1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ የካቲት 30 ቀን 2012 ዓ.ም

ሰኞ፣ የካቲት 30 2012

 በዚህ ሳምንት ኹለት የጀርመን የእግር ኳስ ቡድኖች የሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ያደርጋሉ። ባየር ሙይንሽን ለሚቀጥለው ሳምንት ቀጠሮ ይዟል። በቡንደስሊጋው መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። በኮሮና ተሐዋሲ የተነሳ በርካታ ሰዎች የሚታደሙባቸው የስፖርት ክንዋኔዎች እየተሰረዙ ነው። አንዳንዶቹም ለሌላ ጊዜያት ተሸጋግረዋል።

https://p.dw.com/p/3Z6kQ
UEFA Champions League | Real Madrid - Manchester City
ምስል Reuters/J. Medina

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የቶኪዮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ ችቦ ትናንት መቀሌ ከተማ ውስጥ በተከናወነ ስነስርዓት ከትግራይ ለጋምቤላ ክልል ተላልፏል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ኹለቱ ማንቸስተር ዩናይትዶች ድንቅ ጨዋታ አከናውነዋል። በኮሮና ተሐዋሲ የተነሳ በርካታ ሰዎች የሚታደሙባቸው የስፖርት ክንዋኔዎች እየተሰረዙ ነው። አንዳንዶቹም ለሌላ ጊዜያት ተሸጋግረዋል።

ሻምፒዮንስ ሊግ 

ወደ ሩብ ፍፃሜ ለማለፍ 16 በድኖች በሚያደርጉት ፍልሚያ፦ ሦስት የጀርመን ቡድኖች ግጥሚያቸውን ያከናውናሉ። ቸልሲን 3 ለ0 ድል ያደረገው ባየር ሙይንሽን ከሳምንት በኋላ የመልስ ጨዋታውን በሜዳው ያከናውናል። ከሦስቱ የጀርመን ቡድኖች  የመልስ ጨዋታውን በቅድሚያ የሚያደርገው ላይፕሲሽ ነው።

በነገው ዕለት ማታ በሚኖረው ግጥሚያ ቀዳሚ ድሉን ለማስጠበቅ የሚፋለመው ላይፕሲሽ ቶትንሀምን በሜዳው 1 ለ0 አሸንፎ ባገኘው ሰፊ ዕድል ተማምኖ ነው ወደ ሜዳ የሚገባው። በተመሳሳይ ሰአት ነገ አታላንታ እና ቫለንሺያም ለሻምፒዮንስ ሊግ ይጋጠማሉ።  ቶትንሃም ያለፈው ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ተፋላሚ የነበረ ብርቱ ተፎካካሪ ነው። ፍፃሜው በሊቨርፑል ሞሀመድ ሳላህ እና ጂቮክ ኦሪጂ 2 ግቦች ባያምርም።

Bundesliga Fanprotest   FC Bayern München - FC Augsburg
ምስል Imago Images/MIS

ረቡዕ ዕለት ደግሞ ዶርትሙንድ ፓሪስ ሴንጄርሜንን ይገጥማል። ቀደም ሲል በሜዳው ዶርትሙንድ 2 ለ1 ነው ያሸነፈው። ሊቨርፑል ከአትሌቲኮ ማድሪድ በተመሳሳይ ምሽት ይጋጠማሉ።

በሳምንቱ ባየር ሙይሽን ከቸልሲ ጋር ይፉለማል። ቦርስያ ዶርትሙንድ አጠቃላይ የአቋም ግምገማ ግጥሚያ ቅዳሜ ማታ ከRacing Strasbourg ነብረው፤ ኾኖም በኮሮና ተሐዋሲ ፍራቻ ጨዋታው ተሰርዞታል። ፓሪስ ውስጥ የሊግ 1 ግጥሚያም ተሰርዟል። የፈረንሳይ መከላከያ እና የሚንስትሮች ምክር ቤት ከ5000 በላይ ሰዎች የሚሰበሰቡበት ማናቸውም ዝግጅቶች እንዳይካሄዱ ወስኗል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ተደጋጋሚ ድል የተቀዳጀው ባየር ሙይንሽን መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። 55 ነጥብ አለው።  በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ ግጥሚያዎች ድል የቀናው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ደግሞ ከላይፕሲሽ የኹለተኛ ደረጃውን ተረክቧል። ትናንት አውስቡርግን 2 ለ0 ላሸነፈው ባየር ሙይንሽን ቀዳሚዋን ግብ ያስቆጠረው አጥቂ ቶማስ ሙይለር ቡድኑ በማሸነፉ ደስተኛ ቢኾንም ቅር ያለው ነገር እንዳለም ገልጧል።

