ቻይና ከኢትዮጵያ የሸመተችው ቡና በ196 በመቶ ጨምሯል?
ዓርብ፣ ሐምሌ 22 2014ቻይና ባለፈው ዓመት ከኢትዮጵያ የሸመተችው ቡና በ196 በመቶ መጨመሩን በአገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ዉ ፔንግ ባለፈው ሳምንት ገልጸዋል። ባለሥልጣኑ በተረጋገጠ የትዊተር ገጻቸው ሐምሌ 15 ቀን 2014 ባሰፈሩት አጭር መልዕክት ቻይና በ2020 እና በ2021 ከኢትዮጵያ የሸመተችውን የቡና መጠን በዝርዝር አላቀረቡም። በቻይና ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል የጠቀሱት የዕድገት መጠን ግን የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ካጠናቀረው መረጃ የሚጣጣም አይደለም።
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ጸሀፊ አቶ ግዛት ወርቁ "በ2013 ቻይና ከኢትዮጵያ የገዛችው የቡና መጠን 8 ሺህ 214 ቶን ነው። ከዚያ በፊት በ2012 ያለው ወደ 4 ሺህ 200 ቶን ነው የገዛችው። ዘንድሮ እስከ ሰኔ 30 ባለው የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር መሠረት ቻይና ከኢትዮጵያ የገዛችው የቡና መጠን 11 ሺሕ 28 ቶን ነው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የቡና ላኪዎች ማህበር መረጃ መሠረት በ2013 ቻይና ከኢትዮጵያ የገዛችው ቡና መጠን ከ2012 ጋር ሲነጻጸር በ96 በመቶ ገደማ ጨምሯል። የዘንድሮው ከ2013 ከተወዳደረ ደግሞ ጭማሪው በ34 በመቶ ገደማ ነው።
የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር በ2013 ወደ ቻይና የተላከው ቡና መጠን 8 ሺህ 214 ቶን ገደማ መሆኑን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። አቶ ሻፊ እንዳሉት ኢትዮጵያ በ2013 ወደ ቻይና ከላከችው ቡና ያገኘችው 35.5 ሚሊዮን ዶላር ነው። ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በ2014 በቻይና ገበያ ከሸጠችው ቡና 65.3 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች።
አማላዩ የቻይና ገበያ
ኢትዮጵያ ወደ ቻይና ገበያ የምትልከው ቡና መጠን ዉ ፔንግ እንደ ጠቀሱት ባይሆንም በየዓመቱ ማደጉን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር እና የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ጸሀፊ አቶ ግዛት ወርቁ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። የቻይና ገበያ የኢትዮጵያ ቡና ላኪ ማህበር አባላትም በጉጉት የሚመለከቱት ነው።
"የቻይና የቡና ፍጆታ በዓመት በ16 እስና 17 በመቶ እያደገ ነው። ይኸ በአራት አምስት አመት ውስጥ በእጥፍ ያድጋል" የሚሉት የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ጸሀፊ አቶ ግዛት ወርቁ "ለኢትዮጵያ ቡና ሽያጭ የቻይናን ገበያ ሁሌም አሰፍስፈን ማየት አለብን" ሲሉ አስረድተዋል።
