የመጋቢት 18 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ መጋቢት 18 2015የአፍሪቃ ዋንጫ እና የአውሮጳ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለዋል ። ምሽቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታውን በርካታ በአውሮጳ ቡድኖች የሚጫወቱ ተጨዋቾችን ከሚያሰልፈው የጊኒ ቡድን ጋር እዛው ሞሮኮ ውስጥ ያደርጋል። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በዓለም አቀፍ ውድድሮች በመሰለፍ እና ለብሔራዊ ቡድኑ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ክብረወሰን ሰብሯል ። የአርጀንቲና እግር ኳስ ፌዴሬሽን የማሰልጠኛ ማእከሉን በሊዮኔል ሜሲ ስም ሰይሟል ። የጀርመኑ ባየርን ሙይንሽን ፓሪ ሳን ጃርሞን ከሻምፒዮንስ ሊግ ካሰናበተው ወጣት አሰልጣኝ ጋር ውሉን ማቋረጡና ቶማስ ቱኁልን ማስፈረሙ በርካቶችን አስገርሟል ።
አትሌቲክስ
ላለፉት ዐሥር ዓመታት ሲከናወን የነበረው የኢትዮጵያ አጭር፣ መካከለኛ፣ 3 ሺህ ሜትር መሰናክል፣ ርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ፉክክር ትናንት ተጠናቋል ። በዝግጅቱ የከፍታ እና የርዝመት ዝላይ፤ የአጭር እና የመካከለኛ ርቀት እንዲሁም የአሎሎ እና የጦር ውርወራን ጨምሮ የተለያዩ የአትሌቲክስ ስፖርት ውድድሮችን ለአምስት ተከታታይ ቀናት ተከናውኗል ። ዝግጅቱ የተጠናቀቀው እሁድ መጋቢት 17 ነበር ። በውድድሩ 19 ቡድኖች እና ተቋማት፤ 398 ወንዶች፣ 288 ሴቶች፣ በአጠቃላይ 677 አትሌቶች እንደተሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዐስታውቋል ። ውድድሩ ለአትሌቶች የፉክክር መድረክ በመፍጠር የአትሌቶቹን አቋም ለመገምገም እና አሸናፊዎችን ሸልሞ ለማበረታታት ያለመ መሆኑም ተገልጧል ።
እግር ኳስ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪቃ ዋንጫ ማጣርያ አራተኛ የምድብ ጨዋታውን ከጊኒ ብሔራዊ ቡድን ጋር ዛሬ ማታ 4 ሰዓት ላይ ሞሮኮ ራባት ከተማ በሚገኘው ልዑል ሞውላይ አብደላ ስታዲየም ያደርጋል ። የጊኒ ቡድን በሙሉ በውጭ ሀገር የሚሰለፉ ተጨዋቾችን ያካተተተ ጠንካራ ቡድን ሲሆን በፊፋ መስፈርትም ደረጃው 83ኛ ነው ። በአንጻሩ ኢትዮጵያ 138ኛ ላይ ትገኛለች ። ዐርብ ዕለት በነበረው የመጀመሪያ ጨዋታ የጊኒ ቡድን ሙሉ ለሙሉ በውጭ ሃገራት በአብዛኛው በአውሮጳ የሚሰለፉ ተጨዋቾችን አሰልፎ ነበር ወደ ሜዳ የገባው ። በዚሁ የመጀመሪያ ጨዋታም የጊኒ ቡድን የኢትዮጵያ ቡድንን 2 ለ 0 አሸንፏል ። ካዛብላንካ መሐመድ አምስተኛ ስታዲየም ውስጥ በነበረው ግጥሚያ ለጊኒ ሁለቱን ግቦች በ39ኛው እና በ73ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠሩት አጥቂዎቹ ለሩስያው ሎኮሞቲቭ ሞስኮው ተሰላፊው ፍራንሱዎ ካማኖ እና ለፈረንሳዩ ሊል ቡድን የሚጫወተው ሞሐመድ ባዮ ናቸው ። በዕለቱ የጊኒ ቡድን ከፓሪ ሳንጃርሞ እስከ ሎኮሞቲቭ ሞስኮው፤ ከቫሌንሺያ እስከ ሊቨርፑል ወሳኝ የሚባሉ ተጨዋቾችን አሰልፎ ነበር ።
