ኢትዮጵያ ለኤርትራ ስደተኞች በርዋን ወለል አድርጋለች
ኤርትራዉያን ተፈናቃዮች በየቀኑ አደገኛዉን ድንበር በመሻገር ኢትዮጵያ ዉስጥ ጥገኝነት ይጠይቃሉ። ኢትዮጵያም እነዚህን ስደተኞች ተቀብላ ተገን በመስጠትዋ ደስተኛ ናት።
በምድረ በዳ መባዘን
«ከአስመራ የአራት ቀናት ጉዞን ይፈጃል» ሲል የሚናገረዉ የ 31 ዓመቱ ኤርትራዊ ከአስመራ እስከ ሰሜናዊ ኢትዮጵያ ድንበር ያለዉን 80 ኪሎ ሚትር የጉዞ ሁኔታን ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ ይተርካል። ቀን ቀን በረሃ ዉስጥ እየተኛን ለሊት ለሊት ደግሞ አስር አስር ኪሎ ሜትር ተጉዘን ነዉ የደረስነዉ። ከ31 ዓመቱ ኤርትራዊ ጋር ሌሎች ሦስት ወንዶች፤ ሦስት ሴቶች፤ ስድስት ሴቶች ልጆችና አራት ትንንሽ ወንድ ልጆች ነበሩ።
ወደኋላ መመለስ የለም
« የኤርትራን ድንበር ከማቋረጥ ይልቅ፤ በኤርትራ ያለዉ የኑሮ ሁኔታ ይበልጥ አደገኛ ነዉ» ሲል አንድ የኤርትራ ጦርን ለ 20 ዓመት ሲያገለግል የነበረና ጦሩን የከዳ የ 39 ዓመት ኤርትራዊ ወታደር ይናገራል። ኤርትራዉያኑ ስደተኞች ኢትዮጵያ ድንበር ላይ ሲደርሱ በኢትዮጵያዉያን ድንበር ጠባቂዎች ከተያዙ በኋላ የተገን ጥያቄ ወደሚያቀርቡበት ትግራይ ዉስጥ ወደሚገኘዉ ስደተኛ ጣብያ ማዕከል ይላካሉ።
የመጠለያ ጣብያ ሕይወት
ከኤርትራ አዲስ የሚመጡ ተገን ጠያቂዎች በትግራይ ዉስጥ ከሚገኙት አራት መጠለያ ጣብያዎች አንዱ ጋር ቦታ ይሰጣቸዋል። ከነዚህ የስደተኞች መጠለያ መካከል ሕንዓፅ የተባለዉ አዲሱ መጠለያ ጣብያ ወደ 11 ሺ ስደተኞች የሚኖሩበት ትልቁ ካንፕ ነዉ። በዚህ የስደተኞች መጠለያ ቦታ ከሚኖሩት መካከል 80% ተገን ጠያቂ ከ 35 ዓመት እድሜ ክልል በታች ያለ ነዉ። «ስደተኞቹ የፖለቲካ ጥገኝነት ቢጠይቁም እንኳ፤ ወጣቶች በመሆናቸዉ ሕይወታቸዉን አድሰዉ ኑሮአቸዉን መኖር ስለሚያስፈልጋቸዉ ጉዳያቸዉ የኤኮኖሚ ጥያቄንም ያካትታል» ሲሉ የጣብያዉ አስተባባሪ አቶ ሃፍቶም ተክለሚካኤል ተናግረዋል።
ሁኔታን ማመቻቸት
በመጠለያዉ ጣብያ የኑሮዉ ሁኔታ ቀለል ያለና ንጹሕ ነዉ። ስደተኞቹ የራቸዉ ቤት ሆኖ እንዲሰማቸዉ ያሉበትን ቦታ በተቻላቸዉ ሁሉ አስተካክለዉ ነዉ የሚኖሩት። አካባቢዉ ላይ ወድቆ የሚታየዉ ቆሻሻም ጥቂት ነዉ። የ 40 ዓመቱ የጣብያዉ ነዋሪ አቶ ዮሃንስ «አበባ ተክል ዉስጥ ሆኜ ቡናን ስጠጣ ደስታ ይሰማኛል» ይላሉ ሕንዓፅ ጣብያ በሚገኘዉ መኖርያ ቤታቸዉ አጠገብ የተከሉትን አነስ ያለች የአበባ ተክል ቦታ እያሳዩ። አቶ ዮሃንስ ከ 10 ዓመት ሴት ልጃቸዉ ጋር ነዉ የሚኖሩት። ባለቤታቸዉ ያሉት ደግሞ አሜሪካ ነዉ።
የጠንካራ ትግል ዉጤት
ኤርትራዉያኑ ስደተኞች ወደመጠለያ ጣብያ ከመወሰዳቸዉ በፊት የማስተባበር ርዳታ የሚሰጡት አቶ ሉሌ አበራ፤ «ኤርትራዊያን ጥሩ ሕዝብ ናቸዉ። ለነጻነታቸዉ 30 ዓመታት ተዋግተዋል» ነገር ግን ከመጀመርያዋ እለት ጀምሮ ኢሳያስ የራሱን ሕዝብ ፍላጉት ሳይጠብቅ ሃገሪቱን ገዝቶአል።» ይላሉ። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኤርትራን ከ 25 ዓመት በላይ በመምራት ላይ ይገኛሉ ።
የማያቋርጠዉ ጎርፍ
«ድንበር የተሻገርንበትን ምክንያት መናገር አልፈልግም» የምትለዉ ደግሞ የ 18 ዓመትዋ ሃይማኖት ናት። ሃይማኖት በሕንዓፅ የስደተኞች መጠለያ ጣብያ አንድ አነስ ባለች ዛኒጋባ ቤት አንድ ብር እያስከፈለች የተንቀሳቃሽ ስልክ ባትሪ ትሞላለች። በኢትዮጵያ የስደተኞች ድርጅት መረጃ መሰረት፤ በጎርጎረሳዊ 2017 ዓ.ም የካቲት ወር 3367 ኤርትራዉያን ስደተኞች ኢትዮጵያ ገብተዋል። በተመድ መረጃ መሰርት ደግሞ 165 ሺህ ኤርትራዉያን ስደተኞች ኢትዮጵያ ዉስጥ ይኖራሉ።
የሰላም እንቅልፍ
«ሱዳን በጣም ብዙ ችግር አለ። እዚህ የሰላም እንቅልፍ አለን» የምትለዉ ደግሞ አራት ዓመታት በሱዳን የስደተኞች ጣብያ ኖራ፤ የዛሬ አራት ዓመት ከሁለት ልጆችዋ ጋራ ወደ ሕንዓፅ መጠለያ የመጣችዉ የ 32 ዓመትዋ አርያም ናት። ስደተኞች እንደሚናገሩት የኤርትራ ወታደሮች ወደ ሱዳን በመዝለቅ ኤርትራዉያንን ለመያዝ አሰሳ ያካሂዳሉ። ሱዳን ዉስጥ ኤርትራዉያን በኤርትራዉያን ወታደሮች ይታደናሉ። የኢትዮጵያ ኤርትራ ድንበር ግን በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚጠበቅ ለድንግተኛ አሰሳ አይመችም።
ልግስና ወይንስ ስልታዊነት ?
