የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ጥቅምት 14 2009አትሌቲክስ
አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በፖርትስማውዝ ብሪታንያ የ10 ማይልስ የጎዳና ሩጫ ትናንት አሸናፊ ኾናለች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ፤ ጥሩነሽን ተከትላ የሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል እና ቸልሲ አሸናፊ በመሆን ደረጃቸውን አሻሽለዋል። ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ግን ነጥብ ጥለዋል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን፣ ላይፕትሲግ እና ሻልከ ሲያሸንፉ፤ ባየር ሙይንሽን መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። ዘንድሮ የዓመቱ ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ለመምረጥ 30 ተጨዋቾች ዕጩ ኾነዋል። የባለፈው ዓመት አሸናፊ የባርሴሎናው አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ እና ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ዘንድሮም ዋነኛ ተፎካካሪዎችእንደሚሆኑ ተጠብቋል።
ብሪታንያ ፖርትስማውዝ ውስጥ በተከናወነው የ10 ማይልስ የጎዳና ሩጫ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ትናንት 51:49 በመሮጥ አሸናፊ ኾናለች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ ጥሩነሽን በአንድ ደቂቃ ግድም ተከትላ 52:51 በመሮጥ የሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች። የሦስት ጊዜያት የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዋ ጥሩነሽ ዲባባ የፖርትስማውዙ ግሬት ሳውዝ ረን ውድድር እስከሚቀጥለው ታኅሣሥ ወር ድረስ የመጨረሻዋ መሆኑን አትሌቲክስ ዊክሊ የተሰኘው የአትሌቲክስ ውድድር ዘጋቢ ድረ-ገጽ አትቷል። ወንድ ልጅ ከተገላገለች በኋላ በግሬት ማንቸስተር የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ አሸናፊ በመሆን፤ በኦሎምፒክ መድረኩም የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን የበቃችው የ31 ዓመቷ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በመቀጠል ትኩረቷ ማራቶን እንደሚሆን ድረ-ገጹ አክሎ ዘግቧል።
የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድር
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የተከናወኑ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ከመቃኘታችን በፊት የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድርን እንመልከት። የአዲስ አበባ ከተማ የሚያዘጋጀው የእግር ኳስ ዋንጫ ግጥሚያ ዘንድሮ ከተመደበለት ጊዜ ዘግይቶ ነው በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የጀመረው። የአዲስ አበባ ከተማ የእግር ኳስ ጨዋታ ለምን ከተያዘለት የጊዜ ገደብ ሊሸጋሸግ እንደቻለ በይፋ ባይገለጥም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ሊያያያዝ እንደሚችል የሚገምቱ አሉ።
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ ውድድሮች ቅዳሜ ዕለት የመክፈቻ ጨዋታ ያደረጉት ያለምንም ግብ የተለያዩት ጅማ አባቡና እና መከላከያ ናቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮ ኤልክትሪክን በጨዋታ ብልጫ 4 ለ1 አሸንፏል። ትናንት ንግድ ባንክ አዲስ አበባ ከነማን 1 ለ0 አሸንፏል። ደደቢት በአዳማ ከነማ 3 ለ0 ድል ተነስቷል። ውድድሩ ነገም እንደሚቀጥል ተገልጧል። በመርሀ-ግብሩ መሠረት የፊታችን እሁድ መጀመር የነበረበት የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ውድድር ግን ቢያንስ ለዐሥር ቀናት መራዘሙ ታውቋል። ይኽም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነሳ ይኹን በሌላ የተገለጠ ነገር የለም።
