ስፖርት፤ የካቲት 21 ቀን፣ 2008 ዓ.ም
ሰኞ፣ የካቲት 21 2008በእንግሊዝ ካፒታል ዋን የፍጻሜ ፍልሚያ ትናንት ማንቸስተር ሲቲ ሊቨርፑልን አሸንፎ ዋንጫውን ወስዷል። ለማንቸስተር ሲቲ ቀዳሚዋን ግብ ያስቆጠረው ፈርናንዲንሆ ነበር። ሠርጂዮ አጉዌሮ በ49ኛ ደቂቃ ላይ በስተቀኝ በኩል ያቀበለውን ኳስ ፈርናንዲንሆ አጥብቆ በመምታት በሊቨርፑሉ ግብ ጠባቂ ሲሞን ሚኝሌ እግር ስር አሾልኮ ከመረብ አሳርፏል። መደበኛ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሰባት ደቂቃዎች ሲቀሩት ማዕዘን ገጭታ የተመለሰችውን ኳስ ፊሊፕ ኮቲንሆ በማስቆጠሩ ጨዋታው በተጨማሪ ደቂቃ ቀጥሎ ነበር። ኾኖም ተጨማሪ ግብ ሊቆጠር ባለመቻሉ ጨዋታው ወደ ፍፁም ቅጣት ምት አምርቷል።
ለማንቸስተር ሲቲ የ34 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ግብ ጠባቂ ዊሊ ካባሌሮ ሦስት ኳሶችን በማዳን ብቃቱን አስመስክሯል። በእርግጥ ቀደም ሲል ማንቸስተር ሲቲ በኤፍ ኤ ካፕ አምስተኛ ዙር ውድድር በቸልሲ 5 ለ1 በተቀጣበት ግጥሚያ ይኸው ግብ ጠባቂ በከፍተኛ ደረጃ ተተችቶ ነበር። አሠልጣኝ ማኑዌል ፔሊግሪኒ ግን ያ ሁሉ ግብ ቢቆጠርበትም በካባሌሮ ላይ የነበራቸው መተማመን አልተሸረሸረም። እንደውም አሰልጣኙ የኤፍ ኤ ካፕ ውድድር ላይ በርካታ ታዳጊ ተጨዋቾች ማሰለፋቸው ዋናው ቡድናቸው በተደጋጋሚ ውድድሮች እንዳይዳከም የዘየዱት ስልት መኾኑን ጠቅሰዋል። ዋና ትኩረታቸውም በዚህ የሊግ ፍፃሜ እና ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር እንደነበር ተናግረዋል። በእርግጥም ያሰቡትን አሳክተዋል።
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት ማንቸስተር ዩናይትድ አርሰናልን 3 ለ2 ቶትንሐም ስዋንሲቲን 2 ለ1 አሸንፈዋል። ለማንቸስተር ዩናይትድ ተሰልፎ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው የ18 ዓመቱ ታዳጊ ወጣት ማርኩስ ራሽፎርድን ችሎታ አሠልጣኙ ሉዊ ቫን ጋል «ልዩ ክህሎት» ሲሉ አወድሰውታል። ማርኩስ ራሽፎርድ ቀደም ሲል በአውሮፓ ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታውም ሁለት ግቦችን ከመረብ በማሳረፈ ደጋፊዎቹን እጅግ ሲያስደስት በብዙዎች አስደናቂ ተጨዋች ተብለዋል።
ለትናንት ተይዞ የነበረው የሊቨርፑል እና የኤቨርተን እንዲሁም የኒውካስል እና የማንቸስተር ሲቲ ጨዋታ በሊጉ ፍጻሜ የተነሳ ተሸጋሽጓል። ከትናንት በስትያ ቸልሲ ሳውዝሐምፕተንን 2 ለ1 አሸንፏል። መሪው ላይስተር ሲቲ ኖርዊችን አንድ ለዜሮ በመሸኘት ነጥቡን 56 አድርሷል። ከቶትንሀም ጋር የነጥብ ልዩነቱ ሁለት ነው። አርሰናል በ51 ነጥብ ሦስተኛ ነው። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ሲቲ 47 ነጥብ ይዞ ማንቸስተር ዩናይትድን በ3 ነጥብ ይበልጠዋል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሊቨርፑል በ38 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ከነገ በስትያ ምሽት ይጋጠማሉ።
