1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያና ሶማሊያ የማይነጣጠሉ ሕዝቦች ግን የወዳጅ-ጠላቶች ምድር

Negash Mohammedሰኞ፣ ጥር 5 2017

የየዉስጥ ጠላት የበዘባቸዉ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምና ጄኔራል መሐመድ ሲያድ ባሬ አንዱ የሌላዉን ጠላት እየደገፉ፣ መጀመሪያ ጀቡቲ፣ቀጥሎ አዲስ አበባ፣ አሰልሰዉ ሶደሬ ላይ የተጨባበጡ እጆቻቸዉን ሽቅብ እያጓኑ ወንድሜ-ወላሎ የመባባላቸዉ ዚቅ ለብዙ ታዛቢዎች አነጋጋሪ፣ አደናጋሪ፣ አስተዛዛቢም ብጤ ነበር።

https://p.dw.com/p/4p7aa

አምና ይኸኔ አዲስ አበባ ላይ የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ ታሪካዊ ወዳጅነት ፅናት፣ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘትዋ ብስራት ይዘመር፣ይወደስ፣ ይተነተን ነበር። ሞቃዲሾ ላይ ባንፃሩ የኢትዮጵያ የሶማሊያ ታሪካዊ ጠላትነት፣ የሶማሊያን ሉዓላዊነት የመድፈሯ እብሪት በአደባባይ ሰልፍ ጭምር ይወገዝ፣ለአድማ-ብቀላ ይዛት፣ የካይሮ-አስመራ-አንካራዎች ድጋፍ ይሰበክ ነበር።ዘንድሮ ባመቱ የአዲስ አበባና የሙቃዲሾ መሪዎች የሁለቱን ሐገራት ወዳጅነትና አዲስ ትብብርን ሲተርኩ፣አዲስ አበባ፣ በሁለቱ መሪዎች ፎቶ አሸብርቃለች።ካይሮም የሶማሊያና የኤርትራን ሚንስትሮችን አስተናግዳለች።የአፍሪቃ ቀንድ የፍቅር-ጥላቻ፣የትብብር-ሽኩቻ፣የወዳጅነት-ጠላትን አብነት ምድር።ያፍታ ቅኝታችን ነዉ።