1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጋቢት 13 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 13 2013

ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ማዳጋስካር ከነገ በስትያ ዋሊያዎቹን ይገጥማል። በፕሬሚየር ሊጉ ዌስትሀም እና አርሰናል ተጋጥመው ነጥብ መጣላቸው ለሊቨርፑል በጅቶታል። በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን ገና በ12ኛው ደቂቃ አንድ ተጨዋቹ በቀይ ካርድ ከሜዳ ቢሰናበትበትም ሽቱትጋርትን 4 ለ0 አንኮታኩቷል።

https://p.dw.com/p/3qyJu
Deutschland Bundesliga - Bayern München v VfB Stuttgart | Robert Lewandowski
ምስል Andreas Gebert/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ማዳጋስካር ከነገ በስትያ ዋሊያዎቹን ይገጥማል። በወዳጅነት ግጥሚያ ማሊን 4 ለ0 በሆነ ሰፊ ልዩነት የረታው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድሉን ባሕር ዳር ውስጥ ማዳጋስካር ላይ ይደግመው ይሆን? በፕሬሚየር ሊጉ ዌስትሀም እና አርሰናል ተጋጥመው ነጥብ መጣላቸው ለሊቨርፑል በጅቶታል። በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን ገና በ12ኛው ደቂቃ አንድ ተጨዋቹ በቀይ ካርድ ከሜዳ ቢሰናበትበትም ሽቱትጋርትን 4 ለ0 አንኮታኩቷል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ የሳምንቱ መጨረሻ አልቀናውም። ነጥብ ጥሏል። ላይፕትሲሽ ከአዳጊ ቡድን ጋር ተጋጥሞ በጠበበ ልዩነት ቢሆንም 3 ነጥብ ይዞ ወጥቷል። ቮልፍስቡርግ እና አይንትራኅት ፍራንክፉርት ድል ቀንቷቸዋል። በተለይ ፍራንክፉርት ዐርብ ዕለት በግብ ተንበሽብሿል። ባርሴሎና ትናንት ሪያል ሶሲዬዳድን ጉድ አድርጓል። በአሌቲኮ ማድሪድ ግን ይበለጣል።

የአፍሪቃ ዋንጫ

ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ቀሪ ሁለት ግጥሚያዎች በያዝነው እና በቀጣዩ ሳምንት ይከናወናሉ። ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ አይቮሪኮስት በአራት ጨዋታዎች 7 ነጥብ ይዛ ትመራለች። የፊታችን ረቡዕ ባህር ዳር ከተማ ውስጥ ዋሊያዎቹን የሚገጥመው የማዳጋስካር ቡድን በተመሳሳይ ነጥብ ግን በግብ ክፍያ ልዩነት የሁለተኛ ደረጃን ይዟል። በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከማዳጋስካር የሚበለጠው በአንድ ነጥብ ብቻ ነው። ኒጀር 3 ነጥብ ብቻ ይዛ የምድቡ መጨረሻ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማዳጋስካርን ካሸነፈ በዘጠኝ ነጥብ የምድቡ መሪነትን ይረከባል። አይቮሪ ኮስት ግን በኒጀር መሸነፉ አጠራጣሪ ስለሚሆን በመሪነቱ ሊቀጥልም ይችላል።

Logo Africa Cup of Nations

የነገ ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡድን ጋር የሚያደርገው ግጥሚያ ግን እጅግ ወሳኝ ነው። እስካሁን ድረስ አይቮሪኮስት የማዳጋስካር ቡድንን 2 ለ1 አሸንፎታል። በመልሱ ግጥሚያም አንድ እኩል ወጥቷል። ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ጌኔራል ሴይኒ ኩንትቼ ስታዲየም ውስጥ በዮሱፍ ዑማሩ ፍጹም ቅጣት ምት በኒጀር 1 ለ0 ተሸንፋ፤ በመልሱ ግጥሚያ አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ መሱድ ሞሐመድ እና ጌታነህ ከበደ ባስቆጠሯቸው ግቦች 3 ለ0 አሸንፋለች። የማዳጋስካር ቡድን የማክሰኞ ሳምንት ኒጀርን ይገጥማል።

ዋሊያዎቹ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የማላዊ ቡድንን በወዳጅነት ግጥሚያ 4 ለ0 በሆነ ሰፊ ልዩነት ድል አድርገዋል። ማላዊ ከነገ በስትያ ለአፍሪቃ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያዋን ከደቡብ ሱዳን ጋር ታከናውናለች።