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ደግሞ ትናንት ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሆፈንሀይምን እንዲሁም ማይንትስ ሌቨርኩሰንን 3 ለ1 አሸንፈዋል። አውስቡርግ ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ሁለት እኩል አይንትራኅት ፍራንክፉርት ከሻልከ ያለምንም ግብ ተለያይተዋል።
ከትናንት በስትያ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ቶማስ ሙይለር እና ሮበርት ሌቫንዶብስኪ ባስቆጠሯቸው ግቦች ቮልፍስቡርግን ሁለት ለባዶ ረትቷል።
«የዛሬውን ጨዋታ ተቆጣጥረን የመጀመሪያውን ግብ ለማስቆጥር ትንሽ መታገስ ነበረብን። ጥሩ ተጫውተንም ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ሦስት ነጥቦችን ይዘናል»
17 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው ሐኖቨር ሽቱትጋርትን 2 ለ1 ድል በማድረግ ከሆፈንሀይም ጋር ያለውን ነጥብ ወደ አንድ ዝቅ አድርጎታል። ቬርደር ብሬመን ከዳርምሽታድት ሁለት እኩል እንዲሁም ሐምቡርግ ከኢንግሎሽታድት አንድ እኩል በማጠናቀቅ ነጥብ ተጋርተዋል።
በስፔን ላሊጋ 66 ነጥብ ይዞ የሚገሰግሰው ባርሴሎና ትናንት ሴቪላን 2 ለ1 ድል አድርጓል። ሊዮኔል ሜሲ ያስቆጠራት የቅጣት ምት ግብ ባርሴሎናን ከመመራት ወደ ማሸነፍ አሻግራለች። 58 ነጥብ ይዞ የሚከተለው አትሌቲኮ ማድሪድ በአራት ነጥብ ዝቅ ብሎ ከስሩ የሚገኘው ሪያል ማድሪድን ቅዳሜ ዕለት ገጥሞ አንድ ለባዶ ማሸነፍ ችሏል። የሪያል ማድሪዱ አጥቂ ካሪም ቤንዜማ በእግር ጡንቻ ጉዳት የተነሳ ለአንድ ወር ያኽል እንደማይሰለፍ ተገልጧል። ቀጣዮቹን የስፔን ሊግ ግጥሚያዎች እና ለሻምፒዮንስ ሊግ በሚቀጥለው ሳምንት ከሮማ ጋር ለሚኖረው የመልስ ጨዋታ አይደርስም ተብሏል። ሪያል ማድሪድ ሮማን በመጀመሪያው ዙር 2 ለዜሮ አሸንፏል።
በቶኪዮ ማራቶን ኢትዮጵያዊው አትሌት ፈይሳ ሊሌሳ2 ሰአት ከ6 ደቂቃ ከ56 ሰከንድ ሮጦ በመግባት አንደኛ ወጥቷል። እስከ ሰባተኛ ደረጃ ድረስ ኬንያውያን ተከታትለው ገብተዋል።በሴቶች የዓለም ማራቶን ኬንያዊቷ ሔላህ ኪፕሮፕ ኢትዮጵያዊቷ አማኔ ጎበናን በ24 ሰከንድ ቀድማ አሸናፊ ኾናለች። ሔላህ የገባችበት ሰአትም 2:21:27 ነው። ሌላኛዋ ኬንያዊት ኤድና ኪፕላጋት ሦስተኛ ስትወጣ ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች አበሩ ከበደ፣ ብርሃኔ ዲባባ፣ ሹሬ ደምሴ እና አሸቴ ዲዶ እስከ 7ኛ ደረጃን ይዘዋል። የሀትሪክ ጋዜጣ ም/ዋና አዘጋጅ እንዲሁም በሬዲዮ እና በጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሠ የእሁዱን ውጤት በተመለከተ ምሥጢሩ ሴቶች አትሌቶች በጋራ በአንድ አሰልጣኝ በመለማመዳቸው ወንዶቹ በተናጠል ልምምድ በማድረጋቸው ነው ብሏል።
