1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለምአቀፍ ስፖርት

ሰኞ፣ ኅዳር 17 2005

ያለፈው ሣምንት ታላቅ የስፖርት ዜና በተለይም የወጣቱ ጀርመናዊ የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል ዘዋሪ የዜባስቲያን ፌትል በተከታታይ ለሶሥተኛ ጊዜ ትናንት በብራዚል እሽቅድድም የዓለም ሻምፒዮን መሆን ነው።

https://p.dw.com/p/16q8j
ምስል picture-alliance/dpa

ያለፈው ሣምንት ታላቅ የስፖርት ዜና በተለይም የወጣቱ ጀርመናዊ የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል ዘዋሪ የዜባስቲያን ፌትል በተከታታይ ለሶሥተኛ ጊዜ ትናንት በብራዚል እሽቅድድም የዓለም ሻምፒዮን መሆን ነው። ብራዚልን ካነሣን አገሪቱ ለመጪው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ መስተንግዶ በምታደርገው ዝግጅት አዲስ ጅማሮ በመሻት ባለፈው አርብ የብሄራዊ ቡድኗን አሠልጣኝ ሜኔዜስን ማሰናበቷም ሰፊ ትኩረትን መሳቡ አልቀረም። እነዚህ ሁለት ጉዳዮች ዘግየት ብለን በሰፊው የምንመለስባቸው ናቸው።

Bildergalerie Africa Cup of Nations Äthiopien
ምስል Getty Images/AFP

በቅድሚያ በአፍሪቃ እግር ኳስ ላይ እናተኩርና ኢትዮጵያ ኡጋንዳ ውስጥ በሚካሄደው የምሥራቅና ማዕከላዊ አፍሪቃ ፌደሬሺኖች ማሕበር የሴካፋ ዋንጫ ውድድር ባለፈው ቅዳሜ ደቡብ ሱዳንን 1-0 በማሸነፍ የተሳካ ጅማሮ ለማድረግ በቅታለች። 36ኛው የአካባቢ ዋንጫ ውድድር ነጻነቷን ካወጀች ዓመት ከመንፈቅ ገደማ ለሆናት ለደቡብ ሱዳን የመጀመሪያው ይፋ ግጥሚያ መሆኑ ነበር። ከዚህ አንጻር ጠባብ በሆነ 1-0 ውጤት ብቻ መረታቷ ምናልባትም ሊያኮራት የሚገባው ነው።

ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአንጻሩ ድሉ ወደ ተከታዩ ዙር የመዝለቁን ዕድል የሚያጠናክር ነው። በነገራችን ላይ በካምፓላው ናምቦሌ ስታዲዮም በተካሄደው ግጥሚያ ብቸኛዋን ጎል በ60ኛዋ ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ዮናታን ከበደ ነበር። የአካባቢው ውድድር በፊታችን ጥርና የካቲት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ለሚካሄደው የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር አቅም መፈተሻም ሲሆን ለአንዳንድ አዳዲስ ተጫዋቾች መመረጥም በር ከፋች ነው።                                                                                                               

በዚሁ በምድብ-አንድ ውስጥ አስተናጋጇ ኡጋንዳ ኬንያን በተመሳሳይ 1-0 ውጤት ስትረታ አሁን ከኢትዮጵያ ጋር ምድቡን በቀደምትነት ትመራለች። በነገው ዕለት ኢትዮጵያ ያለፈው የአፍሪቃ ዋንጫ አሸናፊ ከሆነችው ከኡጋንዳ የምትጋጠም ሲሆን ደቡብ ሱዳን ደግሞ ከኬንያ ትገናኛለች። ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ይሄው የነገው ግጥሚያ የአስተናጋጇ አገር ጥንካሬ ሲታሰብ ፈታን እንደሚሆን ጨርሶ አያጠራጥርም።

በምድብ-ሁለት ውስጥ ታንዛኒያ፣ ሱዳን፣ ቡሩንዲና ሶማሊያ የተደለደሉ ሲሆን በትናንትናው ዕለት የመጀመሪያ ግጥሚያ ቡሩንዲ ሶማሊያን 5-1 ስታሸንፍ ታንዛኒያም ሱዳንን 2-0 ረትታለች። ቡሩንዲና ታንዛኒያ በእኩል ነጥቦች የምድቡ መሪዎች ሲሆኑ ሁለቱ ቡድኖች ከነገ በስቲያ እርስበርስ ይገናኛሉ። ሌላው የምድቡ ግጥሚያ በሶማሊያና በሱዳን መካከል የሚካሄደው ይሆናል።