«ወሳኙ ነገር ዛሬ አሸንፈናል። አኹን ለኹለት ቀናት ረፍት ወስደን ረቡዕ ጠንከር ብለን ለመግባት ከድካማችን ለማገገም እንሞክራለን። በሚቀጥሉት ሦስት ጨዋታዎች በደንብ ለመሰናዳት እንችላለን። አኹን ነገሮችን ወደኋላ ብንመለከት፦ በፍጥነት የኾነው ከአራት ጨዋታ ወደ ኋላ መጎተት አራት ወደላይ መሳባችን ነው። ሁሉንም ነው ማለት ይቻላል ያሸነፍነው። ማለት አካሄዳችን ፍጹም ጥሩ ነው። ግን ዛሬ ፍጹም ደስተኛ ነን ማለት አይደለም።»

Fußball Bundesliga FC Bayern München - FC Augsburg
ምስል Reuters/M. Dalder

ለባየር ሙይንሽን ማሸነፊያዋን ግብ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው አንድ ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ጎሬትስካ ነው። ማይንትስ ከዱይስልዶርፍ ጋር ትናንት አንድ እኩል ተለያይቷል። ቅዳሜ ዕለት በተከናወኑ ስድስት ጨዋታዎች፦ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 2 ለ1 አሸንፎ ባገኘው 51 ነጥቡ ኹለተኛ ደረጃን ይዟል። ከቮልፍስቡርግ ጋር ያለምንም ግብ የተለያየው ላይፕሲሽ በቦሩስያ ዶርትሙንድ በአንድ ነጥብ ይበለጣል። ሔርታ ቤርሊን ከብሬመን ጋር 2 ለ2፤ ሻልከ ከሆፈንሀይም አንድ እኩል  ተለያይተዋል። ፍራይቡርግ ዩኒየን ቤርሊንን 3 ለ1 ሲያሸንፍ፤  ባየር ሌቨርኩሰን አይንትራኅት ፍራንክፉርትን በሰፋ የግብ ልዩነት 4 ለ0 አደባይቷል።  ዐርብ ዕለት የደረጃ ሰንዘረዡ መጨረሻ ላይ የተዘረጋው ፓዴርቦርንን 2 ለ1 ማሸነፍ የቻለው ኮሎኝ 32 ነጥብ ይዞ 10ኛ ደረጃውን ከዑኒየን ቤርሊን ተረክቧል።

ላይፕሲሽ የግብ ማግባት ችግር ገጥሞታል በቡንደስሊጋው። ቲሞ ቬርነር በቅዳሜው የቮልፍስቡርግ ግጥሚያ ግብ አላስቆጠረም። ቀደም ሲል ከሌቨርኩሰን ጋር በነበረው ግጥሚያ አቻ የምታደርገውን ግብ ከመረብ ያሳረፈው ቲሞ ሳይኾን የቼክ ሪፐብሊኩ አጥቂ ፖትሪክ ሺክ ነው። 

ላይፕሲሽ ሻልከን 5 ለ0 ባንኮታኮተበት በ23ኛው ዙር የቡንደስሊጋ ግጥሚያም ቲሞ አንድ ግብ ነው ያስቆጠረው። ከዚያ በፊት በነበሩትም አራት ግድም ግጥሚያዎች ቲሞ ቬርነር ግብ አላስቆጠረም። 

Tottenham Hotspur - RB Leipzig - Jose Mourinho und Julian Nagelsmann
ምስል picture-alliance/dpa/R. Michael

