1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ጥር 20 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

ሰኞ፣ ጥር 20 2011

በሳምንቱ መጨረሻ ኢትዮጵያውያን ክብር ወሰን በመስበር ዓለምን ባስደመሙበት የዱባይ ማራቶን ውድድር አወዛጋቢ ክስተት ተፈጥሯል። ለኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ የሳምንት ጊዜ ቦታ የለቀቀው የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ 24ኛ ግጥሚያ ነገ ይቀጥላል። በነገው እለት ስድስት ከነገ በስትያ አራት ጨዋታዎች ይከናወናሉ።

https://p.dw.com/p/3CKdc
Premier League | Crystal Palace vs. Tottenham Hotspur
ምስል picture-alliance/empics/Craig Mercer/Sportimage

ሳምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች፦ ዩናይትድ ስቴትስ ቦስተን ከተማ ውስጥ የዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (IAAF) ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ የቤት ውስጥ ሽቅድምድም አሸናፊ በመኾን የሳምንቱ  መጨረሻን  አድምቀዋል። በዱባይ ማራቶን የሩጫ ውድድር በኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች መሀል ከፍ ተደርጎ የተያዘው የኢትዮጵያ ካርታን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በትዊተር ገጹ ላይ ማውጣቱ በርካታ ኤርትራውያንን አስቆጥቷል። ኤምባሲው ካርታው ያለበትን መልእክት ከትዊተር ገጹ በማውረድ ይቅርታ ጠይቋል። የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ፤ የጀርመን ቡንደስ ሊጋን እና ሌሎች ተጨማሪ የስፖርት ክንውኖችን የሚቃኙ ዘገባዎችን አካተናል።

በሳምንቱ መጨረሻ ኢትዮጵያውያን ክብር ወሰን በመስበር ከአንደኛ እስከ ዘጠነኛ ደረጃ በመከታተል እንደተለመደው ዓለምን ባስደመሙበት ውድድር አወዛጋቢ ክስተት ተፈጥሯል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአራተኛ ደረጃ ብቻ አንድ ኬንያዊ ጣልቃ አስገብተው በተርታ በመግባት ደማቅ ድል ባስመዘገቡበት የዱባዩ ማራቶን ከደጋፊዎች መካከል የታየ የኢትዮጵያ ካርታ በርካታ ኤርትራውያንን አስቆጥቷል።

ጌታነህ ሞላ 02 ደቂቃ ከ03 ሰከንድ ከ34 ማይክሮ ሰከንድ ሮጦ በማሸነፍ ክብር ወሰን በሰበረበት ውድድር ኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን በማውለብለብ ደስታቸውን ገልጠዋል። ከደጋፊዎች መካከል አንድ ሰው ከፍ አድርጎ የያዘው የኢትዮጵያ ካርታ ኤርትራን በማጠቃለል አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ተቀብቶ ይታያል። ይህን ፎቶግራፍ ብሪታንያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በትዊተር የማኅበራዊ መገናኛ ድረ ገጹ በማያያዙ ነበር ቁጣው የተከሰተው። ኤምባሲው ኤርትራ የማትታይበት የኢትዮጵያ ካርታን ከገጹ በማንሳት ይቅርታ ጠይቋል። 

Symbolbild Leichtathletik Laufen
ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

በዚሁ የዱባዩ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት የሴቶች ፉክክር ከሁለተኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃ ኢትዮጵያውያት ተከታትለው ገብተዋል። አንደኛ ደረጃ ያገኘችው ኬንያዊቷ ሩት ቼፕንጌቲች ናት።

ዩናይትድ ስቴትስ ቦስተን ከተማ ውስጥ በተከናወነው የዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (IAAF) ዓለም አቀፍ የቤት ውስጥ ሽቅድምድም ደግሞ አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ  3:51.70 በመሮጥ በአንደኛነት ያጠናቀቀበት ሰአት ድንቅ ተብሎለታል። በኦሎምፒክ በአምስት ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳይ ተሸላሚው ሐጎስ ገብረሕይወት የሦስት ሺህ ሜትር የሩጫ ፉክክሩን 7:37,41  በመሮጥ ነበር ድል የተቀዳጀው።