አሁን ባለው ውጤት መሰረት፦ ኢትዮጵያ ከምድቡ ከማላዊ ጋር ተመሳሳይ 3 ነጥብ ይዛ በግብ ክፍያ በመበለጥ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ትገኛለች ። ግብጽ እና ጊኒ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ።
በአፍሪቃ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ጊኒ ቢሳዎ ጠንካራውን የናይጀሪያ ቡድን በሜዳው l ለ0 ማሸነፏ ብዙዎችን አስደምሟል ። የመልሱ ጨዋታ ዛሬ ነው ። የኒጀር እና አልጀሪያ ጨዋታም በተመሳሳይ ሰአት ዛሬ ማታ ይካሄዳል ። በትናንትናው ዕለት ሴራሊዮን ሳዖ ቶሜ እና ፕሪንሲፔን እንዲሁም ዛምቢያ ሌሶቶን 2 ለ0 አሸንፈዋል ። ቅዳሜ ዕለት በነበረ የወዳጅነት ጨዋታ አፍሪቃዊቷ ሞሮኮ ብራዚልን 2 ለ1 አሸንፋለች ።
የአውሮጳ ዋንጫ ማጣሪያ
በአውሮጳ የእግር ኳስ ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያዎች፦ ዛሬ ማታ ኔዘርላንድ ከጂብራልታር እንዲሁም ፈረንሳይ ከአየርናድ ሪፐብሊክ ጋር ይጋጠማሉ ። ቼክ ሪፐብሊክ ከሞልዶቫ፤ ፖላንድ ከአልባኒያ ፤ ኦስትሪያ ከኢስቶኒያ እንዲሁም ስዊድን ከአዘርባጃን ጋር ይጫወታሉ ። ሁሉም ጨዋታዎች የሚከናወኑት በተመሳሳይ ከምሽቱ ሦስት ሰአት ከዐርባ አምስት ደቂቃ ላይ ነው ።
በትናንትናው ዕለት፦ እንግሊዝ ዩክሬንን፤ ጣሊያን ማልታን፤ ስሎቫኪያ ቦስኒያ እና ሔርዜጎቪናን እንዲሁም ስሎቬኒያ ሣን ማሪኖን በተመሳሳይ 2 0 አሸንፈዋል ። ዴንማርክ በካዛክስታን የ3 ለ2 አስገራሚ ሽንፈት ሲገጥማት፤ ፊንላንድ ሰሜን አየርላንድን 1 ለ0 አሸንፋለች ። ፖርቹጋል ሉክዘምበርግን 6 ለ0፤ አይስላንድ ሌሽተንሽታይንን 7 ለ0 የግብ ጎተራ አድርገዋል ።
ዋና አጥቂዋ ኧርሊንግ ኦላንድን በጉዳት የተነሳ ያላሰለፈችው ኖርዌይ ቅዳሜ ዕለት በስፔን የ3 ለ0 ሽንፈት ገጥሟታል ። ስኮትላንድ ሳይፕረስን 3 ለ0 ረትታለች ። ክሮሺያ ከዌልስ እንዲሁም እስራኤል ከኮሶቮ ጋር አንድ እኩል ሲለያዩ፤ ቱርክ አርሜኒያን 2 ለ1፤ ሮማኒያ አንዶራን 2 ለ0 አሸንፈዋል ። ስዊዘርላንድ ቤላሩስን 5 ለ0 አሸንፏል ። የአፍሪቃ ዋንጫ እና የአውሮጳ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ነገም ይቀጥላሉ ። ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ መሪዋ ግብጽ ከማላዊ ጋር የምትጫወተው በነገው ዕለት ነው ።
ባየርን ሙይንሽን
ባየርን ሙይንሽን ዩሊያን ናግልስማንን አሰናብቶ ቀደም ሲል ቦሩስያ ዶርትሙንድ፤ ፓሪ ሳንጃርሞ እና ቸልሲን ያሰለጠኑት ቶማስ ቱኅልን አስመጥቷል ። ባየርን ሙይንሽን ቶማስ ቱኁልን በአሰልጣንነት የዛሬ አምስት ዓመት ግድም ወደ ቡድኑ ሊያመጣቸው ሞክሮ ነበር ። በወቅቱ ግን ዘግይቶ ስለነበር አልተሳካለትም ።
የዩሊያን ናግልስማን መሰናበት በርካታ ትችቶችን አስነስቷል ። ዩሊያን ናግልስማን በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ባየርን ሙይንሽን ፓሪ ሳንጃርሞን በደርሶ መልስ ለ3 ለ0 ድል ቢያበቁም ከመሰናበት ግን አልተረፉም ። የባየርን ሙይንሽን ቡድን ፕሬዚደንት ሔርቤርት ሐይነር ሰኞች ዕለት አሰልጣኙን አወድሰው ነበር ። «ናግልስማን ከፓሪ ሳንጃርሞ ጋር በነበረው ግጥሚያ በታክቲክም ሆነ በስልት ድንቅ ብቃቱን በከፍተኛ ደረጃ አሳይቷል ። ከእሱ ጋርም የረዥም ጊዜ ውል ለማድረግ አቅደናል ። በዚያ ረገድ ግልፅ የሆነ መሻሻል ዕያየን ነው» ሲሉም ኪከር በተባለው በጀርመንኛ ቋንቋ የሚቀርበው የስፖርት ድረገጽ ላይ ተናግረው ነበር ። አፍታም ሳይቆይ ግን ሐሙስ ዕለት የዩሊያን ናግልስማን የስንብት ዜና ተሰምቷል ።