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት ቸልሲ ማንቸስተር ዩናይትድ 4 ለ0 በሆነ ሰፊ ልዩነት ድል አድርጓል። ቸልሲ የማንቸስተርን ግብ የደፈረው ገና ጨዋታው በተጀመረ 30 ሰከንድ ነበር። ፈጣኑ ግብ ኾና ተመዝግቧል። የማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ ዴቪድ ዴ ጊያን መውጣቱን የተመለከተው ፔድሮ በሁለት ተጨዋቾች መሀል ሆኖ ኳሷን ከመረብ አሳርፏታል። በ21ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተላከችው ኳስ ጋሪ ኬል እግር ስር ገብታ ግብ እስኪቆጠር ድረስ የማንቸስተር ተጨዋቾች ምንም ያደረጉት ነገር አልነበም። በ62ኛው ደቂቃ ኤደን ሐዛርድ እንዲሁም ንጎሎ ካንቴ በ70ኛው ደቂቃ ሦስተኛ እና አራተኛ ግቦችን በማስቆጠር የማንቸስተር ዩናይትድ ተጨዋቾችን አሸማቀዋል። ወደ ፕሬሚየር ሊጉ ዳግም የመጡት አሠልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆም በቀድሞ ቡድናቸው ቸልሲ ከባድ የሽንፈት ድባብ ተከናንበው ከሜዳ ወጥተዋል።
የደረጃ ሰንጠረዡን በ20 ነጥብ የሚመራው ማንቸስተር ሲቲ ከሳውዝ ሐምፕተን ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። በቅዳሜው ጨዋታ አርሰናል ከሚድልስቦሮው ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል። ሊቨርፑል ዌስት ብሮሚችን 2 ለ1 በመርታት የሦስተኛ ደረጃውን ይዟል። ከመሪው ማንቸስተር ሲቲም ሆነ ከሚድልስቦሮው ጋር ያለምንም ግብ ከተለያየው ከተከታዩ አርሰናል ጋር ተመሳሳይ 20 ነጥብ አለው። ልዩነቱ የግብ ክፍያ ብቻ ነው። ቸልሲ በአራተኛ ደረጃ ሲገኝ፤ 19 ነጥብ አለው። ማንቸስተር ዩናይትድ በቸልሲ በ5 ነጥብ ተበልጦ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሁሉም ቡድኖች እስካሁን 9 ጨዋታዎችን አከናውነዋል።
ነገ ሊቨርፑል ለካፒታል ዋን ግጥሚያ ከቶትንሀም ጋር ይጫወታል። ከነገ በስትያ ደግሞ ማንቸስተር ዩናይትድ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ይጋጠማሉ። የሊቨርፑሉ አጥቂ ዳኒኤል ስቱሪጅ እስካሁን የአሰልጣኝ የርገን ክሎፕን ልብ ለማግኘት ማግኘት አልቻለም።
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማሕበራት ፌዴሬሽን በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ (FIFA) በየዓመቱ ምርጥ ተጨዋቾችን ይመርጣል። ዘንድሮ የዓመቱ ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ለመምረጥ 30 ተጨዋቾች ዕጩ ኾነዋል። የተወሰኑትን ለመጠቃቀስ ያኽል፦ የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቡድን አጥቂ ፒየር ኤሜሪክ አውቦማያንግ፣ የጁቬንቱሶቹ ግብ ጠባቂው ጂያንሉጂ ቡፎን፣ ፓውሎ ዲባላ እና ጎንዛሎ ሒጉያን፤ የማንቸስተር ሲቲዎቹ ሰርጂዮ አጉዌሮ እና ኬቪን ደ ብሩየን፤ የሪያል ማድሪዶቹ ጋሬት ቤል እና ክሪስቲያኖ ሮናልዶ እንዲሁም የአትሌቲኮ ማድሪዶቹ አንቶኒዮ ግሪዝማን እና ዲዬጎ ጎዲን ይገኙበታል።
ቡንደስ ሊጋ
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ትናንት ሻልከ ማይንትስን 3 ለ0 ላይፕቲስግ ደግሞ ቬርደር ብሬመንን 3 ለ1 አሸንፈዋል። የቬርደር ብሬመን አሠልጣኝ ማርኩስ ቫይንሲርል ቡድናቸው ማሸነፉ ይገባዋል ብለዋል።
«አጀማመራችንን ለማሻሻል ጥሩ እየሄድን ነው። ይህ ድል ለእኛ እጅግ ወሳኝ መሆኑ ግልጽ ነው። ደግሞም ማሸነፋችን በደንብ ነው የሚገባን። ጥሩ ነው የተጫወትነው። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አራቱን አሸንፈን፤ አንዱን አቻ ነው የተለያየነው። ያ ዛሬ የምንጓዝበትን ጎዳና ማረጋገጫ ነው።»
መሪው ባየር ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 2 ለ0 አሸንፏል። እስካሁን በተደረጉት 8 ጨዋታዎች ደረጃውን በ20 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ዘንድሮ የቡንደስሊጋውን የተቀላቀለው ላይፕቲስግ በ18 ነጥብ ይከተላል። የባየር ሙይንሽን ዋነኛ ተፎካካሪ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ14 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡንደስሊጋው ውስጥ ብዙም ልምድ ከሌለው ኢንግሎሽታድት ጋር ቅዳሜ ዕለት ሦስት እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል።
የሜዳ ቴኒስ
የዊምብልደን ውድድርን በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ ያሸነፈው የ29 ዓመቱ አንዲ ሙራይ ካለፉት ሁለት ሳምንታት አንስቶ በሜዳ ቴኒስ የዓለማችን ቁጥር አንድ ኮከብ ተጨዋችነቱን የሚነጥቀው አልተገኘም። አንዲ ሙራይ የአንደኛነት ደረጃውን የቀማው ከኖቫክ ጄኮቪች ነው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