ዓለምአቀፍ ስፖርት
ሰኞ፣ መጋቢት 30 2005በወንዶች ኬንያዊው ፔተር ሶሜ አንደኛ ሲወጣ ያሸንፋል ተብሎ የተጠበቀው ታደሰ ቶላ በሁለተኝነት ተወስኗል። ታደሰ ቶላ ከሶሥት ዓመታት በፊት የፓሪስ ማራቶን አሸናፊ አንደነበር የሚታወስ ነው። የትናንቱ ባለድል ሶሜ ሩጫውን የፈጸመው በ 2 ሰዓት ከ 5 ደቂቃ ከ 38 ሤኮንድ ጊዜ ነበር። በዚሁ ሩጫ ሌላው የኬንያ ተወዳዳሪ ኤሪክ እንዲየማ ደግሞ ሶሥተኛ ሊሆን በቅቷል።
በሴቶች ድሉ የኢትዮጵያ ሲሆን ፈይሤ ታደሰና መሪማ መሐመድ ኬንያዊቱን ኦይኒስ ኪርዋን ከኋላቸው በማስቀረት አንደኛና ሁለተኛ ሆነዋል። ድንቅነሽ ተፈራም አራተኛ ወጥታለች። በፓሪሱ ማራቶን ባቻ መገርሣ፣ ሣህሌ ዋርጋ፣ አብርሃም ግርማና ገዛኸኝ አለማየሁ በወንዶች፤ እንዲሁም ድንቅነሽ ተፈራና ፋንቱ ጂማ ከመጀመሪያዎቹ አሥር ፈጣን ሯጮች መካከል መሆናቸው የኢትዮጵያን አትሌቶች ጥንካሬ ያመለከተ ነበር።
ፓሪስ ውስጥ ለዘብ ባለ የጸደይ አየር በተካሄደው የየከተማ ማራቶን ላይ የተሳተፉት ሰዎች ቁጥር 50 ሺህ ገደማ የሚጠጋ ነበር። ስለ ፓሪ ሱ ማራቶንና ስለ ኢትዮጵያ አትሌቶች አኩሪ ውጤት በስፍራው የተገኘችውን የፓሪስ ወኪላችንን ሃይማኖት ጥሩነህን በቅርቡ በስልክ አነጋግሬ ነበር።
ባለፈው ሰንበት ከፓሪሱ ማራቶን ሌላ በበርሊንና በፕራግም ግማሽ ማራቶን ሩጫዎች ተካሂደው ነበር። በ 33ኛው የበርሊን ግማሽ ማራቶን በወንዶች ኬንያዊው ጄኮብ ኬንዳጎር ሁለት የአገሩን ልጆች አስከትሎ በስፍራው ሬኮርድ ጊዜ ሲያሸንፍ በሴቶችም ኬንያውያቱ ሄላህ ኪፕሮፕና ፊል ኦንጎሪ ቀደምቱ ሆነዋል። ኬንያ በወንዶች በበርሊኑ ግማሽ ማራቶን ከ 2000 ዓ-ም ወዲህ ለ 11ኛ ጊዜ አሸናፊ መሆኗ ነው።
ባለፈው ቅዳሜ ቼክ ሬፑብሊክ ርዕሰ-ከተማ ፕራግ ላይ ተካሂዶ በነበረ ግማሽ ማራቶን ሩጫ ደግሞ በወንዶች ድሉ የኤርትራውያን ሲሆን ዘረሰናይ ታደሰና አማኑኤል መሰል ኬንያዊውን ጆን ኪፕሣንግን ቀድመው አሸንፈዋል። በሴቶች ኬንያዊቱ ግሌዲይስ ቼሬኖ ስታሸንፍ ወርቅነሽ ደገፋም ሩጫውን በሁለተኝነት ፈጽማለች።
እግር ኳስ
በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር በጀርመን ቡንደስሊጋ የጀርመኑ ቀደምት ክለብ ባየርን ሙንሺን ባለፈው ሰንበት ለ 23ኛ ጊዜ የአገሪቱ ሻምፒዮን ሆኗል። የጀርመኑ ሬኮርድ ሻምፒዮን ውድድሩ ሊያበቃ ገና ስድሥት ጨዋታዎች ቀርተው ሳለ ለዚህ ድል ሲበቃ ይህም አዲስ የቡንደስሊጋ ክብረ-ወሰን ነው። ባየርን የዘንድሮውን የቡንደስሊጋ ድል በሃያ ነጥቦች ልዩነት በመምራት ሲያረጋግጥ በፌደሬሺኑ ዋንጫና በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር የማሸነፍ ዕድሉን እንደያዘም ቀጥሏል።
በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮንም ባርሤሎና ሬያል ማዮርካን 5-0 በማሸነፍ በአምሥት የውድድር ወቅቶች ለአራተኛው የዋንጫ ባለቤትነት እየተቃረበ ነው። ቡድኑ በወቅቱ ሊጋውን በ 13 ነጥቦች ልዩነት የሚመራ ሲሆን ከእንግዲህ የሚደረስበት መሆኑ ያጠራጥራል። ያለፈው ሻምፒዮን ሬያል ማድሪድ ምንም እንኳ ሌቫንቴን 5-1 በማሸነፍ ጥንካሬ ቢያሣይም ዘንድሮ ሁለተኝነቱን ወደደም ጠላ ከወዲሁ መቀበሉ ግድ ነው።
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ ማንቼስተር ሢቲይን በ 15 ነጥቦች ልዩነት ከኋላው ጥሎ የሚመራ ሲሆን ሁለቱ ክለቦች ዛሬ ማምሻውን እርስበርስ የሚያደርጉት ግጥሚያ ሁኔታውን እምብዛም የሚለውጥ አይሆንም። በተቀረ በኢጣሊያ ሊጋ ጁቬንቱስ ናፖሊን በዘጠኝ ነጥቦጥ ልዩነት አስከትሎ የሚመራ ሲሆን በፈረንሣይ ሻምፒዮናም ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን በሰባት ነጥቦች ብልጫ ቀደምቱ ነው። በኔዘርላንድና በፖርቱጋል ሻምፒዮና በአንጻሩ በአመራሩ ላይ ያለው ልዩነት ጠባብ በመሆኑ ገና ምኑም የልለየለትም።
ቴኒስ
በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ቀደምቷ የሆነችው አሜሪካዊት ሤሬና ዊሊያምስ በቻርልሰተን-ደቡብ ካሮላይና የዓለም ቴኒስ ማሕበር ፍጻሜ ግጥሚያ ትናንት የሰርቢያ ተጋጣሚዋን የለና ያንኮቪችን በመጀመሪያው ምድብ ከተሸነፈች በኋላ በጥንካሬ በመመለስ በ 2-1 ውጤት ለመርታት በቅታለች። ለሤሬና ዊሊያምስ 49ኛው የዓለም ቴኒስ ማሕበር ውድድር ድል መሆኑ ነው።
በሜክሢኮ-የሞንቴሪይ ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ ሩሢያዊቱ አናስታዚያ ፓብሉቼንኮቫ የጀርመን ተጋጣሚዋን አንጌሊክ ኬርበርን 4-6,6-2,6-4 በሆነ ውጤት ለማሸነፍ በቅታለች።
በእግር ኳስ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድሮች ለማጠቃለል ነገና ከነገ በስቲያ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ሩብ ፍጻሜ የመልስ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። በነገው ምሽት በመጀመሪያው ግጥሚያ ባዶ-ለባዶ ተለያይተው የነበሩት ቦሩሢያ ዶርትሙንድና ማላጋ የሚጋጠሙ ሲሆን በገዛ ሜዳው የሚጫወተው ዶርትሙንድ ወደ ግማሽ ፍጻሜው የማለፍ የተሻለ ዕድል ያለው ይመስላል። ሁለተኛው የምሽቱ ግጥሚያ በጋላታሣራይ ኢስታምቡልና በሬያል ማድሪድ መካከል የሚካሄደው ሲሆን በመጀመሪያው ጨዋታ 3-0 አሸንፎ የነበረው ሬያል ታላቅ የማለፍ ዕድል አለው።
በማግሥቱ ረቡል ጁቬንቱስ ቱሪን ባየርንን የሚያስተናግድ ሲሆን በመጀመሪያው ግጥሚያ የደረሰበትን የ 2-0 ሽንፈት ለማረም በጣም መታገል ሳይኖርበት አይቀርም። የስፓኙ ቀደምት ክለብ ባርሤሎና ደግሞ ከፓሪስ-ሣንት-ዠርማን 2-2 ወጥቶ መመለሱ ሲታወስ በሜዳው በሚያካሂደው ግጥሚያ ለድል ለመብቃት የተሻለው ዕድል ያለው ነው የሚመስለው።
ለማንኛውም በሣምንቱ መካከል ወደ ግማሽ ፍጻሜው የሚያልፉት አራት ክለቦች ማንነት ይለይለታል። በአፍሪቃ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ደግሞ የኢትዮጵያው ቀደምት ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ የማሊውን ጆሊባን በሜዳው 2-0 ከረታ በኋላ ትናንት በመልሱ ግጥሚያ 1-1 ሲለያይ ወደተከታዩ ዙር ማለፉ ተሳክቶለታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በሶሥተኛው ዙር ቀጣይ ግጥሚያው የሚገናኘው ከግብጹ ዛማሌክ ጋር ነው።
መሥፍን መኮንን