1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ የካቲት 4 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

ሰኞ፣ የካቲት 4 2011

በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በወላይታ ድቻ ተሸንፏል። የማንቸስተር ሲቲው ሠርጂዮ አጉዌሮ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በተከታታይ ሄትሪክ በመሥራት ክብርወሰን ሊሰብር ተቃርቧል። ክብርወሰኑ በቀድሞው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን እና የኒውካስትል አጥቂ አላን ሺረር በብቸኝነት ነበር ተይዞ የቆየው።

https://p.dw.com/p/3DAL2
Champions League - Gruppe F - Manchester City v TSG 1899 Hoffenheim
ምስል Reuters/A. Yates

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በወላይታ ድቻ ተሸንፏል። የማንቸስተር ሲቲው ሠርጂዮ አጉዌሮ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በተከታታይ ሄትሪክ በመሥራት ክብርወሰን ሊሰብር ተቃርቧል። ክብርወሰኑ በቀድሞው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን እና የኒውካስትል አጥቂ አላን ሺረር በብቸኝነት ነበር ተይዞ የቆየው። በማንቸስተር ሲቲ ብርቱ ቅጣት የተፈጸመበት ቸልሲ አሰልጣኝ እና አምበል ደጋፊዎቻቸውን ይቅርታ ጠይቀዋል። በቡንደስሊጋው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ነጥብ መጣሉ ባየር ሙይንሽን የነጥብ ልዩነቱን ማጥበብ አስችሎታል። በጣሊያን ሴሪ ኣ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ  ለጁቬንቱስ 20ኛ ግቡን አስቆጥሯል።

በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ዐሥራ አምስተኛ ዙር ውድድር ወደ ወላይታ ሶዶ አቅንቶ የነበረው መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በወላይታ ድቻ 2 ለ0 ተሸንፏል። ከ9 ተከታታይ ጨዋታ በኋላ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስን ማሸነፍ የቻለው ወላይታ ድቻ በደረጃ ሰንጠረዡ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ለትናንቱ ጨዋታ ድል የወላይታ ዲቻ ደጋፊዎች አስተዋጽዖም ከፍተኛ ነበር።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የነጥብ ልዩነታቸው የጠበበው ማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል በደረጃ ሰንጠረዡ አንደኛነትን እየተቀያየሩ ነው። ባለፈው ሳምንት አንደኛ ደረጃውን ይዞ የነበረው ማንቸስተር ሲቲ ተስተካካይ ጨዋታውን ባደረገው ሊቨርፑል መሪነቱን ተነጥቆ ነበር። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ማንቸስተር ሲቲ ዳግም መሪነቱን ተረክቧል። በእርግጥ ሊቨርፑል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ቢቀረውም ማለት ነው።

በትናንትናው ጨዋታ በማንቸስተር ሲቲ 6 ለ0 የተንኮታኮተው ቸልሲ አሰልጣኝ እና አምበል ለውድቀታቸው ደጋፊዎችን ይቅርታ ጠይቀዋል። አሰልጣኝ ማውሪትሲዮ ሣሪ እና አምበሉ ሴዛር አዝፒሊኩዌታ ከ28 ዓመታት ወዲህ ከባዱ ሽንፈት ለገጠመው ቡድናቸው ደጋፊዎች ይቅርታ ብለዋል። ቸልሲን ለሦስት ዓመት ለማሰልጠን ከመጡ ስምንት ወር የኾናቸው ጣሊያናዊው አሰልጣኝ በትናንቱ አሳፋሪ ሽንፈት ከስታምፎርድ ብሪጅ መባረር ያሰጋቸው እንደኾን ተጠይቀዋል። «ያን አላውቅም፤ እሱን ክለቡን መጠየቅ ነው» ብለዋል። ትናንት ጨዋታው በተጀመረ በ25 ደቂቃዎች ብቻ ቸልሲ አራት ግቦችን ማስተናገዱ አሰልጣኙን ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል።

አርጀንቲናዊው የማንቸስተር ሲቲ አጥቂ ሠርጂዮ አጉዌሮ
አርጀንቲናዊው የማንቸስተር ሲቲ አጥቂ ሠርጂዮ አጉዌሮ ምስል picture-alliance/Offside/S. Stacpoole

በእርግጥ አሰልጣኝ ማውሪትሲዮ ሣሪ በቸልሲ አሰልጣኝነት ዘመናቸው የመጀመሪያዎቹ ወራት አመርቂ ነበሩ ። እስካለፈው ኅዳር ወር ድረስ በሊጉ አምስት ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ በቡድኑ ተስፋ ዘርተው የነበሩት አሰልጣኝ ማውሪትሲዮ ሣሪ የትናንቱ የማንቸስተር ሲቲ 6 ለ0 ሽንፈት አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቷቸዋል።

