ስፖርት
ሰኞ፣ መጋቢት 8 2006ቡንደስ ሊጋ፣ ላሊጋ እና ሴሪ ኣም ቅኝት ይደረግባቸዋል። ኢትዮጵያኖች በተሳተፉበት የኒውዮርኩ ማራቶን የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ ባለድሉ ሞ ፋራህ ተዝለፍልፎ ወድቋል።
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ሊቨርፑል ትናንት ማንቸስተር ዩናይትድን ጉድ አድርጎ ቸልሲን መጣሁብህ እያለው ነው። ሊቨርፑል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ከቸልሲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት አራት ብቻ ለማድረግ ችሏል። በትናንቱ ግጥሚያ የሊቨርፑሉ የቁርጥ ቀን ልጅ ሽቴፋን ዤራርድ የመጀመሪያዋን እና ቀጣዩዋን ግብ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሯል። ቢጫ ካርድም አይቷል። የፕሬሚየር ሊጉን በ25 ከመረብ ያረፉ ግቦች በኮከብ ግብ አግቢነት እየመራ የሚገኘው ሉዊስ ሱዋሬዝ ሶስተኛዋን የማሳረጊያ ግብ ለሊቨርፑል ከመረብ አሳርፏል።
በትናንቱ ጨዋታ ሊቨርፑሎች አራት ቢጫ ካርዶች ሲመዘዝባቸው፤ በሜዳው ግብ ማስቆጠር ለተሳነው ማንቸስተር ዩናይትድ ግን የከፋ ነበር። ማንቸስተሮች ሁለት ቢጫ ካርድ ከተሰጣቸው በኋላ በ77ኛው ደቂቃ ላይ ኔማንያ ቪዲች የፕሬሚየር ሊጉ ሁለተኛ ኮከብ ግብ አግቢ የሆነው ዳንኤል ስቱሪጅ ላይ ዳግመኛ ጥፋት በመፈፀሙ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ዳንኤል ስቱሪጅ ለሊቨርፑል 18 ግቦችን በማስቆጠር ሶስተኛ ኮከብ ግብ አግቢ ከሆነው ከማንቸስተር ሲቲው ሠርጂዮ አጉዌሮ በሶስት ግቦች ከፍ ብሎ ይገኛል።
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የትናንቱ ሁለተኛ ጨዋታ አርሰናል ቶትንሐምን 1 ለዜሮ መርታት ችሏል። ከትናንት በስትያ ደግሞ ማንቸስተር ሲቲ ሁል ሲቲን 2 ለባዶ፣ ሣውዝ ሀምፕተን ኖርዊችን 4 ለ2 ቀጥተዋል። ኤቨርተን ካርዲፍን 2 ለ1 ሲያሸንፍ፤ ፉልሐም ኒውካስልን 1 ለምንም አሰናብቷል። ዌስትሐም በስቶክ ሲቲ 3 ለ1 ሲረታ፤ ዌስት ብሮሚች ስዋንሲን 2 ለ1 ሸኝቷል። ሠንደርላንድና ክሪስታል ፓላስ ያለምንም ግብ ሲለያዩ፤ ጠንካራው ቸልሲ በአስቶን ቪላው ፋቢያን ዴልፍ ብቸኛ ግብ ጉድ ሆኗል።
ፕሬሚየር ሊጉን ቸልሲ በ66 ነጥቦች ሲመራ በሜዳው አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሊቨርፑል በ62 ነጥብ ይከተለዋል። አርሰናልም አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ከሊቨርፑል ጋር ልዩነቱ የግብ ክፍያ ብቻ ነው። ሶስት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ማንቸስተር ሲቲ ከመሪው ቸልሲ ጋር ልዩነቱ የ6 ነጥቦች ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ48 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ እየተሰቃየ ይገኛል።
የማንቸስተር ዩናይትዱ ዝነኛው አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰንን የተኩት ዴቪድ ሞየስ የኦልትራፎርድ ቆይታቸው ከጠበቁት በላይ ከባድ እንደሆነ ከትናንቱ ሽንፈት በኋላ ገልጠዋል። እዛው ማንቸስተር ውስጥ አድጎ የጉርምስና ዘመኑን የጨረሰው ግልፍተኛው ዋይኔ ሩኒ በስፖርት ዓለም ቆይታዬ እንደትናንቱ የከፋ ቀን የለም ሲል በሊቨርፑል የደረሰባቸው የ3 ለባዶ ድቀት አሁንም ድረስ ያልለቀቀው «ቅዠት» እንደሆነበት ጠቅሷል።