የስደተኞች ጉዳይ ተንታኝ ጄኒፈር ሪጋን እንደሚሉት የኢትዮጵያ ምላሽ የነበረዉ ከዚህ ከማያቋርጥ የሕዝብ ፍሰት እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ዉሉን ማገናኘቱ ላይ ነዉ። ተገን ጠያቂዎች ወደ አዉሮጳ መሄዳቸዉን ለመግታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረገዉን እንቅስቃሴ ተከትሎ ስደተኞችን ለማስጠለል ተጨማሪ ገንዘብ ወጪ ሆኗል። ኢትዮጵያ ስደተኞችን መቀበልዋና ማስተናገዷ በቅርቡ በሃገሪቱ በነበረዉ ተቃዉሞ ከተፈጠረዉ ዉዝግብ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስምዋን ለማደስ አንዱ መንገድም ይሆናል።
ሽርክና እና ጥላቻ
ከጎርጎረሳዊ 1998 እስከ 2000 ዓ.ም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ከተካሄደዉ ጦርነት በኋላ በሃገራቱ ድንበር ላይ ወታደራዊ ይዞታዎች ፀንተዉ ይገኛሉ። ባለፍ ባገደም የሁለቱም ሃገራት መንግስታት አንዱ ሌላኛዉን ደባ ስርቶብኛል ሲሉም ይወነጃጀላሉ። እንድያም ሆኖ ኢትዮጵያ ይህን ዉዝግብ ከተራ ኤርትራዉያን ዜጎች ጋር አታያይዘዉም። « እኛ አንድ ሕዝብ ነን፤ ከአንድ ደም የተቀዳን ነን፤ አያቶቻችን እንኳ አንድ ናቸዉ » ሲሉ የኢትዮጵያ የስደተኞች ድርጅት ባልደረባ እስጤፋኖስ ገብረመድሕን ይገልጻሉ።
ሽሽት
«ልጆቼ ሁሉ አሜሪካ ነዉ የሚኖሩት፤ ሽማግሌ ነኝና ወደዝያ መሄድ አይታየኝም።» ሲሉ የሚናገሩት ሺምሌባ ስደተኞች ጣብያ የሚኖሩት የ 74 ዓመቱ ኤርትራዊ አቶ ተስፋዬ ናቸዉ። ሺመልባ በጎርጎረሳዉያኑ 2004 ዓ.ም ለመጀመርያ ጊዜ ትግራይ ዉስጥ ለኤርትራዉያን የተከፈተ የስደተኞች መጠለያ ጣብያ ነዉ። ከመቀሌዉ የስተኞች ጣብያ በሽዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዉያን የኢትዮጵያ ከተሞች ይኖራሉ። በርካታ ኤርትራዉያን ኢትዮጵያን ለቀዉ ለመዉጣት የወሰኑ ናቸዉ። ለምሳሌ እንደ አቶ ተስፋዬ ልጆች ሁሉ ጥቂቶቹ በሕጋዊ መንገድ ከኢትዮጵያ ለመዉጣት ይሞክራሉ። ሌሎች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለመዉጣት እየሞከሩ አብዛኞች በመንገድ ይሞታሉ።
የሚረሳ ጊዜን አላሳለፍንም
«እኛን ያገኘን ኢትዮጵያዊዉ ወታደር ለኛ ልክ እንደ ወንድማችን ነዉ» ያሉት የ 22 ዓመቷ የሁለት ልጆች እናት ወ/ሮ ዮርዳኖስ ናቸዉ። በጎርጎረሳዊዉ 1993 ዓ.ም ኤርትራ በሕዝበ ዉሳኔ በይፋ ነጻነትዋን ከማግኘትዋ በፊት የኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ነበረች። የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረዉ የሚገቡት አብዛኞቹ ኤርትራዉያን ትግርኛ ቋንቋን ይናገራሉ። ባህላቸዉና ልምዳቸዉም ቢሆን አንድ ዓይነት ነዉ። የሚከተሉትም በተመሳሳይ ኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ነዉ።