1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጋቢት 11 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 11 2015

በሳምንቱ መጨረሽያ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል ። አርሰናል ክሪስታል ፓላስን ጉድ ባደረገበት የትናንቱ ግጥሚያ ቡካዮ ሳካ ድንቅ ብቃቱን አስመስክሯል ።

https://p.dw.com/p/4OxJv
Mexiko | Fußballstadion Azteca in Mexiko-Stadt
ምስል Carlos Ramirez/firo Sportphoto/Mexsport/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በሳምንቱ መጨረሽያ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል ። አበበ ቢቂላ በበባዶ እግሩ በማራቶን ፉክክር ድል በተቀዳጀባት የሮም ከተማ በተኪያሄደው የማራቶን ሩጫ ግን አመርቂ ውጤት አልተገኘም ። አርሰናል ክሪስታል ፓላስን ጉድ ባደረገበት የትናንቱ ግጥሚያ ቡካዮ ሳካ ድንቅ ብቃቱን አስመስክሯል።  

አትሌቲክስ

ከግማሽ ምእተ ዓመት በፊት ኢትዮጵያዊው ጀግና አትሌት አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ድል በተቀዳጀባት በጣሊያን ሮም ከተማ ትናንት በተከናወነው የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ከ1ኛ እና 6ኛ ውጪ ከ2ኛ እስከ ሰባተኛ ድረስ ተከታትለው ገብተዋል። ኬኒያዊቷ ብሬንዳ ኪፕሮኖ ጣልቃ በመግባት የ6ኛ ደረጃን ይዛለች ። ውድድሩን ኬኒያዊቷ ቤቲ ቼፕክዎኒ 2 ሰአት ከ23 ደቂቃ ከ01 ሰከንድ በመሮጥ ስታሸንፍ፤ ፎይዛ ጀማል 2:25:09 በመሮጥ የ2ኛ ደረጃ አግንታለች። ከአምሳ ሰከንድ በኋላ ደግሞ ዝናሽ ደበበ ተከትላ በመግባት የሦስተኛ ደረጃን አግኝታለች ። ጀሚላ ሹሬ 4ኛ፤ ሙሉ ጎጃም አምባዬ 5ኛ እንዲሁም እፀገነት እዝጊ የ7ኛ ደረጃን ይዘዋል ። በወንዶች ዘርፍ ውጤት ባይገኝም አትሌት ብርሃኑ ሄዬና ሲሳይ ፍቃዱ የ5ኛ እና 7ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል ።

በዚህ ማራቶን የወንዶ ፉክክር የሞሮኮው ቶፊቅ ዓላም 2 ሰአት ከ07 ደቂቃ ከ42 ሰከንድ  ሲያሸንፍ፤ ኬንያውያኑ ዊልፍሬድ ኬጊ እና ሮጀርስ ኬረር የሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል ። በውድድሩ ኢትዮጵያውያን በወንድም በሴትም ባያሸንፉም አንድ ክስተት ግን የብዙዎችን ትኩረት ስቧል ። ስለዚያ ጉዳይ የሮም ማራቶን ውድድር ይፋዊ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የቀጥታ ዘጋቢ አንገስ ቶሮድ ይነግረናል ።

የሚሮጡ ሰዎች እግር እና ጥላ
የሚሮጡ ሰዎች እግር እና ጥላምስል picture-alliance/imageBROKER/M. Dietrich

«ሆኖም ትናንት ኢትዮጵያውያንን ያስደመመ ነገር ነበር ። የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድ የቀድሞ ኃላፊ ኤርሚያስ አየለ በሮም ማራቶን በጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር በ1960 ያሸነፈው እና የአትሌቶች አባት በሚል ክብር የሚሰጠው አበበ ቢቂላን በመዘከር በጣሊያን ዋና ከተማ ሮም በባዶ እግሩ ሮጦ ውድድሩን አጠናቋል ። ከኮሎሲየሙ ሲወጣም የሰው ስሜት እጅግ በጣም ልዩ ነበር ። ኤርሚያስ ውድድሩን ለመጨረስ ረዥም ጊዜ ቢወስድበትም በጉጉት እየጠበቅነው ነበር ። በግሩም ሁኔታ ነው የሮጠው ። እከመጨረሻውም በጀግንነት ታግሏል ። ውድድሩን ሲያጠናቅቅም ሞቅ ያለ ድጋፍ ነው ያገኘው። ጣሊያኖች በዚህ በጣም ነው የተደመሙት ።»

