1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስከረም 25 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 25 2013

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በለንደን ድል ተቀዳጅተዋል፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አባላት 5ቱ የኮሮና ተሐዋሲ እንደተገኘባቸው ተዘግቧል። ማንቸስተር ዩናይትድ እንደ ሊቨርፑል የጎል ጎተራ ኾኗል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ያለ ጄደን ሳንቾ አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል። ባየር ሙይንሽን በትግል ማሸነፍ ችሏል።

https://p.dw.com/p/3jT0E
England | London Marathon | Gewinner Shura Kitata
ምስል Richard Heathcoate/AP Photo/picture-alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ቅዳሜ ዕለት የተሰባሰቡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አባላት ዛሬ ልምምድ ጀመረዋል። በለንደን ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በድል ደምቀው አምሽተዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ሊቨርፑል ከግማሽ ምእተ ዓመት ወዲህ ዐይቶት የማያውቀው ሽንፈት በሳምንቱ መጨረሻ ላይ አስተናግዷል። ማንቸስተር ዩናይትድም እንደ ሊቨርፑል ሁሉ የጎል ጎተራ ኾኗል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ያለ ጄደን ሳንቾ አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል። ቅሳሜ ዕለት ለንደን ከተማ ውስጥ የልደት ፓርቲ ላይ የታየው ጄደን ሳንቾ በቦሩስያ ዶርትሙንድ እንደሚቆይ ተዘግቧል። ባየር ሙይንሽን በትግል ማሸነፍ ችሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የእግር ኳስ ቡድን

ቅዳሜ ማምሻውን «ካፍ አካዳሚ» የገቡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የእግር ኳስ አባላት ልምምድ ጀመሩ። የቡድኑ አባላት በአዲሱ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየታገዙ የመጀመሪያ ልምምዳቸውን ዛሬ ከረፋዱ 3 ሰዓት ላይ ማድረጋቸው ተዘግቧል።  የኮቪድ ምርመራ አድርገው የኮሮና ተሐዋሲ የተገኘባቸው አምስት ተጨዋቾች «ራሳቸውን አግልለው ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል» ተብሏል። «ለእያንዳንዱ ተጫዋች የግል ሕይወት ነጻነት ሲባል እና በስነ ልቦናም እንዳይጎዱ የተጫዋቾቹን ስም ይፋ ባለ ማድረግ» የመገናኛ አውታሮች ኃላፊነት እንዲወጡ ሲል ፌዴሬሽኑ በጥብቅ አሳስቧል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተምስል Omna Taddele/DW

ቅዳሜ ማምሻውን የኮቪድ 19 ምርመራ አድርገው ከኮሮና ተሐዋሲ ነፃ እንደኾኑ የተነገረላቸው «የተቀሩት 31 የቡድኑ አባላት [እሁድ] ማምሻውን የካፍ አካዳሚ» መግባታቸውን ፌዴሬሽኑ ዐሳውቋል። ከ72 ሰዓታት በኋላ የኮሮና ተሐዋሲ የሌለባቸው «ተጫዋቾች እና የቡድኑ አባላት በሙሉ ምርመራ የሚደረግላቸው ይሆናል» ሲልም ፌዴሬሽኑ አክሎ ጠቅሷል።  በ

ፌዴሬሽኑ ጥሪ ከተደረገላቸው 41 ተጨዋቾች መካከል 36ቱ እስከ ትናንት ድረስ ተገንተው ምርመራ ማድረጋቸው ተገልጧል። «ተከላካዩ አንተነህ ተስፋዬ እና ሱራፌል ዳኛቸው እንዲሁም የቡድኑ ወጌሻ» ቡድኑን ዘግይተው መቀላቀላቸውን ፌዴሬሽኑ ገልጦ ዛሬ የኮቪድ ምርመራ እንደሚደረግላቸው በትናንትናው ዕለት ዐሳውቆ ነበር።