ወደ ጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ እናቅና። ኃያሉ ባየር ሙንሽን አሁንም በድል ጎዳና ለብቻው እየገሰገሰ ነው። በደረጃ ሠንጠረዡ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሌቨርኩሰንን ከትናንት በስትያ 1 ለባዶ አሸንፏል። ሔርታ በርሊን በሐኖቨር 3 ለዜሮ ተሸኝቷል። ስቱትጋርት ከ ቬርደር ብሬመን አንድ እኩል ወጥቶ ነጥብ ተጋርቷል። ትናንት ሐምቡርግ ኑረንበርግን 2 ለ1 ሲረታ፤ ፍራይቡርግ አይንትራኅት ፍራንክፉርትን በኮሜርስ ባንክ አሬና 4 ለ1 አርበትብቶ ጉድ አሰኝቷል።
በቡንደስ ሊጋው የደረጃ ሠንጠረዥ ሻልካ በ47 ነጥብ ሶስተኛ ነው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሻልካን በአንድ ነጥብ በልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ኃያሉ ባየር ሙንሽን ከተፎካካሪዎቹ በ23 ነጥብ ርቆ በሰበሰበው 71 ነጥቡ ከላይ ተኮፍሷል።
ባየር ሙንሽንን በነጥብም ሆነ በኮከብ ግብ አግቢነት ማንም የሚስተካከለው አልተገኘም። የባየር ሙንሽኑ ማሪዮ ማንቹኪ 15 ግቦችን ከመረብ አሳርፎ በቡንደስ ሊጋው ኮከብ ግብ አግቢነቱን እንዳስጠበቀ ነው። የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ልክ እንደቡድኑ ሁሉ የባየር ሙንሽኑ ማንቹኪን በ13 ከመረብ ያረፉ ግቦች እየተከተለው ይገኛል። የቦሩስያ ሞንሽንግላድባኹ ራፋኤል ደ አራዉም በተመሳሳይ ከመረብ ያረፉ ኳሶች ከሌቫንዶቭስኪ እኩል በሁለተኛ ደረጃ ላይ ነው። እስካሁን በቡንደስ ሊጋው 12 ግቦችን አስቆጥረው በሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት የሔርታ በርሊኑ አድሪያን ራሞስ እና የባየር ሙንሽኑ ቶማስ ሙለር ናቸው።
በነገራችን ላይ የባየር ሙንሽኑ ፕሬዚዳንት ኡሊ ሆኔስ ግብር ሊከፈልበት የሚገባውን በሚሊዮናት የሚቆጠር ዩሮ ለዓመታት ሸሽገው በመገኘታቸው ሶስት ዓመት ከመንፈቅ እስር ተፈርዶባቸዋል። ፕሬዚዳንቱ በህይወቴ ከሰራሁዋቸው ስህተቶች ሁሉ የከፋው ነው፤ እንደአመጣጡ እቀበለዋለሁ ሲሉ ጥፋታቸውን አምነዋል። በተላለፈባቸው ውሳኔ ላይም ይግባኝ እንደማይጠይቁ ባለፈው አርብ አስታውቀዋል። የባየር ሙንሽን የእግር ኳስ ቡድን ፕሬዚዳንትነት ስልጣናቸውንም መልቀቃቸው ቀደም ሲል ተዘግቧል።
በስፔን ላሊጋ ትናንት እድለ ቢሱ ኦሳሱና የጎል ጎተራ ሆኖ ነው ያመሸው። በጠንካራው ባርሴሎና 7 ለ ባዶ እስኪበቃው ተዶቅሷል። አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ ከሰባቱ ግቦች ገሚስ ያህሉን ለእራሱ አድርጎ ሀትሪክ ሰርቷል። በላሊጋው ያስቆጠራቸውን ግቦችም ወደ 18 በማድረስ ሶስተኛ ኮከብ ግብ አግቢ ለመሆን ችሏል። የአትሌቲኮ ማድሪዱ ዲዬጎ ኮስታ 22 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሁለተኛ ነው። የሪያል ማድሪዱ ክሪስትያኖ ሮናልዶ ግን እየገሰገሰ ነው። እስካሁን በላሊጋው 25 ግቦችን ከመረብ አሳርፎ የላሊጋው ኮከብ ግብ አግቢነቱን እንዳስጠበቀ ነው።
ትናንት የስፔን ላሊጋ አፍቃሪዎች በግብ ተንበሽብሸው ነው የዋሉት ማለት ይቻላል። ሴቪላ በበኩሉ ሪያል ቫላዶሊድ ላይ 4 ግቦችን አስቆጥሮ በባዶ ከመለየት በሚል አንድ ግብ አስተናግዷል። ሪያል ሶሴዳድ ቫሌንሺያን 1 ለምንም ሲያሸንፍ ኤልሼ እና ሪያል ቤቲስ ያለምንም ግብ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። ከትናንት በስትያ ኃያሉ ሪያል ማድሪድ ማላጋን የረታው አንድ ግብ ብቻ በማስቆጠር ነበር።
ሪያል ማድሪድ 70 ነጥብ ይዞ የደረጃ ሠንጠረዡን እየመራ ይገኛል። አትሌቲኮ ማድሪድ በ67 ነጥብ ይከተለዋል። ባርሴሎና 66 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ደረጃውን በመልቀቅ ወደ ሶስተኛ ዝቅ ብሏል።
በጣሊያን ሴሪኣ ደግሞ የደረጃ ሠንጠረዡን ጁቬንቱስ በ75 ነጥብ እየመራ ነው። ትናንት ጌዎናን 1 ለ ባዶ አሸንፏል። ሮማ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት በ58 ነጥብ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ናፖሊ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል፤ 55 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሠንጠረዡ ሶስተኛነትን የሙጥኝ ብሏል።
ትናንት ኢንተር ሚላን ቬሮናን 2 ለዜሮ አሸንፏል። ከትናንት በስትያ ኤስ ሚላን በፓርማ 4 ለ 2 ተቀጥቷል። ላትሲዮ ካግሊያሪን 2 ለ ባ፤ ሊፎርኖ ቦሎኛን 2 ለ 1 አሸንፈዋል። ፊዮሬንቲና ቺዬቮን እንዲሁም ሳሱዎሎ ካታኒያን 3 ለ 1 ሸኝተዋል።
የጁቬንቱሱ ካርሎስ ቴቬዝ 15 ከመረብ ባረፉ ኳሶች ሴሪ ኣውን በኮከብ ግብ አግቢነት እየመራ ይገኛል።የፊዮሬንቲናው ጁሲዬፔ ሮሲ በ14 ግቦች ሲከተለው፤ የኢንተር ሚላኑ ሮድሪጎ ፓላቺዮ በ13 ግቦች ይሰልሰዋል።
አሁን ደግሞ አትሌቲክ ነክ ስፖርታዊ ዘገባዎችን ነው የምናቀርብላችሁ። ከኢትዮጵያ እንጀምራለን። 15ኛው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ስፖርታዊ ፉክክር ለአራተኛ ጊዜ በባሕር ዳር ከተማ ትናንት ተከፍቷል። ውድድሩ እስካሁን አዲስ አበባ ላይ ለሁለት ጊዜያት የተካሄደ ሲሆን፤ አዳማ ላይ አንድ ጊዜ ተሰናድቷል። በ17 የስፖርት አይነቶች በሚካሄደው ውድድር ወደ 5ሺህ የሚጠጉ ስፖርተኞች እንደሚሳተፉ ተነግሯል።
የሶቺ ፓራሊምፒክ ውድድር ትናንት ተጠናቋል። ሩስያ ምንም እንኳን በዩክሬኗ ልሳነ ምድር ክሬሚያ ውዝግብ የፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ ብትገባም በአካል ጉዳተኞች የሚካሄደው የሶቺውን ፓራሊምፒክ ግን በደማቅ ሁናቴ እንዳጠናቀቀች ተዘግቧል።
በኒውዮርኩ የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር ኬኒያዊው ጌኦፍሬይ ሙታይ በ1 ሠዓት ከ00 ነጥብ 50 ሠከንድ በማሸነፍ አንደኛ ሲወጣ፤ የሁለት ጊዜያት የኦሎምፒክ ባለድሉ ትውልደ ሱማሌው የብሪታንያ ሯጭ ሞ ፋራሕ ሁለተኛ ለመውጣት ችሏል። ሞ ፋራሕ በፉክክሩ ወቅት የቀኝ እግሩ ከግራው ጋር ተደናቅፎ ቢወድቅም ውድድሩን በ 1 ሰዓት ከ61 ነጥብ 07 ሠከንድ በማጠናቀቅ ቆራጥነቱን አስመስክሯል። ሞ ሩጫውን በሁለተኛነት ካጠናቀቀ በኋላ በተሽከርካሪ ወንበር እገዛ እየተደረገለት ከሜዳ ወጥቷል። ኢትዮጵያውያኑ አስቻለው ንጉሤ እና መንግስቱ ታቦር አምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃን ለማግኘት ችለዋል። በእዚህ ፈጣን በተባለለት የሩጫ ፉክክር ጀርመናዊው አርኔ ጋቢዩስ በስምንተኛነት አጠናቆዋል።
ፍርሙላ 1 በመባል የሚታወቀው የመኪና ሽቅድምድም የዘንድሮ ፉክክር ትናንት አውስትራሊያ ውስጥ የተከፈተ ሲሆን፤ ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ በመርሴዲስ መኪና አንደኛ ሆኖ አጠናቆዋል። የአራት ጊዜ የፎርሙላ አንድ ባለድሉ ሌላኛው ጀርመናዊ ሰባስቲያን ፌትል በትናንቱ ሽቅድምድም በ18ኛነት ጨርሷል። የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ፉክክር ዓመቱን ሙሉ በተለያዩ የዓለማችን ሃገራት የሚካሄድ ሲሆን፤ አሸናፊው የሚለየው መጨረሻ ላይ በሰበሰበው ውጤት ይሆናል።
በሜዳ ቴኒስ ጨዋታ ሠርቢያዊው ኖቫክ ጆኮቪች ዋነኛ ተፎካካሪው የስዊዘርላንድ ተወላጁ ሮጀር ፌደረርን ትናንት ህንድ ውስጥ 2 ለ ዜሮ በሆነ አጠቃላይ ውጤት ማሸነፉም ታውቋል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አርያም ተክሌ