1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኤርትራ የዴሞክራሲ ለዉጥ ይደረግ ይሆን ?

ሰኞ፣ መስከረም 7 2011

የተለያዮ ዴፕሎማቶችና የብዙኃን መገናኛዎች የሰመረ ያሉት የኤርትራና የኢትዮጵያ የወዳጅነት ግንኙነት በኤርትራ ለዴሞክራሲንና ለገደብ የለሹ ብሔራዊ ዉትድርና ተሃድሶ ያመጣል ሲሉ መናገራቸዉ ህልም ነዉ ሲል መቀመጫዉን ለንደን ብሪታንያ ያደረገዉ የኤርትራ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ገልፆአል።

https://p.dw.com/p/352fl
Eritrea Präsident Isaias Afwerki
ምስል Eritrea Minister of Information/Y.G. Meskel

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የጀመረችዉን ሰላም እንደግፋለን

ኢትዮጵያ ና ኤርትራ 20 ዓመት ያስቆጠረ ጠብ እና ዉዝግባቸዉን አስወግደዉ መልካም ግንኙነት ከጀመሩ በኋላ በኤርትራ ዉስጥ የዴሞክራሲ ለዉጥ እንዲሁም ሃገሪቱ የምታራምደዉ የብሔራዊ ዉትድርና አገልግሎት ተሃድሶ ይደረግለት ይሆን ሲል? ለኤርትራ ሕዝቦች ሰብዓዊ መብት መቆሙን የሚናገረው « Human rights concern Eritrea » የተባለው ድርጅት ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እና ዴፕሎማቶች ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ከተወዳጁ በኋላ በኤርትራም ለውጥ ይመጣል የሚል ተስፋ እንዳላቸዉ ቢናገሩም እስካሁን ግን የኤርትራዉ ፕሬዚዳንት ለሕዝባቸዉ ያሉት የለም ሲል መቀመጨዉን ብሪታንያ ያደረገዉ ይኽው ድርጅት ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።

Äthiopischer Ministerpräsident Abiy Ahmed beim Staatsbesuch in Eritrea
ምስል Twitter/@fitsumaregaa

የተለያዮ ዴፕሎማቶችና የብዙኃን መገናኛዎች የሰመረ ያሉት የኤርትራና የኢትዮጵያ የወዳጅነት ግንኙነት በኤርትራ ዴሞክራሲንና ለገደብ የለሹ ብሔራዊ ዉትድርና ተሃድሶ ያመጣል ሲሉ መናገራቸዉ ህልም ነዉ ሲል መቀመጫዉን ለንደን ብሪታንያ ያደረገዉ የኤርትራ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በእንግሊዘኛ መጠሪያው „Human rights concern“ Eritrea ዋና ፀሐፊ ኤልዛቤት ጭሮም ለ«DW» ተናግረዋል።

« ይህን ስንል ምን ማለታችን ነዉ የኢትዮጵያና የኤርትራ በኩል እየተፈፀመ ግንኙነት ጥሩ ሆኖ ሳለ በኤርትራ በኩል ግን ድርድሩ እየተፈፀመ ያለዉ በአንድ ሰዉ ብቻ ነዉ። …»

የኤርትራ ሕዝብ ወንድም ከሆነዉ ሕዝብ ጋር የጀመረዉን ሰላም እንደግፋለን ያሉት የድርጅቱ ተጠሪ በሁለቱ ሃገሮች የድንበር ጦርነት ወቅት ለተጎዳዉ የኤርትራ ሕዝብም ቁስሉ እንዲድን ፕሬዚደንቱ ሕዝቡን ሊያነጋግሩት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። እንደ ኤርትራ ሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ምዕራባዉያን ዴፕሎማቶች በኤርትራ ለዉጥ እንደሚመጣ ተስፋ አለን ቢሉም ለራሳቸዉ ጥቅም ነዉ ባይናቸዉ።

Karte Eritrea Djibouti DEU
ምስል DW

«ምዕራባዉያኑ ችግራቸዉ የስደተኛ ጉዳይ ብቻ ነዉ። ወደ ሃገራቸዉ የሚመጡ  ስደተኞችን ለማስቆም ሲሉ ለራሳቸዉ ጥቅም ነዉ…»

የኤርትራ መንግሥት ወጣቱን በገደብ የለሽ ብሔራዊ አገልግሎት ይይዝ የነበረዉ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ የድንበር ዉዝግብ አልተፈታም በሚል ነበር ያሉት ኤልሳቤት ጭሮም በዉትድርና የተያዙት ወጣቶች እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።

በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ 20 ዓመት ያስቆጠረ ጠብ እና ዉዝግባቸዉን ማስወገዳቸዉን ዩናይትድ ስቴትስ እንደምትደግፍ የሃገሪቱ የአፍሪቃ ጉዳይ ረዳት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቲቦር ናጊይ ለሃገሪቱ ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። ቲቦር ናጊይ እንደነገሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም ማስፈናቸዉ የሚበረታታ ቢሆንም የኤርትራ የሠብአዊ መብት ይዞታ የዋሽግተን እና የአስመራን ግንኙነት ለማሻሻል እንቅፋት ሆኗል።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