1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ ታጣቂዎችን የማቋቋም ዕቅድ

ዓርብ፣ ነሐሴ 25 2010

የኢትዮጵያ መንግሥት ከውጭ የተመለሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚረዳ ፕሮጀክት መንደፉን አስታወቀ :: በመጭው እሁድም ለመጀመሪያዎቹ 270 ያህል ተመላሽ ታጣቂዎች የመጠለያ እና የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ መስጠት እንደሚጀመር አቶ ፍጹም ገልጸዋል::

https://p.dw.com/p/346vx
Symbolbild - Afrikanische Miliz
ምስል Getty Images/AFP/A. Pungovschi

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ በተለይ ለዶቼቨለ እንደገለጹት በፌደራል ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በኩል የተደራጀው ይኸው የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ትጥቅ የሚፈቱ የተቃዋሚ ድርጅቶች አባላት የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ እና በዘላቂነትም አማራጭ የገቢ ምንጭ አግኝተው ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው በሰላም ኑሮዋቸውን የሚመሩበት ሥልት ተነድፏል :: በመጭው እሁድም ለመጀመሪያዎቹ 270 ያህል ተመላሽ ታጣቂዎች የመጠለያ እና የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ መስጠት እንደሚጀመር አቶ ፍጹም ገልጸዋል::  

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መቀመጫቸውን ውጭ አገር ያደረጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትጥቃቸውን በመፍታት በሃገር ውስጥ ሰላማዊ ትግል በማካሄድ የተጀመረውን የዲሞክራሲ እና ለውጥ ሂደት እንዲያጠናክሩ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል :: በትጥቅ ትግል የሚንቀሳቀሱ አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ድርጅቶችም አሁን በአገሪቱ የተፈጠረውን ምቹ የለውጥ እንቅስቃሴ በመጠቀም ሃገር ውስጥ ገብተው ሰላማዊ የፖለቲካ ተሳትፎ በማድረግ የለውጡ አጋዥ ለመሆን አዎንታዊ ምላሻቸውን እየሰጡ ይገኛሉ :: ድርጅቶቹ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አብረው ለውጡን ከዳር እንደሚያደርሱም ሲገልጹ ቆይተዋል :: በመንግሥት በኩልም ከውጭ የተመለሱ እና የሚመለሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚረዳ ፕሮጀክት መንደፉ ይፋ ሆኗል :: አቶ ፍጹም አረጋ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ለዶቼቨለ እንደገለጹት ትጥቅ የማስፈታቱ ስራ ከተከናወነ በኋላ ከሕብረተሱቡ ጋር ተቀላቅለው ሰላማዊ ኑሮ የሚጀምሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በሶስት ምዕራፎች የሚከናወኑ ዘላቂ ድጋፎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በኩል በተደራጀው የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ ነው::

Afrika Bildergalerie Kindersoldaten im Süd-Sudan
ምስል DW/A. Stahl

ትጥቅ ለሚፈቱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት የሰራዊት አባላት በዘላቂነት ሰላማዊ ኑሮዋቸውን ለማመቻቸት ከአስቸኳይ ድጋፍ ጀምሮ መረጃቸውን በተገቢው መንገድ የማጥናቀር ስራ እንደሚካሄድም ታውቋል::  በመጭው እሁድም ለመጀመሪያዎቹ 270 ያህል ተመላሽ ታጣቂዎች የመጠለያ እና የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ መስጠት እንደሚጀመር ነው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ ያስታወቁት::

የኢትዮጵያ መንግሥትን በኃይል ለመጣል የትጥቅ ትግል ሲያራምዱ ከነበሩ የተለያዩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ላለፉት አምሥት ወራት ሰፊ ውይይት ድርድር እና ስምምነት ሲያካሂድ ቆይቷል :: ለስምምነቱ በጎ ምላሽ ከሰጡ መካከል በተለይም በአስመራ የሚገኙ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ እና ለሎችም የተቃዋሚ ኃይላት በአገሪቱ በተፈጠረው ምቹ የለውጥ እንቅስቃሴ እና የፖለቲካ ምህዳሩ በመስፋቱ ከሕዝቡ ጎን ተሰልፈው ሰላማዊ ትግል ለማድረግ መወሰናቸውን አስታውቀዋል :: ከነዚህም መካከል የጦር መሳሪያ ትጥቅ ፈተው ሃገር ውስጥ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ የወሰኑት የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች እና አባላት የአቀባበል መርሃ ግብር በተለያዩ አካባቢዎች መዘጋጀቱ ታውቋል ::

 

እንዳልካቸው ፈቃደ

አርያም ተክሌ