ኤርትራ 6 ጋዜጠኞችን መፍታቷ
ዓርብ፣ ጥር 15 2007ምሥግና ፣ ይርጋ ዓለም ፍስሐ መብርሃቱ ና ባሲሎስ ዘሞ፣ ለባናና ራዲዮ ዛራ ይሠራ የነበረው መለስ ንጉሤ ክፍሉ፣ የራዲዮ ድምፂ ሐፋሽ ግርማይ አብርሃም እንዲሁም ጴጥሮስ ተፈሪ ናቸው። የጋዜጠኞቹን መለቀቅ በተመለከተ ፤ የድንበር አያግዴውን የጋዜጠኞች ድርጅት ፤ የአፍሪቃ ክፍል ኀላፊ ፣ ክሌ ካን ስሪበር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዓለም ውስጥ ጋዜጠኞችን በብዛት እሥር ቤት በመወርወር ከሚወቀሱትና ከሚከሰሱት ሀገራት መካከል አንዱ የኤርትራ መንግሥት 6 ጋዜጠኞችን የፈታበት ድርጊት ሠናይ መሆኑ ተነግሯል። የኤርትራ መንግሥት ፤ ያሠራቸውን ጋዜጠኞች እንዲፈታ ፣ የፕረስ ነጻነትን እንዲያከብር በየጊዜው ይቀርብለት ለነበረ ጥያቄ ጆሮ ዳባ ልበስ ሲል ከቆየ በኋላ እ ጎ አ በ 2009 ዓ ም ይዞ ያሠራቸውን የራዲዮ ጋዜጠኞች መልቀቁ የተሰማው ትናንት ማታ ነው። ለጋዜጠኞች መብት የሚታገለው ድንበር አያግዴው የጋዜጠኞች ድርጅት (RSF) ምን ተሰማው ? የድርጅቱ የአፍሪቃ ጉዳዮች ኀላፊ ክሌ ካን ስሪበር--
«እኛ የደንበር አያግዴው ጋዜጠኞች ማሕበር ሐገ ወጥ በሆነ መንገድ ተይዘው 6 ዓመት ያህል የታሠሩ 6 ኤርትራውያን ጋዜጠኞች ተለቀው ከሚወዷቸው ፣ቤተሰቦቻቸው ጋር እንደገና መገናኘት በመቻላቸው ደስ ብሎናል። እርግጥ የተለቀቁት በቅድመ ግዴታ ነው። ያ ደግሞ ምን እንደሆነ ገና አልታወቀም። ስለጤንነታቸው ይዞታም ያን ያህል የተብራራ መረጃ የለንም። ምክንያቱም ፣ የአሥር ቤት ይዞታ እጅግ ዘግናኝ ነውና! ያም ሆነ ይህ፤ በሚመጡት ቀናትና ሳምንታት ተጨማሪ መረጃ እናገኛለን ብለን ነው ተስፋ የምናደርገው። ለጊዜው ግን ፣ ከእሥር ቤት በመውጣታቸው በእርግጥ ደስ ብሎናል። »
የኤርትራ መንግሥት፣ የሰብአዊ መብት ጥያቄ በተለይም የፕረስ ነጻነት ጥያቄን የሚያነሱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ክፉኛ ይዘልፍ እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም፤ በተለይ የቀድሞው ማስታወቂያ ሚንስትር አቶ አሊ አብዶ RSF ንና ባልደረቦቹን ፣ እጅግ ያጥላሉ እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም። የታሠረቱን ጋዜጠኞች እንዲፈታ ለፕረስ ነጻነትም በሩን እንዲከፍት ይጠየቅ የነበረው የኤርትራ መንግሥት ለ 6 ቱ ጋዜጠኞች ልቡ የራራ መምሰሉ ምን ቢገፋፋው ነው?
«እንደሚታወቀው የኤርትራ መንግሥት የግንኙነት በር የዘጋ ፤ እምብዛም መነጋገር የማይሻ ነው። ታሥረው የነበሩትን ጋዜጠኞች የፈታበትን ምክንያት በትክክል ለማወቅ መጀመሪያውንም፤ የታሠሩበት ሁኔታ እንቆቅልሽ እንደነበረ ሁሉ የተለቀቁበት ምክንያትም ግልፅ አይደለም። በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ የተደጠ አይመስልም። የሰበሰብነው መረጃ እንደሚያመላክተው የተለቀቁት ጋዜጠኞች ለምን እንደተፈቱ የተሰጣቸው ማብራሪያ የለም። ከእሥራት መለቀቃቸው ብቻ ነው የተነገራቸው።ምናልባት ፣የኤርትራ መንግሥት የሰብአዊ መብት እንዲያሻሽል የቀረበለትን ጥያቄ መነሻ አድርጎ፣ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብና እንደብረት በጠበቀ አገዛዝ ሥር ላለውና ለሚያማርረው የኤርትራ ሕዝብ በጎ ምልክት ማሳየቱም ይሆናል። »
6 ጋዜጠኞች መለቀቃቸው በጎ ነገር ነው። እዚህ ላይ ብዙ ተማጽኖ የተደረገለት በትውልድ ኤራትራዊ በዜግነት ስዊድናዊ የሆነው ዳዊት ይስሐቅ፤ ያልተለቀቀበት ምክንያት ወይም ምሕረት ያልተደረገለት ለምን ይሆን?
« እ ጎ አ በ 2001 ተይዘው የታሠሩት ፤ ፍርዱ ይበልጥ የጠበቀባቸው ይመስለኛል። ከዚያ በኋላ የተያዙትንና አሁን የተለቀቁትን 6 ቱን ጋዜጠኞች፤ በተጨማሪም እ ጎ አ በ 2013 ነጻ የተለቀቁትን 7 ጋዜጠኞች መንግሥት እምብዛም ክሡን አላጠበቀባቸውም። በ 2001 ተይዘው የታሠሩቱን ጉዳይ ግን የሚያስፈራ ነው። ጉዳያቸውን ከተቃውሞ የፖለቲካ ድርጅት ጋር ነው መንግሥት ያያያዘው። ዳዊት ይሥሐቅ ፤ እርሱ ብቻ አይደለም፣ አብዛኛውን ጊዜ የሱ ስም ይወሳል እንጂ ሥዩም ፀሐዬና ሌሎችም አሉ--ለረጅም ጊዜ የታሠሩ! »
የ ድንበር አያግዴው የጋዜጠኞች ማሕበር (RSF) የአፍሪቃ ክፍl ኀላፊ፤ ክሌ ካን ስሪበር ፤ የኤርትራ መንግሥት፤ አሁን የጀመረውን ድርጊት እንደሚገፋበትና ቀሪዎቹን እሥረኞች እንደሚለቅ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ኤርትራ 6 ጋዜጠኞችን ከእሥር መፍታቷን ፤ RSF ያስታወቀው፤ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት (HRW) የኢትዮጵያ መንግሥት ከመጪው ግንቦት ምርጫ በፊት በነጻው ፕረስ ላይ ጫናውን ይበልጥ አጥብቋል ፤ እ ጎ አ ከ 2010 ወዲህ ብቻ ከ 60 የማያንሱ ጋዜጠኞጽች አገር ለቀው እንዲሰደዱ ሰበብ ሆኗል 19 ጋዜጠኞችንም ወህኒ አውርዷል ሲል መግለጫ በሰጠበት ዕለት ነው።
ተክሌ የኋላ
ኂሩት መለሰ