በአዲስ አበባ የበግ፣ ፍየል እና ሠንጋ ዋጋ እጅግ አሻቅቧል
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 15 2014ለበዓሉ ማድመቂያ እንደ ወትሮው የቀረቡት የበግና ፍየል ዋጋም የሚቀመስ አይመስልም። የፍየል አነስተኛ የመሸጫ ዋጋ ደግሞ ከ3 ሺህ 500 ብር እንደሚጀምር፤ ከፍተኛ ዋጋው ደግሞ እስከ 15 ሺህ ብር እንደሚጠራ በስፍራው የሚገኙ ነጋዴዎች ተናግረዋል። አቅራቢ ነጋዴዎች እንደሚሉት የአገሪቱ ወቅታዊ የፀጥታ ተግዳሮቶች፤ የእንስሳት መኖ እና የመጓጓዣ ወጪዎች ከፍ ማለት ለአቅርቦቱ ማነስ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። የአዲስ አበባው ዘጋቢችን ሥዩም ጌቱ የቁም እንስሳት ገበያዎቹን ገብኝቶ ነበር።
መዳረሻችንን በሰሜን አዲስ አበባ አዲሱ ገበያ ሸጎሌ አካባቢ በሚገኘው ትልቁ የቁም እንስሳት መገበያያ ስፍራ አድርገናል። ከትልቅ እስከ ትንሽ ደግሞም መካከለኛ ደረጃ ያላቸው ከወይፈን እስከ ግዙፍ ሰንጋ መገበያያ ስፍራዎቹን አጨናንቀውታል። ሻጭ እና ሸማቾች እንደሚሉት የአንድ በሬ ዋጋ እስከ 130 ሺህ እና 150 ሺህ ዘልቋል። አነስተኛ የቅርጫ ከብት ደግሞ ከ30 ሺህ እስከ 80 ሺህ ይሸጣል። ለዓመት በዓሉ ለቅርጫ ከብት ግዢ ፍለጋ ላይ ያሉትን አንድ ሰው እዚሁ ተዋወኩአቸው። በገበያው ለቅርጫ የሚሆን ከብት ለመግዛት ቢገኙም የቁም ከብቶች ካለፈው ዋጋቸው መጨመራቸውን ተናግረዋል።
አቶ ዳዊት አበበ ነጋዴ ናቸው። ለፋሲካ በዓልም በርከት ያሉ የደለቡ ሰንጋዎችን ይዘው በዚሁ ገበያ ታድመዋል። የፀጥታ ችግር፤ የእንስሳት መኖ መወደድ እና የመጓጓዣ ዋጋ ከፍ ማለት ለጭማሪው ሰበብ መሆኑን ገልጠዋል። ከጅሩ የመጡ አንድ ነጋዴ 18 ከብቶችን ይዘው ገበያ ሥፍራ ቢገኙም ወኪላችን ገበያውን በጎበኘበት ወቅት አንድም ከብት ሳይሸጡ በተስፋ እየተጠባበቁ እንደነበር ገልጠዋል። በዚሁ የቁም እንስሳት ግብይት አቅራቢያ በሚገኘው የበግ እና ፍየል ገበያ የተገኙ ነጋዴ አንድ ፍየል አነስተኛው ከ3 ሺህ 500 ብር እንደሚጀምር ከፍተኛ ዋጋው ደግሞ እስከ 15 ሺህ እንደሚጠራ ተናግተዋል። እንደ ፍየል ሁሉ የበግ ዋጋም ከትንሹ 4000 ሺህ እስከ 15 ሺህ ብር ገደማ ዋጋ ተቆርጦላቸዋል። የበግ ፍየል ዋጋ መናሩ ሸማቹን እጅግ አማሯል። ንቡረ እድ ግዛው በዚሁ ገበያ በእጥፍ በጨመረው የዋጋ ንረት ሲያማርሩ ተመልክተናቸዋል።
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