ዓለምአቀፍ ስፖርት
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 9 2004የለንደን ኦሎምፒክ ጨዋታ እየተቃረበ መጥቶ አንድ መቶ ቀናት ያህል ብቻ ቀርቶት ሳለ አትሌቶችም ለተሳትፎ ለመብቃት በየዘርፉ የሚያደርጉትን ዝግጅትና ፉክክር አጠናክረዋል። እና ያለፈው ስንብትም በየቦታው በተለይ የማራቶን ሩጫ ውድድሮች የተካሄዱበት ነበር። በነዚሁ ውድድሮች ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቶችም ጠንክረው ሲታዩ ተሥፋ ሰጭ ወጤቶችንም ለማስመዝገብ በቅተዋል።
በትናንቱ ሰንበት የሮተርዳም ማራቶን የኢትዮጵያው ተወዳዳሪ የማነ አድሃኔ ግሩም በሆነ የሁለት ሰዓት ከአራት ደቂቃ ከ 47 ሤኮንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ጌቱ ፈለቀም ኬናያዊውን ሞሰስ ሞሶፕን ከኋላው በማስቀረት ሁለተኛ ሆኗል። የማነ አደሃኔ ከማራቶኑ ርቀት የመጀመሪያውን አጋማሽ ለአዲስ ክብረ-ወሰን በሚያበቃ ፍጥነት ቢያቋርጥም በሁለተኛው አጋማሽ ሕልሙ በአንጻራዊ ነፋስ ተገትቷል። እንደዚህም ሆኖ ኬንያዊው ፓትሪክ ማካዉ ባለፈው ዓመት ካስመዘገበው የዓለም ክብረ-ወሰን ላይ ሊድረስ የቀሩት 68 ሤኮንዶች ነበሩ።
በሮተርዳሙ ማራቶን በሴቶችም ኢትዮጵያዊቱ ቲኪ ገላና ስታሸንፍ ሩጫውን ከሁለት ሰዓት ከ 19 ደቂቃ በታች በሆነ ጊዜ በመፈጸም አራተናዋ ሴት አትሌት ሆናለች። ቲኪ ሩጫውን በሁለት ሰዓት ከ 18 ደቂቃ ከ 57 ሤኮንድ ጊዜ ስትፈጽም እስካሁን እንግዲህ የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ከሆነችው ከእንግሊዛዊቱ ከፓውላ ሬድክሊፍና ከሩሢያዊቱ ከሊሊያ ሾቡኮቫ በስተቀር ከርሷ የፈጠነ ሌላ የለም። ኢጣሊያዊቱ ቫሌሪያ ስትራኔኦ ሁለተኛ ስትወጣ ማሪማ ሃሰን ከኢትዮጵያ ሶሥተኛ ሆናለች።
በትናንቱ ዕለት በተጨማሪ ከፓሪስ እስከ ቪየና ሌሎች የማራቶን ሩጫዎችም ሲካሄዱ በፓሪሱ ማራቶን በወንዶች ኬንያዊው ስታንሊይ ቢዎት ባለፈው መጋቢት በጋማሽ ማራቶን ባሸነፈበት በዚያው ቦታ እንደገና ለድል በቅቷል። ቢዎት ያሸነፈው ሁለት የኢትዮጵያ ተፎካካሪዎቹን ራጂ አሰፋንና ሲሣይ ጂሣን በማስከተል ነው። በፓሪሱ ማራቶን የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች የተሻለ ዕድል ሲገጥማቸው ቲርፊ በየነ አሸናፊ ሆናለች። ቲርፊ አትሌት አጸደ ባይሣ ከሁለት ዓመታት በፊት በዚያው በፓሪስ አስመዝግባ የነበረውን ጊዜ ስታሻሽል የቱርኳ ሱልጣን ሃይዳር ሁለተኛ፤ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ማቅዳ ሃሩን ሶሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል።
በኢጣሊያ የሚላኖ ማራቶን ድሉ በወንዶችም ሆነ በሴቶች በሙሉ የኬንያውያን ነበር። በውንዶች ዳኒየል ኪፕሩጋትና ኒክሰን ኩርጋት ቀዳሚ ሲሆኑ ኢትዮጵያዊው ብሩ ገመቹ ሶሥተኛ ውጥቷል። በሴቶችም ኬንያዊቱ ኢሬነ ጄሮቲች ስታሸንፍ ኤማ ካግሊያ ከኢጣሊያ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ነዲያት ሃ/ማርያም ከኤርትራ ሶሥተኛ ሆናለች። በቪየና ማራቶን ደግሞ በወንዶች ኬንያዊው ሄንሪይ ሱጉት ሲያሸንፍ በሴቶች ኢትዮጵያዊቱ ፋጤ ቶላ ባለድል ሆናለች። በቪየና ግማሽ ማራቶን ሃይሌ ገ/ሥላሴ ኬንያዊውን ፊልሞን ሮኖን አስከትሎ ሲያሸንፍ በሴቶችም የብሪታኒያዋ ፓውላ ሬድክሊፍ ኬንያዊቱን ቫሌንቲን ኪቤትን በመቅደም ለድል በቅታለች።