ከማንቸስተር ሲቲ ጋር የሚጋጠመው ባየርን ሙይንሽንን ለሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ያበቁት ወጣቱ አሰልጣኝ የመሰናበት ዜናም ብዙዎችን አስደምሟል ። ስለ አሰልጣኙ ስንብት ዐርብ ዕለት የተጠየቁት የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክ እና የባየርን ሙይንሽን ተጨዋች ጆሱዋ ኪሚሽ በድንገተኛ ውሳኔው መገረማቸውን በመግለጥ ብዙም ማለት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል ። የቡድኑ ደጋፊዎች በድንገተኛ ስንብቱ መበሳጨታቸውን ገልጠዋል ። ሽቴፋን ዛይፈርት የተባሉ የባየርን ሙይንሽን ደጋፊ ዐርብ ዕለት ተጠይቀው በአሰልጣኙ መሰናበት ተቃውሟቸውን ገልጠዋል ።
«ለእኔ ድንገተኛነቱ በጣም ነው ያስገረመኝ ። እንደዚያ ይሆናል ብዬ ፈጽሞ አልገመትሁም ። ከጥቂት ሳምንት በፊት እኮ ቦርዱ አሰልጣኙን ሲደግፍ ነበር ። ስለዚህ ዜናው ትናንት ማታ የእጅ ስልኬ ላይ ሲመጣ በጣም ደንቆኝ ነበር። እኔ በግሌ ቶማስ ቱኁልን አሁን እንዲመጡ አልፈልግሁም ነበር ።»
ሉዊ ሆልትሲንገር የተባሉ ሌላ የባየርን ሙይንሽን ቡድን ደጋፊ ደግሞ ቀጣዩን ብለዋል ። «እኔ እንኳን አሁንም ድረስ እጠራጠራለሁ ። ምክንያቱም ቱኁል ዶርትሙንድ ውስጥ ያለፈ ታሪክ አላቸው ። በእርግጥ ጥሩ ባይሆንም ከቸልሲ እና ከፓሪ ሳንጃርሞ ጋርም እንደዚሁ ። ግን ደግሞ ብዙ ልምድ ያላቸው አሰልጣኝም ናቸው ። በርካታ ከዋክብትንም አሰልጥነው ለስኬት አብቅተዋል ። ስለዚህ በባየርን ውስጥም ያ ይሠራል ብዬ እገምታለሁ ። »
በእርግጥ ባየርን ሙይንሽን በቡንደስ ሊጋው በባየር ሌቨርኩሰን የደረሰበት የ2 ለ1 ሽንፈት እንደ ዋና ሰበብም ተወስዷል ። በዘንድሮ የቡንደስሊጋ ውድድር ባየር ሌቨርኩሰን ባየርን ሙይንሽንን ሲያሸንፍ ሦስተኛው ቡድን ነበር ። በአንጻሩ በቡንደስ ሊጋው ዋነኛው ተፎካካሪው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ኮሎኝን 6 ለ1 አንኮታኩቶ በደረጃ ሰንጠረዡ የመሪነት ቦታውን መያዙ የባየርን ሙይንሽን አመራርን ሳያስደነግጥ አልቀረም ። ባየርን ሙይንሽን በባየርን ሌቨርኩሰን ሁለት ግቦች በፍጹም ቅጣት ምት ከተቆጠረበት እና ከተሸነፈ በኋላ የቡድኑ የስፖርት ክፍል ኃላፊ በሰጡት አስተያየት አመራሩ መከፋቱን በደንብ ማየት ይቻላል ። ሽንፈቱን በተመለከተ ሲናገሩ፦ «ያ የባየርን ሙይንሽን አቋም አይደለም» ያሉት ኃላፊው የተጋጣሚ ቡድኑ በልጧቸው እንዲጫወት ቡድናቸው «መፍቀዱን» በብርቱ ነቅፈዋል ። ባየርን ሙይንሽንን ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ዓመት ከሦስት ወራት ለማሰልጠን ውል እንደፈረሙም የተዘገበላቸው ቶማስ ቱኁል «በባየርን ሙይንሽን መጠየቄ ለእኔ ክብር ነው» ብለዋል ።