ምድብ-ሶሥት ማላዊ፣ ኤርትራ፣ ሩዋንዳና ዛንዚባር የሚገኙበት ሲሆን በዛሬው ዕለት ዛንዚባር ከኤርትራ፤ እንዲሁም ሩዋንዳ ከማላዊ ይጋጠማሉ። ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያልፉት የየምድቡ አንደናኛ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ሁለት ጠንካራ ሶሥተኛች ናቸው። ውድድሩ እስከፊታችን ሕዳር 29 ቀን የሚዘልቅ ሲሆን ከተከታዩ ሩብ ፍጻሜ አንስቶ እስከ ፍጻሜው ድረስ ግጥሚያዎቹ የሚካሄዱት እንደተለመደው በጥሎ ማለፍ መልክ ነው። መለስ ብሎ ለማስታወስ ያህል ኢትዮጵያ የምሥራቅና ማዕከላዊ አፍሪቃ ፌደሬሺኖች ዋንጫን እስካሁን ሶሥት ጊዜ አግኝታለች።

Olympia London 2012 100 Meter Männer Usain Bolt
ምስል Reuters

አትሌቲክስ

ዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር IAAF ባለፈው ቅዳሜ ባርሤሎና ላይ በተካሄደ የክብር ስነ ስርዓት ዩሤይን ቦልትንና አሊይሰን ፌሊክስን የዓመቱ ድንቅ አትሌቶች ብሎ ሰይሟል። ጃማይካዊው ቦልት ባለፈው ነሐሴ ወር የለንደን ኦሎምፒክ በ 100፣ በ 200 እና በአራት ጊዜ 100 ሜትር ሩጫዎች በአስደናቂ ውጤት የወርቅ ሜዳሊያዎች ተሸላሚ ሲሆን ሽልማቱን አራት ጊዜ ሲያገኝም የመጀመሪያው አትሌት መሆኑ ነው።                                                                                                            

ዩሤይን ቦልት አራት ዓመታት ቀደም ሲል በቤይጂንግ ኢሎምፒክም የሶሥት ወርቅ ሜዳሊያዎች አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል። አሜሪካዊቱ አሊይሰን ፌሊክስም ለንደን ላይ በ 200 ሜትር ከ 27 ዓመታት በፊት በ 1985 በምሥራቅ ጀርመን ተመዝግቦ የነበረውን ክብረ-ወሰን በመስበር ስታሸንፍ በአራት ጊዜ መቶ ሜትር ሩጫም የአሸናፊው ቡድን አካል ነበረች። እጅግ ጠንካራ አትሌት ናት።                                                                                                         

ከዚሁ ሌላ ኬንያዊው ዴቪድ ሩዲሻ በ 800 ሜትር ሩጫ ለንደን ላይ ባስመዘገበው አዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን ዕውቅና ሲያገኝ የትሪኒዳድና ቶባጎ የጦር ውርወራ ወርቅ ተሸላሚ  ኬሾም ዋልኮትና የባሃማሱ ሯጭ አንቶኒክ ስትራሃን ደግሞ መጤዎቹ ከዋክብት ተብለው ተሰይመዋል። ለዴቪድ ሩዲሻ ሽልማቱ ከ 2010 ወዲህ ሁለተኛው መሆኑ ነው። ለማስታወስ ያህል የዓመቱ ድንቅ አትሌት በመባል እስካሁን በዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ከተመረጡት ታላላቅ ስፖርተኞች መካከል ከኢትዮጵያ ሃይሌ ገ/ሥላሴ፣ ቀነኒሣ በቀለና መሠረት ደፋርም ይገኙበታል።