በቶኪዮ ጎዳና ለ10ኛ ጊዜ በተከናወነው የትናንቱ የዓለም ማራቶን ውድድር 36,000 ሯጮች ተሳታፊ ኾነዋል። ይኽ በእንዲህ እንዳለ የዓለም አቀፉ የጸረ- አበረታች መድሐኒት ድርጅትወደ ዘጠኝ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል።
የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማሕበራት ፌዴሬሽን በእንግሊዘኛ ምኅጻሩ FIFA አዲስ ፕሬዚዳንት ባሳለፍነው ሣምንት ዐርብ እለት መርጧል። በሙስና ቅሌት በታገዱት የቀድሞው የፊፋ ፕሬዚዳንት የ79 ዓመቱ ሴፕ ብላተር ምትክ የተመረጡት ጊያኒ ኢንፋንቲኖ ናቸው። የ45 ዓመቱ ጎልማሳ የፊፋ ፕሬዚዳንት ቀደም ሲል የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበር ዋና ጸሓፊ ኾነው አገልግለዋል።
ተፎካካሪያቸው የባሕሬኑ ሼክ ሣልማን ቢን ኤብራሒም አል ካሊፋን በድምጽ ብልጫ አሸንፈው የተመረጡት አዲሱ ፕሬዚዳንት ጊያኒ ኢንፋንቲኖ በፊፋ የ112 ዓመት ታሪክ ዘጠነኛው ፕሬዚዳንት ናቸው።
ፊፋ ከምርጫው በፊት ባካሄደው ጉባኤ መጠነ ሰፊ የውስጥ አሠራር ማሻሻያዎችን አጽድቋል። እነዚህ ማሻሻያዎችም በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆኑ ተገልጿል። አዲሱ የፊፋ ፕሬዚዳንት የመጀመሪያ ቀን ሥራቸውን ዛሬ የጀመሩት የፊፋ ዋና ጽ/ቤት በሚገኝበት ዙሪክ ስዊዘርላንድ ካሉ የሥራ ባልደረቦቻቸው እና እንግዶች ጋር የእግር ኳስ ግጥሚያ በማድረግ ነበር።
የቀድሞው የባየር ሙይንሽን ፕሬዚዳንት ኡሊ ሆኔስ የተበየነባቸውን የሦስት ዓመት ከመንፈቅ የእስር ጊዜያቸውን እኩሌታ አጠናቀው ዛሬ በገደብ ከእሥር መፈታታቸውን የባቫሪያ የፍትኅ ሚንስትር አስታወቀ ሲል ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዘግቧል። የቀድሞው የባየርን ሙይንሽን ተጨዋች የነበሩት ኡሊ ሆኔስ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2009 ዓመት የቡድኑ ፕሬዚዳንት ከመኾናቸው አስቀድሞ ለ30 ዓመታት በዳይሬክተርነት አገልግለዋል። በግብር መክፈል የነበረባቸውን 31.14 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ አሽሽተዋል በሚል ተከሰው ዘብጥያ የወረዱት በ2014 ነበር።
በ1974ቱ የዓለም ዋንጫ ለጀርመን ቡድን ተሰልፈው አሸናፊ የነበሩት ኡሊ ሆኔስ ከባየር ሙይንሽን ፕሬዚዳንትነት ተነስተው እስር ቤት የተላኩት ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በፊት ነበር። ከባለፈው ዓመት ጥር ወር አንስቶ ግን ቀን ቀን ከእስር ቤት እየወጡ ለባየር ሙይንሽን የወጣቶች ክፍል በመማገልገል ማታ ማታ ወደ እስር ቤታቸው ይመላለሱ ነበር። ወደ ባየር ሙይንሽን ዋናው ቡድን ኃላፊነት ይመለሱ እንደሆን የታወቀ ነገር የለም።በእርግጥ የሚታወቀው ነገር ኡሊ ሆኔስ ከፕሬዚዳንትነታቸው ተነስተውም ቢሆን ባየር ሙይንሽን ከግስጋሴው የሚገታው አልተገኘም።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አርያም ተክሌ