ትናንት በባዶ እግሩ ማራቶን ሮጦ ያጠናቀቀው ኤርሚያስን በስፍራው የእንግሊዝኛ ኮሜንታተር የነበረው አንገስ ጠይቆት ነበር ። አበበ ቢቂላ ውድድሩን በባዶ እግሩ ሲያደርግ ስነበረው ስሜት ውድድሩን ስትጨርስ ምን ተሰማህ ሲልም ለጠየቀው ኤርሚያስ ቀጣዩን ብሏል ።

በስፔን ባርሴሎና ማራቶን፣ በሴቶች ዘይነባ ይመር 1ኛ ደረጃን አግኝታለች ። በደቡብ ኮርያ ሴኡል ማራቶን፣ የወንዶች ፉክክር አምደወርቅ ዋለልኝ 1ኛ፤ ሺፈራው ታምሩ 2ኛ፤  ኃፍቱ ተክሉ 3ኛ፤  ኦሊቃ አዱኛ 4ኛ እንዲሁም አሸናፊ ሞገስ 5ና ደረጃን አግኝተው በድል አጠናቀዋል ። በዩናይትድ ስቴትስ ኒው ዮርክ ማራቶን በሴቶች ሰንበሬ ተፈሪ የ2ኛ ደረጃ አግኝታለች ። በፈረንሳይ የ10 ኪሎ ሜትር ፉክክር ገመቹ ዲዳ 1ኛ ሲወጣ፤ በሴቶች በልቅና አምባው የ3ኛ ደረጃ ተገኝቷል ። በዚሁ የፈረንሳይ ውድድር የ5 ኪሎ ሜትር ፉክክር ዮሚፍ ቀጀላ 1ኛ ሆኖ ሲያሸንፍ፤ ጥላሁን ኃይሌ 3ኛ ደረጃን አግኝቷል ።  በሴቶች መቅደስ አበበ የ2ኛ ደረጃን ይዛለች ።

እግር ኳስ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪቃ ዋንጫ የ2023 ላለበት ሦስተኛ እና አራተኛ የምድብ ጨዋታ ምክንያት በማድረግ በፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ዛሬ ከሰአት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል ። መግለጫውን የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ባሕሩ ጥላሁን ናቸው የሰጡት ።

ፎቶ ከማኅደር፦ የካሜሩን ደጋፊዎች በአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፉክክር ጊዜ
ፎቶ ከማኅደር፦ የካሜሩን ደጋፊዎች በአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፉክክር ጊዜምስል Pius Utomi Ekpei/AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የጊኒ አቻው ስቴዲየማቸው የፊፋ መስፈርትን አያሟሉም በሚል ሁለቱ ሃገራት የደርሶ መልስ ውድድራቸውን መጋቢት 15 እና 18 ሞሮኮ ውስጥ ነው የሚያካሄዱት ። ምናልባት ከሞሮኮ ጋር ባለው ትብብር የተነሳ ቡድኑ እዛ ድረስ ሲሄድ የሚያወጣው ወጪ የተወሰነው ይቀንስ ይሆናል ።

ቡድኑ እንዲህ በየሃገራቱ እየዞረ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ሲያደርግ ግን ብዙ ነገሮችን እንደሚያጣ ይታወቃል ። የስቴዲየም ወጪ ገቢ፤ በሀገር ውስጥ ሜዳ በሀገር ደጋፊዎች ከሚሰጠው ድጋፍ ለተጨዋቾች የሚኖረው የመንፈስ መነቃቃት፤ ተጨዋቾች ረዥም በረራ በማድረግ ከሚኖረው መጉላላት እና ድካም ነጻ መሆን የመሳሰሉት ጥቅሞችን ያጣል ። ፌዴሬሽኑን ይሄ ምን ያህል አሳስቦታል? በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታትስ በመግለጫው የተጠቆመ ነገር አለ? በካናል ፕላስ ኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ የዛሬውን ጋዜጣዊ መግለጫ ተከታትሏል ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከሩዋንዳ አቻው ጋር በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ትናንት ባደረገው የአቋም መለኪያ ጨዋታ 1 ለ0 አሸንፏል ። ለኢትዮጵያ የማሸነፊያዋን ግብ በ83ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ከነዓን  ማርክህ ነው ። ብሔራዊ ቡድኑ አሁን ያለው አቋም በአሰልጣኙ እና በፌዴሬሽኑ ግምገማ መሰረት ምን ይመስላል? ከቀጣይ ውድድሮችስ ምን አይነት ውጤት ይጠበቃል ተባለ? 

