1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት

ሰኞ፣ ኅዳር 30 2006

በሣምንታዊው የስፖርት ጥንቅራችን፤ የሻምፒዎንስ ሊግና የአውሮፓ ዋና ዋና የእግር ኳስ ሊጋ ግጥሚያዎች ዋነኛ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። የምስራቅና መካከለኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ማኅበር የዋንጫ ውድድር፣ ብራዚል ውስጥ የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ እና ሌሎች አጫጭር ስፖርታዊ ክንውኖችም ተዳሰዋል።

https://p.dw.com/p/1AVjk
ምስል picture-alliance/dpa

ምስራቅና መካከለኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ማኅበር የእግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በሱዳኑ አቻው 2 ለ ባዶ ተረትቷል።ኃያሉ ባየር ሙንሽን ቬርደር ብሬመንን 7 ለ ምንም በሆነ ሰፊ ልዩነት አብረክርኮታል። ፕሬሚየር ሊግ፣ ቡንደስሊጋ፤ ሴሪ ኣ እና ላሊጋ እንደየ ቅደምተከተላቸው ትንታኔ ይደረግባቸዋል። ሌሎች አጫጭር ስፖርት ነክ ዘገባዎችንም አካተናል።

ኬንያ ውስጥ እየተካሄደ በሚገኘው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ማኅበር የእግር ኳስ ፍልሚያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትናንት ሞምባሳ ስታዲየም ውስጥ ከሱዳኑ አቻው ጋር ገጥሞ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ ደርሶ የነበረ ቡድን እንደመሆኑ አንፃር በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት ነበር። ይሁንና ዋሊያዎቹ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ተሽለው ቢገኙም ኳስ ከመረብ ለማሳረፍ ተስኗቸዋል። ይልቁንስ እጅግ በጥንቃቄ ሲጫወት የነበረው የሱዳን ቡድን በ23ኛው ደቂቃ ላይ ድንገት ያላሰበውን ሲሳይ አፍሷል። ሣላሀዲን ባርጌቾ በገዛ ቡድኑ ላይ ያስቆጠራትን ግብ ተከትሎ በ69ኛው ደቂቃ ላይ ታሊስማን ሣላህ ኢብራሒም ለሱዳን የማሳረጊያውን ኳስ ከመረብ አሳርፏል።

Südafrika Äthiopien Fußball Africa Cup DW-Reporter Haimanot Turuneh in Johannesburg
ምስል DW/H. Turuneh

ትናንት የዛምቢያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንም በሩብ ፍፃሜው ከቡሩንዲ ጋር የገጠመ ሲሆን፤ ጨዋታው ዘጠናውን ደቂቃ በሙሉ ያለምንም ግብ እጅግ አሰልቺ ሆኖ ተመዝግቧል። አሸናፊውን ለመለየት በተሰጠው የፍፁም ቅጣት ምት ዛምቢያ የማታ ማታ ቡሩንዲን 4 ለ3 ለማሸነፍ ችሏል። ከነገ ወዲያ ዛምቢያ ኢትዮጵያን ያሸነፈውን የሱዳን ብሔራዊ ቡድን በግማሽ ፍፃሜው ሲገጥም፤ አስተናጋጇ ኬንያ ከታንዛኒያ ጋር ትፋለማለች። የዋንጫ ፍልሚያው የፊታችን ሐሙስ 10 ሰዓት ላይ ንያዮ ስታዲየም ውስጥ ይከናወናል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ ከትናንት በስትያ ያልተጠበቁ ሁናቴዎች ተከስተዋል። ቸልሲ በ90ኛው ደቂቃ ላይ በስቶክ ሲቲ ነጥብ ሲነጠቅ፤ ማንቸስተር ዩናይትድ በአራት ቀናት ልዩነት ብቻ በሜዳው ዳግም ለሁለተኛ ጊዜ ሽንፈት ቀምሷል። ማን ዩናይትድን ጉድ ያደረገው ኒውካስል ነው፣ ኦልድ ትራፎርድ ላይ በእንግድነት መጥቶ ማንቸስተርን 1 ለባዶ ጉድ አድርጎት ሄዶዋል።

ማንቸስተር ሲቲ በበኩሉ ሳውዝሐምፕተን ላይ አንድ እኩል አቻ መለያየቱ ሊቨርፑል ወደ ዋነኛ ተቀናቃኙ አርሰናል እንዲገስገስ አስችሎታል። ሊቨርፑል አንፊልድ ላይ ዌስትሐምን 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ ልዩነት ነው የረመረመው። አርሰናል ትናንት ከኤቨርተን ጋር አንድ እኩል ተለያይቶ ነጥብ ቢጋራም የደረጃ ሠንጠረዡን አሁንም በ5 ነጥብ ልዩነት በመምራት ላይ ይገኛል። የጆዜ ሞርሂኖ ቸልሲ በስቶክ ሲቲ 3 ለ 2 መሸነፍ ቡድኑ በጎል ልዩነት ከሊቨርፑል በታች ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንዲሰፍር ግድ ሆኖበታል።

ማንቸስተር ዩናይትድ ዋንጫ ለመጨበጥ ከሚፎካከሩት ተርታ ለመሰለፍ የነበው ደብዛዛ ህልም በኒውካስል በደረሰበት የ1 ለ0 ሽንፈት ወደ ጭላንጭልነት ተለውጧል። የማንቸስተር ዩናይትድ ባለታሪክ ሆነው የሚታሰቡት ሰር አሌክስ ፈርግሰንን የተኩት አሰልጣኝ ዴቪድ ሞዬስ ቡድናቸው ከአርሴናል በ12 ነጥብ ርቆ ማሽቆልቆሉ እንዳልተዋጠላቸው ገልፀዋል «ደጋፊዎቻችንም ሆኑ እኔ በእዚህ ወቅት አምስት ጊዜ እንሸነፋለን ብለን አልጠበቅንም።» ሲሉ ነበር ሞዬስ በቡድናቸው አቋም መከፋታቸውን ያሳዩት።

የሊቨርፑሉ ሉዊስ ሱዋሬዝ
የሊቨርፑሉ ሉዊስ ሱዋሬዝምስል Reuters

ትናንት ፉልሐም አስቶን ቪላን 2 ለ ባዶ አሸንፏል። ከትናንት በስትያ ቶትንሐም ሰንደርላንድን 2 ለ1፣ ክሪስታል ፓላስ ካርዲፍ ሲቲን 2 ለ ባዶ እንዲሁም ኖርዊች ዌስት ብሮሚችን 2 ለ 0 አሸንፈዋል። የደረጃ ሠንጠረዡን አርሰናል በ35 ነጥብ ሲመራ፤ ሊቨርፑል 30 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ ቸልሲን አስከትሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማንቸስተር ሲቲ በ29 ነጥብ፣ ኤቨርተን በ28 አራተኛ እና አምስተኛ በመሆን ይከታተላሉ። ማንቸስተር ዩናይትድ በ22 ነጥብ ታች 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

14 ግቦችን በማስቆጠር የሊቨርፑሉ ሉዊስ ሱዋሬዝ ፕሬሚየር ሊጉን በኮከብ ግብ አግቢነት እየመራ ይገኛል። የማንቸስተር ሲቲው ሰርጂዮ አጉዌሮ 12 ግቦችን በማስቆጠር ሁለተኛ ሲሆን፤ ሌላኛው የሊቨርፑል ግብ አዳኝ ዳንኤል ስቱሪጅ 9 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የአርሰናሉ አሮን ራምሴይ፣ የማንቸስተር ዩናይትዱ ዋይኔ ሩኒ፣ የኤቨርተኑ ሮሜሉ ሉካኩ እና የኒውካስል ዩናይትዱ ሎይች ሬሚ እያንዳንዳቸው 8 ግቦችን በማስቆጠር በአራተኛ ደረጃ ግብ አግቢነት ተሰልፈዋል።

በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ ደግሞ በኮከብ ግብ አግቢነት እየመራ የሚገኘው የዶርትሙንዱ ሌቫንዶቭስኪ ነው። እስከትናንት ድረስ ሌቫንዶቭስኪ ለቡድኑ 11 ግቦችን ከመረብ ለማሳረፍ ችሏል። የሽቱትጋርቱ ኢቢሴቪች 9 ግቦችን በማስቆጠር ሁለተኛ ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው 8 ግቦችን በማስመዝገብ 6 ተጨዋቾች በሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። እነሱም የዶርትሙንዱ አውባምዬንግ፣ የሆፈንሀይሙ ፊርሚኖ፣ የሞንሽንግላድባኾቹ ክሩዘ እና ራፋኤል፣ የሐምቡርጉ ላሶጋ እንዲሁም የሔርታ ቤርሊኑ ራሞስ ናቸው።

የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ሌቫንዶቭስኪ
የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ሌቫንዶቭስኪምስል Reuters

