1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከክትባቱ ዘመቻ ጎን ለጎን የኮቪድ 19 መስፋፋት

ማክሰኞ፣ ጥር 10 2014

በበለጸጉት ሃገራት የኮቪድ 19 ክትባት በስፋት እየተሰጠ በሚገኝበት በዚህ ወቅት በተሐዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መበራከቱን ቀጥሏል። በተለይም ኦሚክሮን የሚል ስያሜ የተሰጠው ልውጡ የኮሮና ተሐዋሲ ከተከሰተ ወዲህ በዚህ አይነቱ የሚያዙት ሰዎች ከዕለት ወደ ዕለት ቁጥራቸው እየጨመረ መሄዱን መረጃዎች ያሳያሉ።

https://p.dw.com/p/45iOS
Berlin Impfung in der Sage Beach Bar und Restaurant
ምስል Markus Schreiber/AP/picture alliance

በጀርመን የተባባሰው የኮሮና ስርጭት

የጀርመን የተላላፊ በሽታዎች ተከታታይ ተቋም ሮበርት ኮኽ ይፋ ባደረገው መሠረት ባለፉት ሰባት ቀናት በተከታታይ በታየው መሠረት በ100 ሺህ ሰዎች ውስጥ በተሐዋሲው የተያዙት ከ553 በልጠዋል። በአንድ ቀን ብቻም ከ70 ሺህ በላይ አዲስ ተሐዋሲው መያዛቸው በምርመራ ተረጋግጧል። የተከተቡ ሰዎች በመቶኛ ሲሰላ ከጠቅላላው የጀርመን ነዋሪ ከ70 በመቶ በልጠዋል። በተሐዋሲው የመያዙ አጋጣሚ ግን ለሁሉም የሚቀር አልሆነም። 

ጀርመን ውስጥ ክትባት ተደጋግሞ እየተሰጠ በሚገኝበት በዚህ ወቅት የኮሮና ልውጥ ተሐዋሲ ኦሚክሮን በርካቶችን እያዳረሰ ነው ።  ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 74,405 ሰዎች አዲስ በኮሮና ተሐዋሲ መያዛቸው መረጋገጡን በዛሬው ዕለት የጀርመን የተላላፊ በሽታዎች ተከታታይ ተቋም ሮበርት ኮኽ አስታውቋል። ባለፈው ሳምንት ከፍተኛ የተባለው ቁጥር በ24 ሰዓታት ውስጥ የተመዘገበው የ45,690 ሰዎች መያዝ ነበር።  በርሊን የሚገኘው ባልደረባችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል በተለይ ፈጣን የመተላለፍ አቅም አለው የሚባለው ኦሚክሮን የተሰኘው ልውጡ የኮሮና ተሐዋሲ የመስፋፋቱ ነገር ብዙዎችን እያነጋገረ እንደሆነ ገልጾልናል።

Symbolbild | Impfstoff Corona Omikron Variante
ምስል Fleig/Eibner-Pressefoto/picture alliance

ከዚህ ቀደም ጀርመን ውስጥ 100 ሺህ ሰዎች መካከል 100 ሰዎች ለሰባት ቀናት በተከታታይ በተሐዋሲው መያዛቸው ከተረጋገጠ አጠቃላይ የእንቅስቃሴ እገዳ ይጣል ነበር። በአሁኑ ጊዜ በ100 ሺህ ሰዎች መካከል በኮሮና የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ500 አልፏል። የሀገሪቱ የጤና ጉዳይ ባለሥልጣናት ኅብረተሰቡ ክትባቱን እንዲወስድ እያበረታቱ በመሆኑ አጠቃላይ የእንቅስቃሴ እገዳ ይጣል ይኾን የሚለው የአብዛኛው ኅብረተሰብ ስጋት ለጊዜው ቀለል ያለ መስሏል። ይልቁንም ያልተከተበው በ20 እና 30 በመቶ መካከል የሚገመተው የኅብረተሰብ ክፍል እንዲከተብ በተለያዩ አጋጣሚዎች ግፊት ለማድረግ ሲሞከር ይታያል። ከዚህ ቀደም በየዓመቱ ለኢንፍሉዌንዛ ወይም ከባድ ጉንፋን ለመከላከል ክትባቶችን የሚወስዱ ወገኖች ጥቂት አልነበሩም። በአሁኑ ወቅትም የኮሮና ክትባትን ብዙዎች ተቀብለውታል። ክትባቱ በወራቶች ልዩነት ከሁለት ወደ ሦስት እያለም ለአራተኛ ጊዜ እንዲወስዱ እየተደረገ ነው። በዚህ አያያዝም ኮሮና ተሐዋሲ ጋር አብረን መክረማችን አልቀረምና ክትባቱም ቀጣይ መሆኑ አይቀርም የሚሉ ወገኖች አሉ።  እዚህ ጀርመን ሀገር የአጥንት ህክምና ከፍተኛ ባለሙያው የሆኑት ዶክተር ውብታየ ዱሬሳ ተክሌ ይኽንኑ ሃሳብ ያጠናክራሉ።