Formel 1 Großer Preis von Brasilien
ምስል Getty Images

የአውቶሞቢል እሽቅድድም

ጀርመናዊው ዘዋሪ ዜባስቲያን ፌትል ትናንት ብራዚል ውስጥ በተካሄደ የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም በተከታታይ ለሶሥተኛ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ሊሆን በቅቷል። በዚሁ በዓመቱ ማጠቃለያ እሽቅድድም በፌትልና በዋነኛ ተፎካካሪው በፌርናንዶ አሎንሶ መካከል የጦፈ ፉክክር ሲታይ የስፓኙ ተወላጅ በአንደኝነት ከግቡ መግባቱ በመጨረሻ አልጠቀመውም። ዜባስቲያን ፌትል በአንጻሩ እሽቅድድሙን በስድሥተኝነት ሲፈጽም  በሶሥት ነጥቦች ልዩነት ቁንጮ መሆኑ ተሳክቶለታል። በአጠቃላይ ነጥብ፤ ዜባስቲያን ፌትል 281፤ ፌርናንዶ አሎንሶ 278!

የ 25 ዓመቱ ጀርመናዊ በተከታታይ ድሉ አቻ ያልታየለት ወጣት ዘዋሪ ሆኖ ስሙን በታሪክ ማሕደር ውስጥ ሲያሰፍር የሰባት ጊዜው የዓለም ሻምፒዮን የሚሻኤል ሹማኸር አልጋ ወራሽ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ሹማኸርን ካነሣን ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት ትቶት ወደነበረው ውድድር የተመለሰው ጀርመናዊ ወደ ቀድሞ ጥንካሬው ሊመለስ ባይችልም ትናንት ሰባተኛ በመውጣት ከአውቶሞቢሉ ስፖርት መድረክ ስንብት አድርጓል። ሚሻኤል ሹማኸር ቀደም ባሉ ድሎቹ ስለ ፎርሙላ-አንድ በተወራ ቁጥር ስሙ ሲነሣ የሚኖር ታላቅ አሽከርካሪ ነው፤ ጥሩውን እንመኝለታለን።

Bundesliga 24.11.12 Bayern Hannover
ምስል picture alliance / dpa

ቡንደስሊጋ/የአውሮፓ ሊጋዎች

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ የተነጠቀውን አመራር መልሶ ሲይዝ በዚህ በጀርመን ደግሞ ባየርን ሙንሽን ሃያል እንደሆነ ቀጥሏል። በስፓኝ ላ-ሊጋ እንጀምርና ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ሬያል ማድረድ ትናንት በቤቲስ 1-0 ሲረታ ይሄው ሶሥተኛ ሽንፈቱ ከቀደምቱ ከባርሤሎናና ከአትሌቲኮ ማድሪድ ይበልጥ እንዲርቅ ነው ያደረገው። ባርሣ ሌቫንቴን 4-0 ሲረታ አትሌቲኮም እንዲሁ ሤቪያን በተመሳሳይ ውጤት አሸንፏል። ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ ባርሤሎና በ 37 ነጥቦች በአንደንነት የሚመራ ሲሆን አትሌቲኮ በ 34 ሁለተኛ፣ ሬያል ማድሪድ በ 26 ሶሥተኛ ነው። በዚሁ በሬያልና በባርሣ መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ 11 ከፍ ብሏል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ሢቲይ ከቼልሢይ 0-0 በመለያየቱ የተነሣ የከተማ ተፎካካሪው ማንቼስተር ዩናይትድ ኩዊንስ-ፓርክ-ሬንጀርስን 3-1 አሸንፎ አመራሩን መልሶ ለመያዝ ችሏል። ማኒዩ ከ 13 ግጥሚያዎች በኋላ 30 ነጥቦች ሲኖሩት ሢቲይ በአንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ ይከተላል፤ ይገርማል ያለፈውን የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር አሸናፊ ቼልሢይን ከኋላው አስከትሎ ሶሥተኝነቱን የያዘው ዝቅተኛው ክለብ ዌስት-ብሮንዊች-አልቢዮን ነው። ኤቨርተን አምሥተኛ፤ አርሰናል ስድሥተኛ!