የኢትዮጵያ አትሌቶች ባለፈው ሰንበት በየቦታው ያስመዘገቡትን ግሩም ውጤት ካነሣን የኦሎምፒኩ የአምሥትና የአሥር ሺህ ሜትር ሻምፒዮን ቀነኒሣ በቀለም ትናንት በአየርላንድ የአሥር ኪሎሜትር የመንገድ ሩጫ በዓመቱ ፍጣን ጊዜ ሲያሸንፍ ካለፉት ሁለት ዓመታት የአካል ጉዳቱ በማገገም ወደ ቀድሞ ጥንካሬው በመመለስ ላይ መሆኑን አስመስክሯል። ቀነኒሣ በፍጹም ልዕልና ሁለተኛውን የስፓኙን አያድ ላምዳሣምን በአንድ ደቂቃ ያህል ከኋላው አስቀርቶ ሲያሸንፍ መንገዱን ለማቋረጥ የፈጀበት ጊዜ 27 ደቂቃ ከ 49 ሤኮንድ ነበር።
ቀነኒሣ ከውድድሩ በኋላ እንደገለጸው እንደ ቤይጂንግ ሁሉ በለንደኑ ኦሎምፒክም በአምሥትና በአሥር ሺህ ሜትር የመወዳደር ሃሣብ አለው። ለዚሁ ጥሩ ዝግጅት ለማድረግ እየጣረ መሆኑንም አስረድቷል። ሆኖም አያይዞ እንደገለጸው በቅድሚያ ለኦሎምፒኩ ውድድር ማጣሪያውን ማለፉ ግድ ነው።
ሰንበቱን ከሮተርዳም እስከ ሚላኖ የተካሄደው የማራቶን ሩጫ ውድድር ዛሬ ደግሞ በቦስተን ማራቶን ይቀጥላል። ታዲያ ዋናውን ትኩረት የሳበው ያለፈው ዓመት አሸናፊ ኬንያዊው ጆፍሪይ ሙታይ ሳይሆን የሚጠበቀው ከሰላሣ ዲግሪ ሤንቲግሬድ የማያንስ ጠንካራ ሙቀት ነው። ሙታይ ባለፈው ዓመት ሁለት ሰዓት ከሶሥት ደቂቃ ከሁለት ሤኮንድ ጊዜ በማስመዝገብ ሲያሸንፍ ይሄው ተዓምራዊ ክብረ-ወሰን ስፍራው የዓለምአቀፉን አትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር መስፈርት ስለማያሟላ ዕውቅና ስይሰጠው መቅረቱ የሚታወስ ነው።
ሆኖም ሌላው ኬንያዊ ፓትሪክ ማካዉ በዚያው ዓመት በመስከረም ወር በርሊን ላይ የሃይሌ ገ/ሥላሴን ክብረ-ወሰን ወደ 2 ሰዓት ከሶሥት ደቂቃ ከ 38 ሤኮንድ ማሻሻሉ ሆኖለታል። ለማንኛውም በዛሬው የቦስተን ሙቀት ትልቁ ነገር ቀድሞ ከግብ መድረስ እንጂ ክብር-ወሰን ማስመዝገቡ የሚሆን አይመስልም። በጠቅላላው ከ 26 ሺህ የሚበልጡ ሯጮች ሲመዘገቡ ከሙታይ ቀደምት ተፎካካሪዎች አንዱ ገ/እግዚአብሄር ገ/መድህን እንደሚሆን ይጠበቃል። በሴቶችም አሰለፈች መርጊያና ፍሬሕይወት ዳዶ ከጠንካሮቹ ሯጮች መካከል የሚመደቡት ናቸው።
እግር ኳስ
በአውሮፓ በመጠቃለል ላይ በሚገኘው የቀደምቱ ሊጋዎች የ 2011/2012 የውድድር ወቅት ሂደት በስፓኝ ላ-ሊጋ ሬያል ማድሪድ ባለፈው ሰንበት ስፖርቲንግ ጊዮንን ከኋላ ተነስቶ 3-1 በመርታት በአራት ነጥቦች መምራቱን እንደያዘ ቀጥሏል። ሁለተኛው ባርሤሎናም በበኩሉ ግጥሚያ ሌቫንቴን 2-1 ሲያሸንፍ አሁንም በሻምፒዮንነት ረገድ የሬያል ብቸኛ ተፎካካሪ ነው። ሁለቱ ክለቦች በፊታችን ሰንበት በባርሣ ኖው-ካምፕ ስታዲዮም ለመልስ ግጥሚያ የሚገናኙ ሲሆን የጨዋታው ወጤት በሻምፒዮናው ላይ ትልቅ የወሣኝነት ሚና ሊኖረው ይችላል።
