የመጋቢት 25 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ መጋቢት 25 2015የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በሞሮኮ ቆይታው በጊኒ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ተሸንፎ ለአፍሪቃ ዋንጫ የማለፍ ዕድሉን አጨልሞ ባለፈው ሳምንት ተመልሷል ። በምድቡ እንደ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ሦስት ነጥብ ያላት ማላዊ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኟን አሰናብታለች ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዝቅተኛ ነጥብ ስላስመዘገበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል ። ለመሆኑ ለተደጋጋሚ ሽንፈቱ ኃላፊነት የሚወስደው ማን ነው ተባለ? ምንስ አይነት ርምጃስ ተወሰደ? ጋዜጣዊ መግለጫውን በተመከተ መረጃዎችን ያሰባሰበ የስፖርት ተንታኝ አነጋግረናል ። ኢትዮጵያውያን ለድል ስለበቁበት የአትሌቲክስ ፉክክሮች መረጃዎችን እናቀብላችኋለን ።
አትሌቲክስ
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት የፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ተማ እና ዴጉ ደቡብ ኮሪያ ውስጥ የተደረጉ የማራቶን ውድድሮች ለድል በቅተዋል ። ዴጉ ደቡብ ኮሪያ ውስጥ በተደረገ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያኑ አሸናፊ የሆኑት በሁለቱም ጾታዎች ነው ። በወንዶቹ ሚልኬሳ መንገሻ 2 ሰዓት ከ6 ደቂቃ ከ49 ሰከንድ በመግባት አሸናፊ ሲሆን፤ በሴቶቹ ምድብ አያንቱ አበራ አሸናፊ ሆናለች ። መዲና ደሜ ደግሞ የሁለተኛ አግኝታለች ። አያንቱ አበራ ውድድሩን ለማጠናቀቅ 2 ሰዓት ከ25 ደቂቃ ከ44 ሰከንድ ወስዶባታል። በወንዶቹ ምድብ ኬንያዊው ስታንሌ ቤት ኪፕሮች ሁለተኛ እንዲሁም ኤርትራዊው ብርሃነ ጸጋይ ሦስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።
በተመሳሳይ ትናንት በፓሪስ ፈረንሳይ በተካሄደ የማራቶን ውድድር የ20 ዓመቱ ወጣት አበጀ አያና አሸናፊ ሲሆን ፤ ሌላው ኢትዮጵያዊ እና ለውድድሩ አስቀድሞ ለአሸናፊነት ተጠብቆ የነበረው ጉዬ አዶላ 2ኛ ሆኗል። አበጀ አያና ውድድሩን 2 ሰዓት ከ7 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ በመግባት ነው ያሸነፈው ። አበጀ የፓሪሱን ማራቶን ሲያሸንፍ በአራት ዓመት ውስጥ ሦስተኛው ኢትዮጵያዊ ሆኗል። ኬንያዊው ጆስፋት ቦይት ደግሞ በአምስት ሰከንዶች ብቻ ተቀድሞ ሶስተኛ ሆኗል። በሴቶች ምድብ በተደረገው የማራቶን ውድድር ኬንያዊቷ ኪፕሮፕ አሸናፊ ሆናለች ። ኢትዮጵያውያኑ አታለል አንሙት እና ፍቅርተ ወረታ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሆነው አጠናቀዋል። ኪፕሮብ በውድድሩ ማጠናቀቂያ ችቂት ሜትሮች ሲቀራት ከኋላ ተነስታ ያሸነፈችበት መንገድ አድናቆት አስገኝቶላታል። ውድድሩን ለማጠናቀቅም 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ19 ሰከንድ ወስዶባታል ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መግለጫ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሞሮኮ ቆይታው ከጊኒ ብሔራዊ ቡድን ጋር ያከናወናቸውን ሁለት ጨዋታዎች ተሸንፎ ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል ። የጊኒ ቡድን በመጀመሪያው ጨዋታ ዋሊያዎቹን 2 ለ0፤ በመልሱ ጨዋታ ደግሞ 3 ለ2 በድምሩ 5 ለ2 በሆነ ውጤት አሸንፏል ። ቡድኑን በተመለከተ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሰኞ መጋቢት 25 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ከቀኑ በ9፡00 ሰአት በፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል ። ኢትዮጵያ እስካሁን ባደረገቻቸው ጨዋታዎች፦ እንደ ማላዊ 3 ነጥብ ይዛለች ። በአንጻሩ ምድቡን ግብፅ በ9 ነጥብ ይመራል ። ተመሳሳይ ነጥብ ያለው የጊኒ ቡድን በግብ ክፍያ ተበልጦ የሁለተኛ ደረጃን