1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"እባካችሁ ሕዝባችን የሚገለገልበት መንገድ ሊመቻችለት ይገባል" የመቐለ ነዋሪ ጥሪ

ረቡዕ፣ ሰኔ 22 2014

ኢትዮ-ቴሌኮም በትግራይ ለደንበኞቹ የሚያቀርበው የስልክ አገልግሎት ከተቋረጠ አንድ ዓመት ሞላው። ይኸ በጦርነቱ ምክንያት ከተቋረጡ ሌሎች መሠረታዊ ግልጋሎቶች ጋር ተደምሮ በበትግራይ ተወላጆች ላይ ጫና አሳድሯል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የክልሉ ነዋሪ "እባካችሁን ሕዝባችን የሚገለገልበትን መንገድ ሊመቻችለት ይገባል" ሲሉ ተማጽነዋል።

https://p.dw.com/p/4DQx8
Äthiopien Reportage aus Mekelle
ምስል Million Hailessilassie/DW

ከኤኮኖሚው ዓለም፤ አንድ ዓመት ያለ ስልክ አገልግሎት-ትግራይ

መዝገቡ ከወላጆቹ፣ ከቤተ-ዘመዶቹ ለመጨረሻ ጊዜ በአይነ ሥጋ የተያየው በ2012 ነበር። እግሩ ለስደት ከመውጣቱ፣ የባብ አል መንደብን ሰርጥ በጀልባ ከማቋረጡ በፊት…ሰላም በራቃት የመን ብርቱ ሥቃይ ከመጋፈጡ በፊት…

"የተሻለ ሥራ ፍለጋ" ከኢትዮጵያ በየመን በኩል መዝገቡ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያመራው በየካቲት 2012 ገደማ ነው። ሳዑዲ አረቢያ ለመድረስ ጅቡቲ እና የመንን ያቋረጠው ወጣት በርካታ ኢትዮጵያውያን የተጋፈጡት ድካም እና ሥቃይ አልቀረለትም። ጅቡቲን "የሞት አገር" ይላታል። ውኃ አይገኝም፣ ምግብ ይቸግራል። በኮቪድ ምክንያት የመንቀሳቀስ ገደብ በየመን ሲጣል መዝገቡ ሑቲዎች በሚቆጣጠሯት ሰንዓ እና የስደተኛው መንግሥት መቀመጫ በሆነችው አደን መካከል ይንከላወስ ይል ነበር።

"የመን ትክክለኛ ሥርዓት የሌለበት አገር ነው። የርስ በርስ ጦርነት ስላለ ሁሉም የታጠቀ ነው፤ ሁሉም መንግሥት ነው። ስለዚህ ዝም ብለህ እየሔድክ አንዱ የታጠቀ ከያዘህ ምንም ማድረግ አትችልም" ይላል መዝገቡ።  በየመን ማሪብ ግዛት በምትገኘው የማሪብ ከተማ እና አካባቢ ጦርነት በበረታበት ወቅት መዝገቡ መላወሻ ተከልክለው በቦታው ከነበሩ በበርካታ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አንዱ ነው።

Äthiopien Reportage aus Mekelle
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የመቐለ ነዋሪ የስልክ ጥሪ ለማድረግ "አንድ የነበረችው አማራጭ ቀይ መስቀል ነች፤ ቀይ መስቀል በሁለት በሶስት ወር ወረፋ ነው የሚደርሰው" ሲሉ ተናግረዋል። በስልክ ግልጋሎት መቋረጥ ሳቢያ ከክልሉ ውጪ ያሉ የትግራይ ተወላጆች ቤተሰቦቻቸውን መገናኘት አልቻሉም። ምስል Million Hailessilassie/DW

በረሐማው የማሪብ አካባቢ "ምንም የሌለበት" እንደሆነ የሚያስታውሰው መዝገቡ "በዚያን ጊዜ የተያዘ ኢትዮጵያዊ ወደዚያ ነው የሚጣለው" ሲል ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።  "ወደ ፊት እንዳትገፋ በጣም ኃይለኛ ጦርነት አለ። ወደ ሳዑዲ እንዳትመጣ ደግሞ ይዘው ወደ በረሐ ይጥሉሃል" ይላል።