ሁለቱ ክለቦች ለስፓኝ ሻምፒዮንነት በሚታገሉበት በዚህ ወቅት የዋና ዋናጎል አግቢዎቻቸው ፉክክርም እንደጦፈ መቀጠሉ አልቀረም። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በሰንበቱ ግጥሚያ አንድ ጎል አስገብቶ 41 ሲደርስ ሊዮኔል ሜሢም ጥቂት ዘግየት ብሎ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ከፖርቱጋሉ ኮከብ መስተካከሉ ሆኖለታል። ሁለቱ ተጫዋቾች ለብቻቸው እስካሁን በጥቅሉ 82 ጎሎችን ማስቆጠራቸው በጣሙን እንዲደነቁ የሚያደርጋቸው ነው።
በእንግሊዝ የፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር ቼልሢይ ትናንት ቶተንሃም ሆትስፐርን በለየለት ውጤት 5-1 አሸንፎ ለፍጻሜ ሲያልፍ ከ 2007 ወዲህ ለአራተኛ ጊዜ ዋንጫውን የመውሰድ ዕድል ይኖረዋል። በሁለተኛው ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ ሊቨርፑል ኤቨርተንን 2-1 ሲያሸንፍ በሚቀጥለው ወር በዌምብሌይ ስታዲዮም የቼልሢይ የፍጻሜ ተጋጣሚ ነው።
በሌላ በኩል በሣምንቱ የፕሬሚየር ሊግ ውድድር ማንቼስተር ዩናይትድ ትናንት ኤስተን ቪላን 4-0 በመሸኘት የአምሥት ነጥብ አመራሩን አስከብሯል። ቀደም ሲል ሁለተኛው ማንቼስተር ሢቲይም ኖርዊችን 6-1 አሰናብቶ ነበር። ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ ሶሥተኛው አርሰናል ሲሆን አራተኛው ደግሞ ቶተንሃም ሆትስፐር ነው። ከዚያም ኒውካስል ዩናይትድ፤ ቼልሢይ፤ ኤቨርተንና ሊቨርፑል ይከተላሉ።
በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ቦሩሢያ ዶርትሙንድ በአንድ ሣምንት ጊዜ ውስጥ ከባየርንና ከሻልከ ጋር ያካሄዳቸውን ሁለት ከባድ ግጥሚያዎች በድል በመወጣት እንደገና ሻምፒዮን ለመሆን ተቃርቧል። ዶርትሙንድ በፊታችን ቅዳሜ ካሸነፈ ሻምፒዮንነቱን ቀድሞ ሊያረጋግጥ ይችላል። ከማይንስ 0-0 ለተለያየው ለሁለተኛው ለባየርን በአንጻሩ ውድድሩ ሊጠቃለል ሶሥት ግጥሚያዎች ብቻ ቀርተው ሳለ ባቡሩ ከወዲሁ ያመለጠው ነው የሚመስለው።
በኢጣሊያ ሻምፒዮና የሁለተኛው ዲቪዚዮን ተጫዋች የፒርማሪዮ ሞሮሢኒ ሜዳ ውስጥ በልብ ድካም ወድቆ መሞት ሕዝብን ብርቱ ሃዘን ላይ ሲጥል መላው የፌደሬሺኑ ግጥሚያዎች እንዲሸጋሸጉም ተደርጓል። የ 25 ዓመቱ የሊቫርኖ ተጫዋች አሟሟት በአምቡላንሱ መዘግየት ላይ ምርመራን ሲያሳነሣ በስፖርት ውድድሮች ላይ ተጨማሪ የህክምና መሣሪያዎች በቦታው እንዲገኙ የሚደረገውን ጥሪም አጠናክሯል።
ከሮማ እንደተገለጸው የአምቡላንሱ ተሽከርካሪ ለሶሥት ደቂቃዎች የዘገየው የፔስካራ ስታዲየም ድንገተኛ መግቢያ በቦታው በቆመ የፖሊስ መኪና በመታገዱ ነው ተብሏል። የስፖርኛው ሞት ምክንያት ዛሬ በሚካሄድ ምርመራ እንደሚጣራ ይጠበቃል። በተረፈ በፈረንሣይ ሻምፒዮና ሞንትፔሊየርና በኔዘርላንድ የክብር ዲቪዚዮን ውድድርም አያክስ አምስተርዳም በቀደምትነት ይመራሉ።
ቴኒስ
በሂዩስተን የቴኒስ ሻምፒዮና የአርጄንቲናው ሁዋን ሞናኮ ትናንት አሜሪካዊ ተጋጣሚውን ጆን ኢስነርን 6-2,3-6,6-3 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለአምሥተኛ የ ATP ድሉ በቅቷል። በካዛብላንካ ፍጻሜ ግጥሚያም የስፓኙ ፓብሎ አንዱሃር የአገሩን ልጅ አልበርት ራሞስን 6-1,7-6 ሲረታ በባርሤሎና የሴቶች ፍጻሜ ደግሞ ኢጣሊያዊቱ ሣራ ኤራኒም ስሎቫኳን ዶሚኒካ ቺቡልኮቫን 6-2,6-2 አሸንፋለች። ከዚሁ ሌላ በኮፐንሃገን የዓለም ቴኒስ ማሕበር ፍጻሜ ግጥሚያ ጀርመናዊቱ አንጌሊክ ኬርበር የሁለት ጊዜዋን የዴንማርክ ሻምፒዮን ካሮሊን ቮስኒያችኪን 6-4,6-4 በማሸነፍ ከዙፋኗ አውርዳለች። ይህ አስደናቂ ድል ኬርበርን በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ወደ 11ኛው ቦታ ከፍ የሚያደርግ ነው።