Deutschland, Marburg | Covid-19 Impfstoff-Herstellung bei BioNTech
ምስል Thomas Lohnes/AFP/Getty Images

ከዚህ ቀደም በየዓመቱ በተለያዩ ሃገራትም ሆነ እዚህ ጀርመን ከመተንፈሻ አካላት ጋር በተያያዙ የተለያዩ የጤና ችግሮች በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት እንደሚያልፍ መረጃዎች ያሳያሉ። ኮሮና በአጣዳፊ ሁኔታ በርካታ ሰዎች መግደሉ ካልሆነ እና ብዙም ስለተወራለት ካልሆነ በቀር ከሌሎቹ የመተንፈሻ አካላትን ከሚጎዱ የጉንፋን እና ኢንፍሉዌንዛ ዘሮች በምን ይለያል በሚል የሚሞክቱ ጥቂት አይደሉም። 

በዛሬው ዕለት የወጡ የተለያዩ ሃገራት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ጀርመን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎች በርካታ ሃገራትም በተመሳሳይ በኮሮና ተሐዋሲ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ዳግም እየጨመረ ነው። አውስትራሊያ ውስጥ በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ሀኪም ቤቶች መጨናነቃቸው ተሰምቷል። ጃፓን በ24 ሰዓታት ውስጥ 27 ሺህ ሰዎች በተሐዋሲው በመያዛቸው መንግሥት ስርጭቱን ለመግታት ርምጃዎች ሊወስድ ተዘጋጅቷል። ሮማኒያ ባለፉት ሦስት ወራት ያላየችው በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ብዛት ገጥሞኛል ብላለች። ግሪክ በበኩሏ ተሐዋሲው የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ ከ60 ዓመት በላይ ሆነው ያልተከተቡ ሰዎች 100 ዩሮ መቀጫ እንዲከፍሉ ትዕዛዝ አስተላልፋለች።

Deutschland Bochum | Covid-19 Intensivstation
ምስል Ina Fassbender/AFP/Getty Images

የጀርመን ኅብረተሰብ በእረፍት ቀናት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስን ልማድ ያደረገ እንደመሆኑ ወደ አጎራባች ሃገራት መጓጓዙ ከወረርሽኙ መስፋፋት ጋር በተገናኘ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። ካሳለፍነው የሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ታዲያ አዲስ ድንጋጌ ወጥቶ በርከት ያሉ የጀርመን አጎራባች ሃገራት በወረርሽኙ ስጋት ቀይ መዝገብ ውስጥ ገብተዋል። ጀርመኖች በክረምቱ ወራት ለበረዶ ሸርተቴ ስፖርት የሚያዘወትሯት ኦስትሪያ ቀዳሚዋ ከፍተኛ ስጋት ያለባት ሀገር ተብላለች። ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም፣ ሉክሰምበርግ፤ ኔዘርላንድስ፤ ቼክ ሪፑብሊክ፤  ስዊዘርላንድ፤ ፖላንድ እና ዴንማርክም በተመሳሳይ መዝገብ ገብተዋል። ባጠቃላይ ጀርመን በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም 140 የሚሆኑትን ሃገራት ነው የወረርሽኙ ስጋት አለባቸው በሚል በቀይ መስገቡ ያሰፈረቻቸው። ኮሮና ተሐዋሲ ከተከሰተ ጀምሮ ጀርመን ውስጥ 8 ሚሊየን 122 ሰዎች በተሐዋሲው መያዛቸውን ሮበርት ኮኽ ተቋም አመልክቷል። እንዲያም ሆኖ ሁሉም ታማሚዎች ተመርምረው ተመዝግበዋል ብሎ ድርጅቱ እንደማያምን በመግለጽ ቁጥሩ ከዚህም ሊበልጥ ይችላል ባይ ነው። ሆኖም ግን 7 ሚሊየኑ ከህመሙ ማገገማቸውን መዝግቧል። በነገራችን ላይ ኦክስፋም የተሰኘው የእርዳታ ድርጅት ይፋ ባደረገው ጥናት መሠረት ባለፉት ሁለት የኮሮና ወረርሽኝ ዓመታት 10 የዓለማችን ቱጃሮች ሃብት በእጥፍ አድጓል። ኦክስፋም እንደሚለው የእነዚህ የዓለም ባለጸጎች ሀብት ከ700 ቢሊየን ዶላር ወደ 1,5 ትሪሊየን ዶላር አድጓል። እንደኦክስፋም መረጃ ከሆነው የእነዚህ ቱጃሮች ሀብት ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት በነበሩት ባለፉት 14 ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ መጠን ነው ከፍ ያለው። በተቃራኒው ወረርሽኙ የ160 ሚሊየን ሕዝብን ኑሮ ወደባሰ ድህነት መክተቱን በማመልከትም ባለጸጎቹ ባሉበት ሃገራት ባለው የግብር ስርዓት አማካኝነት የሚገኘው ገንዘብ አቅም ለሌላቸው ሃገራት ክትባቱን ለማቅረብ እንዲውል ጠይቋል።

Deutschland Corona-Pandemie Maskenpflicht
ምስል Jochen Tack/imago images

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