1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ጥቅምት 5 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

ሰኞ፣ ጥቅምት 5 2011

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በፍጥነት ራሱን መፈተሽ እንደሚገባው ብዙዎች እየተናገሩ ነው። አዲስ በተዋቀረው የአውሮጳ ኔሽንስ ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ ተሰልፎ የነበረው የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በሆላንድ በሰፊ ልዩነት መረታቱ በርካቶችን አስደምሟል።

https://p.dw.com/p/36aoW
LOG CAF 2012 Orange Africa Cup of Nations

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ ጥቅምት አምስት ቀን፣ 2011 ዓም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በፍጥነት ራሱን መፈተሽ እንደሚገባው ብዙዎች እየተናገሩ ነው። በደረጃ ብዙም ከማይርቀው የኬንያ ቡድን ጋር ትናንት ያካሄደው ጨዋታ በእርግጥም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሳይውል ሳያድር ራሱን መፈተሽ እንዳለበት ያመላከተ ነበር። የትናንቱን ከባድ ሽንፈት በተመለከተ የእግር ኳስ ጋዜጠኛ አነጋግረናል። አዲስ በተዋቀረው የአውሮጳ ኔሽንስ ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ ተሰልፎ የነበረው የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በሆላንድ በሰፊ ልዩነት መረታቱ በርካቶችን አስደምሟል። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 የዓለም ዋንጫ ባለድል የነበረ ቡድን አዲስ በመጡ የሆላንድ ተጨዋቾች መሸነፉ የጀርመን እግር ኳስ አፍቃሪዎችን እጅግ አበሳጭቷል። በሀገሪቱ ስፖርት አፍቃሪዎችም ዐቢይ መነጋገሪያ ኾኗል። 

የሐራምቤ ከዋክብት የተሰኘው የኬንያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የትናንቱን ጨዋታ እንደሚያሸንፍ ኬንያውያን የስፖርት ተንታኞች አስቀድመው ሲናገሩ ነበር። ለዚያም ኬንያውያን የኳስ ደጋፊዎች በነቂስ ወደ ስታዲየም እንዲመጡ እጅግ ሲያበረታቱ ነበር። በተለይ ደግሞ ባህር ዳር ላይ ኢትዮጵያውያን ኳስ አፍቃሪዎች እንዲያ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ስታዲየሙን አሸብርቀው እጅግ የሞቀ ድጋፍ መስጠታቸው ኬንያውያንን እንቅልፍ የነሳቸው ነበር የሚመስለው። እናም የኬንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እግር ኳስ አፍቃሪያን ስታዲየም በነጻ እንዲገቡ ግብዣውን አቀረበ።

እሁድ ዕለት መዲናዪቱ ናይሮቢ ካሳራኒ በተሰኘው ሥፍራ ወደሚገነው የሞይ ዓለም አቀፍ ስፖርቶች ማዕከል ስታዲየም የሚጎርፈው ሰው ከቁጥር በላይ ነበር። ስታዲየሙ ከአቅሙ በላይ መያዝ እንደማይችል ቢነገራቸውም ስታዲየም ካልገባን ሲሉ ያንገራገሩ ደጋፊዎችም ነበሩ። ፖሊስ ወደስታዲየም ካልገባን ሲሉ የነበሩትን በርካታ ኬንያውያን በአስለቃሽ ጢስ ለመበተን ሲሞክርም ታይቷል።

እንዲያ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ጨዋታ በተጀመረ 23ኛ ደቂቃ ላይ ኬንያውያን የመጀመሪያውን ግብ በማስገባት መሪነቱን ጨበጡ። እናም አከታትለው በማስቀጠር የኢትዮጵያ ቡድንን 3 ለ0 በኾነ ሰፊ ልዩነት ድል አድርገዋል። የእግር ኳስ ጋዜጠኛው ኦምና ታደለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሜዳው ውጪ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተደጋጋሚ ሽንፈቶችን ማስተናገዱ የተለመደ መኾኑን ይናገራል።

UEFA Nations League - Niederlande - Deutschland 3:0
ምስል picture-alliance/J. Niering

ከእግር ኳስ ዘገባ ሳንወጣ፦ ለዓለም ዋንጫ ድል የበቁ አንጋፋ ተጨዋቾችን ያካተተው የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በወጣት እና አዲስ ተጨዋቾች በተዋቀረው የሆላንድ ቡድን ቅዳሜ ዕለት 3 ለ0 በኾነ ሰፊ ልዩነት መሸነፉ ጀርመናውያንን እንቅልፍ ነስቷል።የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ የ58 ዓመቱ ዮዓሒም ሎይቭ በወጣቶች አይተማመኑም ሲሉ በርካታ ደጋፊዎች ቅሬታቸውን ገልጠዋል።

በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ፍልሚያ ብቃታቸውን ያሳዩ ወጣት ተጨዋቾች ለዚያ ሁሉ ጥረታቸው ችላ ተብለዋል፤ በ20፣21 እና 22 ዓመት የሚገኙ ወጣቶች ላይ አሰልጣኙ እምነት ሲያሳድሩ አልታዩም የሚሉ ቅሬታዎች ተበራክተዋል። አንዳንዶችም እንደውም አሰልጣኙ መቼ ነው የሚበቃቸው እና ዘወር የሚሉት ሲሉም ይደመጣሉ።  ተጨዋቾቹ ራሳቸው በውጤቱ እጅግ ማፈራቸውን ገልጠዋል። የመሀል ተከላካዩ ማትስ ሁመል፦ «እኛው በራሳችን ላይ ያመጣነው ክብረ-ቢስ ነገር ነው» ሲል መሪር ቅሬታውን አንጸባርቋል። የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ላይ ቡድኑን የመራው ወጣቱ ዩሊያን ድራክስለር፦ «ከእንግዲህ እንዲያ መዝለቅ አልተቻለንም» ብሏል በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ወቅት ወጣቱ ቡድን ያሳየውን ብቃት በማስታወስ። «ውብ ቃላትን መደርደር አያዛልቅም» ያለው ደግሞ ሌላኛው የብሔራዊ ቡድኑ ወጣት ተሰላፊ ዮሹዋ ኪሚሽ ነው።

የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በዓለም ዋንጫ ከደረሰበት ውድቀት ወዲህ ብዙም ያገገመ አይመስልም። ተጨዋቾቹም እስካሁን ካላባራው የሒስ ውርዥብኝ በመንፈስ የተዘጋጁ አይመስልም። ሜዳ ላይ እንደቀድሞው ደስተኝነታቸው እና ቁርጠኝነታቸው ዐይታይም።

እንደ ማትስ ሑመል፣ ጄሮም ቦአቴንግ እና ቶማስ ሙይለርን የመሳሰሉ ተጨዋቾችን ይዞ የጀርመን ቡድን ተደጋጋሚ ሽንፈት ማስተናገዱ የተጨዋቾቹ ሥነ-ልቦና ላይ ኃያል በትር እንዳሳረፈ ማስተዋል ይቻላል። ይኼ ሁሉ ጫና ከየአቅጣጫው እየተሰነዘረ የጀርመን ብሔራዊ ቡድንን የሚገባው ጣራው ላይ ያደረሱት አሰልጣኙ ዮዖሒም ሎይቭ ቡድናቸው እንዲያ ሲፍረከረክ ስለወደፊት የአሰልጣኝነታቸው ዘመን ሲናገሩ አይደመጥም። በአንድ ወቅት  ሥራቸውን ስለመተው እንደማያስቡ የገለጡ ቢሆንም ማለት ነው። በዚህም አለ በዚያ ከሚደርስባቸው የሒስ ውርጅብኝ ጋብ ለማለት ቡድናቸው ከፈረንሳይ አቻው ጋር ማክሰኞ በሚያደርገው ጨዋታ የሚጠበቅበት ማሸነፍ ብቻ ነው። የፈረንሳይ ቡድን ደግሞ እንዲህ እንደዋዛ የሚጠቀስ አይደለም፤ ያለፈውን የዓለም ዋንጫ ያነሳ ብርቱ ቡድን ነው።

Australien Usain Bolt - Debüt mit den Central Coast Mariners
ምስል picture-alliance/dpa/D. Himbrechts

በአትሌቲክሱ ዘርፍ በአጭር ርቀት ለዘመናት እንደነገሠ ገለል ያለው ጃማይካዊው ዩሲያን ቦልት ወደ እግር ኳሱ ፊቱን መልሷል። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2017 ከሩጫ ፉክክር ራሱን ማግለሉን ያስታወቀው ብርቱ አትሌት በአውስትራሊያ የኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን (Asada) የሽንት ምርመራ እንዲያደርግ መታዘዙ እንዳስከፋው ገልጧል። እኔ ከእንግዲህ አትሌት አይደለሁም ኳስ ተጨዋች እንጂ ያለው ቦልት በአትሌቲክስ ባለሥልጣን ምርመራ አድርግ መባሉን አልተቀበለውም ነበር። ሴንትራል ኮስት  ማሪነርስ ለተባለው የኤ ሊግ ቡድን ውስጥ ፈርሞ ለመጫወት በሙከራ ጊዜ ልምምድ ላይ የሚገኘው የቀድሞ አትሌት የእግር ኳስ ተጨዋች ዘግየት ብሎ ግን ምርመራው አድርጓል። ቦልት ኹኔታውን ሲያብራራ፦ «ሴትዮዋን፤ እንዴ ለቡድኑ ሳልፈርም ለምንድን ነው የሽንትን ምርመራ የማደርገው አልኳት። እሷም የነገሯት የታወቅሁ አትሌት በመኾኔ ምርመራውን ማድረግ እንደሚገባኝ መኾኑን ገለጠችልኝ፤ ከዚያም እሺ አልኳት»  ብሏል። የአውስትራሊያው የጸረ ኃይል ሰጪ መሥሪያ ቤት በማናቸውም ስፖርቶች የሚወዳደር ስፖርተኛ እንደ አትሌት ይቆጠራል የሚል እምነት አለው። ያም በመኾኑ አትሌቱ የሽንት ምርመራ ማድረግ ይጠበቅበታል።

Deutschland Erster Titel perfekt: Mick Schumacher wird Formel-3-Europameister
ምስል imago/Kräling

በፎርሙላ አንድ የሰባት ጊዜያት ባለድሉ ጀርመናዊ ማይክል ሹማኸር ልጅ ማይክ ሹማኸር በፎርሙላ ሦስት ውድድር አሸነፈ። የ19 ዓመቱ ወጣት የሆፈንሀይም ጀርመን የቅዳሜ ዕለት ድሉ ልክ እንደ አባቱ በፎርሙላ አንድ ለመሳተፍ ያስችለዋል ተብሏል። አባቱ በፎርሙላ አንድ ተደጋጋሚ ባለድል ከመኾኑ በፊት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1990 የፎርሙላ 3 አሸናፊ ነበር። የማይክ አባት ማይክል ሹማኸር በ2013 ታኅሣሥ ወር ላይ በረዶ ሲንሸራተት በደረሰበት የራስ ቅል አደጋ ራሱን ከሳተ ወዲህ ግን ለሕዝብ ታይቶ ዐይታወቅም። የቀድሞ የፌራሪ አሽከርካሪው ግላዊ ሕይወት ስዊትዘርላንድ በሚገኘው የቤተሰቡ መኖሪያ ተጠብቆ ይገኛል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