አውቶሞቢል
በትናንትናው ዕለት ቻይና ውስጥ የተካሄደው የሻንግሃይ ፎርሙላ-አንድ ግራንድ-ፕሪ እሽቅድድም አሸናፊ ጀርመናዊው የሜርሤደስ ዘዋሪ ኒኮ ሮዝበርግ ሆኗል። ሮዝበርግ በዚህ ውድድር ሲያሸንፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ሜርሤደስም ለዚህ ክብር ሲበቃ ከ 57 ዓመታት በኋላ እንዲሁ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው።
ሁለቱ የብሪታኒያ ዘዋሪዎች ጄንሰን ባተንና ሉዊስ ሃሚልተን ሁለተኛና ሶሥተኛ ሲወጡ ያለፉት ሁለት ዓመታት ሻምፒዮን ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል በአምሥተኝነት ተወስኗል። በአጠቃላይ ነጥብ ሉዊስ ሃሚልተን በ 45 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ጄንሰን ባተን በ 43 ሁለተኛ ነው፤ የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ ደግሞ በሶሥተኝነት ይከተላል።
በተረፈ በእግር ኳስ ለማጠቃለል ነገና ከነገ በስቲያ በዚህ በአውሮፓ የሻምፒዮናው ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። በነገው ምሽት ባየርን ሚዩኒክ ውስጥ ሬያል ማድሪድን የሚያስተናግድ ሲሆን የቡንደስሊጋውን ሻምፒዮንነት ላጣው የጀርመን ክለብ ወጤቱ በጣሙን ወሣኝ ነው። ለስፓኝ ሻምፒዮንነት የተቃረበው ሬያል ማድሪድ በአንጻሩ የተሻለው የመንፈስ ጥንካሬ ያለው ይመስላል።
ለማንኛውም ሁለቱ ታላላቅ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር በግማሽ ፍጻሜ እርስበርስ ሲገናኙ ለአምሥተኛ ጊዜ ሲሆን ጨዋታው ትግል እንደማይለየው ከወዲሁ ግልጽ ነገር ነው። የባየርን አምበል ፊሊፕ ላምም ይህንኑ ዕምነት ነው ያንጸባረቀው።
«ሁለቱ ክለቦች በመገናኘታቸው የሚቻለው መደሰት ብቻ ነው። ግሩም ጨዋታ እንጠብቃለን። በሻምፒዮናው ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ ጥሩ ጨዋታ እንደሚታይ ጨርሶ ጥርጥር የለውም። ለአንድ ተጫዋች ደግሞ ከዚህ የተሻለ ነገር አይኖርም። እናም ደስታው እኛንና አሰልጣኞቹን ብቻ ሣይሆን ጋዜጠኞችንና ደጋፊዎችን ጭምር በሙሉ የሚጠቀልል ነው»
በማግሥቱ ረቡዕ ሁለተኛው ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ በቼልሢይና በባርሤሎና መካከል የሚካሄድ ሲሆን ይህም በጉጉት ነው የሚጠበቀው። የመልስ ግጥሚያቸውን በገዛ ሜዳቸው የሚያካሂዱት ሁለቱ የስፓን ክለቦች ለፍጻሜ ከደረሱ ይሄው ለፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ወቅታዊ ጥንካሬ ተጨማሪ ማረጋገጫ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም።
መሥፍን መኮንን
ነጋሽ መሀመድ