ይዟል ። ሁለት የግብ እዳ ያለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከእንግዲህ ሁለት ቀሪ ጨዋታዎቹን እንኳን ቢያሸንፍ ነጥቡ ከዘጠኝ አይሻገርም ። በአንጻሩ እያንዳንዳቸው ዘጠኝ ነጥብ ያላቸው ግብፅ እና ጊኒ አምስት እና ሦስት ግቦች አሏቸው ። የሐትሪክ ጋዜጣ መስራች እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ይስሐቅ በላይ የዛሬውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋዜጣዊ መግለጫ በተመለከተ መረጃዎችን አሰባስቧል ። ዋልያዎቹ ከምድቡ ግብፅን ሲያሸንፉ ለአፍሪቃ ዋንጫ ለማለፍ የነበረው ከፍተኛ መነቃቃት በጊኒ ተከታታይ ሽንፈቶች መክኗል ።
ፕሬሚየር ሊግ
ቸልሲ በአስቶን ቪላ ትናንት በሜዳው የ2 ለ0 ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ አሰልጣኙ ግርሃም ፖተርን አሰናብቷል ። የቸልሲ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ብሩኖ ሳልቶር ተጨዋቾቻቸው «ሐዘን» ቢገባቸውም ቡድናቸው ከሊቨርፑል ጋር ለሚኖረው ወሳኝ ግጥሚያ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጠዋል። ቸልሲ ዋና አሰልጣኙን ያሰናበተው ጀርመናዊው ቶማስ ቱሁልን እንዲተኩ በከፍተኛ ገንዘብ ከመጡ በኋላ ቸልሲ ካደረጋቸው 28 ጨዋታዎች ዐሥሩን ብቻ በማሸነፋቸው ነው ። ከባየርን ሙይንሽን የተሰናበቱት ጁሊያን ናገልስማን የቸልሲ አሰልጣኝ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ግምት አለ ። ቸልሲ በፕሬሚየር ሊጉ 38 ነጥብ ይዞ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ለአውሮጳ ዋንጫ ለማለፍ ከተደረደሩት አራቱ ቡድኖች አራተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ከማንቸስተር ዩናይትድ በ12 ነጥብ ይበለጣል ።
ፕሬሚየር ሊጉን በ72 ነጥብ የሚመራው አርሰናል ቅዳሜ ዕለት ሊድስ ዩናይትድን 4 ለ1 በማሸነፍ ብቃቱን ዐሳይቷል ። በዕለቱ የዬርገን ክሎፕ ሊቨርፑል በማንቸስተር ሲቲ ተመሳሳይ የ4 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል። ማንቸስተር ሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በአርሰናል የሚበለጠው በ8 ነጥብ ነው ። ኒውካስል እንደማንቸስተር ዩናይትድ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ተመሳሳይ 50 ነጥብ ይዞ ሆኖም በግብ ክፍያ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ሊቨርፑል ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ ቀርቶት በ42 ነጥቡ 8ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ።
ቡንደስሊጋ
በቡንደስሊጋው ባየርን ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት ዋነኛ ተፎካካሪው ቦሩስያ ዶርትሙንድን 4 ለ2 ድል አድርጎ የመሪነቱን ሥፍራ ተረክቧል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድን በ2 ነጥብ የሚበልጠው ባየርን ሙይንሽን ነጥቡን 53 አድርሷል ። በድንገት የተሰናበቱት ጁሊያን ናገልስማን ለተኩት አሰልጣኝ ቶማስ ቱሁል የቅዳሜው ድል መልካም ገድ ሆኗቸዋል ። ቀጣይ ከፍራይቡርግ ጋር ጋር ነገ ለሚያደርጉት ግጥሚያም ከፍተኛ መነቃቃትን የፈጠረ ድል ነበር ። ፍራይቡርግ በዑኒዮን ቤርሊን በ4 ነጥብ ተብልጦ በያዘው 47 ነጥቡ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።
በፈረንሳይ ሊግ ትናንት በሊዮን የ1 ለ0 ሽንፈት የገጠመው ፓሪ ሳን ጃርሞ ነጥብ ጥሏል። ሌን እና ማርሴይ በተመሳሳይ 60 ነጥብ ይዘው በስድስት ነጥብ ብቻ ተበልጠው ተጠግተውታል ። በደጋፊዎች ዘንድ ቅሬታ የተነሳበት ሊዮኔል ሜሲ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል ። ሆኖም አሰልጣኙ ክሪስቶፍ ጋልቲየር የ35 ዓመቱ አርጀንቲናዊ አጥቂን ተከላክለዋል ። «ሊዮ ለቡድናችን ብዙ ያደረገ ተጨዋች ነው» ሲሉም ድጋፋቸውን ሰጥተውታል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