መዝገቡ ከየመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሲሻገር የተመኘውን የሥራ ዕድል አላገኘም። የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተቀሰቀሰው ለዚህ ዘገባ ሲባል ስሙ የተቀየረው መዝገቡ በሳዑዲ አረቢያ ሥራ በማፈላለግ ላይ ሳለ ነው። ጦርነቱ ሲጀመር መዝገቡ ከቤተሰቦቹ የሚገናኝበት የስልክ አገልግሎት ተቋረጠ።

"ኔትወርክ ከመፈቀዱ በፊት አንድ ነገር እርግጠኛ ነበርኩ። የሞተው ይሞታል፤ የቀረው ይቀራል። የሆነ ጊዜ ሰላም ይሆናል ብዬ እል ነበር" የሚለው መዝገቡ መልሶ "መቼም ጭንቀት አልነበረኝም ማለት አይደለም" ሲል የነበረበትን ሁኔታ መለስ እያለ ያስታውሳል።

"ኔትወርክ ከተከፈተ በኋላ እናት እና አባቴ ቤታቸውን ጥለው በረሐ ሲያድሩ፤ ለጓደኞቼ ስደውልም አገራቸውን ጥለው በየጫካው [እንደሸሹ ሰማሁ።] እከሌስ? ስትላቸው እከሌማ እንደዚህ ሞቷል፤ ዝም ብሎ እየሔደ ገደሉት፤ እከሌስ? ስትላቸው እከሌማ እንደዚህ ከእነ እህቱ ከእነ ወንድሙ ነው የተገደለው። እከሌስ? እከሌማ እንደዚህ ቤቱ ተቃጠለ። ይኸን ስሰማ በቃ ግራ ገባኝ። በተለይ እኛ አካባቢ የነበረው የኤርትራ ሠራዊት ስለነበር በጣም ከበድ ይላል" በማለት በስልክ የደረሰው መረጃ እና የፈጠረበትን ስሜት ይገልጸዋል።

መዝገቡ ከማርያም ደንገላት በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው የዕዳጋ ሐሙስ ልጅ ነው። በማርያም ደንገላት የኤርትራ ወታደሮች በጥቅምት 2013 በርካታ ሰላዊ ሰዎች ለመግደላቸው "ተዓማኒ" መረጃ እንደደረሳቸው ጠቅሰው የተ.መ.ድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሸል ባቼሌት አውግዘው ነበር።

እንዲህ ልብ ሰባሪ መርዶ ከትውልድ ቀዬው የሰማው መዝገቡ በሳዑዲ አረቢያ ሶስት ገደማ ወራት ከሰራ በኋላ በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ገባ። በእስር ቤት በኢትዮጵያውያን ላይ የበረታውን ፈተና ዳግም ተጋፈጠ። በሐምሌ 2013 ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ግን የገጠመው ሌላ እስር ሆነ።

"400 ሰው ነበር ሽሮ ሜዳ የሚገኘው። ለሊት መጥተው መቶ ሰው ዝም ብለው አንስተው ወሰዱን በቃ። ጉራ ፈርዳ ወረዳ። እዚያ ነው የጣሉን በቃ። እዚያ ሥሩ ተባልን። በቀን 40 ብር ነው የሚታሰብላችሁ ተባልን" የሚለው መዝገቡ በቂ ምግብ እና አልባሳት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ እንደቆየ ይናገራል።

Infografik Karte Migrationsroute von Äthiepien nach Saudi-Arabien EN
መደበኛ ባልሆነው መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚያመሩ ኢትዮጵያውያን በጅቡቲ በኩል የባብ አል መንደብን ሰርጥ በጀልባ ያቋርጣሉ። በየርስ በርስ ጦርነት በምትታመሰው የመን በኩል ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት ሲሞክሩ ብርቱ ፈተና ይጠብቃቸዋል።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ሒውማን ራይትስ ዎች በታኅሳስ 2013 ይፋ ባደረገው ዘገባ ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱ የትግራይ ተወላጆች በመንግሥት በዘፈቀደ መታሰራቸውን ይፋ አድርጓል። በዘገባው መሠረት እንደ መዝገቡ በተመሳሳይ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ የትግራይ ተወላጆች በአዲስ አበባ፣ በአፋር፣ በደቡብ እና በኦሮሚያ ክልሎች ለእስር ተዳርገዋል።