የእየ ምድቡ አሸናፊ 24 ቡድኖች ካሜሩን የዛሬ ዓመት ግድም በምታስተናግደው 33ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ግጥሚያ ተሳታፊ ይኾናሉ። ለቀጣዩ የአፍሪቃ ዋንጫ ፉክክር አስተናጋጇ ካሜሩንን ጨምሮ አምስት ቡድኖች ከወዲሁ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። ከእየ ምድባቸው አንደኛ ኾነው በማጠናቀቅ ያለፉት ቡድኖች ማሊ፣ አልጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ እና  ቱኒዚያ ናቸው።

አዘጋጇ ካሜሩን፦ መዲናዪቱ ያውንዴ፣ ጉዋላ፣ ጋሮዋ፣ ሊምቤ እና ባፎሳም ከተሞች ውስጥ ከ20 ሺህ እስከ 60 ሺህ ታዳሚዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ስድስት ዘመናዊ ስታዲየሞች አሏት። የመክፈቻ እና የመዝጊያ ግጥሚያዎች የሚከናወኑት ያውንዴ ከተማ የሚገኘው እና በርካታ ታዳሚያን የመያዝ አቅም ያለው ፖል ቢያ ስታዲየም ውስጥ ነው። የአፍሪቃ ዋንጫ እግር ኳስ ተሳታፊዎች ቊጥራቸው ከ16 ወደ 24 በማደጉ አስተናጋጅ ሀገር ቢያንስ ስድስት ዘመናዊ ስታዲየሞች ሊኖሩት ይገባል።

መዲናዪቱ ያውንዴ ከተማ የሚገኘው ታዲየም (ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደራችን)
መዲናዪቱ ያውንዴ ከተማ የሚገኘው ታዲየም (ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደራችን)ምስል Getty Images/AFP/A. Huguet

በሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ፦ የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ የነገ ሳምንት ከእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ ጋር ይገጥማል። ዶርትሙንድ በቡንደስሊጋው ውሉ ጠፍቶበታል። ሲቲ በአንጻሩ ዘንድሮ የፕሬሚየር ሊጉን ጨምሮ አራት ዋንጫዎችን ለመሰብሰብ ቋምጧል። በቡንደስሊጋው መሪነቱን ያስጠበቀው ባየርን ሙይንሽን የፈረንሳይ ሊግ አንድ መሪው ፓሪ ሳን ጃርሞን የዛሬ ዐሥራ አምስት ቀን ረቡዕ ዕለት ይፋለማል። ቸልሲ ከፖርቶ እንዲሁም በፕሬሚየር ሊጉ ከመሪነት ወደ 7ኛ ደረጃ ያሽቆለቆለው ሊቨርፑል በስፔን ላሊጋ ብርቱ ተፎካካሪ የኾነው ሪያል ማድሪድን ይገጥማል።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ  ትናንት አርሰናል እና ዌስትሀም ዩናይትድ ወሳኝ ጨዋታቸውን አከናውነው ሳይሸናነፉ ቀርተዋል። ሦስት እኩል በተጠናቀቀው ጨዋታ አርሰናል በኳስ ይዞታ በሚገባ በልጦ ታይቷል። ሁለቱ ቡድኖች በሚቀጥለው የጨዋታ ዘመን የሻምፒዮንስ ሊግ ደረጃን ለመያዝ ሊቨርፑል እና ቶትንሀምን ጨምሮ በሚያደርጉት ግብግብ የትናንቱ ግጥሚያ ነጥብ ሊይዙበት የሚገባ ወሳኝ ጨዋታ ነበር።

በሻምፒዮንስ ሊጉ እንግሊዝን ወክሎ ለመሰለፍ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ማግኘት ያስፈልጋል። አርሰናል ትናንት አቻ ወጥቶ የተጋራውን አንድ ነጥብ ጨምሮ በ42 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ዌስትሀም ዩናይትድ በ49 ነጥቡ የአምስተኛ ደረጃን ተቆናጧል። አራተኛ ደረጃን ከያዘው ቸልሲ በ2 ነጥብ ይበለጣል። ቶትንሀምን በአንድ ነጥብ ይበልጣል። 7ኛ እና 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሊቨርፑል እና ኤቨርተን በእኩል 46 ነጥብ በቅርብ ርቀት ይገኛሉ። ኤቨርተን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል።

