1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ኢያሱ ዘለቀ» ወጣቱ የዶቼባን መሐንዲስ 

ረቡዕ፣ ጥር 25 2014

ኢያሱ እንደሚለው ጀርመን ከመጣ በኋላ የሚያየውን ሁሉ በማድነቅ እንዴት ተሰራ ?እንዴት ላውቅ እችላለሁ? የሚለው ጉጉቱ ያመዝን ነበር።ፍላጎቱ በአመዛኙ ወደ ቴክኒክ ሞያ የነበረው ኢያሱ ይበልጥ የወደደውን ሲቪል ምህንድስናን ለማጥናት ወሰነ። በሲቪል ምህንድስና የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪውን ከያዘ በኋላም ስራ ለማግኘት አልተቸገረም ።

https://p.dw.com/p/46OHL
Engineer Eyasu Zeleke
ምስል privat

«ኢያሱ ዘለቀ»ወጣቱ የዶቼባን መሐንዲስ 

የሰላሳ ሁለት ዓመት ወጣት ነው።በልጅነቱ በተሰደደባት በጀርመን ምኞቱ ተሳክቶላት፣ በሚወደው ሞያ በአንድ ትልቅ የጀርመን ኩባንያ ውስጥ በፕሮጀክት ሃላፊነት ይሰራል። በትርፍ ጊዜው ደግሞ ጀርመን ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ያስፈልጋል የሚላቸውን መረጃዎች በግሉም ከሌሎች ጋርም በተለያየ መንገድ እንዲደርሳቸው ይጥራል።ጥያቄ ሲቀርብለትም ሆነ በራሱ ፍላጎት የሚሳተፍባቸው የበጎ ፈቃድ ስራዎች አሉ።ጀርመን መኖር ከጀመረ 20 ዓመት ይጠጋዋል። የ13 ዓመት ታዳጊ ወጣት ሳለ ነበር ጀርመን የመጣው። ኢያሱ ዘለቀ ይባላል ። የተሰማረው መርጦ በሰለጠነበት ሞያ ነው። በሲቪል ምህንድስና፣ በባችለርና በማስትሬት ዲግሪ በተመረቀበት በዚሁ ሞያ «ዶቼ ባን» በተባለው በግዙፉ የጀርመን የባቡር አገልግሎት ኩባንያ  ውስጥ በፕሮጀክት ስራ አስኪያጅነት እየሰራ ነው። በወጣትነቱ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ የበቃው በዓላማ ጽናቱ መሆኑን ይናገራል። ኢትዮጵያ እስከ ሰባተኛ ክፍል ከተማረ በኋላ ጀርመን የመጣው ታዳጊ ወጣት ኢያሱ አዲሱ መኖሪያው በሆነችው በጀርመን ትምህርቱን ለመቀጠል ጀርመንኛ ማወቅ ግድ ነበርና አንድ ዓመት ቋንቋ ተማረ።ቋንቋውንም ሆነ ሌላውን ትምህርት በቀላሉ መወጣት ቻለ። ለዚህም ራሱን አስቀድሞ ማዘጋጀቱ እንደጠቀመው ከምንም በላይ ደግሞ የታላቅ ወንድሙ ምክር ትልቁን ቦታ እንደሚይዝ ያስታውሳል።

Engineer Eyasu Zeleke
ምስል privat

ኢያሱ እንደሚለው ጀርመን ከመጣ በኋላ የሚያየውን ሁሉ በማድነቅ እንዴት ተሰራ እንዴት ላውቅ እችላለሁ? የሚለው ጉጉቱ ያመዝን ነበር። በቋንቋ ትምሕርት ወቅት ተማሪው ሁሉ የውጭ ዜጋ በመሆኑ ብዙም ችግር አልገጠመኝም ያይላል ወደ መደበኛው ትምህርት ሲገባ ግን ብዙም ባይሆን ጥቂት ፈተናዎች አላጡትም። ፍላጎቱ በአመዛኙ ወደ ቴክኒክ ሞያ የነበረው ኢያሱ ፣ተማሪዎች ወደፊት በዩኒቨርስቲ መማር የሚፈልጉትን የትምህርት ዘርፍ በቀላሉ እንዲመርጡ ወደ ተለያዩ ኩባንያዎች እየሄዱ በዚያ የሚሰራውን በሚያዩበት አጋጣሚ ይበልጥ የሳበውን ሲቪል ምህንድስናን ለማጥናት ወሰነ። በሲቪል ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪውንና ሁለተኛ ዲግሪውን ካገኘ በኋላም ስራ ለማግኘት አልተቸገረም ።
ወጣቱ መሐንዲስ እያሱ ከመደበኛ ስራው ውጭ በትርፍ ጊዜው በልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች ይሳተፋል።በተለይ ኢትዮጵያውያን ሊያውቁት ይገባል የሚላቸው መረጃዎች በተለያየ መንገድ እንዲደርሳቸው ይጥራል። ከመካከላቸው በዩትዩብ ቻናሉ የሚያስተላልፋላቸው የተለያዩ መረጃዎች ይጠቀሳሉ። እዚህ የተወለዱና ያደጉ ኢትዮጵያውያን ስለ ሀገራቸው ታሪክ እና ፖለቲካ በደጉበት አገር ቋንቋ እንዲረዱ ጀርመናውያንም ትክክለኛውን መረጃ እንዲያውቁ ምሁራን በጀርመንኛ ገለጻ የሚያደርጉባቸውን መድረኮችንም ከሌሎች አጋሮቹ ጋርም ያመቻቻል። ኢንጅነር ኢያሱ በጀርመን ብሔራዊና አካባቢያዊ ምርጫዎች ላይም እገዛ እንዲያደርግ ሲጠየቅም ሆነ በራሱ ፈቃድ ይሳተፋል።


ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