1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወደ ብሪታንያ ለመሻገር የሞከረ ስደተኛ በመኪና ተገጭቶ ሞቷል

ሰኞ፣ ጥር 15 2009

ወደ ብሪታንያ ለመሻገር የሞከረ አንድ ኢትዮጵያዊ  ስደተኛ በፈረንሳይ የድንበር ከተማ ካሌ በመኪና ተገጭቶ መሞቱ ተሰማ፡፡ ስደተኛው ለሞት የበቃው ባህር አቋርጠው ወደ ብሪታንያ የሚሄዱ የጭነት መኪናዎች በሚያዘወትሩት አውራ ጎዳና ላይ ነው፡፡ 

https://p.dw.com/p/2WGeH
Frankreich, orthodoxes Weihnachten in Calais
ምስል Getty Images/C. Court

mmt Ethiopian Migrant run down in Calais (FINAL) - MP3-Stereo

በስም ያልተጠቀሰው የ20 ዓመት ኢትዮጵያ ወጣትን ለሞት የዳረገው አደጋ የተከሰተው ቅዳሜ ጥር 13 ጠዋት እንደነበር ከአካባቢው የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አደጋው የደረሰው ወደ ብሪታንያ የሚጓዙ የጭነት መኪናዎች ወደ ካሌ ወደብ ለመግባት በሚጠቀሙበት አውራ ጎዳና ላይ ነበር፡፡ 

ወደ ብሪታንያ መጓዝ የሚፈልጉ ስደተኞች በእነዚህ የጭነት መኪናዎች ላይ ለመንጠላጠል ሲሞክሩ ተመሳሳይ አደጋዎች ከዚህ በፊት ሲከሰቱ ቆይተዋል፡፡ በጎርጎሮሳዊው 2016 ህይወታቸውን ካጡ 14 ስደተኞች መካከል ዘጠኙ በግጭት የሞቱት የቅዳሜው አደጋ በደረሰበት አውራ ጎዳና ላይ እንደነበር የፈረንሳይ ጋዜጦች ዘግበዋል፡፡ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን አስጠልሎ የነበረውና የ“ካሌ ጫካ” ተብሎ የሚታወቀው የስደተኞች መጠለያ በይፋ ከተዘጋ በኋላ እንዲህ ዓይነት አደጋ ሲደርስ የቅዳሜው የመጀመሪያ ነው ተብሎለታል፡፡

የካሌ ስደተኞች መጠለያ በፈረንሳይ መንግስት እንዲፈርስ ከተደረገ በኋላ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሌሎ ሀገር ስደተኞችም በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ወደሚገኙ ጊዜያዊ የስደተኞች ማቆያ ተወስደው ነበር፡፡ በቅዳሜው አደጋ ህይወቱ ያለፈው ኢትዮጵያዊውም ከእነዚህ ማቆያዎች ወደ አንዱ ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ተወስዶ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በዚያ የቆየ እንደነበር በፈረንሳይ የሚገኙ ስደተኞች ይናገራሉ፡፡ 

አደጋው ሲደርስ በቦታው የነበረው አብዲ በከር ስለቅዳሜው ሁነት እንዲህ ያስረዳል፡፡ 

“እኔ መንገድ ላይ የሆነ ድልድይ ስር ተቀመጬ እያየሁ ነበር፡፡ እርሱ እንደ ድንገት ወደ እንግሊዝ የሚሄድ መኪና ስር ገብቶ፣ ተንሸራትቶም ይሁን እንጃ መንገድ ላይ ወደቀ፡፡ ከኋላ ጎማው ረገጠው፡፡ በቃ ሞተ” ይላል አብዲ ከሀዘኑ ጋር እየታገለ ለዶይቸ ቨለ በሰጠው ቃለ ምልልስ፡፡ 

ሟቹ ስደተኛ ወደ ብሪታንያ ለመሻገር መቆያ ጣቢያውን ጥሎ ወደ ካሌ ከመጣ በኋላ ለሶስት ሳምንት አብረው እንደቆዩ አብዲ ይናገራል፡፡ ሌሎች አራት ኢትዮጵያውያንም ከእነሱ ጋር በፈረሰው የ“ካሌ ጫካ” የስደተኞች መጠለያ አንድ ጥግ እንደከረሙ ያወሳል፡፡ አብረዋቸውም በቁጥር 20 የሚጠጉ ኤርትራውያን፣ ሱዳናውያን እና አፍጋኒስታናውያን እንደነበሩ ያስታውሳል፡፡ ሟቹ ለሳምንት ያህል በፖሊስ ጣቢያ ታስሮ እንደነበር እና በስተኋላም እንደተፈታ ይገልጻል፡፡