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በ40ኛው የለንደን ማራቶን የዘንድሮ ውድድር በሳምንቱ መጨረሻ ላይ እጅግ አመርቂ ውጤት አስመዝግበዋል። በውድድሩ ኹለተኛ ደረጃ ብቻ በኬንያ አትሌት ቪንሴንት ኪፕቹምባ ሲያዝ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ድሉ የተመዘገበው በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ነው። በትናንቱ ውድድር 02:05:41 ሰከንድ በመሮጥ ሹራ ቂጣታ በአንደኛነት አሸንፏል። ኬንያዊው አትሌት በሹራ የተበለጠው በአንድ ሰከንድ ነው።

በዚህ ውድድር ያሸንፋል ተብሎ የተጠበቀው ኬንያዊው አትሌት ኤሊውድ ኪፕቾጌ ከሹራ በአንድ ደቂቃ ከስምንት ሰከንድ ዘግይቶ በ8ኛ ደረጃን አጠናቋል። ለመሸነፉ ምክንያቱን ትዊተር ገጹ ላይ እንደሚከተለው አስፍሯል። «ከ25 ኪሎ ሜትሮች በኋላ ጆሮዬ ተደፈነ፤ እናም ሊከፈት አልቻለም። ግን ስፖርት እንደዚህ ነው፤ ሽንፈት ተቀብለን በሚቀጥለው ለማሸነፍ ትኩረት ማድረግ ይገባናል» ብሏል።  በለንደን ማራቶን የአራት ጊዜያት አሸናፊ የነበረው ኪፕቾጌ ዓመት ጠብቆ እንዳለው የተቀማ ድሉን ያስመልሳል? ከዓመት በኋላ የሚታይ ነው። ዋነኛ ተፎካካሪው ኢትዮጵያዊው አትሌት ሹራ ቂጣታ ግን ዓምና ለድል ባይበቃም ዘንድሮ እንደሚያሸንፍ ቃል ገብቶ ቃሉን ጠብቋል።

የ40ኛው የለንደን ማራቶን የዘንድሮ ውድድር አሸናፊ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሹራ ቂጣታ
የ40ኛው የለንደን ማራቶን የዘንድሮ ውድድር አሸናፊ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሹራ ቂጣታምስል Richard Heathcoate/empics/picture-alliance

ሹራ የዛሬ ዓመት ተመሳሳይ ውድድር ላይ 02:05:01 ሮጦ በአራተኛነት ነበር ያጠናቀቀው። በስሙ በተከፈተ የትዊተር ገጽ ላይ በውድድሩ ወቅት ስህተት መፈጸሙን በወቅቱ ገልጦ ለሚቀጥለው ዓመት ማለትም ለዘንድሮ ውድድር ለመካስ ቃል እንደገባ የሚገልጥ ጽሑፍ ሰፍሯል። እንዲህ ይነበባል የትዊተር መልእክቱ፦ «ዛሬ የማይኾን ስህተት ፈጽሜያለሁ። ቊርሴን አልበላሁም፤ ጥቂት ፍራፍሬ ብቻ ነው የበላሁት። ምንም አልኾንም ብዬ ነበር፤ ግን 35 እና 36 ኪሎ ሜትር ላይ አንጀቴ ሲጣበቅ ተሰማኝ፤ እጅግ በጣም ነበር የተራብኹት።  ጉልበቴ በመላ ነው የተሟጠጠው። ተመልሼ መጥቼ ውድድሩን አሸንፋለሁ።» በእርግጥም ዓመት ጠብቆ ዘንድሮ ድሉን ተጎናጽፏል።  

ከውድሩ በኋላ ተጠይቆም ሲመልስ፦ «ቀነኒሳ በቀለ ረድቶኛል። ይኽን ውድድር በማሸነፌም ደስተኛ ነኝ» ብሏል። አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በውድድሩ ያሸንፋሉ ተብለው ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች ቀዳሚው ነበር። በውድድሩ መቃረቢያ ላይ ግን ባቱ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት እና መሳተፍ እንደማይችል ገልጦ በውድድሩ አልተገኘም። የለንደን ማራቶን ፉክክር አሯሯጭ የነበረው ብሪታኒያዊው የአራት ጊዜያት የኦሎምፒክ ባለድል ሞ ፋራህ በትናንቱ ውጤት መደመሙን አልሸሸገም።

