ዐማርኛ ቋንቋን በአፍሪቃ ደረጃ ለመጠቀም ባለው አቅምና ብቃት ላይ ምሁራዊ ውይይት ተካሄደ
ሐሙስ፣ ግንቦት 24 2015የዐማርኛን ፊደል ለአፍሪቃ ቋንቋዎች በጥቅም ለማዋል ያለው ብቃትና አቅም፣ዐማርኛ በቴክኖሎጂ ዕድገት ጉዞ፣ተግዳሮቶችና መልካም ዕድለኞች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ነው ጉባዔው የተካሄደው።
የድርጅቱ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዕርቁ ይመር ጉባዔውን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር፣ የዐማረኛ ፊደል ለተለያዩ ቋንቋዎች ድምፀት አጠቃቀም፣ ባለው አቅምና ችሎታ በሃገር ውስጥ ላሉ ቋንቋዎች ብቻ ሳይሆን ለአፍሪቃም ጭምር ይረዳል የሚል ንቅናቄ ስላለ ጉባኤው ይህንን ዐሳብ የሚያጠናክርና የሚያግዝ እንደሆነ ገልጸዋል።
ዶክተር ዕርቁ፣በዐማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም ላይ ተከታታይ ጉባኤ ማካሄድ ያስፈለገበትን ምክንያትም እንደሚከተለው አስረድተዋል። "አሁን በዐለም ላይ ካሉት 18 ፊደሎች የግዕዝ ፊደል ወይም ኢትዮጲስ ወይም የዐማርኛ ፊደል በብዙ መንገድ የተሻለና ቀልጣፋ አጠቃቀም ያለው ቫውሉን በላቲን የሚጠቀሙበትን እያንዳንዱ ፊደል በአንድ ላይ የሚይዝ ከፍተኛ የጥበብ ሥራ ውጤት ነው።እና ይሄ ፊደል ምን ያህል ታዋቂነትና ጠቃሚነት እንዳለው፣ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው አንዱ ምክንያታችን።"
ሌላው ምክንያት ደግሞ የዐማርኛ ፊደል ከኢትዮጵያዊነት መገለጫዎች አንዱ በመሆኑ ጭምር እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል። "ሌላው ይህ ተአምራዊ የሆነ ፊደል፣ ከኢትዮጵያዊነት መገለጫዎች አንዱ ነው።ዐድዋን እንደምንኮራበት ሁሉ ፊደላችንም የሚያኮራና የሚያስመሰግን ነው።ለአባቶቻችን ይህን ለፈጠሩ፣ ክብርና ምስጋና ይግባቸው። የሃገራችን ኢትዮጵያዊነት ታሪክ መንፈሣዊም ሆነ ባህላችን በጽሑፍ ተመዝግቦ የሚገኘው በዚሁ ፊደል ነው። የእኛ የሃገራችን ታሪክ ብቻ ሳይሆን የዓለም ሁኔታን የሚገልጽ በዚህ ፊደል ውስጥ ተጠናቅረው በብራና ተጽፈው የሚገኙ ብዙ ስነጽሑፍ ስላሉ ያንንም ማወቁ ጠቃሚነት አለው።
ዐማርኛ ቋንቋ ከአፍሪቃ ህብረት ይፋዊ የስራ ቋንቋዎች አንዱ እንዲሆን በምዕራብ አፍሪቃ ዕውቅ የፊልም ባለሙያ፣ራማቱ ኪያታና በሌሎችም የሚደረግ እንቅስቃሴ እንዳለ ይታወቃል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን ምሁራንም፣ዐማርኛ ቋንቋ አህጉራዊ ቋንቋ የመሆን የላቀ ዐቅም እንዳለው የሚያሳዩ ስራዎችን በመስራት ላይ ናቸው።
ከዚህ አኳያ ምሁራኑ ውስብስብ የሆኑ ሳይንሳዊ ጽንሰ ዐሳቦችን በዐማርኛ ጽፈው ያበረከቱ ሲሆን፣ ከነዚህ መኻከልም የሳይንሳዊ ጹሁፎችን በሦስት መጽሐፍት አዘጋጅተው ያቀረቡት ዶክተር ባህሩ ከሳሁን ይገኙበታል።
ለፊዚክስ ሂሳባዊ ዝግጅት፣ነጠላ ተባራይ ንፍቅ ስነ ስሌት እና ጥርንቅ የተሰኙ የዐማርኛ መፀሐፍት ያበረከቱት ዶክተር ባህሩ፣ በጉባኤው ላይ የምርምር ስራዎቻቸውን ካቀረቡት ምሁራን አንዱ ናቸው።
"እነዚህን ሦስት መጽሃፍት ስጽፍ፣ የዐማርኛ ቃል አላገኘሁም ብዬ፣እንግሊዝኛ ቃል የወሰድኹበት ጊዜ አልነበረም።አግኝቻቸዋለሁ።የዐማርኛ ቃላት አንደኛው ቋንቋው ክህሎት እንዳለው እነዚህን ስጽፍ ነው የተገነዘብኹት፤ችሎታ እንለው።"
በባህል ከበለጸገው የኢትዮጵያ ማኀበረሰብ የተገኘው የግእዝ ፊደል፣ በኮምፒውተር በመታገዝ ከሌላው ዓለም ጋር በቴክኖሎጂ ለሚዋኻድ ስለሚካሄዱ ጥረቶች በጉባኤው ላይ ተወስቷል።
በዚህ ረገድ የላቀ ዕውቀትና አበርክቶ ያላቸው ዶክተር አበራ ሞላ፣ የኢትዮጵያን ዐማርኛ ፊደል አፍሪቃዊ ፊደል ለማድረግ እየተደረጉ ስላሉ ጥረቶች ለጉባኤውተኞቹ አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ ጥረቶች በተመቻቸ መንገድ ሳይሆን ተግዳሮቶች እንዳሉባቸው ተጠቅሷል።
ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲሁም በሃገር ቤት ከጎሳ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ የሚደረጉ ግፊቶችና ፈተናዎች፣ የገንዘብ ድጋፍ አለማግኘትና፣ ጥረቱን አስተባብሮ ሊመራ የሚችል ጠንካራ ማኀበር አለመኖር የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው።
ኢትዮጵያዊነት ድርጅት በዚህ ረገድ፣ባለሙያዎች በአንድነት ማኀበር የሚፈጥሩበት ዕድል ለማመቻቸት ዐሳብ እንዳለው፣ የድርጅቱ ኘሬዝደንት፣በጉባኤዉ መዝጊያ ላይ አስታውቀዋል። "በዚህ በፊደልና በቴክኖሎጂ የተያያዙ ጉዳዮች ላይ፣ የኢትዮጵያዊነት በዐሳብ ደረጃ ተነጋገርንበት እነዚህ የተለያዩ ባለሙያዎች በአንድ ጋር መጥተው ማኀበር ፈጥረው፣በጋራ ቴክኖሎጂውንም ሆነ ማንኛውንም ነገር እንዲያዳብሩት የሚያስችል ፕሮግራም ለማዘጋጀት እያሰብን ነው።"
ታሪኩ ኃይሉ
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