ቸልሲ ትናንት የገጠመው ሽንፈት በፕሪሚየር ሊጉ ያለፉ አራት ግጥሚያዎች ሦስተኛው ነበር። ከዚህ ቀደም በአርሰናል 2 ለ0፤ ከታችኛው ዲቪዚዮን ካደገ ሦስት ዓመታት ብቻ ባስቆጠረው በርመስ ቡድን 4 ለ0 ከባድ ሽንፈት ገጥሞት ነበር። የትናንቱን ሽንፈት የከፋ ያደረገው በረዥም ጊዜያት ተፎካካሪው ማንቸስተር ሲቲ ስድስት ግቦች ሲቆጠሩበት ለማስተዛዘኛ እንኳን አንዲት ግብ ማግባት አለመቻሉ ነበር። ቸልሲ በትናንትናው ሽንፈት በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ ስድስተኛ ዝቅ ብሏል።

አርሰናል በተመሳሳይ 50 ነጥብ ኾኖም በግብ ክፍያ አምስተኛ ደረጃ ይዟል። ማንቸስተር ዩናይትድ ከቸልሲና አርሰናል በአንድ ነጥብ በልጦ ደረጃው አራተኛ ነው። ትናንት ላይስተር ሲቲ ላይ የ3 ለ1 ድል የቀናው ቶትንሀም 60 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ፊጥ ብሏል።

ትናንት በግብ የተንበሸበሸው ማንቸስተር ሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ከሚቀረው ሊቨርፑል እኩል ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ ልዩነት የደረጃ ሠንጠረዡ መሪ መኾን ችሏል። አርጀንቲናዊው አጥቂው ሠርጂዮ አጉዌሮም ከትናንቱ ስድስት ግቦች ሦስቱን በመቋደስ ሔትትሪክ ሠርቷል። ያም ብቻ አይደለም ላለፉት 14 ዓመታት በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በርካታ ሔትትሪኮችን በመሥራት ክብርወሰን  ይዞ የቆየው የኒውካስትሉ አጥቂ አለን ሺረር ላይ ደርሶበታል። የሠርጂዮ የትናንትና ሦስት ግቦች በፕሬሚየር ሊጉ ዐሥራ አንደኛ ሔትሪክ ተብለው ተመዝግበዋል። ገና በርካታ ጨዋታዎች ስለሚቀሩ ሠርጂዮ አጉዌሮ የአለን ሺረርን ክብር ወሰን የመስበር ሰፊ ዕድል አለው። እስካሁን ድረስ በፕሬሚየር ሊግ በርካታ ሄትሪኮችን በመሥራት  የቀድሞው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን እና የሊቨርፑል አጥቂ ሮቢ ፎውለር ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  በጨዋታ ዘመኑ ለ9 ጊዜ ሄትሪክ ሠርቷል። ቲዬሪ ኦንሪ፤ ሔሪ ኬን፤ ሚካኤል ኦውን እና ዋይኔ ሩኒ እያንዳንዳቸው ስምንት ሔትሪክ በመሥራት ይከተላሉ።

Der englische Stürmer Alan Shearer
የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን እና የኒውካስትል የቀድሞው አጥቂ አላን ሺረርምስል picture-alliance / dpa

ባለፈው ጨዋታ በርመስን 3 ለ0 ያሸነፈው ሊቨርፑል ተስተካካይ ጨዋታውን የሚያከናውነው በጊዜያዊ አሰልጣኙ መመራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ድንቅ መሻሻል ካሳየው ማንቸተር ዩናይትድ ጋር ነው።  ማንቸስተር ዩናይትድ ቅዳሜ ዕለት ፉልሀምን 3 ለ0  ሲያሸንፍ በኖርዌያዊው ጊዜያዊ አሰልጣኝ ኦሌ ጉነር ሶልካዬር አመራር በተከታታይ ካደረጋቸው 11 ግጥሚያዎች 10ኛ ድሉ ኾኖ ተመዝግቦለታል።  ባለፉት 11 ጨዋታዎች የተመዘገቡት ድሎች በነገው የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያም የሚደገም ከኾነ የ45 ዓመቱ ጎልማሳ ኖርዌያዊ አሰልጣኝ በማንቸስተር ዩናይትድ የቀድሞው አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪኞን ቦታ ሙሉ ለሙሉ የመረከብ ዕድላቸው ይሰፋል።