ማንቸስተር ሲቲ በ71፣ ማንቸስተር ዩናይትድ በ57፣ ላይስተር ሲቲ በ56 ነጥብ ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ማንቸስተር ሲቲ እና 18ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ፉልሃም ብቻ 30 ጊዜ ተጫውተዋል። ሌሎቹ በአብዛኛው 29 የተወሰኑት 28 ጨዋታዎችን አከናውነዋል።

የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞሐመድ ሳላህ
የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞሐመድ ሳላህ ምስል picture-alliance/AP/S. Botterill

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሊቨርፑሉ ሞሐመድ ሳላህ እና የቶትንሀሙ ሐሪ ኬን 17 ግብ አስቆጥረው በጋራ የኮከብ ግብ አግቢነቱን ረፍድ ይዘዋል። የማንቸስተር ዩናይትዱ ብሩኖ ፈርናንዴዝ በ16 ከመረብ ያረፉ ኳሶች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 14 ግቦችን ያስቆጠሩት የሊድስ ዩናይትዱ ፓትሪክ ባምፎርድ እና የኤቨርተኑ ካልቬር ሌዊን የሦስተኛ ደረጃን ተጋርተዋል።

ኤፍ ኤ ካፕ

በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ግማሽ ፍጻሜ ለስምንት ጊዜያት ዋንጫ ያነሳው ቸልሲ ዘንድሮ አራት ዋንጫዎችን ለመሰብሰብ የሚንደረደረው ማንቸስተር ሲቲን ይገጥማል። ላይስተር ሲቲ ከሳውዝሀምፕተን ጋር ይፋለማል። ማንቸስተር ሲቲ ከኤፍ ኤ ካፕ በተጨማሪ፣ የፕሬሚየር ሊግ ፣ የሊግ እና የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን የማሸነፍ ዕድሉ ክፍት ነው። የኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያዎቹ አንድ ወር ግድም ይቀራቸዋል።

ቡንደስሊጋ

ቦሩስያ ዶርትሙንድ በሚቀጥለው የጨዋታ ዘመን ለሻምፒዮንስ ሊግ የማያልፍ ከሆነ ኖርዌጂያዊው አጥቂ በቡድኑ አንደማይቆይ እየተነገረ ነው። የ20 ዓመቱ አጥቂ ኧርሊንግ ብራውት ኦላንድ ቡድን ቦሩስያ ዶርትሙንድ በቡንደስሊጋው 43 ነጥብ ይዞ የአምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አይንትራኅት ፍራንክፉርት በ47 ነጥብ የሻምፒዮንስ ሊግ ደረጃውን አስጠብቋል። ቮልፍስቡርግ በ51፣ ላይፕትሲሽ በ57 እንዲሁም ባየርን ሙይንሽን በ61 ነጥብ ከሦስተኛ እስከ አንደኛ ያለውን ደረጃ ተካፍለዋል።  

ኮሎኝ በ23፣ አርሜኒያ ቢሌፌልድ በ22 እንዲሁም ሻልከ በ10 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ከ16ኛ እስከ 18ኛ ተደርድረዋል። ሻልከ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን መባረሩ የማይቀር ሲሆን፤ 24 ነጥብ ያላቸው ሔርታ ቤርሊን እና ማይንትስ ወደ ወራጅ ቃጣናው ለመግባት ያሰጋቸዋል።

የባየርን ሙይንሽኑ አጥቂ ሠርግዬ ግናብሬ
የባየርን ሙይንሽኑ አጥቂ ሠርግዬ ግናብሬምስል Carmen Jaspersen/REUTERS

በቡንደስሊጋው የባየር ሙይንሽኑ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ በ35 ከመረብ ያረፉ ኳሶች ኮከብ ግብ አግቢነቱን ያለማንም ተቀናቃኝ እየመራ ነው። የአይንትራኅት ፍራንክፉርቱ አንድሬ ሲልቫ እና የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ኧርሊንግ ኦላንድ እያንዳንዳቸው 21 ግብ አላቸው። 17 ግብ ያለው የቮልፍስቡርጉ ቩውት ቬግሆርስት በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባየርን ሙይንሽን ሽቱትጋርትን 4 ለ 0 ባሸነፈበት የቅዳሜው ግጥሚኢ አልፎንሶ ዳቪስ 12ናው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ሔትትሪክ ሠርቷል። አራተኛ ግቧ የሠርግዬ ግናብሬ ናት።