በዘንድሮ የለንደን ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ሲሳይ ለማ፤ ሞስነት ገረመው፤ ሙሉ ዋሲሁን እና ታምራት ቶላ በተከታታታይ ከሦስተኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።  

በለንደን ማራቶን 02:18:58 በመሮጥ አንደኛ የወጣችው ኬንያዊት አትሌት ቢርጊድ ኮስጌይ
በለንደን ማራቶን 02:18:58 በመሮጥ አንደኛ የወጣችው ኬንያዊት አትሌት ቢርጊድ ኮስጌይምስል Richard Heathcote/Reuters

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አሸቴ በከሪ የ4ኛ ደረጃ ይዛ ባጠናቀቀችበ በሴቶች ተመሳሳይ ውድድር ኬንያውያን ድል ቀንቷቸዋል። ቢርጊድ ኮስጌይ 02:18:58 በመሮጥ አንደኛ ወጥታለች። አሜሪካዊቷ ሣራ ሃል ሦስት ደቂቃ ከሦስት ሰከንድ ዘግይታ ኹለተኛ ደረጃ አግኝታለች። አሜሪካዊቷን በአራት ሰከንድ ተከትላ በሦስተኛ ደረጃ ያጠናቀቀችው ሌላኛዋ ኬኒያዊት ሩት ቼፕንጌቲች ስትኾን 02:22:05 ሮጣለች። አሸቴ በከሪ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት 02:22:51 ነበር።

ቡንደስሊጋ

በቡንደስሊጋው የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች፦ ዑኒዮን ቤርሊን ማይንትስን፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ፍራይቡርግን እንዲሁም ላይፕሲሽ የፈረደበት ሻልከን 4 ለ0 አሸንፈዋል። ባየር ሙይንሽንም ሔርታ ቤርሊንን 4 ለ3 ነው ያሸነፈው። ሆፍንሃይም በፍራንክፉርትን 2 ለ1 ተረትቷል። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ኮልንን 3 ለ1 አሸንፈዋል። አርሜኒያ ቢሌፌልድ በቬርደር ብሬመን 1 ለ0 ሲሸነፍ፤ ሽቱትጋርት ከባየር ሌቨርኩሰን ጋር አንድ እኩል እንዲሁም ቮልፍስቡርግ ከአውግስቡርግ ጋር ያለምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ባየር ሙይንሽን ከሁለት ሱፐርካፕ ዋንጫዎች ድል እና በቡንደስሊጋው የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያ ሻልከን 8 ለ0 ካሸነፈ በኋላ ወደ ቀድሞ ብርታቱ አልተመለሰም። መደበኛ 90 ደቂቃ ተጠናቆ በተጨመረው 3 ደቂቃ ላይ የፍጹም ቅጣት ምቱ ባይገኝ ኖሮ ባየር ሙይንሽን 88ኛው ደቂቃ ላይ በንጋንካም በተቆጠረበት ሦስተኛ ግብ ሦስት እኩል ኾኖም ይወጣ ነበር።

ቶማስ ሙይለር ለስካይ ስፖርት፦«የገባብንን ለማስመለስ መታገላችን የሚያስደስት አይደለም» ሲል በቡድኑ የገባው ቅሬታ ገልጧል። ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ የነገሰበት ምሽት ነው። አንዱን በፍጹም ቅጣት ምት ሌሎቹን 3 በጨዋታ አስቆጥሮ ብቃቱን አስመስክሯል። ከ32 ሙከራዎች 29 ኳሶችን ማስቆጠር ችሏል።

ግብ አዳኙ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ አራተኛ ግቡን ሔርታ ቤርሊን ላይ ካስቆጠረ በኋላ
ግብ አዳኙ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ አራተና ግቡን ሔርታ ቤርሊን ላይ ካስቆጠረ በኋላምስል Andreas Gebert/Reuters