ቻይናውያን በሻይ ጠጪነታቸው አገሪቱም በሻይ ባህል እና ምርት የሚታወቁ ናቸው። የቻይና አፍሪካ አማካሪ ተቋም መሥራች እና ዳይሬክተር አቶ አሌክሳንደር ደምሴ "ቻይና አሁንም ሻይ ጠጪ አገር ነች፤ ወደፊትም ሻይ ጠጪ አገር ነው የምትሆነው። አሁን ግን በአኗኗር ለውጥ የተነሳ በትልልቅ ከተማዎች በተለይ ደግሞ በወጣት ተጠቃሚዎች የተነሳ ቡናም በጣም ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል" ሲሉ የኢትዮጵያውያን ቡና ላኪዎችን ቀልብ የሚስብ ገበያ ከወደ ቻይና ብቅ ማለቱን ያስረዳሉ።
አቶ አሌክሳንደር እንደሚሉት በአገሪቱ ለታየው የቡና መጠጣት ባህል ዕድገት የአሜሪካው ስታር ባክስ ኩባንያ ከፍ ያለ ሚና ተጫውቷል። "ቻይና ውስጥ ትልቁን የቡና ካፌዎች መረብ የዘረጋው የአሜሪካው ስታር ባክስ ኩባንያ ነው። በቻይና የስታር ባክስ እንደዚህ ማደግ ቡና ላይ ያለውን ትኩረት በጣም ከፍ ለማድረግ ችሏል" የሚሉት አቶ አሌክሳንደር የኢትዮጵያን ቡና ለማስተዋወቅ የተደረገው ጥረትም በጥቂቱም ቢሆን ፍሬ እያፈራ ለመሆኑ እምነታቸው ነው። "በእርግጥ እንደ ጀርመን፣ አሜሪካ ወይም እንደ ሌሎች የኢትዮጵያን ቡና የሚገዙ የታወቁ አገሮች ባይሆንም መንገዱ በደንብ እየተከፈተ እየመጣ ነው። ወደ ፊትም በጣም ብዙ ዕድገት የምናይበት አንድ ሥፍራ ነው ብለን እንገምታለን" ብለዋል።
ከቻይና ገበያ "ግዙፍነት" አኳያ ኢትዮጵያ የላከችው የቡና መጠን በቂ አይደለም የሚል አቋም ያላቸው አቶ ግዛት እስካሁን የታየውን ዕድገት "ጥሩ" ይሉታል። ለዚህም ከ2012 እስከ 2014 ባሉት ዓመታት የታየውን ዕድገት በማሳየት ያነሳሉ። ዋና ጸሀፊው እንደሚሉት ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያ ቡና በቻይና የሚሸጥበት የዋጋ ተመን ዕድገት አሳይቷል።
ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ቡናቸውን ወደ ቻይና ለመላክ በኢትዮጵያ ጉምሩክ እና በቻይና አቻው መካከል በተዘረጋ ሥርዓት መመዝገብ አለባቸው። የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎችም አሉ። "ያልተመዘገቡ እና ወደ ቻይና ገበያ ቡና መላክ የማይችሉ ኩባንያዎች አሁንም አሉ። ብዙዎቹ ግን ተመዝግበው እየላኩ ነው" ሲሉ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ጸሀፊ አቶ ግዛት ወርቁ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
በቻይና ገበያ የኢትዮጵያ ቡና የሚሸጥበት የዋጋ ተመን ሌላው የላኪዎችን ቀልብ የሚገዛ ጉዳይ ነው። "በአማካኝ ቻይና ለአንድ ቶን የኢትዮጵያ ቡና የከፈለችው 5 ሺህ 420 ዶላር ነው" የሚሉት አቶ ግዛት አሜሪካ ለአንድ ቶን በአማካኝ 6 ሺህ 140 ዶላር እንደከፈለች አስረድተዋል። ደቡብ ኮሪያ እና ታይዋን ለኢትዮጵያ ቡና የተሻለ ከከፈሉ አገሮች መካከል ናቸው።
"ሌሎቹ ከዚያ በታች የሚከፍሉ ናቸው" ያሉት የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ጸሀፊ ቻይና "ደረጃ አንድ እና ደረጃ ሁለት ቡናዎችን ትገዛለች። ልዩ ጣዕም ያላቸው ቡናዎች ትገዛለች" ሲሉ አስረድተዋል። "የእኛ ነጋዴዎች የጥራት ደረጃ በመጠበቅ ማርካት አለባቸው። አንዳንዴ የሚጠየቁ ጥያቄዎች ጥብቅ ናቸው። የታዘዘውን ቡና በውሉ መሠረት በጊዜው ማድረስ አለብህ፤ በተስማማኻው መሠረት ያንን ጥራት ያለው ቡና ማድረስ አለብህ" ሲሉ መደረግ አለበት ያሉትን ዘርዝረዋል።