አሰልጣኝ ጁሊያን ናግልስማን በቡንደስሊጋው ለመጀመሪይ ጊዜ ቲሞ ቬርነርን ተቀያሪ ወንበር ላይ አስቀምጠዋል። የሻምፒዮንስ ሊጉን ቀጣይ ግጥሚያ አስበው ወይንም ፖትሪክ ሺክ ስለመጣ ቲሞ ፉታ እንዲያገኝ አቅደውም ይኾናል።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ ዛሬ ማታ ላይስተር ሲቲ ከአስቶን ቪላ ጋር ይጋጠማሉ። ከነገ ወዲያ ደግሞ በደረጃ ሰንጠረዡ 57 ነጥብ ይዞ ኹለተኛ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ ተስተካካይ ጨዋታውን ከአርሰናል ጋር ያከናውናል።  በ82 ነጥብ በመሪነቱ እየገሰገሰ ከሚገኘው ሊቨርፑል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማንቸስተር ሲቲ ለማጥበብ የነበረውን ዕድል አምክኗል። ማንቸስተር ዩናይትድ 2 ለ0 ድል ያደረገበት የትናንቱ ግጥሚያ ውብ ነበር። በተለይ መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመረው 6ኛ ደቂቃ ላይ በማንቸስተር ሲቲ ግብ ጠባቂ ስህተት ማክ ቶሚናይ ከርቀት ጠልዞ ከመረብ ያሳረፋት ኹለተኛ ግብ ኦልድትራፎርድን በአንድ እግሩ ያቆመች ነበረች። የመጀመሪያዋን ግብ በ30ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ማርሺያል ነው። በአጠቃላይ የጨዋታ ይዞታ  72 ከመቶ ይዞ የነበረው ማንቸስተር ሲቲ ግብ ማስቆጠር ተስኖት በመሸነፉ ከሊቨርፑል ጋር የነበረውን ነጥብ እንዲሰፋ አድርጓል።

Schweiz Lausanne Olympische Ringe
ምስል picture-alliance/KEYSTONE/J.-C. Bott

አትሌቲክስ

የቶኪዮ ኦሎምፒክ ችቦ በትናንትናው ዕለት መቀሌ ከተማ ውስጥ በተደረገ ስነስርዓት ከትግራይ ክልል ለጋምቤላ ክልል ተሰጥቷል። በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የምትዘዋወረው ይኽች የቶክዮ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ ችቦ በትግራይ ተለኩሳ ወደ ጋምቤላ ተላልፋለች፡፡ በኦሎምፒክ ችቦ ማብራቱ ስነ ስርዓት ላይ በ2020 ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን በቶክዮ ኦሎምፒክ ከሚወክሉት አትሌቶች በተጨማሪ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች ታድመዋል፡፡ በስነ ስርዓቱ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ ኢትዮጵያን በኦሎምፒክ በሴቶች ብስክሌት ውድድር ለምትወክለው ሰላም አምሃ የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቷል፡፡

አትሌት መሰረት ደፋር የዚህ ዓመት የ(AIMs Inspirational women award) ተሸላሚ ሆና የተመረጠች ሲሆን በመጋቢት 4 ቀን በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል በሚደረገው 2012 ቮዳኮም ቅድሚያ ለሴቶች ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሽልማቷን የምትወስድ መኾኑን የታላቋ ሩጫ በኢትዮጵያ በላከው የኢሜል መልእክት ገልጧል።   

Fußball Bundesliga Bayern München - FC Augsburg
ምስል picture-alliance/dpa/S. Hoppe

በኮሮና ተሐዋሲ መዛመት የተነሳ በተለይ በአውሮጳ ሃገራት በርካታ የስፖርት ዝግጅቶች መርሐ ግብሮች እየታጠፉ ነው። በፖላንድ ከ20 ቀናት በኋላ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የዓለም ግማሽ ማራቶን  ወደ ሚቀጥለው ዓመት  ጥቅምት ወር ተዛውሯል። ከግዲኒያ ከንቲባ ጋር ተነጋግሮ በመስማማት ውድድሩ መዛወሩ እንዳሳዘነው የቀድሞው ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር  ማለትም የዓለም አትሌቲክስ ድርጅት በድረ-ገጹ ይፋ አድርጓል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