በአንጻሩ ዶርትሙንድ ፍራይቡርግ ላይ በግብ በተንፏለለበት ግጥሚያ አጥቂው ኧርሊን ሆላንድ ኹለት ግቦችን ከመረብ አሳርፎ አንድ አመቻችቷል። ኹለተኛውን ግብ ቻን፣ የመጨረሻውን ደግሞ መደበኛው ጨዋታ አልቆ በጭማሪው 2 ደቂቃ ላይ ፌሊክስ ፓስላክ ለቦሩስያ ዶርትሙንድ አስቆጥሯል። 84ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ቶማስ ሞይኒርን ቀይሮ የገባው።

ቦሩስያ ዶርትሙንድ ባለፈው በኹለተኛው ዙር በአውግስቡርግ 2 ለ0 ረቡዕ እለት ደግሞ በጀርመን ሱፐር ካፕ 3 ለ2 ከተሸነፈ በኋላ በጄደን ሳንቾ እና ቡርኪ ፈንታ ማርቪን ሂትስ እና ማርኮ ሮይስ ተሰልፈዋል።

ፕሬሚየር ሊግ

የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ጄደን ሳንቾን ለማስመጣት ጥረት ሲያደርግ የቆየው ማንቸስተር ዩናይትድ እና ሊቨርፑል ትናንት ጉድ ኾነዋል። ሊቨርፑል ከግማሽ ምእተ ዓመት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ 7 ግብ ተቆጥሮበታል። ወሳኝ ተጨዋቾቹ ሳዲዮ ማኔ እና ከባየር ሙይንሽን ያስመጣው ተከላካዩ ቲያጎ አልካንትራ በኮሮና ተሐዋሲ በመጠቃታቸው በትናንቱ ጨዋታ አለመሰለፋቸው በግልጽ ሊቨርፑልን ጎድቶታል። በቀኝ የተከላካይ መስመር ጎሜዝ ተደጋጋሚ ጥፋት እየሠራ ሌሎች ተከላካዮችች እጅግ ደክመው በታዩበት ግጥሚያ በአስቶን ቪላ የ7 ለ2 ከባድ ሽንፈትም ገጥሞታል።

ቸልሲ ክሪስታል ፓላስን 4 ለ0፤ ኤቨርተን ብራይተንን 4 ለ2 አሸንፈዋል። ኒውካስል በርንሌይን 3 ለ1፤ ዌስትሀም ላይስተር ሲቲን 3 ለ0፤ ኒውካስል በርንሌይን 3 ለ1፤ ሳውዝሀምፕተን ዌስትብሮሚችን 2 ለ0፤ ዎልቨርሀምፕተን ፉልሃምን 1 ለ0 እንዲሁም አርሰናል ሼፊልድ ዩናይትድን 2 ለ1 አሸንፈዋል። ማንቸስተር ሲቲ ከሊድስ ጋር አንድ እኩል ተለያይተዋል።

ሌላ ትናንት በተከናወነ ግጥሚያ በቶትንሃም 6 ለ1 ሰፊ የግብ ልዩነት የተረታው ማንቸስተር ዩናይትድ በእርግጥም ጄደን ሳንቾ ሳያስፈልገው አይቀርም። ግን የዝውውሩ ነገር ያከተመለት ይመስላል።  ጄደን ሳንቾ ቅዳሜ ዕለት ለቦሩስያ ዶርትሙንድ ጎሮሮዬን አሞኛል ብሎ ከልምምድ በመቅረት ለንደን ሲዝናና ታይቷል።

የእንግሊዝ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አጋሩ እና ጓደኛው ታሚ አብራሃም ቤት ያለ አፍ እና አፍንጫ መሸፈኚያ በመገኘቱ ዶርትሙንድ ጉዳዩን በቅርበት እንደሚከታተለው ዛሬ ዐሳውቋል። የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ታሚ አብርሃም በ23ኛ የልደት በዓሉ ቀን እቤቱ ውስጥ ከስድስት በላይ ሰዎች በመገኘታቸው ይቅርታ ጠይቋል።

 ሊቨርፑል በአስቶን ቪላ የ7 ለ2 ከባድ ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ የተጨዋቾቹ ስሜት
ሊቨርፑል በአስቶን ቪላ የ7 ለ2 ከባድ ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ የተጨዋቾቹ ስሜትምስል Rui Vieira/Reuters

