1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለሊቲየም የሚደረገው ሩጫ በአፍሪካ ሙስናን እያባባሰ ነው?

ረቡዕ፣ ኅዳር 12 2016

የኢትዮጵያ መንግሥት በማዕድን ቁፋሮ ተስፋ ካደረገባቸው ሊቲየም የሞባይል ስልኮች እና የኤሌክትሪክ መኪኖች ባትሪ ለማምረት ቁልፍ ግብዓት ነው። በዘርፉ የተደረጉ ምርመራዎች የአፍሪካን ሊቲየም ለመቆጣጠር የሚደረገው እሽቅድምድም ሙስናን እያስፋፋ፣ ነባር ማኅበረሰቦችን እና ከባቢን እየጎዳ እንደሆነ አሳይተዋል።

https://p.dw.com/p/4ZEaj
በዚምባብዌ ጎሮሞኒ የማዕድን ማውጪያ ቡልዶዘር በሥራ ላይ
በዚምባብዌ የሚገኘው የማዕድን ማውጪያ በዓለም ትልቁ የሊቲየም ዓለት ክምችት ያለበት እንደሆነ ይታመናልምስል Tafadzwa Ufumeli/Getty Images

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ ለሊቲየም የሚደረገው ሩጫ በአፍሪካ ሙስናን እያባባሰ ነው?

በናሚቢያ የሚገኘው የቻይና የሊቲየም ማዕድን ማውጫ ሠራተኞች ለወራት በአስቀያሚ አኗኗራቸው እና ደሕንነቱ ያልተጠበቀ የሥራ ሁኔታ ቅሬታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ዚንፌንግ ኢንቨስትመንትስ በተባለ የቻይና ኩባንያ እጅ የሚገኘው የኡዊስ ማዕድን ማውጫ ከናሚቢያ ብራንድበርግ ተራሮች ግርጌ የሚገኝ ነው። 

የናሚቢያ የሠራተኞች ማኅበር ባለፈው ነሐሴ ይፋ ያደረገው ምርመራ በማዕድን ማውጫው የተቀጠሩ የአካባቢው ሰዎች ከቆርቆሮ በተሰሩ ትናንሽ ሞቃታማ ቤቶች እንደሚኖሩ አጋልጧል። ከቆርቆሮ የተቀለሱት ቤቶች ማቀዝቀዣ እንኳ የላቸውም። የመጸዳጃ እና የመታጠቢያ ክፍሎች ያለ መከለያ በመደርደራቸው ሠራተኞች የግል ጉዳያቸውን ሲፈጽሙ ነጻነት እንደሌላቸው የሠራተኛ ማኅበሩ ነቅፏል። 

በንጽጽር ቻይናውያን የማዕድን ማውጫው ሠራተኞች ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው ምቹ ክፍሎች እና ጥሩ መጸዳጃ ቤቶች አሏቸው። የቻይናው ዚንፌንግ ኢንቨስትመንትስ ኩባንያ የሠራተኞች ደሕንነት ለመጠበቅ የሚያስፈልጉ አልባሳት እንዳላቀረበ፤ ለናሚቢያውያን ሠራተኞች በቂ የደሕንነት መጠበቂያ እርምጃዎች ገቢራዊ እንዳላደረገ ማኅበሩ ተችቷል። 

ሞሪታኒያን ወደ አጎዋ ስትመለስ የኢትዮጵያ ውትወታ መልስ ሳያገኝ ቀረ

የቻይናው ዚንፌንግ ኢንቨስትመንትስ ኩባንያ የገጠመው ውዝግብ ግን ይኸ ብቻ አይደለም። ኩባንያው የኡዊስ ማዕድን ማውጫን ፈቃድ ያገኘው በሙስና እንደሆነ መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገ “ግሎባል ዊትነስስ” የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ይፋ ያደረገው አዲስ ምርመራ አጋልጧል። ምርመራው የቻይናው ኩባንያ የማዕድን ማውጫውን የገነባው ለባሕላዊ ማዕድን አውጪዎች በተሰጠ ፈቃድ ነው የሚል ውንጀላ ጭምር አቅርቧል። 

ለንደን በኤሌክትሪክ የሚሰራ መኪና
በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ፍላጎት ሲጨምር የሊቲየም ገበያም አብሮ አሻቅቧልምስል John Walton/PA Wire/picture alliance

የማዕድን ማውጪያውን ለአነስተኛ ሥራዎች በሚሰጥ ፈቃድ ኩባንያው አለማ ማለት የሊቲየም ማዕድን ክምችቱን ከእጁ ለማስገባት “እጅግ ዝቅተኛ ገንዘብ” መክፈሉን እንደሚያሳይ ምርመራው አትቷል። ከዚህ በተጨማሪ የቻይናው ኩባንያ የተከተለው መንገድ የተወሰኑ የአካባቢ ጥበቃ ደንቦችን ገሸሽ ለማድረግ እንደፈቀደለትም ሪፖርቱ ይጠቁማል። 

