1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጉጂ ዞን ድርቅ እና የፀጥታ ችግር ያስከተለው የኑሮ ውድነት

ቅዳሜ፣ መጋቢት 10 2014

የፀጥታ ችግር እና ሰላም እጦት ባለባቸው የጉጂ ዞን ህብረተሰቡ ለከፋ የኑሮ ውድነትና እንግልት እተጋለጠ መሆኑን ነዋሪዎች እና ባለስልጣናት ገለፁ፡፡ በዞኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት በድርቅ ሲሞቱ የፀጥታ ችግር ያፈናቀላቸው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ደግሞ ወደ ከተሞች ተሰደው አስከፊ ህይወት ለመምራት መገደዳቸውም ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/48jHJ
INFOGRAFIK Äthiopien: Konfliktreiche Grenzregion -DE

በጉጂ ዞን ድርቅ እና የፀጥታ ችግር ያስከተለው የኑሮ ውድነት እና የነዋሪው ምሬት

የፀጥታ ችግር እና ሰላም እጦት ባለባቸው የጉጂ ዞን ህብረተሰቡ ለከፋ የኑሮ ውድነትና እንግልት እተጋለጠ መሆኑን ነዋሪዎች እና ባለስልጣናት ገለፁ፡፡ በዞኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት በድርቅ ሲሞቱ የፀጥታ ችግር ያፈናቀላቸው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ደግሞ ወደ ከተሞች ተሰደው አስከፊ ህይወት ለመምራት መገደዳቸውም ተገልጿል።

አቶ ኃይሌ ሜንጎ በጉጂ ዞን የነጌሌ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ እሳታቸው ከልጅነት እስከ እውቀት የኖሩባት ከተማዋ አሁን አሁን የስደተኞች መናሃሪያ መስላለች ነው የሚሉት፡፡ ምክኒያት ስባሉም በአከባቢው ከሚገኙ ወረዳዎች እና ቀበሌያት በድርቅ እና በፀጥታ ችግር የሚፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ያሏቸው ተፈናቃዮች በአከባቢው ብቸኛ መሸሸጊ ያደረጉት ይህቺን ከተማ ነው፡፡ የሰባት ልጆች አባት እና የስምንት ቤተሰቦቻቸው አስተዳዳሪ አቶ ኃይሌ ይህ ሁሉ ያባባሰው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ህይወትን ለመግፋት አታካች እንዳደረገባቸውም ያብራራሉ፡፡ 

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን አምስት ወረዳዎች በከፊልና ሙሉበሙሉ መንግስት ኦነግ ሸነ ባለው ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ከአንድ ወር በፊት ነዋሪዎች እና ባለስልጣናትን ዋቢ አድርገን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በዚህ ላይ ለውጥ ስለመኖር አለመኖሩ የተጠየቁት የዞኑ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሓንስ ኦልኮ የዞኑ ዋና መንገዶች ላይ አንቅስቃሴ እንዳይገታ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ጥበቃ ቢያደርጉም ከዚህ በፊት በታጣቂ ቡድኑ በተያዙት ስፍራዎች ላይ ለውት የለም ባይ ናቸው፡፡ 

እንደ ኃላፊው ገለጻ ጉሚየልደሎ ወረዳ ሙሉ በሙሉ፣ ሊበን ወረዳ ከአምስት ቀበሌዎች በስተቀር ሁሉም፣ ዋደራ ወረዳ ከከተማ ውጪ ያሉ የገጠር ቀበለያት፣ ሰባ ቦሩ እና ጎሮ ዶላ በተባሉ ወረዳዎችም እንዲሁ በርካታ ቀበሌያት ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ ናቸው፡፡ በመሆኑም ከነዚህ አከባቢ የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ከፍተኛ የህልውና አደጋ ተጋርጦባቸዋልም ነው ያሉት፡፡ 

በዞኑ ያለው የፀጥታ ችግሩ ምርት እና አቅርቦቶችን ለማጓጓዝ ፈታኝ መሆኑ ከሌላው አገሪቱ ክፍል በባሰ የከፋ የዋጋ ንረት የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም እንዳመነመነውም አክለዋል፡፡ በዚህ ላይ ተጨመሮ በአከባቢው በተከሰተው የድርቅ ሁኔታም ህብረተሰቡ ባዶ እጅ እቀረ ነው ብለውታል፡፡ 

የውሃ ችግሩም ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ዮሓንስ ድርቁ በዞኑ ወደ ዘጠኝ ወረዳዎች መስፋፋቱም ከዚህ ቀደም ረጂ የነበረው ማህበረሰብ ለእርዳታ እጁን እንዲዘረጋ አስገድዶታልም ብለዋል፡፡

ስዩም ጌቱ 

ታምራት ዲንሳ