ቅዳሜ ዕለት የቸልሲው ቤን ቺልዌል እና ጄደን ሳንቾን ጨምሮ ከስድስት በላይ ሰዎች ምንም መከላከያ ሳያደርጉ ታይተዋል። የኮሮና ተሐዋሲ ሥርጭትን ለመግታት በሚል በቅርቡ በእንግሊዝ መንግሥት በወጣው ሕግ መሠረት ከስድስት ሰዎች በላይ አንድ ቤት ውስጥም ኾነ ውጪ መሰባሰብ አይፈቀድላቸውም።

ምንም እንኳን ታሚ አብራሃም እሱ ሳያውቀው የቤተሰቡ አባላት እና ጓደኞቹ ወደ ቤት ሲገባ ባልጠበቀበት ኹኔታ ለልደት ቀኑ ተዘጋጅተው እንደተገኙ ቢገልጥም «ከልቤ ይቅርት እጠይቃለሁ» ብሏል።  

የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጋሬት ሳውዝጌት ከዚህ ቀደም የኮሮና መከላከያ ደንብን የጣሱ ኹለት ተጫዋቾቻቸውን ከቡድኑ ቀንሰው ነበር። ፊል ፎደን እና ማሶን ግሪንዉድ ደንቡን ስለጣሱ እንግሊዝ ለኔሽን ሊግ ባደረገችው ግጥሚያ ከቡድኑ ጋር ወደ አይስላንድ እንዳይጓዙ ተከልክለዋል። እንግሊዝ ሐሙስ እለት ከዌልስ ጋር የወዳጅነት ግጥሚያ አድርጋ ቤልጂየም እና ዴንማርክን በኔሽን ሊግ ትፋለማለች።

ጄደን ሳንቾ

እንግሊዛዊ አማካይ ጄደን ሳንቾ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር የገባው ውል እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር እስከ 2022 ድረስ የሚቆይ ነው። በ2017 ከማንቸስተር ዩናይትድ ባላንጣ ማንቸስተር ሲቲ ወደ ቦሩስያ ዶርትሙንድ የተዛወረው በ7,84 ሚሊዮን ዩሮ ነበር። ዛሬ በዚኽ አማካኝ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከ120 ሚሊዮን ዩሮ በታች አልቀበልም ብሏል።  

 ጄደን ሳንቾ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር የገባው ውል እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር እስከ 2022 ድረስ የሚቆይ ነው
ጄደን ሳንቾ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር የገባው ውል እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር እስከ 2022 ድረስ የሚቆይ ነውምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

ከሚያዝያ ወር አንስቶ ጄደን ሳንቾን ወደ ኦልትራፎርድ ለማስመጣት ሲታገል የቆየው ማንቸስተር ዩናይትድ የተሳካለት አይመስልም። ማንቸስተር ዩናይትድ 91.3 ሚሊዮን ፓውንድ ቢያቀርብም ቦሩስያ ዶርትሙንድ ጥያቄውን በዚህ ሳምንት ውድቅ አድርጎታል። የቦሩስያ ዶርትሙንድ ዳይሬክተር ሚካኤል ዞሪች በዚህ የዝውውር ወቅት የጄደን ሳንቾ ዝውውር ዕውን አይኾንም ብለዋል። «የዝውውር መስኮቱ ተዘግቷል። ይኼን 27 ጊዜ ብዬዋለሁ» ሲሉ ሚካኤል ዞሪች ትናንት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። የፕሬሚየር ሊግ ዝውውር መስኮቱ የሚዘጋው ዛሬ ነው።

ጄደን ሳንቾ ቡድኑን ለቅቆ እንደማይኼድ አሰልጣኝ ሉቺያን ፋቭሬ ተስማምተዋል። የቡድኑ አምበል ማርኮ ሮይስ በበኩሉ፦ የጄደን ሳንቾ በሲግናል ኢዱና ፓርክ መቆየቱ እንዳስደሰተው ገልጧል። ሌሎች ተጨዋቾች ስለቡድኑ መናገር አልተፈቀደላቸውም። ቶማስ ሞይኒር ወደ ልምምድ ቦታ ሲያመራ ለስካይ ስፖርት፦ «ሳንቾ እኛ ጋር ይቆያል» ብሎ ተናግሯል።