ቡንደስ ሊጋውን ባየር ሙንሽን በ41 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ባየር ከትናት በስትያ የፈረደበት ዶርትሙንድን 7 ለ ባዶ በሆነ ሰፊ የጎል ልዩነት ነበር ጉድ ያደረገው። ባየር ሙንሽን የመጀመሪያውን ግብ ያገኘው የብሬመኑ አሳኒ ሉኪሚያ በ21ኛው ደቂቃ ላይ ጨርፎ በገዛ ግቡ ላይ በማስቆጠሩ ነበር። ብዙም ሳይቆይ 27ኛው ደቂቃ ላይ ምንም እንኳን በሶስት የብሬመን ተጨዋቾች ተከቦ የነበረ ቢሆንም፤ ዳንኤል ቫን ቡይተን ሁለተኛዋን ግብ በጭንቅላቱ ገጭቶ ከመረብ አሳርፏል። በዕለቱ ኮከብ ሆኖ ሲንቀሳቀስ የነበረው ፍራንክ ሪቤሪ በ38ኛው እና 82ኛ ደቂቃዎች ላይ ለባየርን ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። ማሪዮ ማንቹኪ በ60ኛው ደቂቃ እንዲሁም ቶማስ ሙለር በ68ኛው ደቂቃ ላይ በተከታታይ አግብተዋል። የማሳረጊያዋን ኳስ ከመረብ ያሳረፈው ማሪዮ ጎትሰ ነው። ሬበሪ ካስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ባሻገር ገደኞቹ ግብ እንዲያስቆጥሩ በማመቻቸት ድንቅ ተጨዋችነቱን አስመስክሯል። ፍራንክ ሪቤሪ ከብሬመኑ ድል በኋላ ተጠይቆ ሲመልስ እንዲህ ነበር ያለው።

ፍራንክ ሪቤሪ
ፍራንክ ሪቤሪምስል picture-alliance/dpa

«እንደሚመስለኝ ጥሩ እንጫወታለን። ጥሩ እየተሳካልን ነው። እስከመጨረሻው ፍልሚያ ድረስ በጥንቃቄ መጫወት ይገባናል። እስከ ወሩ መጨረሻ ድረስ አራት ጨዋታዎች ይቀሩናል። አንደኛው በቡንደስ ሊጋው ነው። አንዱ ለሻምፒዮንስ ሊግ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ ለዓለም ዋንጫ የምናደርጋቸው ናቸው። ሁሉንም ለማሸነፍ እጥራለሁ።»

ባየር ሌቨርኩሰን 37 ነጥቦችን ይዞ በአራት ነጥብ ልዩነት ባየር ሙንሽንን ይከተላል። ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በ31 ነጥብ የደረጃ ሰሠንጠረዡ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቦሩሲያ ሞንሽንግላድባኽ ከትናንት በስትያ ዶርትሙንድን 2 ለ1 በመርታት ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ በተመሳሳይ ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት በአራተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል። ዎልፍስቡርግ በ26 ነጥብ አምስተኛ ደረጃውን ሲያስጠብቅ፤ 24 ነጥብ ብቻ ይዞ የሚንገታገተው ሻልካ ከዋንጫ ተፎካካሪነቱ ወጥቷል።

በሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያው 16 አላፊዎች መካከል ስምንቱ ታውቀዋል። እነሱም የጀርመኑ ባለድል ባየር ሙንሽን፣ የእንግሊዞቹ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ቼልሲ፤ የፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንጀርሜን፣ የስፔኖቹ ሪያል ማድሪድ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ እና ባርሴሎና ናቸው። ቀሪዎቹ ስምንት ቡድኖች ነገ እና ከነገ ወዲያ በሚደረጉ ግጥሚያዎች የሚለዩ ይሆናል።

ከሰባት ወራት በፊት በሁለቱ የጀርመን ቡድኖች ባየር ሙንሽን እና ቦሩሲያ ዶርትሙንድ መካከል በተደረገው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ባየርን ባለድል የመሆኑን ያህል አሁንም ከምድቡ ነጥብ ሳይጥል እየገሰገሰ ነው። አርሰናል የሚገኝበትን ምድብ በ12 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ከዶርትሙንድ እኩል 9 ነጥብ ካለው የጣሊያኑ ናፖሊ ጋር ይገጥማል። ዶርትሙንድ ብዙም ግምት ካልተሰጠው ኦሎምፒክ ማርሴይ ጋር ይገናኛል። የፕሬሚየር ሊጉ መሪ አርሴናል ነጥብ ተጋርቶም ቢሆን ማለፍ ሲችል፣ ዶርትሙንድ ለማለፍ የግድ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

አሁን ደግሞ በስፔኑ ላሊጋ እና በጣሊያኑ ሴሪ ኣ የተካሄዱ ጨዋታዎችን በአጭሩ እንዳስሳለን። ትናንት ማዮካ ኑማንቺያ ጋር ያለምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል። ሚራንዴስ ከሙርቺያ ጋር አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርተዋል። ዛራጎዛ ኮርዶባን 2 ለባዶ ረትቷል። ፖንፌራንዲና ኢeበርን 2 ለ1 አሸንፏል።

Mönchengladbach - Dortmund: Duell zwischen Stefan Effenberg und Heiko Herrlich
ምስል picture-alliance/dpa

የጣሊያን ሴሪኣን ጁቬንቱስ በ40 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ሮማ በ37 ነጥብ ይከተላል። ናፖሊ በአራት ነጥብ ልዩነት ኢንተር ሚላንን ርቆ በ32 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ተቆናጧል። ትናንት ኢንተር ሚላን ከፓርማ 3 እኩል ተለያይቷል። ሮማ ፊዮሬንቲናን፣ ሔላስ ቬሮና አትላንታን 2 ለ 1 አሸንፈዋል። ሳምፕዶሪያ ካታንያን 2 ለ ባዶ ሲሸኝ፤ ሺየቮ ቬሮና ሳሱዎሎን 1 ለምንም አሸንፏል። ከትናንት በስትያ ናፖሊ ከኡዴኔዚ 3 እኩል፣ ሊቮርኖ ከኤስ ሚላን ሁለት እኩል አቻ ወጥተዋል።

በ12 ከመረብ ያረፉ ግቦች የፊዮሬንቲናው ጂውሴፖ ሮሲ የሴሪ ኣው ግብ አዳኝነቱን አስመስክሯል። የኢንተር ሚላኑ ሮድሪጎ ፓላቺዮ በ9 ግቦች በሁለተኛ ደረጃ ይከተላል። የቶሪኖው አሌሲዮ ሴርቺ 8 ግቦችን ከመረብ አሳርፎ ይከተለዋል።

እስኪ አሁን ደግሞ አጫጭር ዓለም አቀፍ የስፖርት ዘገባዎችን እናሰማችሁ። የዓለም ዋንጫን ለማስተናገድ ደፋ ቀና በማለት ላይ በምትገኘው ብራዚል ሳኦ ፖሎ ከተማ ውስጥ ትናንት የእግር ኳስ ደጋፊዎች ስታዲየም ውስጥ አምባጓሮ በመፍጠራቸው የብራዚል ሊግ ተስተጓጉሎዋል። ፖሊስ ፀቡን ለማርገብ የፕላስቲክ ጥይቶችን የተኮሰ ሲሆን፤ አንድ የተጎዳ ተመልካችን ለማንሳት ሄሊኮፕተር ሜዳው ውስጥ አሳርፎዋል።

ብራዚል ውስጥ ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት የዓለም ዋንጫ ለምድራችን የእግር ኳስ ግጥሚያ ታላቅ ቢሆንም፤ ለምንኖርባት ምድር ብክለት ግን ጥሩ ያልሆነ ነገር የሚያስከትል መሆኑ ተነገረ። ፊፋ እንደተናገረው ከሆነ በ2014ቱ የብራዚል የዓለም ዋንጫ ለመታደም በዓየር በረራ በሚደረግ ጉዞ የተነሳ ወደ 2.72ሚሊዮንሜትሪክ ቶን ገደማ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ልቀት ወደ ከባቢ ዓየር መሰራጨቱ አይቀርም። ይህ ደግሞ 560,000 አሽከርካሪዎች የሚነዷቸው መኪናዎች በዓመት ወደ ከባቢ ዓየር ከሚለቁት መርዛማ የካርቦንዳይ ኦክሳይድ መጠን ጋር ይመጣጠናል ተብሏል።

የብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ድልድል
የብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ድልድልምስል AFP/Getty Images

እንግሊዝ ውስጥ ስድስት ተጨዋቾች ገንዘብ ለማጋበስ በሚል በተለያዩ ክለቦች በማጭበርበር ተጫውተዋል በሚል በቁጥጥር ስር ዋሉ። እጎአ በ1936 የበርሊኑ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች በጄሴ ኦዌንስ የተገኘው ሜዳይ ኢንተርኔት ላይ በተደረገ ጨረታ በ1.4ሚሊዮን ዶላር በመሸጥ ክብርወሰን ጨበጠ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ ነኝ

ነጋሽ መሀመድ