ላሊጋ

በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ትናንት ሪያል ሶሲይዳድን 6 ለ1 ድባቅ በመታበት ግጥሚያ ሊዮኔል ሜሲ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። አርጀንቲናዊው አጥቂ ሳን ሰባስቲያን ውስጥ ትናንት ልዩ ምሽት አሳልፏል። ሁለት ግብ ብቻ አይደለም፤ ለ768 ጊዜ ለባርሴሎና ቡድን በመሰለፍም ክብረ ወሰን ሠብሯል። አንቶኒ ግሪዝማን በቀድሞ ቡድኑ ላይ ሁለት ማግባት ችሏል። 43ኛው ደቂቃ ላይ የተቆጠረችው ግብ ለሠርጂኖ ዴስት የመጀመሪያ የሊግ ግብ ሆና ተመዝግባለታለች። አሜሪካዊው የቀኝ ክንፍ ተከላካይ በዚያም አላበቃ።  ከ10 ደቂቃ በኋላ ሁለተኛ ግቡን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ተጋጣሚው ሪያል ሶሲዬዳድ ቡድንን በባዶ ከመሸነፍ ያዳነችውን ብቸና ግብ 77ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው አንድሬ ባሬኔትክስያ ነው።

የሜሲ፣ ጆርዲ አልባ እና በአንቷን ግሪዝማን ተቀይሮ የገባው ሪኩዊ ፑውጊ ቅንጅት አጭር ቢሆንም ድንቅ ነበር። ባርሴሎና በላሊጋው 62 ነጥብ ይዞ የሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። መሪው አትሌቲኮ ማድሪድ ትናንት አላቬስን 1 ለ0 ድል በማድረጉ ባርሴሎናን በ4 ነጥብ ይበልጠዋል። ሪያል ማድሪድ በካሪም ቤንዜማ እና ማርኮ አሴንሲዮ ግቦች 3 ለ1 አሸንፏል። ካሪም ቤንዜማ በ20 እና 30ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ለሴልታ ቪጎ 40ኛው ደቂቃ ላይ ሳንቲ ሚና በባዶ ከመሸነፍ ያተረፈቻቸውን ግብ አስቆጥሯል።

የ33 ዓመቱ አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ
የ33 ዓመቱ አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ ምስል Christophe Ena/AP/picture alliance

የ33 ዓመቱ አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ በ23 ግቦች የላሊጋው ኮከብ ግብ አግቢ ነው። የአትሌቲኮ ማድሪዱ ሉዊ ሱዋሬዝ በ19 ይከተላል። የሪያል ማድሪዱ ካሪም ቤንዜማ በ17 ከመረብ ያረፉ ኳሶች በኮከብ ግብ አግቢነት ተርታ የሦስተኛ ደረጃን ይዟል። የቪላሪያሉ ጌራርድ ሞሬኖን በአንድ ግብ ብቻ ነው የሚበልጠው። የአትሌቲኮ ማድሪዱ ሉዊስ ሱዋሬዝ በጨዋታ ዘመኑ 500ኛ ግቡን አላቬስ ላይ አስቆጥሯል። የትናንቱ የማሸነፊያ ብቸኛ ግቡ በአትሌቲኮ ማድሪድ 19ኛ ግቡ ኾኖ ተመዝግቦለታል።

በጣሊያን ሴሪአ ጁቬንቱስ በሜዳው ቤኔቬንቶን ገጥሞ የ1 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። 10ኛ የሴሪኣ ዋንጫን ለማንሳት የነበረውን ሕልም አዶልፎ ጋይቺ በታትኖታል። ፍጹም ቅጣት ምት የተነፈገው እና የክርስቲያኖ ሮናልዶ ግቡ የተሻረበት ጁቬንቱስ በ10 ነጥብ ልዩነት ከመሪው ኢንተር ሚላን ርቆ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ኢንተር ሚላን በ65 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ሲይዝ፤ ኤሲ ሚላን በ59 ነጥቡ የሁለተኛ ደረጃን ተቆናጧል። የጁቬንቱስ ቡድን ኃላፊ ፋቢዮ ፓራቲች ቡድናቸው የ36 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶን ወደ ሌላ ቡድን እንዳይኼድ የተቻለውን ሁሉ ጥረት እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