ዶርትሙንድ ፍራይቡርግን 4 ለ0 ሲያሸንፍ መሰለፍ አልቻለም። የዝውውሩ ዜና ከተሰማ በኋላ ሳንቾ በልምምድ ላይ አልነበረም። በበጋ ዝውውር ወቅት ጄደን ሳንቾ የማንቸስተር ዩናይትድ ቊጥር አንድ ተፈላጊ ተጨዋች ኾኖ ቆይቶ ነበር።

ጄደን ሳንቾ ለቦሩስያ ዶርትሙንድ ለ102 ጊዜ ተሰልፎ 35 ግብ አስቆጥሯል፤ 45 አመቻችቷል።  ከዶርትሙንድ ሽያጭ ማንቸስተር ሲቲ 15 በመቶ ተጠቃሚ ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ በ120 ሚሊዮን ቢገዛው ኖሮ 17 ሚሊዮኑ ለማንቸስተር ሲቲ ገቢ ይኾን ነበር።

ሚያዝያ 30 ቀን፦ከባርሴሎና ባሻገር ማንቸስተር ዩናይትድ ጄዶን ሳንቾን እንደሚፈልግ ይፋ አደረገ።

ግንቦት 8 ቀን፦ዶርትሙንድ ከጄደን ሳንቾ ዝውውር ቢያንስ 120 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚፈልግ ዐሳወቀ። ቀደም ሲል እንደውም ፍላጎቱ 147 ሚሊዮን ዩሮ ነበር። በ2017 ዖስማኔ ዴምቤሌን ወደ ባርሴሎና ባገኘው ገቢ ልክ ማለት ነው።

Bundesliga - Borussia Dortmund v Hertha BSC
ምስል Getty Images/L. Baron

ግንቦት 25 ቀን፦ የቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድ ተከላካይ ዌስ ብራውን ከክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር ነው የሚያመሳስለው። ሦስት አራት ተጨዋቾችን እንደ ሮናልዶ ማታለል የመቻል ብቃቱንም አመሳስሎታል። ከ2003 እስከ 2009 ድረስ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በማንቸስተር ዩናይትድ የነበረውን ዝና ወጣቱ ጄደን ሳንቾም ማምጣቱ አይቀርም ብሎ ነበር።

ሰኔ 22 ቀን፦ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ምናልባት ሳዲዮ ማኔ ቡድኑን የሚለቅ ከኾነ እሱን የሚተካው ጄደን ሳንቾ ነው ብሎ ነበር። ማኔ እንደውም የሊቨርፑል አለኝታ ነው አኹን ሦስት ግጥሚያዎች ሦስት ግብ ማስቆጠር ችሏል። እንደውም ሊቨርፑል ከ1963 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ 7 ግብ በተቆጠረበት የትናንቱ ግጥሚያ እሱ እና ከባየር ሙይንሽን የተዛወረው ቲያጎ በኮሮና ተሐዋሲ በመጠቃታቸው ምክንያት አለመሰለፋቸው ሊቨርፑልን ምን ያህል እንደጎዳው ማየት ይቻላል።

ሰኔ 25 ቀን፦ ሳንቾ ወደ ቀድሞ ቡድኑ ማንቸስተር ሲቲ ሊመለስ ነው ተብሎ ነበር። የሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ግን፦ «ወደ ዶርትሙንድ የቀየረው በዓመቱ ወደ እኛ ሊመለስ አይደለም» በማለት ነበር የሚወራውን ያጣጣሉት።

ነሐሴ 2 ቀን፦ ማንቸስተር ዩናይትድ በሳምንት 340,000 ዩሮ ደሞዝ ሊከፍለው ለአምስት ዓመት ሊያስፈርመው እንደነበር የጀርመኑ ቢልድ ጋዜጣ ዘግቦ ነበር። በዓመት 17,6 ሚሊዮን ዩሮ ማለት ነው። በወቅቱ ስለ ዝውውር ስምምነቱ ግን ግልጽ አልነበረም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