፤ 12ቱ ግቦች በፕሬሚየር ሊጉ የተቆጠሩ ነበሩ፡፡

አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ቸልሲ በኦልትርፎርድ ስታዲየም የማሸነፍ ዕድሉ ከእጁ ማፈትለኩ እንዳበሳጫቸው ተናግረዋል፡፡ ከእንግዲህም ቡድናቸው ለሻምፒዮንስ ሊግ የማለፍ ዕድሉ አስቸጋሪ እንደሚሆን አልሸሸጉም፡፡ በአንፃሩ ድል የቀናቸው የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ ቡድናቸው የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ አይሎ የነበረውን ተግጣሚ በማሸነፉ ለተጨዋቾቻቸው አድናቆታቸውን ቸረዋል፡፡

ለመጀመሪያ ከተገናኙበት ጊዜ አንስቶ በባላንጣነት የሚተያዩት ሁለቱ አሰልጣኞች በትናንቱ ጨዋታ ሲጨባበጡ ታይተዋል፡፡ መጨብበጡንም «ለሁሉም ማሳየት የምንፈልገው» ነው ብለዋል ሞሪንሆ፡፡ ኮንቴ በበኩላቸው «መጨባበጡን ማይት ትፈልጉ ነበር፤ አደረግነው፡፡ «አሁን አቁሙ» ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

Premier League - Swansea City vs Arsenal
ምስል Reuters/A. Couldridge

ትናንት በሌላ ጨዋት ቶትንሀም ክሪስታል ፓላስን 1 ለ0 አሸንፏል። ቅዳሜ በተደረጉ ሰባት ጨዋታዎች ብራይቶን እና ሊቨርፑል ተጋጣሚዎቻቸውን በተመሳሳይ 4 ለ1 አንኮታኩተዋል፡፡ ብራይቶን በሰፋ ልዩነት ድል ያደረገው ስዋንሲ ሲቲን ሲሆን፤ ሊቨርፑል የጎል ጎተራ ያደረገው ዌስትሀም ዩናይትድን ነው፡፡

አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ የፊታችን ሐሙስ የሚያደርጉት ተስተካክካይ ጨዋታ በብዙዎች ዘንድ በጉጉት ይጥበቃል፡፡ ማንቸስተር ሲቲ እስካሁን 72  ነጥቦችን ሰብስቦ በደረጃ ስንጠረዡ ግስጋሴውን እንደቀጠለ ነው፡፡ ማንቸስተር ዩናይትድ በ59 ነጥብ በሁለተኛነት ይከተላል፡፡ ሊቨርፑል በ57፤ ቶትንሀም በ55 ነጥብ የሦሰተኛ እና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ ቸልሲ በ53 ነጥቡ አምስተኛ ነው፡፡ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው አርሰናል በመሪው ማንቸስተር ሲቲ በ27 ነጥብ ርቀት ተበልጦ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

አርሰናል በአውሮጳ ሊግ የጣሊያኑ ኤስ ሚላንን ሐሙስ ዕለት ይገጥማል። በዕለቱ የስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ከሩስያው ሎኮሞቲቭ ሞስኮው፤ ሌላኛው የስፔን ቡድን አትሌቲኮ ቢልባዎ  ከፈረንሣዩ ማርሴይ ጋር ተቀጣጥረዋል። ሊዮን ከሲኤስካ ሞስኮው፣ ላትሲዮ ከዲናሞ ኪዬቭ እንዲሁም የፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዛቦን ከቼክ ሪፐብሊኩ ቪክቶሪያ ፒልዘን ጋር ይጋጠማሉ።  የጀርመኖቹ ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ላይፕሲሽም ከተጋጣሚዎቻቸው ጋር ይፋለማሉ። ሐሙስ ዕለት ዶርትሙንድ  የኦስትሪያውን ሬድ ቡል ሣልዝቡርግን ሲገጥም፤ ላይፕሲሽ  የሚጫወተው ከሩስያው ዜኒት ጋር ነው።

Spanien Fußball FC Barcelona gegen Deportivo Alaves 1:2
ምስል picture alliance/Cordon Press/E. Ivanova

ላሊጋ

በላሊጋው አተሌቲኮ ማድሪድ ትናንት ሴቪላን 5 ለ2 ድል በማድረግ መሪው ባርሴሎናን በ7 ነጥብ ርቀት ይከተላል፡፡ 65 ነጥብ ይዞ በቀዳሚነት የሚገሰግሰው ባርሴሎና በበኩሉ ቅዳሜ ዕለት ጂሮናን 6 ለ1 አንኮታኩቷል፡፡ ለባርሴሎና ሉዊስ ሱዋሬዝ ጨዋታው በተጀመረ ከ5ኛው ደቂቃ አንስቶ በማግባት ሔትሪክ ሠርቷል። ሌላኛው የባርሴሎና የግብ ቀበናኛ ሊዮኔል ሜሲ ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፏል። በስድሳ ስድስተኛው ደቂቃ ላይ የተቆጠረችው አንዷ ግብ የፊሊፕ ኮቲንሆ ናት። ሊዮኔል ሜሲ እና ፊሊፕ ኮቲንሆ ተከላካዮችን አታለው ሰውነታቸውን በቅልጥፍና በማጠማዘዝ ያስቆጠሯቸው ግቦች ተጨዋቾቹ ብቃታቸው የታየበት ነበር።