መዝገቡ የተለቀቀው "ለመታወቂያ" ከፍሎ እንደሆነ ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።  መንገዶች ሁሉ በመዘጋጋታቸው ወደ ትውልድ ቀዬው ማቅናት አልሆነለትም። ቤተሰቦቹ ያሉበትን ኹኔታ የሚረዳው "በሰው በሰው" በሚደርሰው ወሬ ብቻ ነው። መደበኛ የስልክ አገልግሎት በመቋረጡ የእናቱን እና የአባቱን ድምጽ ከሰማ ረዥም ጊዜ አልፏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ንብረት የሆነው ኢትዮ-ቴሌኮም በትግራይ ክልል ለሚገኙ ደንበኞቹ የሚያቀርበው አገልግልሎት ከተቋረጠ ትላንት ማክሰኞ አንድ አመት ሞላው። አገልግሎቱ የተቋረጠው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከክልሉ ወጥቶ በህወሓት የሚመሩት የትግራይ ኃይሎች መቐለን ሰኔ 21 ቀን 2013 ሲቆጣጠሩ ነበር። ይኸ እንደ መዝገቡ ከትግራይ ውጪ የሚገኙ ዜጎችን ብቻ ሳይሆን እንደ መዋዕል ገብረ ያሉ የመቐለ ነዋሪዎችን ከግንኙነት ውጪ አድርጓል።

Äthiopien Reportage aus Mekelle
በትግራይ የኢንተርኔት አገልግሎት መስጪያ ተቋማት ሥራ ከጥቅምት 24 ቀን 2013 በኋላ ሥራ አቁመዋል። የተቋማቱ ባለቤቶችም ሥራ ለመቀየር ተገደዋል። ምስል Million Hailessilassie/DW

"እኔ አሁን ባለትዳር ነኝ። አንድ ልጅ አለችኝ። ሰርቼ ነበር የምኖረው። አሁን ባለው ኹኔታ ግን መሥራትም አይቻልም" የሚለው መዋዕል ገብረ "ኮምዩንኬሽንም የለም። አዲስ አበባ ወይም ውጪ ያሉ ዘመዶቻችን ጋር እንኳን ደውለን ብር ለማስላክ እጅግ በጣም ችግር ውስጥ ነን ያለንው" በማለት የገጠመውን ይዘረዝራል።

ትግራይ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ያጣችው ግን መደበኛ የስልክ ግልጋሎት ብቻ አይደለም። ጥቅምት 24 ቀን 2013 የተቋረጠው የኢንተርኔት ግልጋሎት ዛሬም ወደነበረበት አልተመለሰም። ይኸ የኢንተርኔት አገልግሎት ያቀርብ የነበረው ማስረሻ ገብሩ የተሰማራበትን የሥራ ዘርፍ እንዲቀይር አስገድዶታል።

ከአስር አመት በላይ የኢንተርኔት አገልግሎት ለደንበኞቹ በማቅረብ ይተዳደር የነበረው ማስረሻ "አሁን ሙሉ በሙሉ በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ከዚያ ሥራ ውጪ ሆነን ተገደን ወደ ገባንበት ሌላ የሥራ ዘርፍ ቢዝነስ እየሰራን ነው የምንገኘው። ለእኛ ትልቅ የሆነ ኪሳራ ነው ያስከተለብን" ይላል።  "ዕቃዎቻችን ከሥራ ውጪ ሆነዋል። ዘግተናቸው የአቧራ ሰለባ ነው የሆኑት። እንሽጣቸው እንኳ ብንል የሚገዛ ሰው የለም። ምክንያቱም አገልግሎት ስለሌለ ማንም ሰው ሊገዛህ አይችልም። ከዚያ በተጨማሪ ስናገለግላቸው የነበሩ ደንበኞቻችንን አጥተናል። ሌላ ደንበኛ ፍለጋ ነው እየዞርን ያለንው" በማለት ማስረሻ በኑሮው የተፈጠረውን ገልጾታል።

