ኤርትራ እና መጻኤ ዕድሏ
ረቡዕ፣ ጥቅምት 28 2011ይሁን እና አሁንም እንደቀድሞው በርካታ ኤርትራውያን ከሀገራቸው መሰደዳቸው ቀጥሏል። በዚያው ልክ ሀገራቸው የቆዩ እንዲሁም እድገት እውን እንዲሆን እና ገደብ የሌለው ብሔራዊ ውትድርና ይቆማል ብለው ተስፋ የሚያደርጉ በርካታ ሰዎችም አሉ።
አስመራ ውስጥ የኢትዮጵያ ሸቀጦች በሚገኝበት አንድ ገበያ ጠባብ መንገድ በርካታ ሸቀጥ የተጫነበት መኪና እያለፈ ነው። ብዙም ሳይቆይ ሾፌሩ መኪናውን አቁሞ ፓስታ ማውረድ ጀመረ። ድምጹን ከፍ አድርጎም ያመጣቸውን ሸቀጦች ማሻሻጥ ያዘ።
በስፍራው ከነበሩት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ገብያተኞች መካከል አንዱ የሆነው ተኬ ማሽላ እና አተር የያዙትን ጆንያዎች፣ በካርቶን የመጡትን ብስኩቶች እና የሚጥሚጣ ዛላ ያገላብጣል። በከተማዋ ማዕከል አንድ አነስተኛ ሱቅ ያለው ተኬ ለሱቁ የሚሆን ሸቀጥ በመፈለግ ላይ ነው።
«ከዚህ በርካሽ መግዛት እችላለሁ። ስለዚህ በርካሽ እሸጣለሁ»
ይላል ተኬ። እርሱ እንደሚናገረው ለምሳሌ ፓስታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድሮ ከሚሸጥበት ዋጋ በአንድ ሦስተኛ ቀንሷል።
«ለዚህ ነው ሰላም አስፈላጊ የሆነው። ሰዎች በሰላም መኖር እና መነገድ ይችላሉ፤ ሁሉም ነገር በመርከሱ የኤርትራ የኑሮ ደረጃም ይሻሻላል። »
በሰላም ስምምነቱ መሠረት ከሁለት አሥርት ዓመታት ጦርነት እና መለያየት በኋላ በዚህ ዓመት መስከረም መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበራቸውን ከከፈቱ በኋላ ነው በዚህ ስፍራ ንግዱ የጦፈው።
«የቤተሰቤ አባላት ከ20 ዓመት በኋላ ነው ከኢትዮጵያ ወደ አስመራ የመጡት። ምን ያህል እንደተደሰትኩ መግለጽ ያዳግተኛል። ከሰውነቴ የተቆረጡ አካላትን መልሼ ያገኘሁ ያህል ነው የተሰማኝ። »
ይህን የሚለው ሳሙኤል ሀብቴ በኤርትራ የተሻለ ህይወት ይኖራል ብሎ ተስፋ ያደርጋል። በአሁኑ ጊዜ ከኢትዮጵያውያ የሚመጡ ነጋዴዎች ትልቅ ንግድ እያካሄዱ ነው። ግን ይህ ወደፊት መስተካከሉ አይቀርም ይላሉ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል።
«እኛ አገልግሎቶች እና የኢንዱስትሪ ውጤቶች አሉን። ውድድር ያለበት ንግድ በትክክለኛ መንገድ የሚካሄድ ከሆነ ንግድ በአንድ አቅጣጫ ብቻ አይሄድም ።እኔ ምንም አያሳስበኝም። ከኢትዮጵያ ጋር በሚካሄድ ተጨማሪ ንግድ እና ውረታ ፣አትራፊ እንሆናለን። ይመስለኛል ኢትዮጵያም እንደዚሁ።»
በዚህ ረገድ ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ኢትዮጵያ ያጣችውን ቀይ ባህርን መጠቀም ነው። እስካሁን ምርቶችን ከፍተኛ ወጪ እየከፈለች በጅቡቲ ወደብ በኩል ነው የምታስገባው ኢትዮጵያ። ኤርትራ አሁን ወደቦችዋን ለኢትዮጵያ መርከቦች ክፍት አድርጋለች።
በምጽዋው ወደብ ላይ አንድም መልህቁን የጣለ መርከብ አይታይም ፤
« እዚህ የምንጠብቀው ተጨማሪ መርከቦችን ብቻ አይደለም። ይልቁንም የተለያዩ እቃዎች ከመላው ዓለም ይገባሉ ብለን እንጠብቃለን። ሁላችንም ተስፋ ሰንቀናል። ሰላም ሲሰፍን ማንኛውንም ነገር ማድረግ ይቻላል። አሁን እኛ ህዝባችን ጥሩ ትምህርት እንዲያገኝ ኤኮኖሚያችን እንዲያድግ እና እንዲበለጽግ እንፈልጋለን። ሁሉም እንዲሆን እንፈልጋለን።»
የሚለው ቬልደር ማልቱንግ ሼፊክ ነው። በዌልደር እይታ የኤርትራ መጻኤ እድል እንደ ጽጌረዳ አበባ የፈካ ነው። እውነተኛ ስሙን መናገር ያልፈለገው ቶማስ ግን ተጠራጣሪ ነው። እስካሁን ብዙ ለውጥ አላየሁም ባይ ነው። የኤርትራ መንግሥት ከጎረቤት ሃገራት ጋር ቢታረቅም ከራሱ ሕዝብ ገና ገና እንዳልታረቀም ይናገራል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን እንደሚለው ጭቆናና ድህነትን እንዲሁም ገደብ የሌለውን ብሔራዊ ውትድርና በመሸሽ በየወሩ ቁጥራቸው 4ሺህ የሚደርስ ኤርትራውያን ከሀገራቸው ይሰደዳሉ። በዚህ ረገድ አሁን ለውጥ ይደረግ አይደረግ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር በግልጽ አላሳወቁም።
«በህጉ መሠረት ብሔራዊ ውትድርናው ለ18 ወራት የሚዘልቅ ነው። ቆይታው የተራዘመው በጦርነቱ ምክንያት ነው። ይህ በሚመለከታቸው ላይ ጫና አይፈጥርም አልልም። ሆኖም ሰላም ካለ ለ18 ወራት ነው የሚቆየው። ይህ የሚወሰነው እንደሁኔታው ነው ። ህጉ ግን የማያሻማ እና በጣም ግልጽ ነው።»
ሁኔታዎቹ ምን እንደሆኑ እና ብሔራዊ ውትድርናውን ወደ 18 ወራት ለመመለስ ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ ግን አቶ የማነ ገብረ መስቀል አልተናገሩም። ተስፋ የሚደረግበት ለውጥ በርግጥ የሚመጣ ከሆነ የሚሰደደው ቁጥር ይቀንሳል። የ20 ዓመቱ ሜስያም ክብሮም ለምሳሌ ኤርትራን በምንም ዓይነት መንገድ ለቆ መውጣት አይፈልግም። እሱ እንደሚለው ሰላም ይመጣል ብሎ ያሰበ አልነበረም አሁን ግን ሕዝቡ ተስፋ አግኝቷል። የሁሉም የሚፈልጉት ደግሞ ለውጥ መሆኑን አፅንኦት ሰጥቷል።
ሊንዳ ሽታውደ/ ኂሩት መለሠ
ሸዋዬ ለገሠ