'አሳሳቢው' የሙስና ይዞታ

የብሪታኒያው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ምርመራ ከናሚቢያ በተጨማሪ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በዚምባብዌ በሚገኙ የሊቲየም ማውጫዎች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ ሙስና፣ የሰዎች ማፈናቀል እና የሠራተኞች ደሕንነት የማይጠበቅባቸው አሰራሮችን ጭምር የሰነደ ነው። 

ዘገባውን ካጠናቀሩት ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት የግሎባል ዊትነስ ከፍተኛ መርማሪ ኮሊን ሮበርትሰን ባለፉት አስርት ዓመታት "በአፍሪካ የማዕድን ዘርፍ ከሙስና ጋር የተሳሰረ” እንደሆነ ይናገራሉ። መርማሪው እንደሚሉት በአፍሪካ በተዘረጋው አሰራር ማዕድን በሚወጣባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ማኅበረሰቦች የትርፍ ድርሻቸውን አያገኙም። ተቋማቸው በሠራው ምርመራ ይኸ አካሔድ በሊቲየም ማዕድን ቁፋሮ ዘርፍ የሚቀጥል እንደሆነ እንደደረሰበት የሚናገሩት ኮሊን ሮበርትሰን “ይኸ በጣም አሳሳቢ ነው” ባይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “የወለድ ክፍያ ያለበትን ብድር” በተመለከተ የጻፈው ደብዳቤ የሕጋዊነት ጥያቄ ተነሳበት

ግሎባል ዊትነስስ በሰራው ምርመራ “አሳሳቢ የሙስና ጉዳዮች መኖራቸውን” እንደደረሰበት የሚናገሩት ኮሊን ሮበርትሰን “ለምሳሌ ያክል የፖለቲካ ሰዎች በሊቲየም ማውጪያዎች እጃቸውን ያስገባሉ። በአንዳንድ ሀገሮች ተፈጽመዋል በሚባሉ ሙስናዎች ምክንያት አንዳንድ ኩባንያዎች ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል” ሲሉ ተናግረዋል። “እስካሁን ድረስ እኛ የተመለከትናቸው የሊቲየም ፕሮጀክቶች ለማኅበረሰቡ በአንጻራዊነት እጅግ አነስተኛ አዎንታዊ ጥቅም ነው ያላቸው” በማለት ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። 

ለሊቲየም የሚደረግ ሩጫ

ለታዳሽ ኃይል አብዮት “ነጭ ወርቅ” የሚል የቁልምጫ ሥም የወጣለት ሊቲየም ከቅንጡ ስልኮች እስከ የኤሌክትሪክ መኪኖች ለሚያንቀሳቅሰው በኃይል እየተደጋገመ የሚሞላ የሊቲየም ባትሪ ቁልፍ ግብዓት ነው። ዓለም “ቆሻሻ” ከሚባለው ነዳጅ ተላቆ ወደ ታዳሽ ኃይል መሸጋገር ካለበት እንዲህ አይነት ባትሪዎች ከጸሀይ እና ከንፋስ የሚመነጭን ንጹህ ኃይል በአንድ ቋት ለማጠራቀም አስፈላጊ ናቸው። 

የሊቲየም ዓለት
ቅንጡ የእጅ ስልኮች እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚያንቀሳቅሰው እየተደጋገመ በኃይል የሚሞላ ባትሪ ለመሥራት ሊቲየም ዋንኛ ግብዓት ነውምስል Robert Michael/dpa/picture alliance

ሊቲየም ለዓለም ገበያ በማቅረብ አውስትራሊያ፣ ቺሊ እና ቻይና ቀዳሚ ናቸው። ሦስቱ ሀገሮች ባለፈው ዓመት ለዓለም ገበያ ከቀረበው ሊትየም 90 በመቶውን አምርተዋል። ነገር ግን ከዓለም የሊቲየም ክምችት 5 በመቶው የሚገኝባት የአፍሪካ አህጉር አሁንም ከፍተኛ እምቅ አቅም አላት። በአኅጉሪቱ ከሚገኘው የሊቲየም ክምችት አብዛኛው ገና ያልተነካ ነው። 

በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ ሊቲየም ለዓለም ገበያ የምታቀርበው ዚምባብዌ ብቻ ናት። ኢትዮጵያን ጨምሮ ኮንጎ፣ ማሊ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ እና ርዋንዳ የሊቲየም ቁፋሮ ጀምረዋል፤ አሊያም ለመጀመር በዝግጅት ላይ ናቸው። 