በጀርመን ቡንደስሊጋ ከሣምንት ሣምንት ፍጹም የበላይነቱን እያሰረገጠ መራመድ የቀጠለው ባየርን ሙንሽን ባለፈው ሰንበትም በተለየ ልዕልና ሃኖቨርን 5-0 አከናንቦ ሲሸኝ አመራሩን ከሰባት ወደ ዘጠኝ ነጥቦች ሊያሰፋ በቅቷል። ያለፉት ሁለት ዓመታት ሻምፒዮን ዶርትሙንድ ማይንስን 2-1 በመርታታት ለተከታታይ ሶሥተኛ ድል ሲበቃ በዚሁ ወደ ሁለተኛው ቦታ ከፍ ብሏል። ሻልከ በአንጻሩ ከፍራንክፉርት 1-1 በመለያየቱ ወደ ሶሥተኛው ቦታ መንሸራተቱ ግድ ነው የሆነበት።

ከዚህ ሌላ በኢጣሊያ ሻምፒዮና ጁቬንቱስ በአጭር ጊዜ ሁለተኛ ሽንፈት ቢደርስበትም አመራሩን ግን እንደያዘ ቀጥሏል። ጁቬንቱስ በኤ ሲ ሚላን 1-0 ሲረታ አሁን ከሁለተኛው ከኢንተር ሚላን የሚለዩት አራት ነጥቦች ብቻ ናቸው። በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን በ 26 ነጥቦች አመራሩን መልሶ ሲይዝ ሆኖም ኦላምፒክ ማርሤይ አንድ ጨዋታ ጎሎት በአቻነት ይከተለዋል። በኔዘርላንድ የክብር ዲቪዚዮን ደግሞ አይንድሆፈን በአመራሩ ሲቀጥል በፖርቱጋል ሻምፒዮናምፖርቶና ቤንፊካ ቁንጮ እንደሆኑ ነው።

London 2012 Fussball Brasilien Südkorea
ምስል Reuters

ከአውሮፓ ወደ ደቡብ አሜሪካ እንሻገርና ብራዚል የምታሰተናግደው የ 2014 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ዓመት ከመንፈቅ ገደማ ቀርቶት ሳለ የብሄራዊ ቡድኗን አሠልጣን ማኖ ሜኔዜስን ከሁለት ዓመታት የሙከራ ዘመን በኋላ አሰናብታለች። የብራዚል ብሄራዊ ቡድን እንደ ሜኔዜስ የአሠልጣኝነት ዘመን ግርማ ሞገሱን ያጣበት ጊዜ መኖሩ ጨርሶ አይታወስም። የቀድሞው ኮከብ ተጫዋች ሮማሪዮ ዕለቱ በርችት ተኩስና በፈንጠዝያ ሊከበር የሚገባው ታሪካዊ ነው ሲል ነው በአሠልጣኙ መባረር የተሰማውን ደስታ የገለጸው። በርካታ ኳስ አፍቃሪዎችም በአሠልጣኙ መባረር የተሰማቸውን ደስታ በአደባባይ ገልጸዋል።

እርግጥ ብሄራዊው ቡድን ካለፉት ስምንት ግጥሚያዎቹ ስድሥቱን በማሸነፍ የመነቃቃት ባህርይ ማሳየቱ አልቀረም። ይሁን እንጂ ብራዚል የጥንቱ ብራዚል እንዳልሆነች ዓለም በግልጽ ያየው ነገር ነው። የለውጡ ምክንያት ምናልባትም ይህ ሣይሆን አልቀረም። እናም በሁኔታው መቀጠል አልተቻለም። ለማንኛውም ውሣኔው ዘግይቶ አለመምጣቱ ጠቃሚ ነገር ነው። አዲሱ አሠልጣኝ በፊታችን ጥር ወር የሚሰየም ሲሆን ከዕጩዎቹ መካከል ብራዚልን በ2002 የጃፓን/ደቡብ ኮሪያ የዓለም ዋንጫ ውድድር ወቅት ለአምሥተኛ ድል ያበቁት ፌሊፔ ስኮላሪም አንዱ ናቸው።                       

ግን ማንም ሃላፊነቱን ይረከብ አገሪቱ የዓለም ዋንጫ አስተናጋጅ እንደመሆኗ መጠን የሚገጥመው ግፊት ቀላል አይሆንም። ለብራዚል ከአንደኝነት፤ ከዋንጫ ባለቤትነት ሌላ ምርጫ የለምና። 

መሥፍን መኮንን