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን በዓለም አቀፍ ውድድር ላይ 198 ጊዜ በመሰለፍ አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል ። ከዚህ ቀደም የኩዌቱ ባደር አል-ሙታዋ 196 ጊዜ በመሰለፍ ክብረ ወሰን ይዞ ቆይቶ ነበር ።ትናንት ንዑሷ ሉክሰምበርግን በሜዳዋ 6 ለ0 ባደባዩበት የአውሮጳ ማጣሪያ ጨዋታ ቀዳሚዋን ግብ በ9ኛው ደቂቃ እንዲሁም በ31ኛው ደቂቃ ላይ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ማስቆጠር ችሏል ። ፖርቹጋል ሐሙስ ዕለት ሌሽተንስታይንን 4 ለ 0 ባሸነፈችበት ጨዋታም የ38 ዓመቱ አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፏል ። ፖርቹጋል በዓለም ዋንጫ ውድድር ከሩብ ፍጻሜው በሞሮኮ ስትሰናበት ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከሜዳ የወጣው እያነባ ነበር ። ከቡድኑ ጋር የነበረው ግንኙነትም በአሰልጣኙ የተነሳ የተቃቃረ ነበር ። አሁን ግን በሁለቱ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከአጠቃላይ ቡድኑ ጋር ስምምነት ያወረደ ይመስላል ። ክርስቲያኖ ሮናልዶ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ 122 ግቦችን በማስቆጠር ክብረ ወሰኑን አርቆታል ። ከዚህ ቀደም በኢራኑ ተጨዋች ዓሊ ዳዪ ተይዞ የቆየውን ክብረወሰንም በ13 ግቦች ከፍ አድርጓል ።
የአርጀንቲና ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ኤርዛይዛ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የማሰልጠኛ ማእከሉ በካታር የዓለም ዋንጫ ገናናነቱን ዳግም ባስመሰከረው አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ ስም እንዲጠራ ወስኗል ። ይህንንም የአርጀንቲና እግር ኳስ ማኅበር (AFA)ፕሬዚደንት ክላውዲዮ ታፒያ ይፋ አድርገዋል ። በማእከሉ መግቢያ ላይም «ሊዮኔል አንድሬስ ሜሲ» የሚል ይነበባል ። በማእከሉ የዕውቅና ስነስርዓት ላይ የተገኘው የ35 ዓመቱ አጥቂ፦ «ለዚህ ዕውቅና እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ ። ለበጠ ያነቃቃኛል » ብሏል ። ሊዮኔል ሜሲ ዐርብ ዕለት ቡድኑ አርጀንቲና በአቋም መለኪያ ጨዋታ ፓናማን 2 ለ0 ባሸነፈበት ግጥሚያ 800ኛ ግቡን አስቆጥሯል ። ሊዮኔል ሜሲ ከፓሪ ሳንጃርሞ ጋር የገባው ውል የዘንድሮ የጨዋታ ዘመን ሲጠናቀቅ አብሮ ያከትማል ። በዓለም ዋንጫ ወቅት « The Times» የተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አቅንቶ ለሚያሚ ቡድን ይጫወታል ሲል ዘግቦ ነበር ። በእርግጥ ዘገባውን የሜሲ አማካሪ ማርሴሎ ሜንዴዝ ወዲያው ነበር ያጣጣሉት ። እናስ ውሉ ሲያበቃ በርካታ ፈረንሳውያን እንደሚሹት እዛው ፓሪ ሳንጃርሞ ይቆያል ወይንስ ወደ ሌላ ቡድን ያቀናል? ገና በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም የብዙዎች ግምት ግን ወደ ኢንተር ሚላን ያቀናል የሚል ነው ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር