1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቀን 390 ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ ያቀናሉ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 1 2011

ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ ሰዎች ቁጥር በቀን 390 ገደማ መድረሱን የኖርዌይ የስደተኞች መርጃ ምክር ቤት አስታወቀ። ድርጅቱ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበራቸውን ከከፈቱ ጀምሮ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ መጓዛቸውን አስታውቋል። 

https://p.dw.com/p/36OQz
Grenze Äthiopien-Eritrea
ምስል NRC

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለሁለት አስርት አመታት ተዘግቶ የቆየ ድንበራቸውን ከከፈቱ በኋላ ባለፉት 30 ቀናት ብቻ ከ10 ሺሕ በላይ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ መሻገራቸውን የኖርዌይ የስደተኞች መርጃ ምክር ቤት አስታውቋል። ድርጅቱ ያወጣው ሐተታ እንደሚጠቁመው በቀን ድንበር የሚያቋርጡ ኤርትራውያን በመጀመሪያ አካባቢ ከነበረበት 53 ወደ 390 አሻቅቧል። የድርጅቱ የአፍሪቃ ቢሮ የኮምዩንኬሽን ኃላፊ ጄኖ ቴዎፊሎ "ሁሉም ለተመሳሳይ ዓላማ አይደለም ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙት። ወደ 83 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ከቤተሰቦቻቸው ለመገናኘት ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ ናቸው" ሲሉ አስረድተዋል። 

የኖርዌይ የስደተኞች መርጃ ምክር ቤት የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊ ስታይን ፓውስ ለ20 አመታት ገደማ ተለያይተው የቆዩ ቤተሰቦች ከደስታ እንባ ጋር ሆነው መቀላቀል መጀመራቸውን ተናግረዋል። ፓውስ "በርካታ ሰዎች በየቀኑ ድንበር እየተሻገሩ በመሆኑ በድንበር አካባቢ በሚገኙ ከተሞች የንግድ ልውውጥ እያደገ ነው" ብለዋል። 
ከኤርትራዋ ጋሽ ባርካ ተነስታ ወደ ኢትዮጵያ የተሻገረችው ሐረጓ ከቤተሰቦቿ በመገናኘቷ የተሰማትን ደስታ መቆጣጠር እንደተሳናት ለኖርዌይ የስደተኞች መርጃ ምክር ቤት ተናግራለች። በማይ አይኒ በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ለአስር አመታት የተለየችውን ባለቤቷን፣ ሶስት ልጆቿን እና ወዳጅ ዘመደቿን ያገኘችው ሐረጓ እንዳለችው ከቤተሰቦቿ ስትገናኝ ደጋግመው ተቃቅፈዋል፤ ለቅሶም ነበር። 

ለረዥም አመታት ተዘግቶ የቆየው ድንበር ለንግድ ሲከፈት ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ የሚደረገው ጉዞ ጭምር መነቃቃት ማሳየቱን የኖርዌይ የስደተኞች መርጃ ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል። የኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች እና ለኤርትራውያን ጎብኚዎች ሥራ መቀላጠፍ ጀምሯል። ድርጅቱ እንደሚለው ሸቀጥ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ድንበር አቋርጠው ወደ ኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ይተሙ ይዘዋል። 

Grenze Äthiopien-Eritrea
ምስል NRC

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ድንበር በይፋ የተከፈተው ከአንድ ወር በፊት መስከረም አንድ ቀን 2011 ዓ.ም. በዛላምበሳ እና ራማ በኩል ነበር። ድንበሩ ከተከፈተ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ከሚጓዙ ኤርትራውያን አብዛኞቹ በዚያው ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ጋር መቆየት አሊያም ወደ አውሮጳ እና ሌሎች አገሮች ከተጓዙ ቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀል እንደሚሹ የኖርዌይ የስደተኞች መርጃ ምክር ቤት ገልጿል። 

ጄኖ ቴዎፊሎ  "ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት በስደተኛ መጠለያ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ጋር ለመቀላቀል ነው። ቤተሰቦቻቸው ወደሚገኙባቸው ሌሎች አገሮች ለመሔድ የሚያቅዱም አሉ። በአውሮጳ እና በሌሎች ቦታዎች የሚኖሩ ቤተሰቦች ያሏቸው በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ለተወሰ ጊዜ ቆይተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር የመገናኘት ሐሳብ አላቸው። ሌሎች ደግሞ በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተሰቦቻቸውን ለመጎብኘት ከዚያም ለመመለስ ብቻ ድንበር የተሻገሩ ናቸው። ቤተሰቦቻቸውን ጎብኝተው ወደ ሥራቸው እና ማሳዎቻቸው መመለሳቸው ጥሩ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። 

Grenze Äthiopien-Eritrea
ምስል NRC

ባለፈው ወር የአውሮፓ ሕብረት የኤርትራ ውስጣዊ ነባራዊ ሁኔታ ባለመለወጡ እና ሐገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስናት ድንበር በመከፈቱ ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱ ኤርትራዉያን ቁጥር መጨመሩን አስታውቆ ነበር። የሕብረቱ ኮሚሽን እንዳለው ሁለቱ ሐገራት የአዋሳኝ ድንበሮቻቸዉን  ከከፈቱ ወዲሕ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ኤርትራውያን ቁጥር በፊት ከነበረዉ በአራት እጥፍ ጨምሯል። የአዉሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ድረ-ገፅ የጠቀሰዉ የትግራዩ የሽሬ ዞን-አስተዳደር እንዳስታወቀዉ 15 ሺሕ ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። ከነዚሕ መሐል ዘመድ ወዳጅ ለመጠየቅ እና ሸቀጦች ለመግዛት ድንበር የተሻገሩ መኖራቸውን መረጃው ጠቅሶ፤ አብዛኞቹ ግን እዚያው ኢትዮጵያ የሚቆዩ ናቸው ብሏል።

የኖርዌይ የስደተኞች መርጃ ምክር ቤት የአፍሪቃ ቢሮ የኮምዩንኬሽን ኃላፊ ጄኖ ቴዎፊሎ እንደሚሉት ድንበር የሚያቋርጡ ኤርትራውያን ቁጥር በመጪዎቹ ጊዜያት ይጨምራል የሚል ዕምነት አላቸው። ኃላፊው "በርካታ ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ መጓዛቸውን ይቀጥላሉ ብለን እንጠብቃለን። ለዚህም ነው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ወደ ኢትዮጵያ ለሚደርሱ ሰዎች ተጨማሪ እርዳታ እንዲያቀርብ የምናበረታታው" ሲሉ ተናግረዋል። የድርጅቱ መረጃ እንደሚጠቁመው ከ174,000 በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ይገኛሉ።

እሸቴ በቀለ