ፕሬሚየር ሊግ

ቡካዮ ሳካ በ43ኛው እና 74ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል ። ጋብሪዬል ማርቲኔሊ በ28ኛው እንዲሁም ግራኒት ሻቃ በ55ኛው ደቂቃ ላይ ግቦችን አስቆጥረዋል ። ለክሪስታል ፓላስ ብቸኛዋን ግብ ጄፍሪ ሽሉፕ 63ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አሳርፏል። በተለይ ከጥቂት ቀናት በፊት ለወጣት ተጨዋቾች የሚሰጠውን የለንደን የእግር ኳስ ሽልማት ያገኘው ቡካዮ ሳካ እስካሁን 12 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ እና 10 ግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማመቻቸት ድንቅ ተጨዋች መሆኑን አስመስክሯል ። የ21 ዓመቱ አጥቂ ግን ከምንም በላይ የሚያስደስተኝ «ቡድኔን መርዳቴ ነው» ብሏል ።

በድል ጎዳና የሚገሰግሰው የአርሰናል ቡድን
በድል ጎዳና የሚገሰግሰው የአርሰናል ቡድንምስል Nick Potts/picture alliance/empics

በእርግጥም የአውሮጳ ሊግ ጉዞው በፍጹም ቅጣት ምት መለያ በስፖርቲንግ ሊዛቦን ለተሰናከለበት አርሰናል የትናንቱ የፕሬሚየር ሊግ ድል እጅግ ወሳን ነበር ። አርሰናል የትናንቱ ድሉ ታክሎበት ፕሬሚየር ሊጉን በ69 ነጥብ መምራት ችሏል። ማንቸስተር ሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 61 ነጥብ ሰብስቦ ሁለተኛ ደረጃ ይዟል ። ማንቸስተር ዩናይትድ ቀሪ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ከፊቱ እየጠበቁት በ50 ነጥቡ የሦስተኛ ደረጃውን ይዟል ። ዌስትሀም ዩናይትድ፤ ቦርመስ እና ሳውዝሀምፕተን ከ18ኛ እስከ 20ኛ ደረጃ ይዘው ወራጅ ቀጣናው ውስጥ ይገኛሉ ።

ቡንደስ ሊጋ

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ባየርን ሙይንሽን ትናንት ሁለት የፍጹም ቅጣት ምቶች ዋጋ አስከፍለውታል ። ባዬር ሌቨርኩሰን ባየር ሙይንሽንን 2 ለ1 ሲያሸንፍ ሁለቱም ግቦች የተገኙት በቪዲዮ እገዛ ዳኛው በሰጡት የፍጹም ቅጣት ምቶች ነው ።  በዚህ ድልም በዘንድሮው የቡንደስሊጋ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ባዬር ሌቨርኩሰን ባየርን ሙይንሽንን በማሸነፍ ሦስተኛው ቡድን ሆኗል ።

የሪያል ማድሪድ አጥቂ ካሪም ቤንዜማ በሁለት የባርሴሎና ተከላካዮች መካከል ኳስ ለመቆጣጠር እየጣረ
የሪያል ማድሪድ አጥቂ ካሪም ቤንዜማ በሁለት የባርሴሎና ተከላካዮች መካከል ኳስ ለመቆጣጠር እየጣረምስል Bernat Armangue/AP Photo/picture alliance

ተጋጣሚ ኮሎኝን እጅግ በልጦ 6 ለ1 ድል ያደረገው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በቡንደስሊጋው የመሪነቱን ስፍራ ተቆናጧል ። 52 ነጥብ ያለው ባየርን ሙይንሽን በቦሩስያ ዶርትሙንድ በአንድ ነጥብ ይበለጣል ። ዑኒዮን ቤርሊን 48 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ሔርታ ቤርሊን የቡንደስ ሊጋው ወራጅ ቀጣና ጠርዝ 16ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። ሻልከ እና ሽቱትጋርት የመጨረሻ 17ኛ እና 18ኛ ደረጃ ላይ ተደርድረዋል ።

በብዙዎች ዘንድ በሚጠበቀው የስፔን ላሊጋ ኤል ክላሲኮ ግጥሚያ ባርሴሎና ሪያል ማድሪድን  2 ለ1 ድል አድርጓል ። በዚህ ውድድር ለሪባርሴሎና የማሸነፊያ ግቦቹን ሠርጂ ሮቤርቶ እና ፍራንክ ኬሲ አስቆጥረዋል። የሪያል ማድሪድ ብቸኛ ግብ የተገኘችው በሮናልዶ አራኡሆ ነው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