በቻይና ገበያ ማሌዥያ፣ ቪየትናም፣ ኮሎምቢያ እና ብራዚል ከፍ ያለ ቡና በመሸጥ የሚታወቁ አገሮች ናቸው። የቻይና አፍሪካ አማካሪ መሥራች እና ዋና ዳይሬክተር አቶ አሌክሳንደር "የኢትዮጵያ ቡና ብዙ አሲድ የለውም። በዚህ ምክንያት ለቻይና ተጠቃሚዎች በጣም ተቀባይነት አለው" ሲሉ ይናገራሉ። ብራዚል እና ቪየትናም የሚያመርቱት ቡና ሮቡስታ ቢሆንም "ምርታቸውን በማስተዋወቅ ጎበዝ ስለሆኑ በጣም ብዙ ሊሸጡ ይችላሉ" ሲሉ አቶ አሌክሳንደር አስረድተዋል። የኢትዮጵያን ቡና የማስተዋወቅ ሥራ መንግሥት እና ነጋዴዎች የሚሳተፉበት "የበለጠ የተቀናጀ በእውቀት የዳበረ" መሆን እንዳለበት የሚሞክሩት አቶ አሌክሳንደር "ከዚህ በፊት በብዛት የኢትዮጵያን ቡና ቻይና ውስጥ የሚያስተዋውቁት ጃፓናውያን እና ታይዋናውያን ነበሩ። አሁን እኛ እነሱን ተክተን ሥራውን ብንሰራ፤ በራሳችን አካሔድ መራመድ ብንጀምር የበለጠ ዕድል እና የበለጠ ስኬታማ እንደምንሆን እርግጠኛ ነኝ" ሲሉ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ከምታቀርባቸው ሸቀጦች ቀዳሚው የሆነው ቡና በተገባደደው የ2014 በጀት ዓመት ከፍተኛ ገቢ የተመዘገበበት ነው። የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በ2014 በጀት ዓመት ለዓለም ገበያ 300 ሺህ ቶን ቡና አቅርባ 1.4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር አግኝታለች። ይኸ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እንዳሉት በታሪክ ከቡና የተገኘ ከፍተኛው ገቢ ነው። ጀርመን፣ አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ ከፍ ያለ ቡና ከኢትዮጵያ በመግዛት ቀዳሚ ናቸው። ከዚህ ቀደም ባሉት ዓመታት 33ኛ ደረጃ ላይ ትገኝ የነበረችው ቻይና ወደ 7ኛ ከፍ ብላለች።
አቶ ሻፊ ዑመር የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮችን በመለየት ባለፉት ሶስት አመታት ገቢራዊ ያደረጋቸው ማሻሻያዎች አገሪቱ ከቡና ንግድ ላገኘችው ገቢ ዕድገት ሁነኛ ሚና እንደተጫወተ ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ባለፉት ሶስት ዓመታት በቡና ልማት እና ግብይት ዘርፍ የነበሩ አዋጆች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች እንዳሻሻለ የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ "ከፍተኛ ለውጥ ያስገኘው ማሻሻያው ተግባራዊ በመሆኑ ነው" ብለዋል።