ፕሬሚየር ሊግ

13ኛ ሳምንቱን በያዘው የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ውድድር ትናንት ጅማ አባጅፋር አዲስ አበባ ስታዲየም የኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ0 አሸንፏል። በዚህ ውድር የመጀመሪያ አጋማሽ የቡናው ተከላካይ ተመስገን ካስትሮ ጉልበቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ለወራት ከውድድር ውጪ እንደሚኾን ተገልጧል።

ለኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ የሳምንት ጊዜ ቦታ የለቀቀው የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ 24ኛ ግጥሚያ ነገ ይቀጥላል። በነገው እለት ስድስት ከነገ በስትያ አራት ጨዋታዎች ይከናወናሉ። በነገው እለት ከሚደረጉ ግጥሚያዎች አርሰናል አምስተኛ ደረጃውን ለማሻሻል ካርዲፍ ሲቲን ይፋለማል። 19 ነጥብ ብቻ ይዞ 18ኛ ደረጃ ወራጅ ቃጣና ላይ የሚዋትተው ካርዲፍ ሲቲ ከአደጋ ዞኑ ለመውጣት የሚያደርገው የነገው ግጥሚያ ለቡድኑ እጅግ ወሳኝ ነው። 47 ነጥብ ይዞ በፕሬሚየር ሊጉ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቸልሲ ረቡዕ ምሽት 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው በርመስን ይገጥማል። ቸልሲ አርሰናል በነጥብ እንዳይሰተካከለው፤ ከቶትንሀምም በነጥብ ለመጠጋጋት ከነገ በስትያ በሚያከናውነው ግጥሚያ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ሼፊልድ ዌንስዴይን ትናንት በኤፍ ኤ ካፕ ፍልሚያ 3 ለ 0 ያንኮታኮተው ቸልሲ ከበርመስ ጋር የሚጋጠመው በአሸናፊነት መንፈስ ነው።

Tennis Australien Open Novak Djokovic
ምስል Getty Images/AFP/S. Khan

51 ነጥብ የሰበሰበው ቶትንሀምም ቢሆን ከማንቸስተር ሲቲ በአምስት ከመሪው ሊቨርፑል በ9 ነጥብ ርቀት መበለጡን ለማጥበብ ረቡዕ ምሽት ዋትፎርድን ይፋለማል። 44 ነጥብ ሰብስቦ 6ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ በ11 ነጥብ የሚበለጠው ዋትፎርድ ቶትንሀምን የሚገጥመው ወደ ታች ላለመውረድ  ነው።  የቀትፎርድ መሸነፍ ቡድኑን ከነበረበት 7 ደረጃ ቁልቁል 13ኛ ደረጃ ሊወረውረው ይችላል። እስከ 12ኛ ደረጃ ድረስ ያሉት ቡድኖች ከዋትፎርድ ጋር ልዩነታቸው ከ3 ነጥብ  አይበልጥም። ኾኖም ዋትፎርድን የሚገጥመው የማውሩሲዮ ፖቼቲኖው ቶትንሀም በርካታ ተጨዋቾች ስለተጎዱበት ዋትፎርድ ብዙም ጭንቀት የሚገባው አይመስልም። ቶትንሀም ቸልሲን በ4 እንዲሁም አርሰናልን በ7 ነጥብ በልጦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በሚቀጥለው ወር በሻምፒዮንስ ሊግ 16 ተፎካካካሪዎች ውስጥ ከጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር የሚገጥመው ቶትንሀም በኤፍ ኤ ካፕ ውድድር ትናንት በክሪስታል ፓላስ 2 ለ0 ተሸንፏል። የትናንቱ  የቶትንሀም ሽንፈት በሊጉ ዋንጫ  የግማሽ ፍጻሜ ውድድር በፍጹም ቅጣት ምት በቸልሲ ድል ከተነሳ ከሦስት ቀን በኋላ መኾኑ ቡድኑን ውጥረት ውስጥ ከቶታል።