የቀድሞው የሪያል ማድሪድ እና የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪኞ ለማንቸስተር ዩናይትድ ውድቀት ተጠያቂ በመኾን ከቡድኑ ከተሰናበቱ ወዲህ አዲስ ሥራ አግኝተዋል። በሩስያ መንግሥት በጀት በሚተዳደረው ሩሲያ ዛሬ (RT) ለተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ የስፖርት ተንታኝ ባለሞያ ኾነው እንደሚያገለግሉ በማስታወቂያ ገልጠዋል።  

Italien - US Sassuolo v Juventus - Serie A - Sami Khedira
ምስል Getty Images/A. Sabattini

ሴሪኣ

ጁቬንቱስ በጣሊያን ሴሪኣ በመሪነቱ እየገሰገሰ ነው። አጥቂው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ለቡድኑ 20ኛ ግቡን ባስቆጠረበት በትናንትና ድሉ ጁቬንቱስ በደረጃ ሰንጠረዡ የነጥብ ልዩነቱን 11 አድርሶታል። 52 ነጥብ ያለው ናፖሊ ይከተለዋል። የሦስተኛ ደረጃውን በ43 ነጥብ ኢንተር ሚላን ተቆጣጥሯል።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ግን 4 ለ0 ሲረታ፤ ፎርቱና ሽቱትጋርትን 3 ለ0 አሸንፏል። ሻልከ በባየር ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት 3 ለ 1 ተሸንፏል።  ረቡዕ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ የሚጠብቀው ቦሩስያ ዶርትሙንድ 50 ነጥብ ይዞ የደረጃ ሰንጠረዡን እየመራ ነው። ባየር ሙይንሽን 45 ነጥብ ሰብስቦ ይከተላል። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ከባየር ሙይንሽን  በ2 ነጥብ ብቻ ነው የሚበለጠው። ቡንደስሊጋ  ትናንት ቬርደር ብሬመን አውስቡር

ሻምፒዮንስ ሊግ

ነገ እና ከነገ በስትያ ለሻምፒዮንስ ሊግ ስምንት ጨዋታዎች ይከናወናሉ። በነገው ዕለት ምሽት የእንግሊዙ ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድትራፎርድ የፈረንሳዩ ፓሪ ሰንጄርሜንን ያስተናግዳል። በተመሳሳይ ሰአት የፖርቹጋሉ ፖርቶ የጣሊያኑ ሮማን ለመፋለም ወደ ስታዲዮ ኦሎምፒኮ ስታዲየም ያቀናል።  ከነገ በስትያ ደግሞ፦ የጀርመኖቹ ቦሩስያ ዶርትሙንድ፤ ባየር ሙይንሽን እና ሻልከ ከእንግሊዞቹ ቶትንሀም ሆትስፐር፤ ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ ጋር ይፋለማሉ። የስፔኖቹ አያክስ አምስተርዳም እና ሪያል ማድሪድ የሚያደርጉት የረቡዕ ጨዋታም የሚጠበቅ ነው። የስፔኑ ባርሴሎና ከፈረንሳዩ ሊዮን እንዲሁም ሌላኛው የስፔን ኃያል አትሌቲኮ ማድሪድ ከጣልያኑ ጁቬንቱስ ጋር ከነገ በስትያ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

አትሌቲክስ

China Beijing 2015 IAAF Weltmeisterschaft Genzebe Dibaba
ምስል picture-alliance/dpa/S. Suki

ትናንት ሰሜናዊ ፈረንሳይ በፓ ደ ካሌ ሊቪን ውስጥ በተከናወነ የሩጫ ውድድር አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በ1000 ሜትር ፉክክር አሸናፊ ኾናለች። እንደተጠበቀው ግን ክብር ወሰን ሳትሰብር ቀርታለች። የ2 ደቂቃ ከ30.94 ሰከንድ ክብርወሰኑ ከጎርጎሪዮስ አቆጣጠር 1999 አንስቶ በማሪያ ሙቶላ እንደተያዘ ነው። በ800 ሜትር የሩጫ ፉክክርም ሐብታም ዓለሙ ድል አስመዝግባለች።

በሌላ የአትሌቲክስ ሩጫ ዜና፦ 36ኛው የጃን ሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ትናንት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡ በውድድሩ በርካታ ተመልካቾች በጃንሜዳ የታደሙ ሲሆን፤ ከጎረቤት ሃገራት የመጡ አትሌቶችም ተሳትፈዋል፡፡

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