የኢትዮጵያ የቡና አርሶ አደሮች ከዘርፉ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው "ያገራችንን ቡና ለማልማት ያለው ፍላጎት አነስተኛ ነው" የሚሉት አቶ ሻፊ "አርሶ አደር የራሱን ቡና ቀጥታ ወደ ውጪ መላክ የሚችልበት ዕድል ተፈጥሮለታል" ሲሉ ይናገራሉ። ምክትል ዳይሬክተሩ አርሶ አደሩ ቡናውን "ገበያ ወስዶ መሸጥ የሚችልበት ዕድል ተፈጥሮለታል። ለቡና ቆይዎች መሸጥ ይችላል፤ ከባለሐብት ጋር ተነጋግሮ መሸጥ ይችላል። በማህበር ተደራጅቶ ወደ ውጪ መላክ የሚችልበት ዕድል ተፈጥሮለታል" ሲሉ ተግባራዊ የተደረገው ማማሻያ አምጥቷል የሚሏቸውን ትሩፋቶች ዘርዝረዋል።
የቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ጸሐፊ አቶ ግዛት ወርቁ "ባለፈው ዓመት የላክንው 248 ሺህ ቶን ነበር። ከዚያ በፊት 271 ሺሕ ቶን ነው። የዘንድሮው 300 ሺሕ ቶን ነው የተላከው። ስለዚህ በ52 ሺሕ ቶን ገደማ ተጨማሪ ዘንድሮ ልከናል" በማለት ለዓለም ገበያ የተላከው ቡና መጠን መጨመር ለተገኘው ገቢ አስተዋጽዖ እንዳለው ይናገራሉ።
ሁለተኛው ጉዳይ በብራዚል የተከሰተ ድርቅ ነው። በደቡብ አሜሪካዊቷ አገር የተከሰተው ድርቅ 14 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ የብራዚል ቡና የአቅርቦት እጥረት በማስከተሉ በዓለም አቀፍ ገበያ የቡና ዋጋ ከፍ ብሎ ነበር። የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ጸሐፊ "በዓለም አቀፍ ገበያ በብራዚል ድርቅ ምክንያት የቡና ዋጋ በጣም ጨምሯል። ስለዚህ የተሻለ ዋጋ አግኝተናል። ባለፈው ዓመት አንድ ቶን ቡና በአማካይ የተሸጠው 3650 ዶላር አካባቢ ነው። ዘንድሮ ግን የተሸጠው 4660 ዶላር ነው። ባለፈው ዓመት የሸጥንው ከዘንድሮው በአንድ ሺሕ ዶላር ገደማ ልዩነት አለው" ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በሚቀጥለው ዓመት ለዓለም ገበያ ከሚቀርበው ቡና ከ1.5 እስከ 1.8 ቢሊዮን ዶላር የማግኘት እቅድ እንዳለው የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ይኸ ታዲያ የዋጋ መደራደር አቅምን የማጎልበት፣ ጥራትን ማሻሻል፣ በጊዜ ማድረስ እና በቅጡ ማስተዋወቅን የመሳሰሉ በርካታ ሥራዎች ይፈልጋል።
ይሁንና አቶ ግዛት "በሚቀጥለው ዓመት የቡና ዋጋ በዚህ ሊቀጥል ይችላል ብዬ አልገምትም" ሲሉ በ2014 ኢትዮጵያ 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንድታገኝ ያገዛት ሁኔታ ሊቀየር እንደሚችል ጥቆማ ይሰጣሉ። ድርቅ ተጭኗት የነበረችው ብራዚል ቡና በሚመረትበት "የሐምሌ እና ነሐሴ ወራት ወደ 3.5 እና 4 ሚሊዮን ተጨማሪ ኩንታል ታመርታለች ነው የሚባለው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ የተናገሩት አቶ ግዛት "የሚቀጥለው ዓመት የቡና ዋጋ ይረጋጋል፤ የመቀነስ አዝማሚያ ይታያል ተብሎ ነው የሚጠበቀው። ይኸ በአገር ውስጥ ባለው የቡና ዋጋ ላይም ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም" ሲሉ ተናግረዋል። "ቢሆንም የቡና ላኪዎቻችን በደንብ ተደራድረው፤ አስተዋውቀው የጥራት ደረጃ እና የማቅረቢያ ጊዜን ከጠበቁ የኢትዮጵያ ቡና ጥሩ ፈላጊ አለው። መሸጥ ይችላሉ" ሲሉ አስረድተዋል።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