Frankreich Eurotunnel Flüchtlinge LKW
ምስል Reuters/P. Rossignol

በእስሩ ወቅት በዕድሜው ምክንያት አለመግባባቶች ተከስተው እንደነበር አብዲ ያስረዳል፡፡ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ወጣቶች ወደ እንግሊዝ ሲወሰዱ ያዩ ስደተኞች ዕድሜያቸውን ቀንሰው ያስመዘግባሉ፡፡ ሟቹ በፖሊስ ጣቢያ በነበረ ጊዜ ዕድሜው 17 መሆኑን ቢናገርም በግዴታ 20 ተብሎ ተመዝግቦበት እንደነበር አብዲ በቅሬታ ያስታውሳል፡፡

የትውልድ ሀገሩ ከወሎ በመሆኑም “ፖለቲካዊ ችግር የሌለበት አካባቢ ነው” በሚል ወደ ሀገሩ እንዲመለስ ግፊት ተደርጎበታል ይላል፡፡ ሟቹ ኢትዮጵያ በነበረበት ወቅት የመከላከያ ሰራዊት አባል እንደነበር አብዲ ይናገራል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ወደ እንግሊዝ ለመግባት ያገኘውን “ማንኛውም ዕድል እንደሚጠቀም” ሲናገር እንደነበርም ይገልጻል፡፡

አብዲም ሆነ ሌሎች በካሌ የነበሩ ስደተኞች ሟቹን ኢትዮጵያዊ የሚያስታውሱት ከራሱ በላይ ሌሎችን ለመርዳት ብርቱ ጥረት የሚያደርግ ሰው እንደነበር ነው፡፡ ሜዲትራንያን ባህርን ሲሻገሩ ከሟቹ ጋር እንደተዋወቁ የሚናገረው ኡመር ሃጆ በዚያ አስቸጋሪ ጉዞ እንኳ የሟቹ እርዳታ ከፍተኛ እንደነበር ያስታውሳል ፡፡ 

“በሕይወቱ ላይ እንዳየሁት መጀመሪያ ለሰው ነው ቦታ የሚሰጠው፡፡ ባህር ላይ አብረን ነው የመጣነው፡፡ እኛ ከህጻናት ጋር 637 ሰው ነበርን፡፡ [ለጉዞ] ስንነሳ ከደላሎቹ ጋር ተስማምቶ፤ ለሰው ውሃ፣ ምግብ፣ በሁሉ ነገር ቆሞ ህዝባችንን እየረዳ የመጣ ልጅ ነው፡፡ መርከቧ የተሰነጠቀች መርከብ ነበረች፡፡ ሁሉም ሰው ከዚያ የተሰነጠቀች መርከብ ላይ እወርዳለሁ ብሎ ሲሮጥ እርሱ ራሱን ሰጥቶ ምንም ሳይፈራ እስከመጨረሻ 637 ሰውን ከሰዎች ጋር ተባብሮ፣ ከመርከብ ወደ መርከብ አሸጋግሮ፣ ከእግዚያብሔር በታች እንደዚያ አስወጣን፡፡ እስከመጨረሻው እዚህ አስከሚመጣ በደረሰበት ቦታ ሰው የመርዳት ፍላጎት አለው” ይላል የ“ካሌ ጫካ” ከመፍረሱ በፊት በዚያም አብሮት የቆየው ኡመር፡፡   

በካሌ ስደተኞች ዘንድ ታዋቂ የነበረው ሟች አስክሬኑ በፖሊስ ዘንድ ይቆይ ወይም ወደ ሀገር ቤት ይላክ እንደማያውቁ አብረውት የነበሩ ስደተኞች ይናገራሉ፡፡ የእርሱን ዕጣ ካዩ በኋላ የድንበር ከተማይቱን ካሌን ለቅቀው ለጊዜውም ቢሆን ወደ ፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ሄደዋል፡፡   

 

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