ከሊጉ እና ከኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ ፉክክሮች በጊዜ የተሰናበተው የየርገን ክሎፕ ሊቨርፑል ግን ሙሉ ለሙሉ ትኩረቱን የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ ላይ ማድረጉ ይበልጥ ተጠቃሚ ሳያደርገው አልቀረም።  ረቡዕ ላይስተር ሲቲን የሚገጥመው ሊቨርፑል ፕሬሚየር ሊጉን በ60 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ላይስተር ሲቲ 31 ነጥብ ይዞ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማንቸስተር ሲቲ ነገ የሚያደርገው ጨዋታ ከመሪው ሊቨርፑል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ወይንም ባለበት ለማስቀጠል የሚያስችለው ይመስላል። ማንቸስተር ሲቲ ተደጋጋሚ ሽንፈቶችን አስተናግዶ ወራጅ ቃጣናው ጠርዝ 17ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ኒውካስትል ጋር ነው የሚጫወተው። በተመሳሳይ ሰአት ነገ ማንቸስተር ዩናይትድ ከኒውካስትል በአንድ ነጥብ በልጦ 16ኛ ደረጃ ላይ የሚቃትተው በርንሌይን ይገጥማል። ያም በመኾኑ ነገ እና ረቡዕ የሚከናወኑ የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች በጉጉት  ይጠበቃሉ።

ቡድንደስ ሊጋ

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ቅዳሜ ዕለት ሐኖቨርን  5 ለ1 ያንኮታኮተው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በደረጃ ሰንጠረዡ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። ትናንት በተቀራራቢ ውጤት ሽቱትጋርትን 4 ለ1 በኾነ ሰፊ ልዩነት ያሸነፈው ባየር ሙይንሽን  42 ነጥብ ይዞ ዶርትሙንድን  በ6 ነጥብ ዝቅ ብሎ ይከተላል። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ቅዳሜ ዕለት አውስቡርግን 2 ለ0 በማሸነፍ የሰበሰበው ነጥቡ ተደምሮለት በ39 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

Fußball | FC Chelsea -  Callum Hudson-Odoi
ምስል picture-alliance/augenklick/firo Sportphoto

በርካታ የዓለም ምርጥ ተጨዋቾችን ሰብስቦ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የጀርመን ቡንደስሊጋ ተደጋጋሚ ባለድል ባየር ሙይንሽን ተጨማሪ ተጨዋች ለማስመጣት ላይ ታች እያለ ነው። ትናንት ሽቱትጋርትን 4 ለ1 ያደባየው ባየር ሙይንሽን የ18 ዓመቱ የቸልሲው ወጣት አጥቂ ካሉም ሁድሰን ኦዶይ ላይ ዐይኑን ጥሏል። የባየር ሙይንሽን ስፖርት ዳይሬክተር ሐሳን ሳሊሐሚጂክ የቸልሲው ወጣት አጥቂ በ46 ሚሊዮን ዩሮ ወደ ቡድናቸው ሊመጣ ነው መባሉ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። የባየር ሙeይንሽን ቡድን ፕሬዚደንት ኡሊ ሆይኔትስ በበኩላቸው የተጨዋች ዝውውር ይኖር እንደኾን ተጠይቀው ትከሻቸውን በመነቅነቅ «እንጃ» ሲሉ በአጭሩ መልሰዋል። በዚህም አለ በዚያ ግን የፊታችን ሐሙስ የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ከመዘጋቱ በፊት የ18 ዓመቱ የቸልሲ አጥቂ ወደ ባየር ሙይንሽን መምጣት ወይ አለመምጣት ይለይለታል።

የሜዳ ቴኒስ

በአውስትራሊያ ኦፕን የሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ፍልሚያ የዓለማችን ምርጥ ተጨዋች ኖቫክ ጄኮቪች ዋነኛ ተፎካካሪው ራፋኤል ናዳልን ትናንት በማሸነፍ ብቃቱን አስመሰከረ። በሜልቦርን ፍልሚያ እንደ ኖቫክ ለሰባት ጊዜያት ድል በመቀዳጀት ኃያልነቱን ያሳየ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች የለም። ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች የስፔኑ ተቀናቃኙ ራፋኤል ናዳልን ድል የነሳው 6:3፤ 6:2 እና  6:3  በኾነ ውጤት ነው። በዚህ ውጤት መሰረትም ቀድሞውኑም የዓለም ምርጥ ተጨዋች ዝናን የተቀዳጀው ኖቫክ በአውስትራሊያ ፍጻሜ ለሰባት ጊዜያት በማሸነፍ ክብር ወሰን ተመዝግቦለታል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