ፌስቡክ፣ ዩ ቲዩብ እና ትዊተርን በመሳሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ ዜናዎች፣ ዜናዎቹን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች፤ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የሚወጡ ሪፖርቶች በመቐለ መረጃ ለጠማው የማኅበረሰብ ክፍል ይሸጣሉ። መግዛት የሚይችሉ ደግሞ በመሸጫ ማዕከላቱ በራፍ ተቀምጠው መረጃዎቹን ያደምጣሉ። በከተማዋ ጎዳዎች በሳንቲም አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጁ ስልኮች ከሥራ ውጪ ሆነዋል። ይኸ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ያስከተለው ምስቅልቅል እንደ መዋዕል ገብረ ያሉ ነዋሪዎች የኢንተርኔት አገልግሎት ያላቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ደጅ ለመጥናት አስገድዷቸዋል።

Äthiopien Reportage aus Mekelle
ፌስቡክ፣ ዩ ቲዩብ እና ትዊተርን በመሳሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ ዜናዎች፣ ዜናዎቹን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች፤ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የሚወጡ ሪፖርቶች በመቐለ መረጃ ለጠማው የማኅበረሰብ ክፍል ይሸጣሉ። መግዛት የሚይችሉ ደግሞ በመሸጫ ማዕከላቱ በራፍ ተቀምጠው መረጃዎቹን ያደምጣሉ።ምስል Million Hailessilassie/DW

"አሁን ባለው ሁኔታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ትጠቀማለህ። እሱም በመልካም ትብብር ማለት ነው። ትሔዳለህ ትጠይቃቸዋለህ" ይላል መዋዕል። "አንድ የነበረችው አማራጭ ቀይ መስቀል ነች፤ ቀይ መስቀል በሁለት በሶስት ወር ወረፋ ነው የሚደርሰው። ስለዚህ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አማራጭ ትጠቀማለህ። እሱም ከተገኘ ነው። አሁን ለምሳሌ እኔ መልዕክት ከላኩ በኋላ እዚያ የሚሰራው ባለሙያ ድንገት መስክ ይወጣል" የሚለው በግል ሥራ የሚተደረው መዋዕል የሚፈለገው በጊዜው ካልተገኘ ጉዳቱ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻል።  "የብር ጉዳይ አሳሳቢ ነው። በጊዜው ካላገኘህ የምትፈልጋቸውን ሰዎች እስከማጣት ልትደርስ ትችላለህ" ሲል በመቐለ ለሚገኘው የዶይቼ ቬለ ዘጋቢ ሚሊዮን ኃይለስላሴ ተናግሯል።

ባለፈው ሣምንት ወደ ኢትዮጵያ ባደረጉት ጉዞ የትግራይ ክልልን የጎበኙት የአውሮፓ ኅብረት የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርቺች በጦርነቱ ምክንያት ትግራይ ላይ የተጣሉት "አብዛኞቹ ገደቦች አሁንም እንዳሉ" መሆናቸውን ተናግረዋል። ኮሚሽነሩ በአዲስ አበባ ሰኔ 14 ቀን 2014 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "የነዳጅ አቅርቦት፣ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ጨምሮ ገደቦቹን ማንሳት ያስፈልጋል" ሲሉ ተደምጠዋል።

ያኔዝ ሌናርቺች "አብዛኞቹ ሰዎች ጥሩ ቁጠባ አላቸው። ነገር ግን ቁጠባቸውን ማግኘት ስለማይችሉ እየተራቡ ነው። መሠረታዊ አገልግሎቶች መልሰው ሥራ ከጀመሩ አብዛኛው መከራ ያበቃል። በነዳጅ አቅርቦት፣ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ላይ የተጣለው ገደብ ከተነሳ አላስፈላጊ የሆነው መከራ ያበቃል። በመጨረሻም ጉዳዩ ሰላማዊ መፍትሔ ሲበጅለት በትግራይ ያለው ሁሉም መከራ ያበቃል" ሲሉ ተናግረዋል።

 እስካሁን እነዚህ ገደቦች መቼ እንደሚነሱ የታወቀ ነገር የለም። ፍንጭም አልታየም። የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና በህወሓት የሚመራው የትግራይ መስተዳድር ለድርድር ተዘጋጅተዋል። ገደቦቹ በማኅበረሰቡ ላይ ብርቱ ጫና ማሳደራቸውን የሚጠቅሰው የመቐለው ገብሩ ግን "የሚመለከታችሁ አካላት እባካችሁን ሕዝባችን የሚገለገልበት መንገድ ሊመቻችለት ይገባል" እያለ ይማጸናል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