የሊቲየም ፍላጎት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ በመሔዱ ምርቱ በሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት በአርባ እጥፍ ሊያድግ እንደሚችል የዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ ትንበያ ያሳያል። በኢንዱስትሪ የበለጸጉት ሀገሮች እና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ታዲያ በአፍሪካ ከሚገኘው ሊቲየም የየድርሻቸውን ከእጃቸው ለማስገባት እየተሯሯጡ ነው። ይኸን ውድድር በርካታ የአፍሪካ ሀገራት እጃቸውን ዘርግተው ተቀብለውታል። 

'የመጪው ጊዜ ማዕድን'

የዚምባብዌ ፕሬዝደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ሊቲየምን “የዛሬ እና የነገ ማዕድን” ሲሉ ይገልጹታል። ከአፍሪካ ከፍተኛው የሊቲየም ክምችት ባለቤት የሆነችው ሀገራቸው በጎርጎሮሳዊው 2023 የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት ብቻ 209 ሚሊዮን ዶላር (193 ሚሊዮን ዩሮ) ከሽያጩ አግኝታለች። ይኸ የገቢ መጠን ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በሦስት እጥፍ ገደማ ከፍ ያለ ነው። ዚምባብዌ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እንደ ናሚቢያ እና ታንዛኒያ ሁሉ ጥሬ ወይም ያልተነጠረ ሊቲየም ወደ ውጪ እንዳይላክ አግዳለች። 

በዚምባብዌ የሚገኝ የሊቲየም ማዕድን ማውጪያ
ዚምባብዌ ጥሬ ወይም ያልተነጠረ ሊቲየም ከሀገሯ እንዳይወጣ አግዳለችምስል Shaun Jusa/Xinhua/picture alliance

የዚምባብዌ ዕገዳ ግን ውኃ የሚቋጥር አልሆነም። የግሎባል ዊትነስስ ምርመራ ከፍተኛ መጠን ያለው ያልተነጠረ ሊትየም ከሀገሪቱ በድብቅ እንደሚወጣ ደርሶበታል። ከዚህ በተጨማሪ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ኅብረት ማዕቀብ የተጣለባቸው እና በዚምባብዌ መከላከያ ሠራዊት ሥር የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ሊትየም ወደ ቻይና እንዲልኩ ልዩ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል። መቀመጫውን በሐራሬ ያደረገው የተፈጥሮ ሐብቶች አስተዳደር ማዕከል ዳይሬክተር ፋራይ ማጉዉ እየሆነ ባለው ሁሉ ደንግጠዋል። ፋራይ ማጉዉ “አንዲት የሊቲየም ማውጫ ባይኖራቸውም ወደ ውጪ የመላክ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል። 

ሊቲየም 'እርግማን' ነው 

ፋራይ ማጉዉ ሊቲየም ለዚምባብዌ የሚያመጣው ጥቅም እንዳለ ሲጠየቁ ምላሻቸው ተስፋ እንደሌላቸው የሚያሳብቅ ነበር። “በፍጹም” ነበር መልሳቸው። “አሁን ባለው የአስተዳደር ሥርዓት ከፍተኛ ሊቲየም መገኘቱ ለሀገሪቱ እርግማን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ሀገሪቱን ለውድቀት ይዳርጋታል” የሚል ሥጋት ያላቸው ፋራይ ማጉው “በማዕድን ቁፋሮው የሚደርሰውን ኪሳራ የሚሸከሙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ገቢ ሀገሪቱ ማግኘቷን ለማረጋገጥ ምንም አይነት የቁጥጥር ሥርዓት አልተዘረጋም። ማዕድን ሲቆፈር ኅብረተሰቡ መሬቱን ያጣል፤ ሥነ-ምኅዳር ይወድማል፤ የአካባቢ ብክለት እና ማኅበራዊ ጣልቃ ገብነት ይፈጠራል” ሲሉ ተናግረዋል።

የፓን አፍሪካ ክፍያ ሥርዓት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የኢትዮጵያን አባልነት ይጠባበቃሉ

ማጉዉ በሀገራቸው ዚምባብዌ ሳንዳዋና በተባለ የማዕድን ማውጪያ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሊቲየም እየቆፈሩ ሲያወጡ የተፈጠረውን በምሳሌነት ያነሳሉ። ይኸ የማዕድን ማውጪያ በጎርጎሮሳዊው 2023 መጀመሪያ ለዚምባብዌ ገዢ ፓርቲ ዛኑ ፒኤፍ እና ለሀገሪቱ ጦር ቅርበት ባላቸው ኩባንያዎች ተወስዷል። 

“የማዕድን ቁፋሮ በተፈጠሮው አውዳሚ የሥራ ዘርፍ ነው” የሚሉት ማጉው “በዚምባብዌ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ ቆፍረው መሸጥ ቢችሉም መንግሥት የሊቲየም ማዕድን ያለበት ቦታ እንዳይደርሱ እስካፍንጫቸው የታጠቁ ወታደሮች ይልክባቸዋል” ሲሉ አስረድተዋል። 

በዚምባብዌ የሊትየም ማውጪያ
በዚምባብዌ በጆንያ የተሞላ ጥሬ ሊትየም ወደሚፈጭበት ፋብሪካ ሊጓጓዝ ተዘጋጅቶ ይታያልምስል Tsvangirayi Mukwazhi/AP Photo/picture alliance

ማጉዉ በአፍሪካ ለሚታየው ሙስና “ቁርጥ ያለ መፍትሔ የለም” የሚል አቋም አላቸው። ነገር ግን የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ኩባንያዎች የአኅጉሪቱን ሊቲየም ለመቆፈር ኢንቨስት እንዲያደርጉ ፍላጎት አላቸው። ይኸ ፍላጎታቸው የምዕራባውያኑ ኩባንያዎች ብዙውን ጊዜ በጠንካራ የአካባቢ ጥበቃ፣ ማኅበራዊ እና አስተዳደራዊ መስፈርቶች ይገዛሉ ከሚል የመነጨ ነው።  

የቻይና ሥጋት

ቻይና በአፍሪካ የሊቲየም ቁፋሮ ከፍተኛ ብልጫ አላት። በእነዚህ አስር ዓመታት ከአፍሪካ ይመረታል ተብሎ ከሚጠበቀው ሊቲየም ከአራት አምስተኛው በላይ ወይም 83 በመቶው ቢያንስ በከፊል በቻይና ከተያዙ ኩባንያዎች የሚገኝ እንደሆነ ቤንችማርክ ሚኒራል ኢንተለጀንስ የተባለ በማዕድን ጉዳዮች ላይ የሚሰራ አማካሪ ተቋም ይገምታል። 

ባለፈው ዓመት ብቻ ሦስት የቻይና ግዙፍ የማዕድን ኩባንያዎች የሊቲየም ቁፋሮ ፈቃድ እና 678 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ፕሮጀክቶች በዚምባብዌ በእጃቸው አስገብተዋል። የዚምባብዌ የአካባቢ ሕግ ማኅበር ግን “የሊቲየም ቁፋሮ በአንድ ሀገር ተጠቅልሎ ሲያዝ የማዕድን ሐብቶችን ከሚገባቸው በታች መተመን፣ የግብር መሰወር እና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን የመሳሰሉ የማይፈለጉ ውጤቶች ሊያስከትል ይችላል” በማለት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት አስጠንቅቋል። 

የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ሀገሪቱ “ያለባትን የዕዳ ጫና ለመቀነስ” ከቻይና የፋይናንስ ተቋማት እንዲደራደር መወሰኑን አቶ አሕመድ ሽዴ ተናገሩ

የግሎባል ዊትነስስ መርማሪ የሆኑት ሮበርትሰን የዘርፉን አስተዳደር ለማጠናከር እና ሙስናን ለመዋጋት የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ በሊቲየም ቁፋሮ ረገድ ከፍተኛ ግልጽነት መኖሩን እንዲያረጋግጡ እና በየሀገራቱ ባሉ አክቲቪስቶች የበለጠ ቁጥጥር እንዲደረግ ጥሪ ያቀርባሉ። ሮበርትሰን እንደሚሉት የአውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ ትኩረት የሚያሻቸውን ሊቲየም ለማግኘት አቅርቦቱን ማሳደግ ላይ ብቻ ሊሆን አይገባም። 

ፋራይ ማጉዉ ግን ከሊቲየም ቁፋሮ የሚገኘው ትርፍ በመንገድ፣ የጤና ተቋማት እና ትምህርት ቤቶች ግንባታ መልሶ ለኅብረተሰቡ ጥቅም የሚሰጥበት መንገድ እንደሚያስፈልግ ይሞግታሉ። “ተቆፍሮ ያልወጣ የማዕድን ክምችታችን ተፈጥሯዊ ሐብታችን ነው ብለን እናምናለን” የሚሉት የተፈጥሮ ሐብቶች አስተዳደር ማዕከል ዳይሬክተር “ያንን የተፈጥሮ ሐብት ቆፍሮ ለማውጣት አንዳች አካል ከመጣ የተወሰደው ምርጥ ዘር ለሕዝብ በሚያስፈልጉ አገልግሎቶች መልክ ተመልሶ ወደ ማኅበረሰቡ መዘራት አለበት” ሲሉ በአጽንዖት ተናግረዋል። 

ኬት ኼርሲን/እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር