ኤርትራ፣የጦር መሳሪያ ማዕቀቡ መራዘም እና ተፅዕኖው
ዓርብ፣ ጥቅምት 26 2008
የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በዚህ ወር መጀመሪያ ገደማ ባካሄደው ስብሰባው በኤርትራ እና በሶማልያ ላይ የጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እስከ ጎርጎሪዮሳዊው ኅዳር፣ 2016 ዓ,ም ለማራዘም ወስኗል። ምክር ቤቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ካሁን ቀደም እንዳደረገው የተመድ የሶማልያ እና ኤርትራ ተቆጣጣሪ ቡድን ኤርትራ በአካባቢው ሃገራት የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችን ትደግፋለች በሚል ያቀረበለን ዘገባ መሠረት አድርጎ ነው። ሆኖም፣ ምክር ቤቱ ይህንኑ የቡድኑን ዘገባ የሚደግፍለት አዲስ መረጃ ማግኘቱን እንደሚጠራጠሩት ነው በለንደን የሚገኘው «ቻተም ሀውስ» የተባለው የፖለቲካ ጥናት ተቋም የአፍሪቃ ክፍል ተባባሪ ተመራማሪ አህመድ ሶሊማን የገለጹት።
«የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ውሳኔውን የወሰደው ኤርትራ ለአካባቢ ታጣቂ እና ለኢትዮጵያ ተቃዋሚ ቡድኖች ትሰጠዋለች ስለሚባለው ድጋፍ ተቆጣጣሪው ቡድን ያቀረበለትን ዘገባ ከተመለከተ በኋላ ነው። በዚሁ ውሳኔው የኤርትራ መንግሥት ቀደም ሲል ስለተጠቀሰው ድጋፍ እና ኤርትራ እና ጅቡቲ በተጋጩበት ጊዜ በግዳጅ ላይ እያሉ ስለጠፉት የጅቡቲ ተዋጊዎች ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ እንዲያቀርብ ለመገፋፋት ነው። እና የምክር ቤቱ ርምጃ የእስካሁኑ ውሳኔው ቅጥያ ሆኖ ልናየው እንችላለን። ይሁን እንጂ፣ በኤርትራ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ከመጀመሪያውም ምክንያት የሆነውን፣ ኤርትራ አሸባብን ለመሳሰሉ ቡድኖች ድጋፍ ትሰጣለች መባሉን የሚደግፍለት ወሳኝ ማስረጃ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አግኝቶዋል ብዬ አላስብም።»
ኤርትራ ወቀሳውን በማጣጣል ማዕቀቡ እንዲያበቃ ጥሪ ብታቀርብም፣ ይህ ጥያቄዋ፣ እንደ አህመድ ሶሊማን ግምት፣ በቅርቡ እዉን ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም።
«የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማዕቀቡ እንዲነሳ በድጋሚ ለፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ጥሪ አሰምተዋል። እንደሚመስለኝ፣ ከዋና ጸሐፊው ፓን ኪ ሙንም ጋር ተገናኝተው ማዕቀቡ ሊነሳ ስለሚችልበት ጉዳይ ተነጋግረዋል። እርግጥ፣ እስካሁን ማዕቀቡ ወደሚነሳበት ሂደት ላይ ባይሰሩም፣ ይህ በዓመታት ውስጥ እውን ሊሆን የሚችል ይመስለኛል። የምናየዉ ከኤርትራ እና በተለይ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ባለው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወይም የአንዳንድ ሃገራት ግንኙነት ላይ የሆነ ለውጥ፣ ምናልባትም የአቋም ለውጥ መኖሩን ነው። ስለዚህ በተለይ በወቅቱ አውሮጳ ውስጥ ትልቅ መነጋገሪያ ርዕስ የሆነው ፍልሰትን የመሰለ ጉዳይ በግንኙነታቸው ላይ ተፅዕኖ አሳርፎ ማዕቀቡ የተራዘመበትን ውሳኔ ሊያስለውጥ ወደሚስችልበት ርምጃ ማምራት አለማምራቱ ወደፊት የሚታይ ይሆናል።»
የአዉሮጳ ኅብረት ከሶርያውያኑ ቀጥለው ወደ አህጉሩ በብዛት የሚገቡት ስደተኞች ኤርትራውያን እንደመሆናቸው መጠን፣ ለችግሩ መፍትሔውን በዚያው ዓይነተኛ የስደተኞች መፍለቂያ ከሆኑት ሃገራት ጋር ለማፈላለግ፣ ስደተኞቹ አውሮጳ ምድር ሳይገቡ ገና በሀገራቸው ሊቆዩ ስለሚችሉበት ጉዳይ ለመምከር በሚቀጥለው ሳምንት በሞልታ ርዕሰ ከተማ ቫሌታ ጉባዔ ጠርቷል።
የጦር መሳሪያ ማይቀቡ መራዘም ግን በዚሁ ጥረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳርፍ ስጋት ቢኖርም፣ ተባባሪው ተመራማሪ አህመድ ሶሊማን ሁለቱ ጉዳዮች ለየራሳቸው እንደመሆናቸው መጠን ውይይቶቹ መቀጠላቸው እንደማይቀር ጠቁመዋል።
«የአውሮጳ ህብረት እና የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን የስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ በጀመሩት ጥረት ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለመሥራት እየሞከሩ ነው። ኮሚሽኑ የስደተኞች መፍለቂያ የሆኑት ሃገራት ዜጎቻቸው ወደ አውሮጳ ሳይሰደዱ በፊት ሁነኛ ዘዴ ያገኙ ዘንድ ወደ ሁለት ቢልዮን ዩሮ ለመስጠት አቅዷል። ስለዚህ እነዚህ ውይይቶች መቀጠላቸው አይቀርም ብዬ አስባለሁ። እንዲያውም፣ ከሌሎች የኤርትራ ውስጣዊ ፖለቲካን ከሚመለከቱት እና በዝግ ስብሰባዎች ከሚካሄዱት ውይይቶች ተነጣጥለው መታየታቸው አይቀርም። »
ምክር ቤቱ በድርጅቱ ሰነድ ምዕራፍ ሰባት፣ አንቀጽ 2244 መሠረት በዚህ ወር መጀመሪያ ገደማ ባስተላለፈው በዚሁ ውሳኔውም የሶማልያ እና ኤርትራ ተቆጣጣሪ ቡድን ተልዕኮውን ለተጨማሪ አንድ ዓመት፣ ብሎም እስከ ታህሳስ 16፣ 2016 ዓ,ም እንዲቀጥል በመወሰን፣ የኤርትራ መንግሥት ቡድኑ ወደ ሀገሩ መግባት የሚችልበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች ትፅቢቱን ገልጾዋል።
አርያም ተክሌ
ሸዋዬ ለገሠ