በተመሳሳይ ቀን ሪያል ማድሪድ ዲፖርቲሾ አላቬስን 4 ለ0 አሽንፏል፡፡ ለሪያል ማድሪድ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የመጀመሪያዋን በ44ኛው ደቂቃ እንዲሁም በ61ኛው ደቂቃ ለራሱ ሁለተኛዋን ለቡድኑ ሦስተኛ የኾነችውን ግብ አስቆጥሯል። ሁለተኛዋን ግብ በዐርባ ስድስተኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው ጋሬት ቤል ነው።  በሰማንያ ዘጠነኛው ደቂቃ ላይ ማሳረጊያው ግብ የካሪም ቤንዜማ ነበር። ሪያል ማድሪድ በ51 ነጥቡ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

ዛሬ ማታ ሪያል ቤቲስ ከሌቫንቴስ ይጋጠማል፡፡ ነገ ምሽት ደግሞ ሪያል ማድሪድ በደረጃ ሠንጠረዡ ታች 15ኛ ከሚገኘው ኢስፓኞላ ጋር ይጫወታል። ከግማሽ በላይ የማሸነፍ ዕድሉ ለሪያል ማድሪድ ተሰጥቷል። ከሁለቱ ጨዋታ አንድ ሰአት ተኩል ዘግየት ብሎ ቅዳሜ ዕለት በመሪው ባርሴሎና ጉድ የኾነው ጂሮና ሴልታቪጎ ይጠብቀዋል።

ቡንደስ ሊጋ 

Fußball | Bundesliga 24. Spieltag | RB Leipzig gegen FC Köln
ምስል Getty Images/AFP/R. Michael

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ኮሎኝ ላይፕሲሽን 2 ለ1 ቢያሸንፍም ከነበረበት ግን ፈቅ አላለም፤ በ17 ነጥብ ተወስኖ የመጨረሻ 18ኛ ደረጃ ላይ ተዘርግቷል።  መሪው ባየር ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት ከሔርታ ቤርሊን ጋር ያለምንም ግብ ቢለያይም፤ በ60 ነጥብ እየገሰገሰ ነው። በሁለተኛነት የሚከተለው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዛሬ ማታ ከአውስቡርግ ጋር ይጋጠማል። ከሻልከ ጋር ተመሳሳይ 40 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ነው። ሻልከ ትናንት በቀይ ካርድ አንድ ተጨዋቹ ከሜዳ የተሰናበተበት ባየር ሌቨርኩሰንን 2 ለ0 አሸንፏል።

የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች

የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ትናንት በመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ተጠናቋል። ኮርያውያን በሀገራቸው ቋንቋ «ጋምሳሃሚንዳ» ሲሉ አመሥግነው በእንግድነት የመጣው የዓለም ማኅበረሰብን ተሰናብተዋል። ደቡብ ኮሪያ ፕዮንግቻንግ ውስጥ ለሁለት ሣምንት በተከናወነው 23ኛው የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ኖርዌይ  በሜዳሊያ ቀዳሚነቷን አስጠብቃለች።  ኖርዌይ በአንደኛነት ያጠናቀቀችው 39 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ነው። ኖርዌይ የሰበሰበችው ሜዳልያ 14 የወርቅ፣ 14 የብር እና 11 የነሐስ ነው።  ተመሳሳይ 14 የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው ጀርመን ትናንት በበረዶ የገና ጨዋታ (ice hockey) ያገኘችው ተደምሮ 10 የብር ሜዳሊያ መሰብሰብ ችላለች። ቀሪው 7 ሜዳሊያ የነሐስ ነው። ካናዳ በ29፤ ዩናይትድ ስቴትስ በ23 ሜዳሊያ የሦስተኛ እና የአራተኛ ደረጃን ሲያገኙ፤ ኔዘርላንድ አምስተኛ ኾናለች፤ የሜዳሊያ ብዛቷ 20 ነው።  

Südkorea Pyeongchang- Abschlussfeier der Olympischen Spiele
ምስል Reuters/P. Kopczynski

በዚህ የፒዮንግ ቻንጉ የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ተሳታፊ የነበረችው ሩስያ አትሌቶቿ በመዝጊያው ሥነ ሥርዓት የሩስያን ባንዲራ ሳይሆን ገለልተኛ ባንዲራ እንዲይዙ ተገደዋል። አትሌቶቹ የሀገራቸውን ባንዲራ በኦሎምፒኩ ማውለብለብ ያልተፈቀደላቸው ሩስያ መንግሥት ዕያወቀ መጠነ-ሰፊ የኃይል ሰጪ ንጥረ-ነገሮችን አትሌቶቿ ተጠቅመዋል በሚል በቀረበባት ክስ ነው። ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ትናንት የሩስያ እገዳ ሊነሳ እንደሚችል ጥቁምታ ሰጥቷል። ያ የሚሆነው ግን ሀገሪቱ በጸረ አበረታች ንጥረ-ነገር ዘመቻ አመርቂ ውጤት ካስመዘገበች ነው ብሏል። ትናንት የክረምት ኦሎምፒክ ሲጠናቀቅ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የዓለም ዋንጫ አዲስ አበባ መድረሱ ተዘግቧል። ዋንጫው አዲስ አበባ የገባው በዓለም ዙሪያ የሚያደርገው ጉዞ አካል በመሆኑ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